Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላም ንፅፅሮሽ

0 403

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላም ንፅፅሮሽ

ዳዊት ምትኩ

ሰላም በግለሰብ፣ በቤተሰብና በሀገር ላይ የሚያስከትለው ችግር ተዘርዝሮ አያልቅም። ሰላም የሰው ልጅ ወጥቶ ሰርቶ እንዲገባ፣ ቤተሰብ ልጅ ወልዶ ስሞ ለወግ ማዕረግ እንዲያበቃ፣ ልጅን ወደ ለማስተማር፣ የተመረተና የተሰበሰበ ምርት እንዲሰበሰብ፣ ሸቀጥ በገብይት እጦት ምክንያት እንዳይበላሽ የሰላም ዋጋ ከፍተኛ ነው። ይህም ሰላም በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ያለው ቦታ የማይተካ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

በአንፃሩም ሰላም ከሌለ ማናቸውም ነገር ይጠፋል፣ ህይወትን በአግባቡ አለመምራት ብቻ ሳይሆን ክቡሩን ህይወት እስከማጣት የሚደርስ አደጋ መከተሉ አይቀርም። የሰላም መኖርና አለመኖር ንፅፅሮሽ ሁለት የማይገናኙ ነገሮች ቢሆኑም፤ ንፅፅሩን መመልከት የሰላም መኖርን ውድነት እንድናውቅ ያደርገናል።

ከሀገራችን ህዝብ በላይ የሰላምን ጥቅም በሚገባ የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም። ላለፉት 27 ዓመታት በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ውስጥ ያገኘውን የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን ጠንቅቆ ያውቃልና። እናም ስለ ሰላም ሲነሳ የመጀመሪያውና ቀዳሚው እማኝ ሊሆን የሚችለው የሀገራችን ህዝብ ይመስለኛል።

እርግጥ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በውጭ ሃይሎችና በሀገራችን የውስጥ ተላላኪዎቻቸው ቅንጅታዊ እኩይ ሴራ ሁከት ተፈጥሮ ነበር። ሁከቱን በቁጥጥር ስር ማዋል እንዲቻልም በህገ መንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቷል። ይህ አዋጅም በወቅቱ ሰላሙን ተነጥቆ በነበረው የየአካባቢዎቹ ህዝቦች በባለቤትነት ስሜት ድጋፍ ያለው ስለነበረ ከፍተኛ ውጤት ማግኘት ተችሏል።

በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተፈጠረውን ሁከት በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። የሁከቱ ተሳታፊ የነበሩ ወገኖችም የተሃድሶ ትምህርት ወስደው በሁለት ዙሮች ተመርቀዋል። በሁከቱ ወቅት የበደሉትን ህዝብ ለመካስ ቃል በመግባትም ወደ የመጡበት አካባቢዎች ተመልሰዋል። በቅድሚያ እነዚህን አጥፊ ዜጎች በመጠቆምና ለእርምት ወደ ተሃድሶ ማዕከሎች እንዲገቡ በማድረግ ረገድ የህዝቡ የማይተካ ሚና እዚህ ላይ ሊደነቅ የሚገባው ይመስለኛል። በአሁኑ ወቅት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም አንፃራዊ ሰላም ተገኝቷል። ለዚህ ሰላም መገኘት ህብረተሰቡ እያበረከተ ያለው ሰላምን የመጠበቅ ተግባሩ ሊመሰገን ይገባዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ያለው አዋጅ በአመዛኙ በየቦታው ለታየው ሁከት፣ ረብሻና ስርዓት አልበኝነት ዋነኛ ምክንያቶችን በመግታት፤ ሀገራችንና ህዝቦቿ ወደ ነበሩበት ጭስ አልባው የቱሪዝም ኢንዱስትሪና አሁንም ድረስ ያልቆመው የኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያደርግ እንጂ እነዚህን የልማት ዘርፎች የሚያላላ አይደለም።

ለቱሪዝም ፍሰት እና ለኢንቨስትመንት መስፋፋት የሰላም መኖር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። በአንድ ሀገር ውስጥ ቱሪዝምም ሆነ ኢንቨስትመንት ሊስፋፉና ሊያድጉ የሚችሉት አስተማማኝ ሰላምና ለዘርፎቹ ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ሲኖር ነው። ከዚህ አኳያ ባባፉት 27 ዓመታት መንግስትና ህዝቡ የሀገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ የሰላም መሰረት ላይ ለማቆም ባረደጉት ጥረት እንዲሁም መንግስት ለቱሪዝምም ሆነ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫን በመከተሉ፤ ሁለቱም ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ እመርታ አሳይተዋል።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሀገራችን ሰላማዊ ሆናለች። ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገቧና የነገ ራዕይዋ ከወዲሁ እየታየ በመሆኑም የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች መዋዕለ ነዋያቸውን ሀገራችን ውስጥ በማፍሰስ አብረውን ለማደግ ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛሉ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለቱሪስቶችና ለኢንቬስተሮች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል እንጂ አያውክም። ቱሪስቱ ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ወደ ሀገራችን ለጉብኝት ሲመጣ፤ ሀገሪቱ ውስጥ አስተማማኝ ሰላም መኖሩን አረጋግጦ ነው። እርግጥ ይህ ሰላም ላለፉት 25 ዓመታት በጥሩ መሰረት ላይ የተገነባ በመሆኑ እንደ ደንቡሽት ቤት በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሚፈራርስ አይደለም። ምንም እንኳን በየትኛውም ማህበረሰብ ውሰጥ ሰላም ያለው እሴታዊ ዋጋ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ያላቸው ሀገራት ሰላማቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሲደፈርስ ብሎም በትርምስና ሁከት ውስጥ ሲቆዩ የተመለከትናቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም።

ከእኛ ሀገር አንፃር ግን ሰላማችን ሲጀመር የተገነባው በህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ በቀላሉ ሊናጋ የሚችል አይመስለኝም። ሆኖም ልክ እንደ አለፈው አንድ ዓመት ሰላማችን የመሸራረፍ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሰላሙ ባለቤቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆናቸው በቀላሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ድንጋጌዎችን በማውጣት መጠገን ይቻላል፤ እየተቻለም ነው። ይህም ወደ ሀገራችን መምጣት ለሚፈልጉ ቱሪስቶች አስተማማኝ ዋስትናን ይሰጣል።

ኢንቬስተሮችም በአዋጁ ዋስትናቸው በአስተማማኝ ሁኔታ የሚረጋገጥ ይመስለኛል። በስራቸው ላይ የሚፈጥረውም ተፅዕኖም ሊኖር አይችልም—ሰላምን ይበልጥ አስተማማኝ በማድረግ መዋዕለ ነዋያቸውን ይበልጥ እንዲያፈሱ ያነሳሳቸዋል እንጂ። ያም ሆኖ ሰላም ስላለ ኢንቬስተሮች የመጣሉ፤ ከሌለ ደግሞ አይመጡም። ይህም ወደ ድህነት እንድናመራ ምክንያት ይሆናል።

ሰላም ከሌለ ምንም ዓይነት የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት አይቻልም። የሁከት ሃይሎች ይነግሳሉ። ሁከት ይቀጣጠላል። በተሳሳተ አቅጣጫ የሚጓዝን ዜጋ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ተሳታፊ ይሆናል። ሚዛናዊነትን አይኖርም። ስሜታዊነትን ይነግሳል። የጥፋት አውድም ይፈጠራል። ጥፋቱ ግን የህዝቡን ክቡርና የማይተካ ህይወት ከመንጠቅ ባሻገር ሃብቶቹንና መጠቀሚያዎቹን ሁሉ ያወድማል። ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲያጤኑት ግን ቁጭትን ይፈጥራል።

የሁከት ኃይሎቹ ያላቸውን የቅጥፈትና የአሉባልታ አቅማቸውን ሁሉ አሟጠው በመጠቀም ህዝቡ ላለፉት ዓመታት ህዝቡ ከሰላም ያገኛቸውን ትሩፋቶች ይነጥቁታል። እነርሱ በዚህም ይሁን በዚያ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ጥቅም እስካሳካላቸው ድረስ እዚህ ሀገር ውስጥ የፈለገው ቢሞትና ንብረቱ ቢወድም ጉዳያቸው አይደለም። ባህር ማዶ ሆነው የሚለኩሱት እሳት ወላፈኑ በእነርሱና በልጆቻቸው ላይ እንደማይደርስ ስለሚያውቁ፤ እሳቱ ሀገር ውስጥ ማንንም ቢያቃጥል ከምንም አይቆጥሩትም። በተገላቢጦሹ በሚፈጠረው የሞትና የንብረት ውድመት እየተደሰቱ በማህበራዊ ሚዲያው ያስተጋባሉ።

የሁከተኞቹ ዓላማ ሁለት ይመስለኛል። አንደኛው፤ ሃይሎቹ ከዚህ ቀደም ሀገር ውስጥ በነበሩበት ወቅት በከሰረ ፖለቲከኝነታቸውና በፀረ-ህገ መንግስታዊነታቸው በህዝብ የተተፉ በመሆናቸው ሳቢያ በህዝቡ እምቢተኝነት ያጡትን ስልጣን በሁከትና በብጥብጥ ለመያዝ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ፤ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ዕድገትና የልማት ጎዳና ማየት የማይሹ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች እያዘዟቸውና ገንዘብ በገፍ እያሸከሟቸው ሰላማችንን እንዲያደፈርሱ ታዘው በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆች ሁከትን መቀመር ነው።

እነዚህ ጥቂት ሃይሎች ይህን ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ እዚህ ሀገር ውስጥ በስውር ያደራጇቸው የጥፋት ቀማሪዎች የሉም ማለት አይቻልም። ይሁንና በመንግስት በኩልም መልካም አስተዳደርንና ሌሎች የህዝቡን እርካታ የማያረጋግጡ ምክንያቶች በወቅቱ ተገቢ ምላሽ አለመሰጠቱ የሁከት ኃይሎቹን ፍላጎት በማገዝ ረገድ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። በአሁኑ ወቅት እንዲህ ዓይነቶቹን ክፍተቶች ለመሙላት መንግሥት ከህዝቡ ጋር ተነጋግሮ አቋም የወሰደ ቢሆንም፤ ዋናው ጉዳይ ለሰላም ማሰብ ነው። ሰላም የሁሉም ጉዳዩች መሰረት ስለሆነ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy