Artcles

የአጋም መጥረጊያ

By Admin

March 21, 2018

የአጋም መጥረጊያ

ለሚ ዋቄ

የአንድ ሃገር ሃብት በእያንዳንዱ ዜጋ እጅ ያለ ሃብት ነው። ድሃ ህዝብ ኖሮ ባለጸጋ ሃገር ወይም መንግስት ሊኖር አይችልም። ህዝብና  ሃገር አብረው ይበለጽጋሉ፣ አብረው ይደኸያሉ፤ አብረው ይጠፋሉ፣ አብረው ይዘልቃሉ። ህዝብና መንግስት የአንድ ነገር ሁለት ፊት ሳይሆኑ አንድና አንድ ናቸው። የበለጸገች ሃገርና ሃብታም መንግስት መፍጠር ማለት እያንዳንዱ ሰው ሃብት እንዲፈጥር፣ ሃብት እንዲያካብት ማድረግ ማለት ነው።

ድህነት ማጣት ነው። ሁሉንም ነገር ማጣት። ጠግቦ መብላት አለመቻል፤ መታረዝ፤ ጤና ማጣት፤ ትምህርት ማጣት፤ ወዘተ። እናም የድሃ የዘውትር ምኞት የድህነትን አጥር ሰብሮ ወደብልጽግና መሻገር ነው። የድሃ ሃገር መንግስትም ምኞት ይሄው ነው።

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ የዓለም ሃገራት አንዷ በመባል መጠቀስ ጀምራለች። ከአንድ ተኩል አስርት ዓመታት በፊት ስትጠቀስ የነበረው መውጫ በሌለው አስከፊ ድህነት ውስጥ በሚኖሩ ህዝቦቿ ነበር። አሁን የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የማንኛውም ደሃ ምኞት የሆነውን ከድህነት የመላቀቅ ወይም ወደብልጽግና የመሸጋገር ጉዞ ለማሳካት እየተፍጨረጨሩ ነው። ተስፋ ማየትም ጀምረዋል። ከሰባት ዓመት በኋላ  ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ የመሰለፍ ተስፋ።

ይህ የብልጽግና ጉዞ ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከዓመታት በፊት በቀን ሶስቴ መመገብ የማይችሉ ኢትዮጵያን አርሶ አደሮች አሁን በቀን ሶስቴ ከመመገብ አልፈው ሃብት ማካበት ጀምረዋል። በሃገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋጋጥ ተችሏል። ወደኢንቨስተር ባለሃብትነት የተሸጋገሩ አርሶ አደሮችም አሉ። አሁን ሁሉም የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ልጆቻቸውን ያስተምራሉ። ሁሉም አርሶ አደሮች በአቅራቢያቸው የጤና አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ። ገቢያቸው በማደጉ የገበያ አቅም ሆነው ለአምራች ኢንደስትሪና አገልግሎት ዘርፎች መፈጠርና ማደግ አቅም የሆነ ሃገራዊ የሃብት ክምችት እንዲፈጠር እያደረጉ ነው።

የከተሜውም ኑሮ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጻር እጅግ ተሻሽሏል። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት አዲስ አበባን ጨምሮ በትላለቅ የሃገሪቱ ከተሞች ከሚኖሩ ዜጎች መሃከል 90 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ቴሌቪዥን እንኳን አልነበራቸውም። አሁን ሁሉም ከተሜ የቴሌቪዥንና የሳተላይት አንቴና ተጠቃሚ ነው። ሁሉም ከተሜ ቤት የተሟላ የቤት መገልገያ እቃ አለ። ማቀዥቀዣ፣ ማብሰያ፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ወዘተ የመሳሰሉት የማዕድ ቤትና የንጽና መገልገያዎችም አብዛኛው ከተሜ ቤት ገብተዋል። በከተሞች የሚገኘውን የቤት አውቶሞቢል ቁጥር መመልከት ምን ያህል ነዋሪዎች አውቶሞቢል የመግዛት አቅም እንደፈጠሩ ያመለክታል።

አሁን አብዛኛው ከተሜ በምርጫው ልጆቹን የተሻለ ትምህርት ይሰጣሉ ብሎ ባመነባቸው የግል ትምህርት ቤቶች ነው የሚያስተምረው። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት እጅግ አብላጫው ከተሜ ልጆቹን የግል ትምህርት ቤት ከፍሎ ማስተማር አይችልም ነበር።

በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ 60 በመቶ ገደማ የነበረውን ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ህዝቦቿን ምጣኔ ወደ 29 በመቶ ዝቅ እንዲል ማድረግ ችላለች።

እነዚህ በከተማና በገጠር በህዝቡ ኑሮ ላይ የተፈጠረውን መሻሻል ለማሳየት ያህል እንደናሙና የጠቀስኳቸው እውነታዎች እንደመና ከሰማይ የወረዱ አይደሉም። በዜጎች ላይ የታየው የተሻለ ህይወት፣ ሰርተው ያፈሩት ሃብት ውጤት ነው። በሃገሪቱ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት የተመዘገበው ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ እድገት የዚህ ውጤት ነው። የኢኮኖሚው እድገቱ መቀጠል፣ የዜጎች ሃብት ፈጠራ መቀጠል ነው። የሃብት ፈጠራውና እድገቱ በቀጠለበት ልክ የህዝቡም የኑሮ ሁኔታ እየተሻሻለ ይሄዳል። አሁን ሃገሪቱ የብልጽግና ማማ ላይ የሚያወጣትን መሰላል ጨብጣለች።

እርግጥ አሁንም ድህነት አለ። 29 በመቶ ገደማ የሚሆኑ ኢትዮጵያውን ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህን ደሃ ዜጎች ሃብት መፍጠር የሚያስችላቸው ስራ ላይ በማሰማራት ድህነትን መቀነስ የዜጎቹና የመንግስት ዋነኛ ተግባር ነው። ድሆችን ሃብት እንዲፈጥሩ በማድረግ ከድህነት ማጥ በማውጣት፣ ሃብት መፍጠር የጀመሩትን የበለጠ ሃብት እንዲፈጥሩ በማድረግ ሃገሪቱ የጨበጠችው የእድገት መሰላል ላይ በመወጣጣት ብልጽግና ላይ የማድረስ ተግባር ዋነኛው የመንግስትና የህዝብ ትኩረት ነው።

ያም ሆነ ይህ፣ በተጨባጭ በህዝቡ ኑሮ ላይ በታየ መሻሻል የተገለጸው የባለፉ ሁለት አስርት ዓመታት የእድገት ጉዙ ስኬታማ ሊሆን የቻለው በመላ ሃገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ስለነበረ ነው። እድገቱና ልማቱ ቀጣይነት እንዲኖረው አስተማማኝ ሰላም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ይህ የእድገትና የተሻለ ህይወት መሰረት የሆነው ሰላም ፈተና እየገጠመው ነው። ሰላም ከጠፋ ህዝቡና ሃገሪቱ መወጣጣት ከጀመሩት የብልጽግና ማማ ላይ ይፈጠፈጣሉ። የሚፈጠፈጡት ደግሞ የድህነት ወለል ላይ ነው። የድህነት ወለል ማጥ ነው። ብዙም ጊዜ ሳይወስድ ማጡ ይውጣቸዋል።

ይህ እንዳይሆን ማድረግ ይቻላል። ይህን ማድረግ አሁን በእጅ ያለውን ሰላም ከመንግስት ጋር ሆኖ መጠበቅ ብቻ ነው የሚፈልገው።

ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ከዘጠኙ ያሀገሪቱ ክልሎች በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ ሰሜናዊ አካባቢና በደቡብ ጥቂት ቦታዎች አውዳሚ ሁከቶች ማጋጠማቸው ይታወቃል። በተደጋጋሚ በመንግስትም በሌሎች አካላትም ሲገለጽ እንደቆየው የዚህ ሁከት መነሻ ምክንያት የመንግስት የአፈጻጸም ችግር ነው። ቅጥ ያጣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ መጓደል፤ አሁን ባለው የመንግስት ፖሊሲ ሃብት ማፍራት ይችል የነበረውን አርሶ አደር በልማት ስም መሬቱን ያለበቂ ካሳ መንጠቅ፣ የከተማ ወጣቶችን ስራ ላይ መሰማራት የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መፍጠር አለመቻል፣ መንግስትና ህዝብ ለልማት የመደቡትን ሃብት በማጭበርበር ለግል ጥቅም ማዋል፣ የመሰረተ ልማቶች ግንባታዎች እጅግ በተጋነነ ሁኔታ መጓተት፣ መቋረጥና ከተጠናቀቁም በኋላ ከደረጃ በታች ሆነው አገልግሎት መስጠት አለመቻል ወዘተ ናቸው። ህዝብ በተለይ ወጣቶች ይህን ልጓም ያጣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ቸልተኝነትና ምዝበራ ተቃውመው አደባባይ ወጥተዋል። እርግጥ ይህ ተገቢ የህዝብ ጥያቄ ተጠልፎ ተጨማሪ ልማት የሚጠይቀው ህዝብ በእጁ ያለውንም እንዲያጣ ያደረገ ሁከት ተቀስቅሷል።

ይህ የህዝብ ተቃውሞ መንግስትን አባንኖታል። በተቃውሞው ማግስት ችግሮቹን ለማቃለል አቅም በፈቀደው ሁሉ ተንቀሳቅሷል። በዚህም ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ታይተዋል። አሁን መንግስት ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበረው ሊያንቀላፋ እንደማይችል አውቋል። ይህ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው። በዚህ ሁኔታ ነቅቶ ራሱን ማከም ለጀመረው መንግስት ስህተቶቹን እንዲያርምና ለቀረበለት የልማትና የስራ ፈጠራ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ ፋታ መስጠት እንደሚያስፈልግ ማስታወስ ብልህነት ነው። መንግስት ራሱን እንዲያክምና ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስ ሰላም ያስፈልገዋል።

አሁን ግን መንግስት የገባውን ቃል ለመፈጸም የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚያደናቅፉ ሁከቶችና አድማዎች እየተካሄዱ ነው። እነዚህ ውጭ ሃገር በሚኖሩ ቡድኖችና ግለሰቦች ጠንሳሽነትና መሪነት የሚካሄዱ ሁከቶችና አድማዎች ጥቂቶች የተሳተፉበት ቢሆንም ህዝቡን እየጎዱት ነው። ሰበብ እየተፈለገ በየጊዜው የሚቀርብ አስገዳጅ ከስራ ውጭ የመሆን ትእዛዝ  ሰርተው የማደር፣ ልጆቻቸውን የማሳደግ፣ ጥሪት ቋጥረው ኑሯቸውን የማሻሻል . . . የዜጎችን ህልም እያመከነ ነው። ባለሃብቶች ሃብታቸውን ኢንቨስት አድርገው መበልጸግ እንዳይችሉ፣ ለሌሎች የስራ እድል እንዳይፈጥሩ፣ አካባቢያቸውን እንዳያለሙ እያደረገ ነው። አድማዎቹ ስራ ከማደናቀፋቸው በተጨማሪ ህግን ተማምነው ከአድማው ውጭ ለመሆን ወስነው የሚንቀሳቀሱ ዜጎች ንብረት እንዲወድም ምክንያት እየሆነ ነው። ዜጎች እንዳይሰሩና እንዳይንቀሳቀሱ የሚያስገድድ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ ነው።

ይህ ሰዎች ሰረተው እንዳያድሩ፣ ባለሃብቶች ራሳቸውና ሌሎችንም የሚጠቅም የልማት ስራ ላይ እንዳይሳተፉ፣ ሰዎች ሃብት አፍርተው ኑሯቸውን እንዳያሻሽሉ የሚያደርግ አድማና ሁከት በቅድሚያ የሚጎዳው ህዝብን ነው። ይህ ድርጊት ህዝብን ነው የሚያደኸየው። እርግጥ የድሆች ሃገር ደሃ ስለሆነች፣ ይህችን የድሆች ሃገር የሚያስተዳድር መንግስትም ደሃ ይሆናል። እናም መንግስትን እናዳክማለን በሚል በቂ ምክንያት ሳይኖር፣ የዜጎችን ሰብአዊ መብት በሚጥስ ሁኔታ የሚካሄድ አድማና ሁከት ህዝቡን የማደኸየት ውጤት ያለው መሆኑን ሁሉም ዜጋ ሊገነዘብ ይገባል።

ይህን ሁከት የሚያስፈጽሙ ወጣቶች አብዛኞቹ የሚሰሩትን አያውቁም። በስሜት ነው የሚነዱት። ወጣቶቹ መንግስትን እየተቃወምን ነው ሊሉ ይችሉ ይሆናል። ጥቃታቸው ያረፈው ግን ደሃና የተሻለ ህይወት የመኖር ተስፋ የሚታየው ወገናቸው ላይ ነው። እርግጥ የተሃድሶ አመራር በተፈጠረበት በአሁኑ ወቅትም በመንግስት ላይ ቅሬታ ሊኖራቸው ይችላል፤ ጥያቄዎች ሊኖሯቸው ይችላል። ቅሬታቸውንና ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ፤ በሰላማዊ ሰልፍ፣ በህዝባዊ ስብሰባ፣ በሚዲያ ወዘተ ማቅረብ ይችላሉ። መንግስት በዚህም አልሰማ ካለ በምርጫ ውክልናቸውን አውርደው ያመኑበትን መወከል ይችላሉ፤ በቃ።

እነማን እንደሆኑ፣ ዓላማቸው ምን እንደሆነ በማያውቋቸው በውጭ ሃገር ያደፈጡ ቡድኖችና ግለሰቦች እየተመሩ አስገዳጅ አድማ በማካሄድና ሁከት በመቀሰቀስ ስራ ማስቆምና ንብረት ማወደም የሰብአዊ መብት ጥሰት ከመሆኑ በተጨማሪ ህዝቡ ከድህነት እንዳይወጣ የሚያደርግ አካሄድ ነው። ይህ አካሄድ መንገድን በእሾሃማው የአጋም ዝንጣፊ እንደመጥረግ ይቆጠራል። ተግባሩ መጥረግ ነው፤ ወጤቱ ግን መንገድን በእሾህ ሞልቶ መንቀሳቀስ አለመቻል ነው። እናም በተቃውሞ ስም የሰብአዊ መብት ጥሰት ከመፈጸምና ድህነትን ከመጋበዝ ተቆጠቡ። መንገዳችሁን በአጋም አትጥረጉ፣ በዘንባባ እንጂ።