የቦርዱ መንገድ
ዳዊት ምትኩ
አገራችን ያወጀችው የአስቸከይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል። የቦርዱ ተደራሽነት በመላው አገራችን ሲሆን፤ ቦርዱ የሚደርሰውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ ችግሩ የተፈጠረበት ቦታ ድረስ በመሄድ ምርመራ ያደርጋል። ለዚህም ከኅብረተሰቡ ጥቆማ በተጨማሪ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግባቸውን ተጨማሪ ሥልቶችን ይከተላል። የክትትልና ቁጥጥር ሥራው አዋጁ በፓርላማው ከመፅደቁ በፊት ያሉትን 15 ቀናት የሚያካትት ነው።
ቦርዱ የዛሬ ዓመት የነበረውን ተሞክሮ በማዳበር በይበልጥ ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ ይሰራል። ኅብረተሰቡ በማንኛውም አካባቢ ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ከተፈጸመ፣ ከቦርዱ በተጨማሪ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀጥታ ሊያቀርብም ይችላል። ቦርዱ የሚከተለው መንገድ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምናልባት የተጣሱ መብቶች ካሉ በማጣራት እርምጃ እንዲወሰድ የሚያደርግ ስለሆነ፤ ህብረተሰቡ ከቦርዱ ጋር በቅርበት መስራት ይኖርበታል።
ይህ ማለት ግን ቦርዱ የተቋቋመው ስርዓቱ ራሱን በራሱ ለማረም በማሰብ እንጂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መብትን ስለሚጋፋ አይደለም። እንደሚታወቀው ሁሉ በዴሞክራሲያዊ ሀገሮች ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩት ሌሎች አካላትን ለማስደሰት ሲባል አይደለም። እነዚህ መብቶች ዜጎች ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚጎናፀፉት መብቶች እንጂ በአዋጅ የሚነጠቋቸው ቁሳቁሶች አይደሉም። እነዚህ መብቶች በህገ መንግስቱ ውስጥ የተካተቱና ላለፉት 27 ዓመታት ዕውን እየሆኑ የመጡ ናቸው። ይህን ሃቅ ፅንፈኞች ሊያጣምሙት ቢችሉም እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው ህዝብ በሚገባ ይገነዘበዋል።
ምንም እንኳን በመንግስት ውስጥ ያሉት ፈፃሚዎች ሰው በመሆናቸው መብቶቹ ያለ አንዳች ሳንካ ተፈፃሚ ሆነዋል ሊባል ባይችልም፤ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት አፈፃፀሞች እንዳይጣሱ ብርቱ ቁጥጥር እየተደረገ ነው። ሰዎች በማንኛውም ስራዎች ውስጥ መሳሳታቸው ነባራዊ በመሆኑ በዚህም መስክ አልፎ…አልፎ ስህተት መኖሩ የሚቀር አይመስለኝም።
ግና እነዚህን ጥቂት የአስፈፃሚዎች ስህተት ለመቆጣጠር የሚያስችል በቂና ለህብረተሰቡ መብቶች ጥብቅና የቆመ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ አለ። ይህ ጥበቃ በአዘቦትም ይሁን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። እናም አዋጁ የዜጎችን መብት የገደበ ነው የሚለው የሁከትና የብጥብጥ ናፋቂዎች ቅጥፈት ቦታ የሚሰጠው አይደለም።
ለነገሩ አንድ አዋጅ ሲታወጅ ለአጠቃላዩ ህዝብ ደህንነትና መብቶች በመከበር ብሎም ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በማሰብ እንጂ ሌላ የተለየ ዓላማን በመያዝ አይደለም። ሰዎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል በመሆናቸው የየትኛውንም የህብረተሰብ ክፍል እንቅስቃሴን ለመገደብ ተብሎም አይወጣም። “የእኩልነት መብት” በሚለው የህገ መንገስቱ አንቀፅ 25 ላይ፤ “ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በህግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል።…” በሚል የተደነገገው ጉዳይም ዜጎች መብቶቻቸው ሳይሸራረፉ በህግ የተጠበቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።
አዋጁ የተቃዋሚንም ይሁን የደጋፊን እንቅስቃሴ ለመገደብ የወጣ አይደለም። ምክንያቱም ከላይ የጠቀስኩት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚመለከት ስለሆነ ነው። እናም እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ያለአንዳች ስጋት እንዲንቀሳቀስ የሚፈቅድ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
ሆኖም ፅንፈኞቹና ሁከት ናፋቂዎቹ የለሌለን ነገር ቆርጠው የሚቀጥሉት ያለምክንያት አለመሆኑን መረዳት ይገባል። ይኸውም በአሁኑ ወቅት አጀንዳቸው ሁሉ አልቆ ተነጠልጥለው የሚገኙት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ በመሆኑ ነው። እዚህ ሀገር ቤት ውስጥ በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ በመተግበር ላይ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መልሰው ‘የህብረተሰቡን መብት እየገታ ነው’ በማለት የዓይኔን ግንባር ያድርገው ዲስኩር የሚያስደምጡንም የአጀንዳ እጥረታቸውን ለመሸፈን ነው።
ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ የእነርሱ ቅጥፈት “ዓይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ” የማለት ያህል መሆኑን ስለሚያውቅ ፍላጎታቸው ሊሳካ እንደማይችል መረዳት አለባቸው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሉባልታ የሚነዳ ህዝብ የለም።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የህዝቦችን ሰላም የሚያረጋግጥ ነው። አዋጁ መብትን የሚያፍን ሳይሆን በአገራችን የተፈጠረውን ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈትቶ ሰላምን ለማምጣት ነው። አዋጁ የኢትዮጵያን ዕድገት ማየት የማይሹና ሀገራችንና ህዝቦቿ ወደ ነበሩበት የድህነት ታሪክ ተመለስው እንዲገቡ ፍላጎት ያላቸው ሀገራትና ኃይሎች ከሀገራችን አሸባሪዎችና አንዳንድ ፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ጋር ለጥፋት ተቀናጅተው በመስራት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በፈጠሩት ሁከት ሳቢያ የዜጎች ህይወት በመጥፋቱ፣ አካል በመጉደሉና ንብረት በመውደሙ ብሎም አገራችን ወደ ትርምስ እንዳትገባና የጀመርነው ፈጣን ልማትና ፍትሐዊ የህዝብ ተጠቃሚነት ደብዛው እንዳይጠፋ በማሰብ የታወጀ ነው።
አገራችን ወደ ለየለት ብጥብጥና ዝርፊያ ከመግቧቷ በፊት፣ እኛም እንደ ሌሎች አገሮች አልባ ዜጎች እንዳንሆን የተተገበረ እንጂ ሆን ተብሎ የዜጎችን መብቶች ለማፈን የታወጀም አይደለም። ቦርዱ በዚህ አሰራር ውስጥ አላስፈላጊ ጥሰቶች እንዳይኖሩ ስራውን ጀምሯል።
ቦርዱ በህገ መንግስቱ ተለይተው የተሰጡት መብቶች አሉ። እነርሱም መርማሪ ቦርዱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የታሰሩትን ግለሰቦች ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ የማድረግ ስልጣንና ተግባር ያለው ሲሆን፥ የታሰሩበትን ምክንያትንም ይገልፃል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብዓዊ እንዳይሆኑ የመቆጣጠር እና የመከታተል ተግባርንም ያከናውናል።
ማናቸውም የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ ኢሰብዓዊ መሆኑን ሲያምንበት መርማሪ ቦርዱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት እርምጃውን እንዲያስተካክል ሀሳብ ይሰጣል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈፅሙትንም ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ መርማሪ ቦርዱ ለሚመለከተው ያሳውቃል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቀጥል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀረብም ያለውን አስተያየት ለምክር ቤቱ ያቀርባል። ይህም ከላይ እንዳልኩት በአዋጁ ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለማጣራት ያስቸለዋል። የቦርዱ ተግባር በአጭር ጊዜ ውስጥ በሰላም ወዳዱ ህዝብ ተቀባይነት አግኝቷል።
ይሁን እንጂ የውጭ ፅንፈኛ ኃይሎችም ይሁኑ የሀገር ውስጥ አምሳያዎቻቸው፤ ህዝቡ የሰላሙ ባለቤት ሆኖ ሀገሩን ከሁከት ኃይሎች ለመከላከል በጥቆማና በማጋለጥ ስራ እያከናወነ ያለውን ተግባር በመመልከት፤ ይህን ህዝባዊ ድጋፍ ዓይቶ ብስጭት ውስጥ በመግባት ሰበብ አስባቦችን በመደርደር ለማስተጓጎል እየሞከሩ ነው።
በአሁኑ ወቅት ህዝቡ አዋጁ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የማይጋፋ እንዲሁም ማንኛውንም ሰው በእኩል ዓይን የሚመለከት መሆኑን በመገንዘቡ አዋጁን ደግፎ የሁከት ተሳታፊዎችን እየጠቆመና እያጋለጠ ነው። እናም ይህን ህዝባዊ ድጋፍ በተራ አሉባልታ ሊቀየር የሚችል አይደለም።