Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዘላቂ ወዳጅነትም ዋጋ ይታወስ

0 345

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዘላቂ ወዳጅነትም ዋጋ ይታወስ

አለማየሁ አ

ባለፉ ሁለት ዓመታት በተወሰኑ የሃገሪቱ አካባቢዎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች አጋጥመዋል። የግጭቶቹ መንስኤ ከማንነትና ከወሰን ይገባኛል ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። ከእነዚሀ መሃከል በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ከቅማት የማነነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ጋር ተያይዞ፣ በዚሁ ዞን በወልቃይት አካባቢ የወሰን ይግባኛል ጥያቄን መነሻ በማድረግ እንዲሁም በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከኮንሶ ብሄረሰብ የአስተዳደር አወቃቀር ለውጥ ጥያቄ ጋር ተያይዞ፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች መሃከል የወሰን ይገባኛል ጥያቄን መነሻ በማደረግ የተቀሰቀሱት ግጭቶችና አለመግባባቶች ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ ግጭቶች በተለያየ ደረጃ ለሰዎች ህይወት መጥፋትና ከኑሮ ለመፈናቀል ምክንያት ሆነዋል። በተለይ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች መሃከል ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት ለበርካታ ንጹሃን ዜጎች የህይወት መጥፋት በሁለቱም ወገን በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

ይህ በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ ውጤት ያስከተለው በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች መሃከል የተቀሰቀሰ ግጭት፣ በሁለቱ ህዝቦች መሃከል እንደተካሄደ ግጭት ተደርጎ ቢቀርብም፣ የህዝቦች ግጭት እንዳልሆነ የሚያመለክቱ እውነታዎች አሉ። የሁለቱ ህዝቦች አብሮነት በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። በሚዋሰኑ አካባቢዎች የሚኖሩት የሁለቱ ብሄሮች ህዝቦች ኑሮ በአርብቶ አደርነት ላይ የተመሰረተ ነው። ከዚህ የአርብቶ አደርነት ባህሪ በመነጨ ሁለቱ ህዝቦች በግጦሽ ሳርና ከውሃ  ሽሚያ ጋር በተያያዘ የሚጋጩበት አጋጣሚ የተለመደ ነው።

ይሁን እንጂ፣ የእነዚህ ግጭቶች ጉዳይ ከአካባቢው አልፎ በክልልም ሆነ በፌደራል መንግስት ደረጃ እንደችግር ቀርቦ አያውቅም። ሁለቱ ህዝቦች የአብሮነታቸውን ያህል እድሜ ባስቆጠረ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአት ችግሩን እየፈቱ ሰላማዊ ግንኙነታቸውን ዘመን ማሻገር ችለዋል። አሁን ያጋጠመው ወሰንን መነሻ ያደረገ ግጭት ግን በዚህ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአት ሊዳኝ አልቻለም። ይህ የሆነው ግጭቱ በአዋሳኝ አካባቢ በሚኖሩ ሁለቱ ህዝቦች መሃከል የተፈጠረ ግጭት ባለመሆኑ ነው። እውነተኛው የግጭቱ መንስኤ ምንድነው? የሚለውን፣ ጉዳዩን እየመረመሩ ለሚገኙ አካላት እንተወው።

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት በሁለቱም በኩል እስከ 1 ሚሊየን ለሚደርሱ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ በሃገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው የዜጎች መፈናቀል ነው። አነዚህ ተፈናቃዮች አብዛኞቹ በጊዜያዊ መጠለያ ካምፖች ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብና ተያያዥ እርዳታ እየተደረገላቸው ተጠልለው ቆይተዋል። የተወሰኑት ከካምፕ ውጭ ዘመዶቻቸው ጋር ተጠግተው የሚኖሩበት ሁኔታም አለ።

በተፈናቃዮቹ አያያዝ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል አካባቢ የተሟላ መረጃ ማግኘት ባይቻልም፣ በኦሮሚያ የተጠለሉ ተፈናቃዮች የፌደራል መንግስት በአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ስራ አመራር ኮሚሽን አማካኘነት ከሚቀርብ እርዳታ በተጨማሪ የክልሉ ህዝብ እርዳታ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል። በኦሮሚያ ለዚሁ ዓላማ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች ወዘተ የተካተቱበት የእርዳታ አሰባሳቢ ህዝባዊ ኮሚቴ ተቋቁሟል።

እነዚህ ዜጎች በተፈናቀሉ ማግስት፣ የሁለቱም ክልሎች መንግስታት ተፈናቃዮቹን ወደነበሩበት እንዲመለሱ የማድረግ ፍላጎታቸውን ገልጸው ለዚህ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ይታወሳል። በዚህ መሰረት በተወሰነ ደረጃ ወደየመጡበት የተመለሱ ተፈናቃዮች መኖራቸውም ይታወቃል። በተለይ ሃብትና ንብረት የነበራቸው ተፈናቃዮች ንብረታቸው ተጠብቆ ወደየመጡበት ክልል የተመለሱበት ሁኔታ አለ። ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በሚፈለገው ልክ የኮሚዩኒኬሽን ስራ ስላለተሰራ ህዝቡ የተሟላ መረጃ የለውም። ያም ሆነ ይህ፣ በርካታ ተፈናቃዮች ወደነበሩበት ተመልሰው ሃብትና ንብረታቸውን ተረክበው የወትሮ ኑሯቸውን የጀመሩበት ሁኔታ መኖሩ መታወቅ አለበት።

እጅግ አብላጫ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች ግን የሁለቱም ክልሎች መንግስታት ወደ የመጡበት እንዲመለሱ ጥሪ ቢያቀርቡላቸውም ለመመለስ ፍቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። ለመመለስ ፍቃደኛ ያለሆኑትን አስገድዶ መመለስ ስለማይቻል በዘለቄታው መቋቋም የሚችሉበት ሁኔታ ላይ ሲሰራ ቆይቷል። በተለይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ባቱ፣ ሻሸመኔ፣ ቢሻን ጉራቻ፣ ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ገላን፣ ለገጣፎ፣ ሱሉልታ፣ ዱከም . . .  ከተሞች በህዝብ ትብብር የመኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ተፈናቃዮቹ ቋሚ ህይወት እንዲጀምሩ የማስፈር ስራ እየተከናወነ ይገኛል። በመጀመሪያው ዙር እስከ 12 ሺህ የሚደርሱ አባወራዎችን በቋሚነት የማስፈር እቅድ ተይዞ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም የቀበሌ የኪራይ ቤቶች እንዲያገኙ የተደረጉ ተፈናቃዮችም አሉ።

ተፈናቃዮቹን በቋሚነት እንዲሰፍሩ በማድረግ ረገድ በተለይ በኦሮሚያ የተከናወነው ስራ የሚደነቅ ነው። ክልሉ ለሌሎች የህዝብ ጥያቄዎችም ምላሽ ለመስጠት በተመሳሳይ ሁኔታ የተቀናጀ ርብርብ ቢያደርግ ምን ያህል ትልቅ ውጤት ሊገኝ እንደሚችል ያመላከተ ነው። ይሁን እንጂ ተፈናቃዮቹን በቋሚነት ለማስፈርና ለማቋቋም ያደረገውን ድንቅ እንቅስቃሴ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሲያከናውን አለመታየቱ ብዙዎችን ግር አሰኝቷል።

ያም ሆነ ይህ፣ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በጊዜያዊ መጠለያ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እየቀረበላቸው ይኖሩ የነበሩ ተፈናቃዮችን በቋሚነት የማስፈሩ ስራ እየተከናወነ ነው። ይሁን እንጂ ከተፈናቃዮቹ ጋር በተያያዘ የሚሰሙና የሚታዩ አንዳንድ ጉዳዮች የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች ዘላቂ ግንኙነት ከግምት ያስገቡ አይመስሉም። ወገን ለወገን ያደረገው የእርዳታ ርብርብ የሚደነቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተፈናቃዮቹንም ሆነ የተቀረው የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ህዝብ ላይ ቂም እንዲቋጥር የሚያደርጉ አካሄዶች ይታያሉ። በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በኩልም ተመሳሳይ አካሄዶች ተስተውለዋል። እነዚህ አካሄዶች ከችግሩ ስፋትና ከሳደረው የመረረ ቅሬታ የመነጨ ስሜታዊነት ያስከተላቸው ቢሆኑም፣ የሁለቱን ህዝቦች ዘላቂ ግንኙነት ሊጎዱ ስለሚችሉ ጉዳዩን  በጥንቃቄ መያዝ አስፈላጊ ነው።

በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተመለከተው ሁለቱ ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀ የእርስ በርስ ትስስርና ወዳጅነት ያላቸው ናቸው። በጋብቻና በመዋለድ ከተፈጠረ የደም ትስስር ባሻገር፣ የአንዱ ጎሳዎች ከሌላው ጋር ተዋህደው በደም እንጂ በብሄር ማንነታቸውን የለወጡበት ሁኔታ አለ። ሁለቱም ህዝቦች በተለይ አዋሳኝ አካባቢ የሚኖሩት በተመሳሳይ የአርብቶ አደርነት ስራ የሚተዳደሩና ለድርቅ የተጋለጡ በመሆናቸው፣ ከዚህ የኑሮ ዘይቤ የመነጨውን ችግርና የችግሩን መፍትሄም ይጋራሉ። ይህ ሁኔታ በጋራ እንዲለሙ የሚያስገድድ ሁኔታ ፈጥሯል። ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱም ህዝቦች ባለፉት ስርአቶች ተመሳሳይ ብሄራዊ ጭቆና ውስጥ የኖሩና መብትና ነጻነታቸውን ለማስከበር በጋራ የታገሉ ናቸው።

በአጠቃላይ ሁለቱ ህዝቦች በታሪክ ብቻ ሳይሆን ቀጣይ እጣ ፈንታቸውም የተሳሰረ ነው። የአንዱ መልማት የሌላው ልማት ነው። የአንዱ ሰላም የሌላው ሰላም ነው። የሶማሌ አርብቶ አደር ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ሳይቀየር የኦሮሞ አርብቶ አደር ህይወት ሊሻሻል አይችልም። የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ሰላም ሳይረጋገጥ፣ የኦሮሚያ ሰላም ሊረጋገጥ አይችልም። በተለይ ዘመናትን ባስቆጠረው መልካም ግንኙነታቸው ውስጥ በአንድ አጋጣሚ ለዛውም ህዝቡ ዋና ተዋናይ ባልሆነበት ሁኔታ የተፈጠረን ግጭት በአግባቡ ባለመያዝ አንዱ በሌላው ላይ ቂም እንዲይዝ ማድረግ ግጭቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ከማደረግ ያለፈ የሚያስገኘው ፋይዳ የለም።

በመሆኑም፤ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች በአንድ አጋጣሚ የተከሰተ ግጭት ያስከተለው ጉዳት – የህይወት መጥፋትና መፈናቀል የሚስተናገደበት መንገድ የሁለቱን ህዝቦች ዘላቂ ግንኙነት እንዳይጎዳ በሁለቱም ወገኖች በኩል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። በአንድ አጋጣሚ ከተፈጠረው ግጭት ጀርባ ዘመናትን ያስቆጠረ መልካም ግንኙነት እንደነበረ፣ ከግጭቱ ባሻገርም ዘላቂ በጎ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሊኖር እንደሚገባው ማሰብ ብልህነት ነው። ካሁን በኋላ ግጭቱንና የግጭቱን ሃንግኦቨር ከማስታመም ይልቅ የሁለቱ ህዝቦች ዘላቂ ወዳጀነት ላይ ማተኮር ይበጃል። የሁለቱ ህዝቦች ዘላቂ ወዳጅነት ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑ እንዳይዘነጋ።

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy