Artcles

የሞት መንገድ

By Admin

March 01, 2018

የሞት መንገድ

                                                    ደስታ ኃይሉ

የውጭ አገር የስራ ስምሪትን በተመለከተ መንግስት ከበርካታ አገሮች ጋር ስምምነቶችን የፈጸመ ቢሆንም፤ አሁንም በርካታ ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ እየተሰደዱ ለአደጋ በመጋለጥ ላይ ናቸው። ማንኛውም ውጭ አገር ለመስራት የሚፈልግ ዜጋ ህጋዊ መንገዱን በመከተል ራሱን ከአደጋ መጠበቅ አለበት።

በተለይ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ደላሎች በህብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ለህግ አሳልፎ የመስጠት ስራ የህብረተሰቡ መሆን ይኖርበታል። ወላጆች ልጆቻቸውን በህገወጥ መንገድ እንዲሰደዱ ማድረግ ወደ ሞት እንደመላክ የሚቆጠር የሞት መንገድ መሆኑን በመገንዘብ ለችግሩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል።

እርግጥ የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኘና በተግባር እየተከናወነ ያለ ጉዳይ ነው። እናም እዚህ ላይ ዜጎች ለምን ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል።

ይሁንና ሰዎች በሀገር ውስጥ ወይም ወደ ውጭ ሀገር ከቦታ ወደ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወይም ስደት የተሻለ ስራ ፍለጋና ህይወት ወይም ልክ ወንድም እንደሆነው የኤርትራ ህዝብ ከጭቆና ለመሸሽ አሊያም የመኖሪያ ቦታን ለመቀየር ሊሆን ይችላል።

ዳሩ ግን የእንቅስቃሴው ዓላማ በሰዎች ለመነገድ ሲባል የሚከናወን ከሆነ ተግባሩ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚፈረጅ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል። እናም በዚህ ፅሑፍ ላይ ለመጥቀስ እየመከርኩት ያለሁት በመግቢያዬ ላይ ያነሳሁትን ዓይነት የዜጎቻችንን ህይወት እየቀጠፈ ስላለው በህገ-ወጥ ደላላዎች አማካኝነት ቤተሰብንና ዘመድ አዝማድን ብሎም ዜጎችን እያስለቀሰ ስላለው ስለዚሁ የዝውውር ዓይነት መሆኑ ልብ ሊባልኝ ይገባል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሁለት ዓመታት በፊት ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ባደረገው ጥናት፤ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል 76 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑት የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች መሆናቸውን አረጋግጧል።

ከእነዚህ ውስጥ እስከ 95 በመቶ የሚደርሱት ወደዚያች ሀገር የሚያቀኑት በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ነው።

ህገ ወጥ ደላሎች ግንኙነት እንደ ሰንሰለት በተያያዘ ሰንሰለት የተቆራኘ ነው። ይሁንና በዚህ አነስተኛ ፅሑፍ ላይ ከህገ-ወጥ ደላሎቹ ማንነት፣ አሰራራቸውና በዝውውሩ ሂደት ከሚኖራቸው ሚና አኳያ አዘዋዋሪዎቹን የአካባቢ፣ ድንበር አሻጋሪ፣ ጉዞ አቀላጣፊ፣ ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በመዳረሻ ሀገራት የሚገኙ ደላሎች በማለት ልንከፍላቸው እንችላለን።

የአካባቢ ደላሎች በመገኙባቸው ቦታዎች የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና በሌሎች ዘዴዎች ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እንዲሁም ተጋላጭ ግለሰቦችን የመለየት ስራን ከሌሎች ጋር በመሆን ያከናውናሉ። ድንበር አሻጋሪዎቹም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን የሚያዘዋውሩ በኮንትሮባንድ ነጋዴነት የሚፈረጁ ናቸው። እነዚህኛዎቹ አዘዋዋሪዎች ሰዎችን በቡድን ከአካባቢ ደላሎች ተቀብለው ለሌሎች ተመሳሳይ አዘዋዋሪዎች የማስተላለፍ ስራዎችን ይተገብራሉ።

ጉዞ አቀላጣፊዎቹም ቢሆኑ መቀመጫቸውን ትላልቅ ከተማዎች ላይ በማድረግ ወደ መዳረሻ ቦታዎቹ የሚደረገውን ጉዞና የቅጥር ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ ሲሆን፣ ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው ደግሞ ዘመድና ጎረቤቶች እናግዛለን በማለት እነርሱ ወደ ነበሩበት ሀገር ሄደው እንዲቀጠሩ በግለሰብ ደረጃ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በመደበኛነት የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

የእነዚህ ከስደት ተመላሽ ዜጎች እንቅስቃሴ በቤተሰባቸውም ይደገፋል። ቤተሰቦቻቸው ልጆቻቸው ውጪ ሀገር ሄደው የሚያመጡት ገንዘብ በምን ሁኔታ የተገኘ መሆኑን ስለማይገነዘቡ ከስደት የተመለሱት ልጆቻቸው ያስገኙላቸውን “ጠቀሜታዎች” በመዘርዘር የህገ-ወጥ ስደቱ ሂደት ተካፋይ ይሆናሉ። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በደላልነት ተሰልፈው የዜጎቻቸውን ህይወት ለአደጋ አሳልፈው ይሰጣሉ።

በመጨረሻም በእነዚህ መንገዶች ከሀገራቸው በህገ-ወጥ ሁኔታ በመውጣት ራሳቸውን ያገለጡት ዜጎች በመዳረሻ ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ ደላሎች እጅ ላይ ይወድቃሉ። እነዚህ ህገ-ወጥ ደላሎችም ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው የተለያዩ ደላሎች አማካኝነት የቀረቡላቸውን ግለሰቦች፤ በማታለል፣ በማስገደድ አሊያም በማስፈራራት በቀጥታ ለብዝበዛ እንዲጋለጡ ያደርጓቸዋል። በዚህ መንገድ ወደ ሌሎች ሀገራት ውስጥ የሚገቡ ዜጎች በመንገድ ላይ ህይወታቸው ካላለለፈና ወደ መዳረሻ ሀገሮች በሰላም ከገቡ ዕጣ ፈንታቸው ብዝበዛ ወይም ለህልፈተ-ህይወት ከሚዳርግ አደገኛ ሁኔታ ጋር መላተም ነው።

ከዚህ ሁኔታ አኳያ አሁንም በሀገራችን የህገ ወጥ ደላሎች ሲሳይ በመሆን ወደ ሞት መንገድ የመሄድ ተግባር አልተገታም። በተለይ መንግስት ህጋዊ የስራ ስምሪት አዋጅን ይፋ አድርጎ ሲያበቃ የችግሩ አመቀረፍ ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል።

የህገ ወጥ ስደት ጉዳይ የእያንዳንዳችንን በር እስኪያንኳኳ ድረስ መጠበቅ የለብንም። እናም ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ጉዳዩችን ማወቅ ይገባል። እነዚህ የችግሩ ተዋናዮች ግብ አንድና አንድ ነው። ሆኖም ገንዘብን አገኛለሁ ብሎ በወጡበት መቅረት መኖሩን ማስታወስ ይገባል። የህገ ወጥ ስደቱን መንገድ ለመቀነስ ብሎም ለመዝጋት መንግስት ፈርጀ ብዙ ጥረት እያደረገ ነው።

በአሁኑ ወትት መንግስት ለስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠር መንግስትነት ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋን ለመከላከልም ከግንዛቤ ማስጨበጥ እስከ ተጨባጭ ርምጃዎችን መውሰድ ደረጃም ደርሷል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በመላ ሀገሪቱ በተዋረድ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል። በዚህም ህበረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሔው አካል እንዲሆን በየክልሉ በርካታ ተግባራት ዕውን ሆነዋል።

ይሁንና እነዚህ ጥረቶች ሀሁሉ ተደርገው ህገ ወጥ ስደትን ማስቆም አልተቻለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርቶ ማንም ባዶ እጁን እንደማይቀር ከወጣቱ ይልቅ የተሻለ ግንዛቤ ያለው ቤተሰብ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ታዲያ ይህንን እውነታ አሳምኖና አስረድቶ የማይጨበጥ ተስፋ አስተሳሰብን በመስማት ቤተሰብም የጉዳዩ ተባባሪ በመሆን የአጋዥነት ሚና ሲጫወት ይታያል። ጥሪታቸውን ሸጠው አሊያም ተበድረው ልጆቻቸውን የሚልኩ ቤተሰቦች በርካታ ናቸው።

ያም ሆኖ አሁንም ቢሆን የህገ ወጥ ስደት ችግር ጉዳይ የእያንዳንዳችንን በር እስኪያንኳኳ ድረስ መጠበቅ የለብንም። እናም ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ጉዳዩችን ማወቅ ይገባል።  መንስአኤዎቹን አውቀንም ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው ርብርብ ሁላችንም ልንሰራ ይገባል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ህጋዊ መንገድ ተቀይሶላቸው እያለ ወደ ሞት መንገድ ሲሄዱ ዝም ብለን ማየት አይኖርብንም።