Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የእሥረኞች መፈታት እንድምታ !!

0 259

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የእሥረኞች መፈታት እንድምታ !!

ዋኘው መዝገቡ

መንግስት በተለያየ ምክንያት ታስረው በፍርድቤት ጉዳያቸው ቀርቦ ተከራክረው ተፈርዶባቸው በእስር ቤት ይገኙ የነበሩ እንዲሁም ጉዳያቸው በፍርድቤት ገና ውሳኔ ያላገኘና በቀጠሮ የሚመላለሱትን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ጋዜጠኞችን ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ አድርጎአል፡፡በዚህም መሰረት በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች በእስር ላይ የነበሩ ሰዎች ተፈተው ከቤተሰባቸው ጋር ተቀላቅለዋል፡፡ይህ በመንግስት በኩል የተወሰደው እርምጃ ሀገራዊ መግባባትን ከማምጣት፤ችግሮችን በጋራ ተነጋግሮ ከመፍታት፤ የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ይበልጥ ከማስፋት አንጻር ትልቅ ትርጉም ያለው እርምጃ ነው፡፡አዎን ሁሉም ዜጋ የሀገሩ ባለቤት ነው፡፡በሀገሩም ጉዳይም ያገባዋል፡፡

የእስረኞች መፈታትን በተመለከተ ቀደም ሲል በዚህ ደረጃና መጠን ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ታስቦ በሀገሪቱ ውስጥ ተወስዶ የማያውቅ ስርነቀል እርምጃ በመሆኑ በበጎ ጎኑ የታየ ሕዝብን ከልብ ያስደሰተ ውሳኔ ነው፡፡መንግስት ይሄን በማድረጉ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡የሕዝቡን ጥያቄዎች ከመመለስ የበለጠ ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋትን ከመፍጠርም አንጻር የጎላ ድርሻ አለው፡፡የመንግስትን በጎና ቅን አስተሳሰብ ካለመረዳትና አጣሞ ከማቅረብ አንጻር አስሩን ሲሉ የሚውሉት አንዳንድ ወገኖች መንግስት ተዳክሞአል የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ያንጸባርቃሉ፡፡ከውጭ ጫና በዝቶበት ነው የሚል ሀሳብ ይሰነዝራሉ፡፡የመብቴ ይከበርልኝ ጥያቄው መነሻ ሕዘቡ ሲሆን እውነትነቱን ተቀብሎ ለማረም እየሰራ ያለው ደግሞ ራሱ ኢሕአዴግ ነው፡፡

ትልቁ ቁም ነገር መንግስት ሕዝብን በመስማት፤ የሕዝብን ችግር በማዳመጥ የተከሰቱትን ችግሮች በሀገር ደረጃ ለመፍታት የወሰደው ቁርጠኛ እርምጃ እንጂ የውጭው ኃይል ጫና የሚባለው ነገር ተቀባይነት የለውም፡፡እንዲያውም የመንግስት መድከም ምልክት ሳይሆን እውነተኛ ችግሩን ለይቶ አንጥሮ በማውጣት የሕዝቡን ጥያቄ ሰምቶ ቢዘገይም አስቸኳይ መልስ መስጠት መቻሉ ጥንካሬውን እንጂ ድክመቱን አያሳይም፡፡እንዲህ  አይነት ተራ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባቱም እንደ ሀገር አስፈላጊ አይደለም፡፡

የተለያየ አስተሳሰብ አመለካከት ያላቸው ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ባለቤትና ባለመብትም ናቸው፡፡ኢሕአዴግ በተለያየ ሁኔታ የጠበበውን የዲሞክራሲ አድማስ ለማስፋት፤በሀገራቸው ጉዳይ ኃሳባቸውን እንዲያንሸራሽሩ በነጻነት መግለጽ እንዲችሉ፤የሀሳብና የአመለካከት ነጻነታቸው የተከበረ በመሆኑ ይህ ቀደም ሲል በተለያየ ሁኔታ ተሸርሽሮ የነበረ ሕገመንግስታዊ መብት እንዲከበር ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም ይዞ በመስራት ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ከሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዘው ሲከሰቱ የነበሩት ንብረት ማውደም፤ መንገድ መዝጋት፤በጎሳና በዘር ላይ ያተኮረ ግጭትና የሰው ሕይወት መጥፋትን ታስረው የተፈቱት ዜጎችም አውግዘውታል፡፡በተለያዩ ሚዲያዎች ሲጠየቁ ያስተላለፉት መልእክት የሰው ሕይወት አይጥፋ፤ንብረት አይውደም የሚል ነው፡፡ለሀገርና ለህዝብ ማሰብ ማለት ይሄ ነው፡፡የጎሳ ግጭት መወገዝ አለበት፤ለሀገር ሰላም አይበጅም፡፡ሀገራችንን እንጠብቅ የሚል መልእክት ነው ያስተላለፉት፡፡ትልቅ መልእክት ነው፡፡ተቃዋሚውም ሆነ ገዢው ፓርቲ ለፖለቲካ ስልጣን ሊፎካከሩ የሚችሉት በመጀመሪያ ደረጃ የተከበረች ሰላምና መረጋጋት ያላት ስትኖር ነው፡፡በድሀ ሀገር የኢኮኖሚ አቅም የተገነቡ የመሰረተ ልማቶችን እያቃጠሉ እያወደሙ ሀገርን መገንባትና ማሳደግ አይቻልም፡፡

የሀገር ሰላም ከሌለ በተረጋጋ ሁኔታ ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት ካልቻለ፤ሰርቶ ወደቤቱ መመለስ ልጆቹን ወደትምህርት ቤት ማድረስና በሰላምም ወደቤታቸው መመለስ ከተሳነው ፤የንግዱ ስራና አቅርቦት በአግባቡ ካልተካሄደ፤በአጠቃላይ ሀገራዊ ሰላም ከተናጋ ችግሩ የሚተርፈው ለመላው ሕዝብ ነው፡፡የችግሩ ገፈት ቀማሽ የአደጋው ዋነኛ ሰለባና  ተጋላጭ ሕዝብና ልጆቹ ናቸው፡፡ትራንስፖርት መዝጋት ሸቀጦች ወደገበያ እንዳይደርሱ መግታት መኪኖች በእሳት ማጋየት ይሄ የለየለት ጸረ ሕዝብና ጸረ ሀገር የወንጀል ድርጊት ነው፡፡ንብረቱ ነገም የሚያገለግለው ለሕዝቡ ነው፡፡

ገበሬው ያመረተውን ለከተሜው እንዳያቀርብ በመከላከልና መንገድ በመዝጋት፤  የከተማውን ሕዘብ በረሀብና በችግር በመቅጣት ሲመረው ይነሳል የሚል የጅል ሰልት የትም አያደርሰም፡፡ይሄን አውሮፓና አሜሪካ ላይ መሽገው የተንደላቀቀ ኑሮ እየኖሩ በድሀው ሕዘብ ሕይወት በልጆቹ ሞትና ጉዳት መጨፈር የሚፈልጉ ለስሙ ኢትዮጵያውያን ነን የሚሉ ሰዎችን ሕዝብ ለመስማት አይፈቅደም፡፡

የሕዝብ ልጅ በስሜታዊነት ቀስቅሰው እያስነሱ ከመንግስት ኃይሎች ጋር እንዲጋጭ ደም እንዲፋሰስ እያደረጉ ይህንን የእልቂት ድራማ መስራት በዚህም በአሉበት ሀገር ሆነው ሰልፍ መውጣት ውግዘት ማሰማት ለኢትዮጵያ ሕዘብና ለልጆቹ የሚጠቅመው አንድም ምንም ነገር የለም፡፡ ይልቁንም ሀገሬ ነች ካሉ እውነተኛ የሀገር ፍቅርም ካላቸው ባዶና አደንቋሪ ፕሮፐጋንዳቸውን ትተው በሰላማዊ መንገድ ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ ነበር ማስላት የሚገባቸው፡፡ ሀገሪቱ ወደ ከፋ የመከፋፈልና የመበታተን አደጋ እንድታመራ ከሚያደርጋት ዘረኛና ጎጠኛ ፕሮፓጋንዳ ሕዝብን ከመዝለፍና ከመሳደብ፤ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማስነሳት ከሚያደርጉት ነውረኛ ድርጊት ሊታቀቡ ይገባቸውም ነበር፡፡

ምንም ተባለ ምን በኢትዮጵያ እየመጣ ላለው ለውጥ በመንግሰት ላይ ግፊት አድርጎ መብቴ ይከበርልኝ ያለው ራሱ ሕዘቡ እንጂ የትኛውም ተቃዋሚ ድርጅት የመራው ያስተባበረው እንቅስቃሴ አይደለም፡፡ እርስ በእርስ ስመ ብዙ ሁነው በተለያየ ጎራ በመሰለፍ ከመናቆር በአንድ ላይ ለመቆም የሚያስችል የጋራ የሆነ መግባቢያ ቢኖራቸው ነበር የሚበጀው፡፡

በየፊናው ከመዛበር ውጭ ለሀገርና ለሕዘብ መፍትሔ ማምጣት የሚያስችል አቅም መፍጠር አልቻሉም፡፡ለመብቱ መከበር ጥያቄ ያቀረበው መንግስት ላይ ጫና ያሳደረው ጥያቄዮ ይመለስልኝ ያለው ሕዝቡ በራሱ ግዜ ተነስቶ እንጂ ባሕርማዶ መግለጫ የሚሰጡት ድርጅቶች አልመሩትም፡፡

እስረኞች ተፈቱ እኛ ነን ያስፈታናቸው፤አንድ ቦታ ጥይት ተሰማ እኛ ነን የተኮስነው፤ መኪና ተቃጠለ እኛ ነን ያቃጠልነው….በእንዲህ አይነቱ ነውረኛ ቅጥፈት ሊያፍሩ ይገባቸዋል፡፡ሳይገሉ ጎፈሬ ሳያጣሩ ወሬ እንዲል የድሮ ሰው፡፡እስረኞች የተፈቱት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ኢሕአዴግ በራሱ ውስጥ በተለይም ስራ አስፈጻሚው ባደረገው ጥልቅ ግምገማ ቀደም ብለው በተሰሩት የአመራሩ ስህተቶች መጸጸቱን ገልጾ ለማረምና ሕዝቡን ለመካስ ዝግጁ መሆኑን በገለጸው ውሳኔ መሰረት ነው፡፡

አሁንም ኢሕአዴግ መውሰድ በጀመረው ስርነቀል እርምጃ የሚታዩና የሚጨበጡ ግዙፍ ለውጦች በየደረጃው ይቀጥላሉ፡፡ስሕተቴን በጥልቀት ፈትሼአለሁ ይህንን በማረም ወደፊት እንዳይከሰቱ ለመከላከል ተገቢ የእርምት እርምጃዎችን እወስዳለሁ ማለት አሁን በአጭር ግዜ ውስጥ ከታዩት የበለጡ ለውጦችን ለሕብረተሰቡ ማምጣት ማለት ነው፡፡የኢትዮጵያ መሪ አሳዳሪ ወሳኝ የሆነው ኃይል ጥንትም ጠብቆአት የኖረው ዛሬም ወደፊትም የሚጠብቃት የኢትዮጵያ ሕዘብ ነው፡፡የባሕር ማዶው ተቃዋሚ እንደአምላክ የሚያመልካቸው ደጅ የሚጠናቸው የውጭ ኃይሎች አይደሉም፡፡

እነሱ በተለያዩ ዘመናት በኢትዮጵያ ላይ የተጫወቱትን ቁማር ልብ ካላቸው ማስተዋል ከቻሉ በውጭ ያሉትም ተቃዋሚዎች አይስቱትም፡፡የሚረሳ አይደለምና፡፡ዛሬም በእነሱ ማመን ዛሬም በእነሱ ስር መንበርከክና እነሱን መማጸኑ እውነትም የጥንት አባቶች እንደሚሉት ሳይወለድ ቢቀር የሚባል አይነት የመከነ ሽል መሆን ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምእራብ አስከ ምስራቅ ጥንትም ዛሬም ለገጠሟት ችግሮች ሁሉ ፈጣሪዎቹ አመሳዮቹ አቡኪዎቹ መሀንዲስና ቀያሽ  አርክቴክቶቹ እነሱውና እነሱው ብቻ ናቸው፡፡ሲጀመር ተስማምቶ ተደማምጦ ተከባብሮ ሀሳብን አቻችሎ ልዩነትን በልዩነት ይዞ ለጋራ ሀገራዊ ጉዳይ በጋራ የመቆም ባሕላችን ገና አላደገም፡፡ከእኛ በፊት ዘመናዊ እውቀት የሚባል ያልነበራቸው በሀገራቸው እውቀት ይኮሩ የነበሩት አባቶቻችን እጅግ የተሻሉ ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ስለሀገራቸው አርቀው አሳቢና ተመልካቾች ነበሩ፡፡

ተተኪው ትውልድ ከአባቶቹ በበለጠ አስተዋይ መሆን በመቻቻልና በመከባባር የጋራ ሀገሩን ሳይለያይ መጠበቅ ማሳደግ የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ ነው የሚጠበቅበት፡፡ ኢሕአዴግ ሀገርን ያሳደገ የለወጠ ስራ ሰርቶአል፡፡ጠንካራና ብርቱ ሀገራዊ ጎኑን ማክበር የተገባ ነው፡፡ደካማ ጎኖቹን በአግባቡ ለይቶ በማስቀመጥ ረገድ እራሱን በጥልቀት የመፈተሽ ባህል ያዳበረ ድርጅትም ነው፡፡ስሕተቶቹን በይፋ አምኖ ተቀብሎ ለማረም በመስራትም ላይ  ይገኛል፡፡መታገዝም ይገባዋል፡፡

የጥላቻ ፖለቲካ የሚዘራበት በጎሳና በዘር ላይ ያተኮረ የበለጠ ሀገርን የሚከፋፍል ግጭት የሚፈጥር ሰላምን የሚያናጋ አስከፊ ዘመቻ የሚያደርጉ ክፍሎች የሚጎዱት ህዝብና ሀገርን ነው፡፡ባሕርማዶ ሁኖ የሀገርን ውደመትና ጥፋት የሕዝብን እልቂት አጥብቆ መሻት ብጥብጥና ሁከቱ እንዲቀጥል የማያባራ ፕሮፓጋንዳ መንዛት ትርፍ አያስገኝም፡፡ሀገር ከወደመችና ከጠፋች ሕዘብ እርስ በእርስ እንዲፋጅ በመቀስቀስ በሚያመጡት ጥፋት ሁሉም ነገር ከፈረሰ ሀገሬ የሚሉዋት ኢትዮጵያ የትኛዋ እንደሆነች ደግመው ደጋግመው ማሰብ ይገባቸዋል፡፡

በነውጥ በሁከት በሽብር ንብረት በማወደምና በማቃጠል የሚመጣ ሀገራዊ ለውጥ የለም፡፡ሊኖርም አይችልም፡፡በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፡፡ አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚመሰክረውም ይሄንኑ ነው፡፡ በሰላምና በሰላማዊ መንገድ ሕዘብ የጠየቃቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ በመመለስ በመወያየት በመነጋገር በጋራ ችግሮችን በመፍታት የሀገር ሰላምና መረጋጋት ሳይደፈርስ  ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡

ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ውስጥ ግዙፍና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በመላው ሀገሪቱ በግንባር ድርጅቶችና በአጋር ድርጅቶቹ አማካኝነት በአባልነት ያቀፈና የያዘ ድርጅት ነው፡፡ይህን ግዙፍ ድርጅት በየትኛውም መስፈርት ቢሆን አብሮ በመስራት፤የሚያርመውን እንዲያርም እንዲያስተካክል እያደረጉ ልዩነትን በልዩነት ይዞ በጋራ መስራት ብቻ ነው ለተቃዋሚውም ለሀገርም የሚበጀው፡፡

ሀገሪቱን በብዙ መልኩ የለወጠ ያሳደገ ግዙፍ የመሰረተ ልማት እድገቶችን ያስመዘገበ የልማትና የእድገት አብዮትንም የመራ በዚህም ትውልድ ተሻጋሪ ስራዎችን የሰራ ስርነቀል ለውጥ ያመጣ የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡እጅግ የገዘፉ ጠንካራ ጎኖቹም አብረው መታየት አለባቸው፡፡ሕዝቡ ኢሕአዴግ አልሰራም ለውጥ አላመጣም አላለም፡፡በአባልነትና በመሪነት የተሰማሩ ሰዎች በፈጠሩት ብልሹ አሰራር የመልካም አስተዳደር፤የፍትሕ፤የሙስና፤ የመሬት ቅርምት፤የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብቶች ሕገመንግስቱን በመጻረር በመጣስ በፈጸሙት ድርጊት የተነሳ ነው የሕዝብ ተቃውሞው የበረታው፡፡ይህንን በጥልቀት የፈተሸው ከፍተኛው አመራር ችግሮቹን ለመፍታት በሰፊው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ስርነቀል ለውጥም እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል፡፡ለለውጡም ግዜ ይጠይቃል፡፡

ተቃዋሚው ከጭፍን ጥላቻ ወጥቶ አብሮ እየሰራ የተሻለ ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣት ነው መትጋት ያለበት፡፡አሁን ባለው ተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታ ሀገሪቱ ዙሪያ ገባዋን በጠላቶች ተከባ ባለችበት፤ተደራጅቶና አደፍጦ ግዜ ሲጠብቅ የነበረው እክራሪ እአስላማዊ ኃይል ዙሪያውን ባሰፈሰፈበት፤ግብጽና ኤርትራ የሀገሪቱን መተረማመስና ውድቀት፤ የሕዝቡን መከፋፈል ሌት ከቀን በሚጠብቁበት ሁኔታ ውስጥ ይሄንን አደጋ ልንመክተው የምንችለው ኢሕአዴግ ራሱን አርሞ ብቁ ሀገራዊ ፖለቲካ ፓርቲ ሁኖ ኢትዮጵያዊነትን አስቀድሞ የተሻለ እንዲሰራ ተቃዋሚውም ዜጎችም ሊያግዙት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡

የእኛ እርስ በእርስ መባላት በጥላቻ መዘፈቅ ጠፍቶ ካላየሁት ማለት የማይመለስ ሀገራዊ አደጋ እንዳያስከትል ብርቱ ማስተዋልና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ለሀገርና ለሕዝብ በፍጹም አይበጅም፡፡ሀገሪቱን ከማትወጣበት ቀውስ ውስጥ መክተት ኃላፊነት የጎደለው ስራ ነው የሚሆነው፡፡

ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ውድድር የማሸነፍ እድል ቢያገኙም ኢሕአዴግ ግዙፍ ድርጅት በመሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲ ሁኖ ይቀጥላል እንጂ በፍጹም ማግለል አይቻልም፡፡ይታረም ይስተካከል በሚለው መንገድም ከታየ ድርጀቱ በራሱ ጥናትና ውሳኔ የሚከተለውን ፖሊሲ ለማረምና ለማስተካከል ይችላል፡፡የማይሻሻል የማይለወጥ ዘመኑንና ግዜውን ተከትሎ በአዲስ አሰራርና አስተሳሰብ የማይተካ ምንም ነገር በምድር ላይ የለም፡፡ ለውጥ የሕብረተሰብ እድገት አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፡፡በሌሎች ሀገራት ሰፊ ተሞክሮዎች ውስጥ ታይቶአል፡፡የእኛም የተለየ  አይደለም፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy