Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአዋጁ ጠቀሜታና ህጋዊነት

0 276

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአዋጁ ጠቀሜታና ህጋዊነት

                                                          ታዬ ከበደ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ጠቃሚ ብቻ አይደለም። ህገ መንግስሥታዊ መሰረት ያለውም ነው። አዋጁ በህገ መንግሥታችን አንቀጽ 93 መሰረት እንደታወጀና ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ ሲባል ተግባራዊ በመሆን ላይ ያለ ነው።

ሥርዓት አልበኝነት ሲሰፍንና ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲያጋጥም የህግ የበላይነትን ማስጠበቂያ መሳሪያም ጭምር ነው። ይህን መሰሉ አዋጅ በሌሎች ዴሞክራሲያዊ አገራትም ጭምር ጥቅም ላይ ይውላል። በእኛ ሁኔታ ምንም የተለየ ተደርጎ የማይታይበት ምክንያት የለም። አዋጁ ወደ ዘላቂ መፍትሄ መዳረሻ መንገድም ነው። የአገራችንና የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ ከአዋጁ ውጭ አማራጭ ያለ አይመስለኝም።

በየትኛውም ህብረተሰብ ውስጥ ማንኛውም አዋጅ ህግና ስርዓትን ለማስከበር ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ ሰላምን ሊያመጣ የሚችል አይመስለኝም። አዋጁ ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ ሰላም እውን ሊሆን አይችልም። ህዝቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአዋጁ ጎን ቆሞ ተግባራዊ እያደረገው ነው።

ይሁን እንጂ እዚህ ሀገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር የማይሹ ሁከትና ብጥብጥ ናፋቂ ፅንፈኞች አዋጁ የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ የገደበ አስመስለው ሲናገሩ ይደመጣል። በእኔ እምነት ይህ ፍፁም ሐሰት ነው። ሁከትና ብጥብጥ ናፋቂዎች ይህ ቅጥፈት የሚያስወሩት እንደለመዱት ኢትዮጵያ ውስጥ አስተማማኝ ሰላም እንዳይኖርና የተጀመረው የልማት ዕድገት እንዲስተጓጎል ካላቸው ፍላጎት በመነሳት ነው።

አዋጁ በህግ በይፋ ከተከለከሉት ውጭ በሂደት የዜጎች መብትና ግዴታዎች በመሰረታዊ የህግ ማዕቀፎች እንዲታዩ የሚያደርግነው። በአሁኑ ወቅት በሁሉም ሊባል በሚችል የአገራችን ክፍሎች ውስጥ ዜጎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር መሆናቸውን እንኳን የሚያውቁ አይመስለኝም። ምክንያቱም በየቦታው የሚታዩት እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆኗን የማያመላክቱ ስለሆኑ ነው።

በዚህም ላይ በአዋጁ አፈፃፀም ምክንያት የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ብርቱ ቁጥጥርና ክትትል ተደርጓል፤ እየተደረገም ነው። ለዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ገቢራዊ እንደሆነ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 ንዑስ አንቀፅ 6 መሰረት የአዋጁን አፈፃፀም የሚመረምር ቦርድ እንዲቋቋም መደረጉንና በተግባር ስራውንም ጀምሯል።

ቦርዱም ሥራውን በይፋ ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ.ም ሲጀምር እንደገለፀው ሥራው በኮማንድ ፖስቱ ማዕከል እንደማይወሰን አስታውቋል። የቦርዱን ሥራ መጀመር አስመልክቶ በቅርቡ መግለጫ የሰጡት የቦርዱ አባላት፣ ባለፈው ዓመት ከነበረው ልምድ በመውሰድ በአሁኑ አዋጅ የምርመራ ሥራው በኮማንድ ፖስቱ ማዘዣዎች ብቻ እንደማይወሰኑ ገልፀዋል፡

የመብት ጥሰቶች ሊከሰቱ በሚችሉበት ቦታ ሁሉ ቦርዱ ተደራሽ እንደሚሆንና ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጅት መደረጉንም አስረድተዋል። የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ በቀለ ሆርዶፋ ይህ ጉዳይ አስመልክተው እንደገለፁት፤ መርማሪ ቦርዱ የሚደርሰውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ ችግሩ የተፈጠረበት ቦታ ድረስ በመሄድ ምርመራ ያደርጋል። ለዚህም ከኅብረተሰቡ ጥቆማ በተጨማሪ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግባቸውን ተጨማሪ ሥልቶች መኖሩንም አመልክተዋል።

የክትትልና ቁጥጥር ሥራው አዋጁ በፓርላማው ከመፅደቁ በፊት ያሉትን 15 ቀናት እንደሚያካትት የጠቆሙት ሰብሳቢ፣ ባለፈው ዓመት የነበረብንን የተደራሽነት ችግር ለመፍታት የሚያስችል አደረጃጀት ተፈጥሮ በይበልጥ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርበን እንሰራለን ብለዋል። 

ህብረተሰቡ በማንኛውም አካባቢ ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ከተፈጸመ፣ ከቦርዱ በተጨማሪ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀጥታ ሊያቀርብ ይችላል። ማናቸውንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ በመብት ጥሰት ፈጽሞ ሲገኝ መርማሪ ቦርዱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤትና ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት እርምጃውን እንዲያስተካክል ሐሳብ ይሰጣል። ቦርዱ በኮማንድ ፖስት ማዘዣ አካባቢዎች ሳይወሰን እስከ ወረዳ ድረስ በመዝለቅ ክትትል እንደሚያካሄድም ታውቋል።

እርግጥ በማንኛውም ሀገር ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው፤ ሀገሪቱ የሚያጋጥማትን በወቅቱ የሚያጋጥማትን ችግሮች ፈጣን መፍትሔ ለመስጠት እንዲቻል በማሰብ ነው። በስራ ላይ ያሉት መደበኛ አሰራሮች የተፈጠረውን ችግር መቋቋም ሲያቅታቸው አዋጁ እውን እንዲሆን ይደረጋል። በዚህም የተፈጠረውን ችግር ተቆጣጥሮ  ሀገሪቱ ከተደቀነባት ግልፅና ወቅታዊ አደጋ ለማውጣትና ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀልበስ እንዲቻል የአዋጁ እውን መሆን አስፈላጊ ይሆናል።

ታዲያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሀገራችን ውስጥ ብቻ የተደረገ አሊያም ከመንግስት መዳከም ጋር የሚታወጅ ተደርጎ መታየት ያለበት አይመስለኝም። ምዕራባዊያኑም ቢሆኑ ሀገራቸው ውስጥ አስቸጋሪ ክስተት በሚፈጠርበት ወቅት ይህን አዋጅ ያወጣሉ። ክስተቱ በእኛ አገር ውስጥ ብቻ የሆነ አይደለም።

በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ውስጥ የሀገራችንን ዕድገት የማይፈልጉ እንደ ግብፅ ተቋማት ያሉ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች ኢትዮጵያ በአሸባሪነት ከሰየመቻቸው ቡድኖችና ከጥቂት የዲያስፖራ ፅንፈኞች ጋር በማበር ሰላማችንን በማወክ ልማታችንን እንዳናከናውን የተፈፀመው ተግባር ሁነኛ ማሳየ ነው።

በእነዚህ ኃይሎች የውጭና የውስጥ ቅንጅታዊ ተግባር ምክንያት በኢሬቻ በዓልና እርሱን ተከትሎ በተከናወኑ የሁከት ተግባሮች የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል፣ አካልም ጎድሏል። ንብረት ወድሟል። መንገዶችን በመዝጋት ኢኮኖሚን ለማዳከም ጥረት ተደርጓል።

በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሰዎችን ህይወት የመቅጠፍና የሀገሪቱን ሃብቶች በኃይል የማውደም ተግባር የሽብርተኞችና ሀገራችን እያስመዘገበች ባለችው ልማት ደስተኛ ያልሆኑ ኃይሎች እንጂ የጤነኛ ተቃውሞ ፍላጎቶች ሊሆኑ አይችሉም።

ሽብርተኞችና የውጭ ሃይሎች ይህን ፀረ-ኢትዮጵያ ተግባራቸውን እንደሚቀጥሉ ስለሚታወቅም፤ ድርጊታቸው የአገሪቱንና የህዝቦቿን ደህንነት ብሎም የመንቀሳቀስና ሃብት የማፍራት ህገ-መንግስታዊ መብትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ከዚህ ባለፈም ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንገስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ከአሸባሪዎቹና ከአገር ውስጥ ጉዳይ ፈፃሚዎቻቸው የውድመት ተግባሮች ማሳያዎች ናቸው። ሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 93 መሰረት አገሪቱ ላጋጠማት ችግር ፈጣንና ወቅታዊ መፍትሔ ለመስጠት እንዲቻል በማሰብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማወጅ የግድ ሆኗል።

በአንድ ሀገር ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት በርካታ ጉዳዩች ከግምት ውስጥ ይገባሉ። ሁሉም መብቶች ሊከለከሉ አይችሉም። ሁሉም መብቶችም አይፈቀዱም። አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ አንዳንድ መብቶች ላይ እንደየ ሁኔታው እየታየ ገደብ ሊጣል ይችላል። ይሁን እንጂ ዜጎች በዚህ ለአገርና ለህዝብ ጠቀሜታ ላለው ህጋዊ አዋጅ አሁን እየሰጡ ያሉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy