Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአርአያነታችን መገለጫ

0 276

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአርአያነታችን መገለጫ

                                                        ታዬ ከበደ

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቀነስ የሚያስችል የአምስት ዓመት ስምምነት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ልማት ፕሮግራም ጋር በቅርቡ ተፈራርማለች። የስምምነቱ መርሃ ግብር ዘላቂ የሆነ የአካባቢ ልማት ፕሮግራም በመተግበር የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል ነው። በአሁኑ ጊዜ አገራችን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው። በዚህም እ.ኤ.አ በ2030 ዓ.ም ወደ አካባቢ አየር የሚለቀቀውን የካርበን መጠን ዜሮ ለማድረስ የምታደርገው ጥረት ለሌሎች የአፍሪካ አገራት አርአያ አድርጓታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ የምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር፤ ለአካባቢ ተስማሚ መሆኑን በተጨባጭ የተገኙ ውጤቶች ህያው ምስክር ናቸው፡፡ ማንኛውም ሀገር ሁኔታዎችን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለመጣጣም መፈታት ያለባቸውን ችግሮች መዘርዘርና መፍትሄ ማፈላለግ ግድ ይለዋል፡፡

ተስማሚ የሆነ፣ የስራ ዕድልን የሚፈጥር፣ ምርትንና ምርታማነትን የሚያሳድግ የአካባቢ መራቆት ሂደትን የሚከላከል፣ የአካባቢውን ለልማት የሚውል ዕቃና አገልግሎት የማቅረብ እንዲሁም ቀጣይ አቅምን የሚያጎለብት፣ በጎ ተሞክሮን እና ቴክኖሎጂን ማሰስ ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ አካላት ሲተገበሩ ከነበሩ የአካባቢ እንክብካቤ ተግባራት በመነሳት መልካም ተሞክሮዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በማስፋፋት ሙከራ በማድረግ ውጤት አግኝታለች፡፡ ከዚህ በመነሳትም የአካባቢ እንክብካቤን መሰረት ያደረገ የእፅዋትና የፍራፍሬ ልማት ቴክኖሎጂን ወደ ሀገራችን በማስገባት ተግባራዊ ማድረግ ተችሎል፡፡

ቴክኖሎጂው ተራራማና ደጋማ በሆኑ አካባቢዎች በዓመታዊ ሰብሎች አመራረት ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የዕፅዋትና የፍራፍሬ ልማት እንዲሁም የአፈርና ውኃ ዕቀባ ስራዎችን በማቀናጀት የሚያራምድ ነው፡፡

ይህም የህብረተሰቡን ገቢ በማሻሻል፣ በተለይም ወጣቶችን እንደ ደን ቆረጣ ካሉ አካባቢን ከሚጎዱ የገቢ ማስገኛ መስኮች በማላቀቅ ህገ አማራጭ ወደ ሆኑ የገቢ ማስገኛ መስኮች እንዲዞሩ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በእርሻ ላይ የተመሰረተው ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ያግዛል፡፡ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ዋጋ የሚያውጡ የሰብል፣ የዛፍ፣ የፍራፍሬና አትክልት ዝርያዎችን የእንስሳት እርባታና ድለባ፣ የንብ ማነብ ስራን አቀናጅቶ በማልማት የገቢ ምንጭን ማሳደግ የሚያስችል ነው፡፡

ክንዋኔው በኢኮኖሚው ላይ ከሚያደርሰው አዎንታዊ ተፅዕኖ ባሻገር፤ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና በመቀነስ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ ፊዚካላዊና ሥነ – ህይወታዊ የአካባቢ ሥራዎችን በመተግበርም የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግም በማድረግ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የአፈር ለምነትን ለመጨመር እገዛ እያደረገ ነው፡፡

በሌላ በኩልም ቴክኖሎጂው የዕፅዋት እና እንስሳት ዓይነቶች እንዲበራከቱ አድርጓል፡፡ አካባቢውም በተለያዩ ዕፅዋቶች ሲሸፈን የአካባቢው ውበት ስለሚያምር ለህብረተሰቡ የመዝናኛ ቦታን ስለሚያበረክት ንፁህ ከባቢን ለመፍጠር የሚደረገውን ርብርብም የሚያግዝ ነው፡፡

የአካባቢ ጥበቃን መሰረት አድርገው እየተሰራባቸው ካሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል፤ የተጎዱ መሬቶችን ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነጻ በማድረግ እንዲያገግሙ የማድረግ ቴክኖሎጂ አንዱ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው በዕፅዋት ሽፋን መሳሳትና በአፈር ለምነት መቀነስ ሳቢያ የተጎዱና ምርታማነታቸው የተቋረጡ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ የሚያደርግ ከማድረግ አንፃር የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

ቴክኖሎጂው የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግሙ ለማድረግ በየአካባቢው መልክዓ ምድር ሊተገበር የሚችል ሲሆን፤ ለአካባቢው አየር ፀባይ ተስማሚ የእፅዋት ዝርያ በመምረጥ ተስማሚ የእርከን ዓይነቶችን መለየት እና የገቢ ምንጭ ሊያስገኙ የሚችሉ ስራዎች ተቀናጅተው የሚሰሩበት ሁኔታ በማጤን ህብረተሰቡ የሚጠቀምበትን መንገድ ለማሳየት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እንዲከናወኑ አስችሏል፡፡

ማህብረሰቡም የተጎዱ ቦታዎችን መልሶ እንዲያገግሙ የማድረግና የማልማት እንዲሁም ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብር ያግዛል፡፡ የመሬት ጥበቃ ችግርን በማሳበብ ህብረተሰቡ ከአካባቢው እንዳይሰደድ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የጓሮ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን አልምቶ ራስንና ቤተሰብን ለመመገብ ብሎም ጤናው እንዲሻሻል በማድረግ ረገድ መንግስት አስቀድሞ በሽታን ለመከላከል ለያዘው ዕቅድ የራሱን ድርሻ ይጫወታል፡፡

በዚህም ምክንያት በየአካባቢው ጠፍተው የነበሩ የእፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች በመመለስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቴክኖሎጂው ለአካባቢ ጥበቃ ከሚያደርገው ጉልህ ድርሻ ባሻገር፤ ከግብዓት አቅራቢዎች ጋር የአቅርቦት ትስስር በመፍጠር በማህብረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጓል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው አስተማማኝ በመሆኑም ለቴክኖሎጂ ዘላቂነት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡

እርግጥ የተጎዱ መሬቶችን መልሶ እንዲያገግሙ ለማድረግ የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎችን መትከል ዋነኛው አማራጭ ነው፡፡ ለዚህም በርካታ የችግኝ ማፍያ ጣቢዎችን በብዛት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶችም ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የዛፍ፣ የፍራፍሬና የአትክልት ችግኞችን ለገበያ በማቅረብ የስራ መስክ በመፍጠር በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ግለሰቦች የሰብል ፍርፍሬና፣ አትክልት የዛፍ ችግኞችን አቀናጅቶ በማምረት የገቢ ምንጭን ማሳደግም ችሏል፡፡

ለአካባቢ ጥበቃ አጋዥ ናቸው ተብሎ እየተሰራባቸው ካሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል የቀርከሃ ልማትና ዕደ ጥበብ ቴክኖሎጂ ተጠቃሽ ነው፡፡ የቆላም ሆነ የደጋ የቀርከሃ ምርት፤ ለማገዶ፣ ለግንባታ ስራዎች፣ ለቤት ውስጥ ቁሳቁሶች እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ግልጋሎትነት መዋል መቻሉ የቀርከሃ ዕደ ጥበብ ውጤቶችን ከማምረትና ለገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ ገቢ ያስገኛል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት፤ የቀርከሃ ተክል ብዛት ያላቸው የሚጠላለፍ ረዣዥም ስሮች ያሉት በመሆኑ አፈርን አቅፎ መያዝ የሚችል ነው፡፡ በአየር ውስጥ ያለውን ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመምጠጥ የምድርን ሙቀት በመቀነስ ረገድም አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተጎሳቀለ መሬት መልሶ እንዲያገግም ያግዛል። በመሆኑም መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራበት ይገኛል፡፡

እርግጥ እዚህ ላይ የአካበቢ ጥበቃን የተሻለ ለማድረግ የተፈጥሮን ሥነ- ምህዳር ለመጠበቅ ከሚደረገው ርብርብ ባሻገር፤ የዕለት ተዕለት ኑሮአችን የምንጠቀምባቸውን መሣሪያዎች መመልከት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሀገራችን ከፍተኛ የሆነ የጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ከፀሃይ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ ቴክኖሎጂዎችን በአማራጭነት እየተጠቀመች በመሆኑ ነው፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ የፀሃይ ሃይልን በመሰብሰብ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ ቴክኖሎጂ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ሃይል ታዳሽ በመሆኑ በዘላቂነት መጠቀም ይቻላል፡፡ በየትኛውም መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና በቂ ፀሃይ ጨረር በሚገኝባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ቴክኖሎጂ ስለሆነም በሀገራችን ተመራጭ ሆኗል፡፡ ታዲያ ቴክኖሎጂው በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ከዚህ ጋር አያይዞ ማንሳት ያስፈልጋል። ንፁህ እና ዘመናዊ የምግብ ማብሰያ በመፍጠር ረገድ በጤና ላይ ሊደርሱ የሚችሉ እክሎችን በመቀነስ አይነተኛ ድርሻ ያለው ነውና፡፡

በአገሪቱ የሚኖረው ሰፊው ህብረተሰብ አርሶ አደር በመሆኑ የኤሌክትሪክ መስመር ባልተዘረጋባቸው አካባቢዎች ተደራሽ በመሆን ከፍተኛ የሃይል አማራጭ ሆኖ ይገኛል፡፡ በባህላዊ የማገዶ አጠቃቀም ምክንያት ወደ አካባቢ አየር የሚለቀቁትን አሟቂ ጋዞችን የሚቀንስ ስለሆነም ለአካባቢ ብክለት መቀነስ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

በደን ሃብት ሽፋን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫናም መቀነሱም ሌላኛው አስተዋፅኦ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የሞተር እና የነዳጅ ሃይል የማይጠቀም በመሆኑ ከድምጽ ብክለት የፀዳ ነው፡፡ ይህን መሰሎቹ የአየር ንብረትን ሊታደጉ የሚችሉ የአረንጓዴ ልማት ስራዎቻችን የአርአያነታችን መገለጫዎችና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሳይቀር እውቅና እንዲቸረን ያደረጉ ናቸው፡፡ ሊጠናከሩና ሊጎለብቱ ይገባል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy