Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የስልጣን ተሸባቢዎቹ…

0 268

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የስልጣን ተሸባቢዎቹ…

                                                     ዘአማን በላይ

ከመሰንበቻው በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የባህር መዝገብ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱት ሰማያዊና መኢአድ የተሰኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው ላይም የስርዓት ለውጥ እንዲኖርና ለዚህም የሽግግር መንግስት መቋቋም እንዳለበት ጠይቀዋል። ርግጥ ፓርቲዎቹ ሚዲያ ጠርተው ያሻቸውን እንደፈለጉ መግለፃቸው፤ ህገ መንግስቱና ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ያጎናፀፋቸው መብት በመሆኑ ምንም ዓይነት ችግር የለውም።

ሆኖም በእኔ እምነት ችግር ሊሆን የሚችለው፤ ህገ መንግስቱን በውል ተገንዝቦና አክብሮ እንደሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲ የሚገልፃቸው ማናቸውም ጉዳዩች ህገ መንግስቱን የሚጋጩ ከሆነ ነው። ከዚህ አኳያ የሰማያዊና የመኢአድ የጋራ መግለጫ፤ በአንድ በኩል፣ በህገ መንግስቱ የተቋቋምኩና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብሬ ነው የምንቀሳቀሰው እያሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሽግግር መንግስት በመተካት መልሶ ህገ መንግስቱን የሚሣረር ሆኖ አግኝቸቼዋለሁ። እናም እንዲህ ዓይነቱ ሁለት እግር ስላለ ብቻ ሁለት ዛፍ ለመውጣት የመፈለግ ሃሳብ ህገ መንግስታዊ አለመሆኑን ማስገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

እንደ ሰማያዊና መኢአድ ያሉ አንዳንድ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ነገር ሁሌም ግርም እንዳለኝ ነው። በተስፋ ተሸብበው ለስልጣን የሚያሳዩት ጉጉትም ግርም ይለኛል። ዳሩ ግን እነዚህን መሰል ተቃዋሚዎች በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ውስጥ የመደራጀት መብታቸው ተከብሮ እንደ ተቃዋሚ ሁለት እግራቸውን ሰድደው የሚንቀሳቀሱት በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሆኑን እንኳን ለማወቅ የሚፈልጉ አይደሉም። የሚሰጡት አስተያየት እንኳን ለሀገር ምን ያህል ይበጃል ተብሎ ከግምት ውስጥ አይገባም። እናም በራሳቸው ‘የትም ፍጪው ስልጣኑን ብቻ አምጪው’ ሽበባ ውስጥ ሆነው፤ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር “እብድና ዘመናይ ያሻውን ይናገራል” እንደሚባለው የፈለጉትን ይናገራሉ። ንግግራቸው ደግሞ ህግና ስርዓትን ከቶም የሚያውቅ አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ህግና ስርዓቱ አይፈቅም እንጂ፤ የስርዓት ለውጥ ይምጣ ቢባል እንኳን፣ አምጪው ማን እንደሆነና ጉዳዩን እንደምን እንደሚከውነው በእነ ሰማያዊና መኢአድ ቤት ግንዛቤው ያለ አይመስልም። ወይም በራሳቸው የስልጣን ፍላጎት ተሸብበው አውቀው የተኙ ናቸው ማለት ይቻላል።

ታዲያ ይህን ውስጣዊ ፍላጎታቸውን መግለጫ በሰጡበት ወቅት ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ነግረውናል። ጋዜጠኞች “ሀገር ተረክቦ ለመምራት ምን ያህል ብቁ እና ዝግጁ ናቸሁ?” ብለው ሲጠይቋቸው፤ በገዛ ሀገራቸው ውስጥ የስልጣን ባለቤቶች እነማን እንደሆኑና ስልጣን እንዴት እንደሚገኝ የማያውቁት ሰማያዊና መኢአድ “…እነሱ ለማስረከብ ዝግጁ ከሆኑ በኛ በኩል ምንም ችግር የለብንም” በማለት በአቋራኝ የስልጣን ኮርቻ ላይ ለመፈናጠጥ ያላቸውን ፍላጎት ግልፅ አድርገዋል። እንዲያውም የሰማያዊ ፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ በሚያስገርም ሁኔታ “ሰማያዊ ፓርቲም ይሁን መኢአድ ከዚህም አልፎ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ጭምር ስልጣን ለመረከብ ዝግጁ ነን” ሲሉ ተደምጠዋል። መቼም እንዲህ ዓይነቱ ፍላጎት ‘አስቂኝም፣ አስገራሚም’ ከማለት ውጭ ሌላ ምንም ሊባል የሚችል አይመስለኝም።

ያም ሆኖ ከፓርቲዎቹ መግለጫ ሁለት ህግና ስርዓትን የማያውቁ አስተሳሰቦችን መመልከት ተገቢ ይመስለኛል። አንደኛው፤ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን ሰጪውም ሆነ ነሺው ማን እንደሆነ በቅጡ አለመገንዘብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ፤ የሰማያዊ ፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ “….በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ጭምር ስልጣን ለመረከብ ዝግጁ ነን” በሚል ከእኛ ባሻገር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ስልጣን ለመያዝ ተዘጋጅተዋል በማለት ያቀረቡት ሌላ ተደማሪ ትርጉም ያለው አስተሳሰብ ነው።  

እንደሚታወቀው በህገ መንግስቱ አንቀፅ 8 ላይ በግልፅ እንደተደነገገው፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዚህች ሀገር ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች ናቸው። ይህን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግም ወይም ሰማያዊና መኢአድ አሊያም ሌላ ፅንፈኛ ሃይል ሊጥሰው አይችልም። መብቱ የስልጣን ባለቤቶቹ ብቻ ነውና።

በዚህ መሰረት ላለፉት አምስት ምርጫዎች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦችም የተሰጣቸውን ህገ መንግስታዊ መብት ተጠቅመው የስልጣን ባለቤትነታቸውን በሚገባ አረጋግጠዋል። በየአምስት ዓመቱ በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫም ይሁን በየበየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው የአዲስ አበባና የማሟያ ምርጫ “ለሁለንተናዊ ዕድገቴ ይበጀኛል” ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ሲመርጡ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የፖለቲካ የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማጠናከር የፖለቲካ ኃይሎች እና መላው ህዝብ ያሳየው ርብርብ ሳይጠቀስ አይታለፍም። ይህም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን በህዝብ ይሁንታ እንጂ “እነርሱ ከሰጡን እኛ ልንቀበል ዝግጁ ነን” እየተባለ አንዱ ለሌላኛው በችሮታ የሚለቀው ጉዳይ አይደለም። ህዝቡ ሳያውቀው ‘ከሰጡኝ ወስዳለሁ’ ብሎ ማሰብም ኢ-ህገ መንግስታዊ ነው። ፖሊሲንና ስትራቴጂን ለህዝቡ ሳያሳውቁ፣ ህዝቡን ሳይቀሰቅሱና ሳይወዳደሩ እንዲሁም በህዝቡ ይሁንታ ሳይመረጡ አዲስ አበባ ቁጭ ብሎ “ስጡኝና እወስዳለሁ” በሚል በአቋራጭ የስልጣን እርካብ ላይ ለመቆናጠጥ የሚነዛ ወሬ በእውነቱ አስቂኝና አሳፋሪ ነው።

ኢህአዴግም ቢሆን ልስጥ እንኳን ብሎ ቢያስብ፤ ህዝቡ በአግባቡ እንዲያስተዳድረው የሰጠውን የኮንትራት ስልጣን ለማንም መስጠት አይችልም። ህጋዊ መብት የለውም። ህገ መንግስቱንም መቃረን ነው። ይህን አደርጋለሁ ብሎ ቢያስብ እንኳን መልሶ የሚጋጨው ከመረጠው ህዝብ ጋር ይሆናል።

ያም ሆኖ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚቻለው እንደ ሰማያዊና መኢአድ ዓይነት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲኖሩ እንደሆነ ግልፅ ይመስለኛል። ይህም የፖለቲካ ኃይሎች በሚያፈልቋቸው መሰረታዊ ሃሳቦች እየተመረኮዙ ህዝቡ ይበጀናል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ እንዲያስችለው ዕድል የሚሰጥ ነው። ታዲያ ይህን መነሻ በማድረግ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እየተደራደረ ነው። በድርድሩም በተለያዩ ህጎችን አሻሽሏል።

ሰማያዊና መኢአድም የሀገራችን ህገ መንግስት በሚፈቅደው መሰረት በመደራጀት አጀንዳቸውን ለህዝቡ ዴሞክራሲያዊ በሆነና በሰለጠነ አካሄድ ይፋ በማድረግ መመረጥ የሚችሉበትን አሰራር በመከተል ገንቢ አስተያየት በመስጠት የጠነከረ የዴሞክራሲ ባህልን ማዳበር ሲገባቸው አንድ ነገር ኮሽ ካለ “ስልጣን ከሰጡኝ እይዛለሁ” በሚል የህልም ዓለም ዲስኩር ለማሰማት መሞከራቸው ያሉበትን የፖለቲካ ምህዳር እንኳን የሚያቁ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በህገ መንግስቱ ውስጥ ሆኖ መልሶ ህገ መንግስቱን መቃረን መሆኑን መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል።

በእነ ሰማያዊ መግለጫ ላይ የተጠቀሰውና “…እኛና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስጣን ለመያዝ ዝግጁዎች ነን” የሚለው ሃሳብ ጥርጣሬን የሚጭር ነው። ይኸውም “ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እነማን ናቸው?” ብዬ ጥያቄ እንዳነሳ ስለገፋፋኝ ነው። በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ለዚህች ሀገር የዴሞክራሲያዊ ስርዓት የበኩሉን ሚና አይጫወትም ባይባልም፤ እንክርዳዱን ከገብሱ መለየት ግን የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

ሰማያዊ ፓርቲም በቅድሚያ መተማመን ያለበት እዚህ ሀገር ቤት ውስጥ ባለው መራጭ ህዝብ እንጂ በምርጫው ቀጥተኛ ተሳታፊ ባልሆነው በውጭ በሚኖረው ኢትዮጵያዊ መሆን የለበትም። በውጭ ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ ውስጥ ጥቂቶቹ ፅንፈኞች መሆናቸውን አምናለሁ—አብዛኛዎቹ የዚህን ሀገር ፖለቲካ ጠንቅቀው የሚያውቁ ቢሆንም። እነዚህ ውህዳን ወገኖች ገሚሶቹ የቀድሞ ስርዓት ባለሟሎች የነበሩ፣ አንዳንዶቹ የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪ በመሆን የሚሰሩ፣ ሌሎቹ ደግሞ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በማናቸውም መንገዶች ለመጣል በጀት ተመድቦላቸው የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

ምናልባት ሰማያዊ ፓርቲ “በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን” የሚላቸው እነዚህን ከሆነ፤ ይህ ከባድ ጥፋት መሆኑን መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም እነዚህ ወገኖች ህገ መንገስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመቃወም የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ነው። እናም ሀገር ቤት ያለውን መራጩን ሀዝብ ወደ ጎን ብሎ ከእነዚህ ፀረ ህገ መንግስት ኃይሎች ጋር ለመሞዳሞድ መሞከር ህገ መንግስቱን ከመፃረር በላይ ወንጀልን በሰከነ መንገድ መገንዘብ ያለበት መሆኑን እንደ ዜጋ ልጠቁመው እወዳለሁ፤ በተለይ የሃሳቡ ባለቤት የሆነውን ሰማያዊ ፓርቲን።

በጥቅሉ ‘የስርዓት ለውጥ’ የሚባለውና ‘የሽግግር መንግስት ይመስረት ጥያቄ’ በየትኛውም መንገድ ተቀባይነት የሌለውና ህገ መንግስቱን ያልተከተለ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው ህዝቡ ለገዥው ፓርቲ በምርጫ 2007 ዓ.ም ለአምስት ዓመት የሚቆይ የኮንትራር ስልጣን ሰጥቶታል። ይህ የስልጣን ጊዜ አምስት ዓመት የሚፈጅ ነው። በዚህ መሐልም የሽግግር መንግስት ይቋቋም ብሎ አልጠየቀም። ህዝቡ ይህን ባላለበት ሁኔታ ሰማያዊና መኢአድ የህዝቡን ስልጣን በአቋራጭ በመንጠቅ ስለ ሽግግር መንግስት የሚያወሩበት ምንም ዓይነት ህጋዊ መሰረት የላቸውም። አይችሉምም። በሌላ አገላለፅ፤ ስለ ስርዓት መለወጥና አለመለወጥ የእነርሱ ጉዳይ ሊሆን አይችልም። የስልጣን ጥማትን ለመወጣት ሲባል የህዝብን ሉዓላዊ መብት መጋፋት አንዳችም ህገ መንግስታዊ መሰረት የለውም። በሀገራችን ውስጥ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተመራጭ እንጂ መራጭ አይደለም። መራጭ ባልሆነበት ሁኔታ ወደ ውጭ ሳያማትር መራጩን ህዝብ ይሁንታ ይጠይቃል እንጂ በሃሳብም ቢሆን እርሱ ራሱ አዛዥና ናዛዥ ሊሆን አይችልም። እናም በስልጣን ፍላጎት የተሸበቡ እንደ ሰማያዊና መኢአድ ዓይነት ፓርቲዎች ይህን እውነታ ሊገነዘቡት ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy