Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአንዱ መብት በሌላው ኪሳራ…

0 284

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአንዱ መብት በሌላው ኪሳራ…

አባ መላኩ

ፌዴራሊዝም በበርካታ የዓለም አገራት በተለይም ብዝሃነት በሚስተዋልባቸው አገሮች ተመራጭ የአስተዳዳር ዘይቤ እንደሆነ በርካታ ምሁራን ይስማማሉ። እኛም በተጨባጭ አረጋግጠናል። ይሁንና ፌዴራሊዝምን ለመተግበር  የሚፈልጋቸው ቅድመ ሁኔታዎችም እንዳሉ ታሳቢ ማድረግም መልካም ነው። ያለጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፌዴራሊዝምን መተግበር ለፈተና የሚዳርግ ይሆናል። የኢትዮጵያ ህዝቦች በባለፉት ስርዓቶች ማለትም በንጉሳዊያኑም ይሁን በደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ወቅት የዴሞከራሲ  ባህልን አያውቁትም ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ ህዝቦች ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የዴሞክራሲ ባህልን መለማመድ ቢጀምሩም የዴሞክራሲው ባህላችን ገና ጅምርና ለጋ ነው። በዴሞክራሲ ስርዓት ምንም ዓይነት ልቅ ነጻነት እንደሌለ መታወቅ አለበት። ከነባራዊ ሁኔታ መታዘብ እንደሚቻለው እያንዳንዷ መብት ግዴታ እንዳላት በርካታ ዜጎቻችን የሚገነዘቡት አይመስልም። በአገራችን  ዴሞክራሲ የራስን መብት መጠየቅ ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም መብት የማክበር ግዴታ መሆኑን ህብረተሰቡ እንዲያውቀው የተደረገበት አካሄድ ደካማ ነው።

ከነእጥረቱም ቢሆን  እንደኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ልዩነቶች የሚስተዋልባቸው አገራት አንድነታቸውን አስጠብቀው ሊቀጥሉ የሚችሉት  የፌዴራል ስርዓትን ሲተገብሩ ብቻ ነው። በ1983 ዓ.ም የነበረውን የአገራችንን ሁኔታ ለሚያስታውስ ፌዴራሊዝም  ለኢትዮጵያ ብቸኛው አማራጭ የአስተዳደር ዘይቤ ነበር ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። በዚያን ወቅት የነበሩ አመራሮች ብልህና  የሰከኑ ባይሆኑ ኖሮ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ላትኖር ትችል ነበር። ይሁንና በወቅቱ ሁሉን ሊያስማማ የሚችል ህገመንግስት መቅረጽ በመቻሉ አገሪቱን ከብተና መታደግ ተችሏል። ይህ ህገመንግስት ለኢትዮጵያ እስትንፋስ እንደመሆኑ ያህል ተገቢውን  ስፍራ የሰጠነው አይመስልም። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚል ዜጋ ሁሉ ይህን ህገመንግስት ማክበር ብቻ ሳይሆን ማስከበር መቻል ሃላፊነቱ እንደሆነ ሊያውቅ ይገባል።

በአገራችን ስለህገመንግስት ተገቢው ትምህርት ሲሰጥ አይስተዋልም። አልፎ አልፎ የሚሰጠው ትምህርትም  በባለሙያዎች ወይም በቂ እውቀት ባላቸው ሰዎች የሚሰጥ አይደለም። አንዳንዴ አስተማሪዎች ተብለው የሚመደቡት ግለሰቦች  ራሳቸው ህገመንግስቱን በትክክለኛው መንገድ የተረዱት አይመስልም። ለአብነት አንድ ነገር ላንሳላችሁ። አንድ ጉምቱ ባለስልጣን ስለህገመንግስት በሚያስተምሩበት መድርክ ላይ ተሳታፊ  ነበርኩ፣ ታዲያ እኚህ ግለሰብ ኢትዮጵያን የተመሰረተችው በክልሎች ይሁንታ ብቻ እንደሆነ አድርገው ሲያስተምሩ እንደነበር አስታውሳለሁ። ተሳታፊዎችም ይህንኑ አምነን ተቀብለን፤ እኛም በየደረጃው  ይህንኑ ጉዳይ ስናስተምር ኖርን። ነገር ግን እውነታው አንቀጽ 50 ላይ እንዲህ ይላል። “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በፌዴራል መንግሥት እና በክልሎች የተዋቀረ ነው፡፡”  ኢትዮጵያ የተመሰረተችው  በክልሎች ይሁንታ ብቻአለመሆኗን ግንዛቤው መያዝ ያለበት ጉዳይ ነው።

የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት ተደጋጋፊ መሆን መቻል ይኖርባቸዋል። ችግሮች ነገም ከነገወዲያም  መከሰታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው። እንኳን አንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርባት አገር ይቅርና በቤተሰብ መካከል ግጭት ይፈጠራል።  ዋናው ጉዳይ ችግሮችን እልባት እንዲያገኙ የሚደረግበት መንገድ የተናበበ መሆን መቻል ነው። በፌዴራል የአስተዳደር ዘይቤ ክልሎች ያለ መዕከላዊ መንግስት እንዲሁም መዕከላዊ መንግስት ያለ ክልሎች አይኖሩም። አንዱ ክልል ቀውስ ሲገጥመው ችግሩ የዚያ ክልል ብቻ  ሆኖ የሚቆም ሳይሆን አገር አቀፍ ችግር ይዞ እንደሚመጣም ጥሩ ትምህርት ቀስመናል። በቅርቡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠሩ ችግሮች በአገር አቀፍ ደረጃ ያስከተሉት ቀውስ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

በኢትዮጵያ ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በኢትዮጵያዊ ማንነትና በብሔር ማንነት መካከል እኩል እንዲዳብሩ ተገቢው ስራ ተሰርቷል የሚል እምነት የለኝም። ይህን ለማለት  ያበቃኝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ መደነቃቀፎች ናቸው። ዜጎች ያለሃጢያታቸው ተገድለዋል፣ ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ተንገላተዋል፣ በመንገዶች መዘጋት የፍጆታ እቃዎች  ዋጋ አሸቅቧል ፣ ወዘተ ብቻ በርካታ መልካም ያልሆኑ ነገሮች ተከስተዋል።

በኢትዮጵያ  የፌዴራል ስርዓት ውስጥ ከሚታዩ ማንነቶች መካከል በጉልህ የሚታዩት  የክልል ወይም የቡድን ማንነትና ኢትዮጵያዊ ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ሁለት ማንነቶች  ሳይዛነፉ እኩል ሊዳብሩና ሊተገበሩ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ችግር ይፈጠራል። ለዚህ ጥሩ ማሳያው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ  የሚስተዋሉ ብሄር ተኮር የሚመስሉ ጥቃቶች በአንዳንድ አካባቢዎች መከሰታቸው ነው። የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ውስጥ እያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ተገቢው ውክልና እንዲኖረው ተደርጓል።  ይህ በመደረጉም ሁሉም ቡድኖች በብሔራዊ ደረጃ በሚከናወኑ እያንዳንዷ ነገር ላይ ተካፋይ እንዲሆኑ እድል ስለተፈጠረላቸው አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር አግዟል ባይ ነኝ። አሁን ላይ ህዝቦች በፌዴራል ደረጃ አልተወከልንም የሚል ቅሬታ እስካሁን ሲነሳ አልተደመጠም።ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሰሳቸው  ማስተዳደር እንዲችሉ በመደረጉም ዛሬ ላይ እከሌ በክልሌ ጣልቃ ገባብኝ የሚሉ ሰንካላ ምክንያቶች ውሃ የሚቋጥሩ አይደሉም።

እንደእኔ በቀጣይ መሰራት ይኖርበታል  ብዬ ከማስባቸው ነገሮች መካከል መንግስት  ከምሁራን ጋር በመቀራረብ ኢትዮጵያዊ ማንነትንና  የቡድን ማንነትን እኩል ማስኬድ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።  በቀጣይ የብሄር ማንነቶችንና ኢትዮጵያዊ ማንነትን አስታርቀን መሄድ ካልቻልን ችግሮቻችን ሊወሳሰቡ ይችላሉ። አንዱ በአንዱ መስዋዕትነት የሚገኝ ሳይሆን ሁለቱንም ማስታረቅ የሚቻልበት ሁኔታ አለ። ከላይ እንዳነሳሁት መንግስት በዘርፉ  በቂ ልምድና እውቀት ካላቸው ምሁራን ጋር በቅርበት በመስራት ለችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ሁላችንም ከተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብንሆንም ሁላችንንም በአንድነት የሚያስተሳስር ወፍራም ገመድ አለ- ኢትዮጵያዊነት። የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ራሱን በራሱ ማስተካከል የሚችልበት ህገመንግስታዊ መሰረት ያለው በመሆኑ ይህን መጠቀም አስፈላጊ  ነው።

የብሔር ማንነችንን በአካባቢያዊ አስተዳደሮች ልንጠቀምባቸው፣ ቡድናዊ ትስስሮቻችንን ልናጎለብትባቸው እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሌሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር የምንተሳሰርበት ልናደርገው  ይገባል። ኢትዮጵያዊ ማንነት ሌሎች ማንነቶችን ደፍጥጦ እንዲገኝ አለማድረግ በተመሳሳይ የቡድን ወይም የብሔር ማንነትን ከሌሎች ማንነቶች በተለይ ከኢትዮጵያዊ ማንነት በላይ እንደሆኑ አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ የፌዴራሊዝም ስርዓት እንዲፈጠር ምክንያት ስለሚሆን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ሁሉንም በልክ በልክ የማናስኬድ ከሆነ እነዚህ  ነገሮች ውለው አድረውም ቢሆን ዋጋ ያስከፍለናል። በመሆኑም መንግስት ይህን ሁኔታ በየወቅቱ እየፈተሸ አዳዲስ አካሄዶችን መተግበር መቻል ይኖርበታል።

ሌላው ማንሳት የምፈልገው  ጉዳደይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የፌዴራል ስርዓት ላይ ራስን በራስ የማስተዳደር ፅንሰ ሐሳብ ላይ የተሳሳተ ዕይታዎችን ነው። ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት የራስን ቋንቋና ባህልን መጠቀም መቻል፣ አካባቢን ማልማት፣ ከልማት ተጠቃሚ መሆን፣  በመረጡት አካል መተዳደር፣ ወዘተ ማለት ነው። ይሁንና ይህን ጽንሰ ሃሳብ በተሳሳተ መልኩ የተረዱት አካላት ክልሉ ወይም ዞኑ ወይም ወረዳው የእነርሱ ብቻ እንደሆነ ሌሎች በእነዚህ አካባቢዎች የመኖር መብት እንደሌላቸው ወይም መኖር ከፈለጉም በእነርሱ (በአካባቢው ብዙሃን ተብለው በሚታሰቡት) መልካም ፍቃድ  አድርገው የሚያስቡ በርካታ ግለሰቦች እየተፈጠሩ ናቸው። ይህ አስተሳሰብ ሊፈጠር የቻለው ህገመንግስቱን በአግባብ ባለማስተማራችን ነው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት ዜጎች በፈለጉት የአገሪቱ አካባቢዎች የመኖር እና ሃብት የማፍራት መብት አጎናጽፏቸዋል። በመሆኑም አሁን ላይ የምናስተውላቸው አጉራዘለል አካሄዶች  በክልል መንግስታትም ይሁን በፌዴራል መንግስቱ በወቅቱ ተገቢው የእርምት እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy