Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላሙ ዳኛ

0 289

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላሙ ዳኛ

                                                          ደስታ ኃይሉ

የሰላም አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ተስፋ ከልማት ጋር ነው። ዘላቂ ሰላም ከሌለን እንደ አገር የህልውና ጉዳይ አድርገን የያዝነውን ልማት እውን ማድረግ አይቻልም። ለዚህም ባለፉት 27 ዓመታት በአስተማማኝ ሰላም ያገኘናቸውን ትሩፋቶች ምስክሮች ናቸው። እናም ዛሬም ቢሆን የሰላሙ ባለቤት የሆነው የአገራችን ህዝብ የሰላሙ መሪና ዳኛ ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት በአገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በርካታ ባለሃብቶችን በመሳብ ላይ ነው፡፡

በዚህም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል፡፡ በዚህም ሳቢያ ቀደም ሲል በምሳሌነት ያነሳኋቸውና አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ነው። ዜጎችንም የስራ ባለቤት አድርገዋል።

እርግጥ አገራችን እየተከተለችው ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ነፃ የመሬት አቅርቦት መዘጋጀቱ፣ የአበባ ማምረቻ ስፍራዎች በመንገድ እና በኤሌክትሪክ እንዲተሳሰሩ መደረጋቸው፣ የታክስ እፎይታ ጊዜ መኖሩ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገራችን እንዲሳቡ ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል።

አገራችን የምትከተለው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር አሁን ለተገኘው የኢንቨስትመንት አመቺነት ምህዳርም ወሳኝ ነው። ዋናው ግን የአገራችን አስተማማኝ ሰላም ይመስለኛል። ያለ ሰላም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አንችልም።

የአገራችን ሀዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታው የሚወሰነው ሀገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሆኑን ስለሚያውቅ ሁሌም ሰላም ወዳድ ኃይሎች ጋር የሚቆም ነው። የሰላምን ጠቀሜታ ስለሚገነዘብም ከምንግዜውም በላይ ሁሌም በየአካባቢው ለሰላሙ  ዘብ ይቆማል።

ህዝቡ በየቀየው ላለው የሰላም ሁኔታ ዋነኛ መሰረት ነው። በዚያ አካባቢ ለሚከሰት ማናቸው የፀረ-ሰላም ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን በመሆኑ ለሰላሙ ይበልጥ መትጋት አለበት።

የሰላምና መረጋጋት እጦት ዕድገትን ያቀጭጫል። በመሆኑም ህብረተሰቡ ለሰላምና መረጋጋት በቂ ትኩረት መስጠት ብቻ ሳይሆን ሰላምና መረጋጋትን ሊያሳጡን ከሚችሉ ጽንፈኛ ሃይሎች ራሱን መጠበቅም ይኖርበታል።

ፅንፈኛ ሃይሎቹ ዋነኛው ግባቸው በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፤ ማንኛውም መንግስታዊ ስራ በመደበኛ መልኩ እንዳይሰራ፤ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲስተጓጎል፤ የንግድ ልውውጥና ግብይት እንዳይኖር፤ ህብረተሰቡ በሰላም ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወር፤ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ወዘተ ለማድረግ እጅግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡  

ከዚህ በተጨማሪም ብዙ ሺህ ዜጎች ሰርተው የሚያድሩበትን ፋብሪካዎች፣ የእርሻ ልማቶች፣ የመንግስት ቢሮዎች፣ የግለሰብ ድርጅቶች፣ በብዙ ሚሊዮን ብር የተገዙ ከባድና ቀላል ተሸከርካሪዎች፣ የህዝብ መገልገያ አምቡላንሶች እንዲወድሙ ሲሰሩ ተመልክተናል፡፡

የእነዚህ ሃይሎች እቅዳቸው ያተኮረው ሀገሪቱ ከድህነት ለመውጣት የጀመረችውን የመሰረተ ልማት ግንባታ ማሰናከል፣ ማጥፋት በተለይም የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታና ሌሎችንም ማስቆም ላይ ያተኮሩ እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

ለዚህ ድርጊታቸው በግንባር የተሰለፉ ሃይሎችን በፋይናንስ፣ በስልጠና፣ በስምሪትና በአማካሪነት በቅርብ የሚረዷቸው እንደ ኤርትራ ዓይነት የሀገራችንን ሰላም ለማወክ ሁሌም የሚሰሩ ሀገሮች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ህዝቡ እነዚህ እውነታዎች መገንዘብ አለበት፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት መርሁ ሰላም ነው። በዚህም ኢንቨስትመንትንና ቱሪዝምን መሳብ ችሏል፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ቱሪዝምም ሆነ ኢንቨስትመንት ሊስፋፉና ሊያድጉ የሚችሉት አስተማማኝ ሰላምና ለዘርፎቹ ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ሲኖር ነው። ይህን ለመፈፀምም በተለይ ህዝቡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሰላሙ ዳኛ ሆኖ ሰላሙን ሲጠብቅ ቆይቷል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላም ይህን ያህል ዋጋ የሰጠው የሞት ሽረት ጉዳይ የሆኑትን ልማትንና ዴሞክራሲን ለማምጣት ያደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል የኋሊት እንዳይቀለበስበት ከመፈለግ ነው።

ሰላም ከቁሳቁስ መጥፋትና መውደም ጋር ብቻ እንደማይያያዝ የሚገነዘበው የአገራችን ህዝብ፤ ነገ የሚገነባው ትልቅ ምጣኔ ሃብት ያለውና ለዘመናት ተነፍጎት የነበረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባት ስር እንዲሰድ ስለሚሻ ነው። ህዝቡ ባገኘው ሰላም ምን ዓይነት ጥቅሞችን እንዳገኘ ያውቃል።

አምባገነኑና የዕዝ ኢኮኖሚ መርህን የሚከተለው የደርግ ሥርዓት ከመውደቁ በፊት የሀገራችን ምጣኔ ሃብታዊ አሃዝ ከዜሮ በታች እንደነበር የማይዘነጋው ይህ ህዝብ ስለ ሰላም ቢናገር የሚበዛበት አይደለም። አምባገነኑ ስርዓት እንደወደቀም በአንድ በኩል ሰላምን የማረጋጋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደቀቀውን ኢኮኖሚ ለማቃናት የከፈለውን ከባድ መስዕዋትነት በሚገባ ይገነዘባል።

ያኔ ተራራ የሚያክለውን የአገሪቱን ድህነት ለመዋጋት የተለያዩ መርሆዎችን ቢሰንቅም የሚፈለገው ዓይነት ለውጥ እንዳልመጣና ለረጅም ጊዜ በሀገራችን ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን የድህነት አዙሪትን ለመቀልበስ እንዳልተቻለ በማወቁ ሌላ መንገድ እንዲቀየስ ማስፈለጉን የሚያስታውስ ህዝብ ነው።

ስለሆነም በአንድ በኩል የሀገሪቱን ሰላም ማረጋጋትና የታጠቁ ሃይሎችን ወደ ልማት የማዞር ስራ፣ በሌላኛው ዘውጉ ደግሞ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን የማምጣትና ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲና ስትራቴጂን እውን ለማድረግ የወሰደው ጊዜና የጠየቀው ሁሉን አቀፍ መስዕዋትነት ከዚህ ህዝብ አዕምሮ ውስጥ የሚጠፉ አይመስለኝም።

ሰላሙም እውን ሆኖ የታሰበው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገብ ሂደት ውስጥ ሁሉም ዜጋ ድህነት በሚባለው አንገት አስደፊ በሽታ ላይ እንዴት እንደዘመተና እስከ አሁነኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ድረስ ምን ያህል ጥቅም እንዳገኘ ያውቃል።

ህዝቡ የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠልና በዚያውም ጎን ለጎንም ዴሞክራሲው አገር በቀል ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲጎለብት የተደረገው ጥረት፤ እንዳለ ሆኖ ይህ ህዝብ በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ውስጥ ከመልካም አስተዳድር ጋር እንዲሁም ፅንፈኛ ኃይሎችና የሀገራችንን መለወጥ የማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካኝነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም ህዝቡ በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዕዋትነት ግልፅ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy