Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቻይና ኩባንያ በኦጋዴን ነዳጅ አገኘ

0 733

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በሶማሌ ብሔራዊ ክልል በኦጋዴን ተፋሰስ ውስጥ በነዳጅ ፍለጋና ልማት ሥራ የተሰማራው ፖሊጂሲኤል የተባለው የቻይና ኩባንያ የተፈጥሮ ጋዝና ዘይት ክምችት እንዳገኘ ታወቀ፡፡

በ2005 ዓ.ም. ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር የነዳጅ ፍለጋና ልማት ስምምነት ተፈራርሞ በኦጋዴን ተፋሰስ ውስጥ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ሲያካሂድ የቆየው ፖሊጂሲኤል፣ ካሉብና ሂላላ በተባሉ ሥፍራዎች የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለማልማት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ዴኤታ ኮአንግ ቱትላም (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ፖሊጂሲኤል በካሉብ አካባቢ በቆፈራቸው ጉድጓዶች ተጨማሪ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አግኝቷል፡፡ ቀድሞ የነበረውን የጊዜ ክምችት መጠን ለማረጋገጥ በቆፈራቸው ጉድጓዶች ተጨማሪ የጋዝ ክምችት ማግኘቱን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡

‹‹ቀደም ሲል የነበረው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ወደ 4.7 ትሪሊየን ኪዩቢክ ጫማ ነበር፡፡ አሁን ግን ፖሊጂሲኤል ባከናወናቸው ሥራዎች የክምችቱ መጠን ስምንት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ እንደሆነ ማረጋገጥ ተችሏል፤›› ብለዋል፡፡

ፖሊጂሲኤል ከተፈጥሮ ጋዝ በተጨማሪ ሂላላ በተባለው አካባቢ የተፈጥሮ ዘይት ክምችት እንዳገኘ አስረድተዋል፡፡ ኩባንያው በቆፈረው አዲስ የፍለጋ ጉድጓዶች የተፈጥሮ ዘይት ማግኘቱን አክለዋል፡፡ ‹‹ኩባንያው በቆፈራቸው ጉድጓዶች ውስጥ የተወሰነ የተፈጥሮ ዘይት አግኝቷል፡፡ ሆኖም መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ አሁን መግለጽ አንችልም፡፡ ምክንያቱም የኩባንያው ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት የተፈጥሮ ዘይት ክምችቱ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ለመለየት ጥናት በማድረግ ላይ በመሆናቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ከፍተኛ የፔትሮሊየም ጂኦሎጂስት ኦጋዴን ውስጥ የተፈጥሮ ዘይት ሲገኝ የመጀመርያ ጊዜ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1973 ቴኔኮ የተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ ሂላላ አካባቢ አነስተኛ መጠን ያለው የተፈጥሮ ዘይት ክምችት ማግኝቱ የገለጹት ባለሙያው፣ በኤልኩራን አካባቢ የዘይት ፍሰት መታየቱን አስታውሰዋል፡፡ በ1970ዎቹ እና 1980ዎቹ በኦጋዴን የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ሲያካሂድ የነበረው ስፒ የተሰኘው የቀድሞ ሶቭየት ኅብረት ኩባንያም በተለያዩ ቦታዎች የዘይት ምልክቶች እንዳገኘ ይታወቃል፡፡ የፔትሮሊየም ባለሙያው ፖሊጂሲኤል ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂ ይዞ በመምጣቱና ባካሄዳቸው ዘመናዊ የከርሰ ምድር ጥናቶች (ሴይስሚክ ሰርቬይ)፣ አሜሪካውያንና ሩሲያውያን ያላገኙትን ክምችት ለማግኘት እንደቻለ ገልጸዋል፡፡

‹‹ቻይናውያን ያገኙት አዲስ ስትራክቸር ሳይሆን በነበረው ላይ በተለየ ተጨማሪ ክምችት ነው ያገኙት፡፡ አሜሪካውያኑ አነስተኛ መጠን ያለው ዘይት ነው ብለው ንቀው የተውቱን ቻይናውያኑ በጥልቀት በመቆፈር የተሻለ መጠን ያለው ነዳጅ ሊያገኙ ችለዋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የተገኘው ውጤት መልካም ዜና ነው፤›› ያሉት ባለሙያው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቱ መጠን በእጥፍ መጨመሩን ገልጸው፣ የተፈጥሮ ዘይት ክምችቱን መጠን ለማወቅ የተለያዩ ሳይንሳዊ ጥናቶች መሠራት የሚኖርበት በመሆኑ፣ መጠኑ ይህን ያህል ነው ብሎ ከወዲሁ ለመንገር እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

ፖሊጂኤሲል በካሉብና በሂላላ የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለማልማት የተለያዩ ሥራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ኩባንያው የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ጂቡቲ ወደብ ድረስ በመዘርጋት፣ ከወደቡ አቅራቢያ በሚገነባው ማቀነባበሪያ የጋዝ ምርቱን ወደ ፍሳሽ በመቀየር ወደ ቻይና የመላክ ዕቅድ እንዳለው ይታወቃል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ፖሊጂሲኤል የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ዝርጋታ ለማካሄድ የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮጵያና ከጂቡቲ መንግሥታት ጋር እንደተፈራረመ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያና የጂቡቲ መንግሥታት ድርድር በማካሄድ ላይ እንደሆኑ ገልጸው፣ ስምምነቱ እንደተፈረመ ፖሊጂሲኤል ግንባታውን እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡

እስከዚያ ኩባንያው የተለያዩ የዝግጅት ሥራዎች በማከናወን ላይ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በ2021 ዓ.ም. የጋዝ ኤክስፖርት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy