Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዴሞክራሲ ዕድገት ግንባታ በኢትዮጵያ

0 329

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዴሞክራሲ ዕድገት ግንባታ በኢትዮጵያ

አባ መላኩ

 

ኢትዮጵያ በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ መሠረት ያደረገ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት  መገንባት በመቻሏ ዘላቂነት ያለው ሠላም በውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ በተለይ በቀንዱ አካባቢ እንዲሰፍን ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች።

ባለፉት 27 ዓመታት አገሪቱ ስትከተለው የነበረው አምባገነን አህዳዊ ሥርዓት ተደምስሶ ያልተማከለና የህዝቦች ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች የተረጋገጡበት ፌዴራላዊ መንግሥት ከተቋቋመ ጀምሮ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ የነበራት ተሰሚነት እየተሻሻለ በመምጣት ላይ ነው። ኢትዮጵያ ትናንት ትታወቅበት የነበረው ድርቅ፣ ረሃብና ጦርነት ዛሬ የለም፤  የአገሪቱ ገጽታ እጅጉን ተሻሽሏል። ዛሬ በአገሪቱ አስተማማኝ ሠላም አለ፤ በረሃብ የሚሞት የለም፤ ሥራ የማማረጥ አባዜ ካልሆነ ሥራ አለ፤ ማንም መሥራት የሚችልና የሚፈልግ ዜጋ ጦሙን የማያድርባት አገር መፍጠር እየተቻለ ነው። ይህ በአትኩሮት ለተመለከተው ትልቅ ጥንካሬና የአገሪቱን በአስተማማኝ መሠረት ላይ እየቆመች ለመሆኗ አመላካች ነው።

 

ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን መፍታት የቻለችው ጠንካራ የፌዴራል ሥርዓት መከተል በመቻሏ ነው። የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ያስተማረን ትልቅ ነገር ቢኖር መቻቻልና መከባበርን ነው። መንግሥት የሚከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ በመሆኑ ዓለምን ያስደመመ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እንዲሁም ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ማፋጠን ተችሏል። መንግሥት ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ማስመዝገብ ከቻሉ ጥቂት የምሥራቁ ዓለም አገራት (ታይዋንና ደቡብ ኮሪያን ከመሳሰሉ) ልምድ በመቅሰም፣ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በመቀመርና የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን በመተግበር ላይ ይገኛል። ይህም ማለት ከታይዋንና ደቡብ ኮሪያ መልካም መልካም ልምዶችን በመቅሰም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም በመደረጉ አገሪቱ ባለፉት 11 ዓመታት፣ ያለምንም የተፈጥሮ (ማዕድን) ሃብት ባለሁለት አኃዝ ዕድገት ማስመዝገብ  ችላለች።

 

ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ በ30 ዓመታት ውስጥ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ህዝባቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት በማላቀቅ በልማት ጎዳና ማራመድ የቻሉ አገሮች ናቸው። እነዚህ አገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ በልማት ጎዳና ሊጓዙ የቻሉት መንግሥት ይከተለው በነበረው ልማታዊ አካሄድ ምክንያት ነው። መንግሥት በተመረጡ የምጣኔ ሀብት መስኮች ጣልቃ በመግባት የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ የሚፋጠንበትንና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንባቸውንና ሁኔታዎች ያመቻች ነበር። ይሁንና ታይዋንም ሆነች ደቡብ ኮሪያ ይከተሉት የነበረው ልማታዊ መንግሥት ይሁን እንጂ ኢ-ዴሞክራሲ አገዛዝን ይተገብሩ ነበር።

 

ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ነው። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ መንግሥትን የሚመራው ድርጅት ኢሕአዴግ ለ17 ዓመታት የታገለለት የዴሞክራሲ ጥያቄ፣ የብሄር ብሄረሰቦች የእኩልነት ጥያቄ እጅግ አንገብጋቢ ዋነኛ የህዝብ ጥያቄዎች በመሆናቸው እነዚህን ጥያቄዎች ልደፍጥጥ ማለት የሚያስከትለውን አደጋ ስለሚረዳ ነው።

 

ከእንግዲህ በኢትዮጵያ የብሄርና ብሄረሰቦችን እኩልነት የማይቀበል  አገዛዝ ተቀባይነት እንደማይኖረው በህገ-መንግሥቱ ተረጋግጧል። በመሆኑም ልማትን ለማፋጠን ተብሎ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በኢትዮጵያ ሊተገበር አይቻልም። በመሆኑም ከታይዋንና ከደቡብ ኮሪያ የሚበጀንን ልምድ በመቅሰም ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣማችን አገራችን ባለፉት ዓመታት ዓለምን ያስደመመ ባለ ሁለት አኃዝ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች።        

 

አገራችን ዓለምን ያስደመመ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ ከመቻሏ በተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በመመሥረቷም ረገድ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ችላለች። ከጥቂት ዓመታት በፊት የድርቅና ረሃብ ተምሣሌት ተደርጋ ትጠቀስ የነበረች አገር ዛሬ ላይ ባለ ብዙ መቶ ቢሊዬን ዶላሮችን ወጪ የሚጠይቁ ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሳይቀር በራስ አቅም የመገንባት አቅም ለመፍጠር የቻለች የተስፋ አገር መሆን ችላለች።

 

ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በአፍሪካ ሆነ  በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ በማደጉ በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱ በተባበሩት መንግሥታት ዘንድ ያላት ተሰሚነት፣ በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረኮች ያላት ከፍ ያለ ቦታ ከሰማይ የወረደ መና ሳይሆን አገሪቱ ማስመዝገብ በቻለችው የምጣኔ ሀብት ዕድገትና በመሠረተችው ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሣቢያ መሆኑን ማመን ተገቢ ነው።

 

ከቅርብ ጊዜ በፊት በምግብ ሰብል ራሷን መቻል የተሳናት አገር በተከታታይ ዓመታት እንዲህ ያለ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ መቿሏ አስገራሚ ጉዳይ ነው። በአካባቢው ካሉ አገሮች በአጠቃላይ ግብርና ምርት ከፍተኛውን ቁጥር ከመያያዟም ባሻገር በቅርቡ በግብርና ውጤቶች ኤክስፖርትም ትልቅ አቅም ልትፈጥር እንደምትችል መረዳት የሚያዳግት አይደለም። ኢትዮጵያ የአካባቢው አገሮች የኃይል ምንጭ ለመሆን እየሰራችው ያለው የታዳሽ ኃይል ግንባታም እጅግ አስገራሚ ነገር ነው።

 

ዛሬ የአገራችን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ከእጅ ወደ አፍ አመራረት ተላቀው ለገበያ የሚሆን ምርት ማምረት መጀመራቸው፣ የተራቆተውን የተፈጥሮ ሃብት መልሶ እንዲያገግም ተጨማሪ ለምርት የሚሆን መሬት ማግኘት መቻሉ፣ የደረቁ ምንጮች፣ ጅረቶችና ወንዞች መመለስ መጀመራቸውና የቀነሱትም የውኃ መጠናቸው መጨመሩ ይህንን ተከትሎ በአርሶ አደሩ የሚሰሩ የመስኖ አውታሮች መስፋፋታቸው ትልቅ ድል ነው፡፡ ከዝናብ ውኃ ጥገኝነት ደረጃ በደረጃ በመላቀቅ አርሶ አደሮች በዓመት ሁለቴና ሦስቴ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማምረት የሚያስችለው መስኖ ሥራ ላይ መሰማራታቸው የገጠሩ ህዳሴ መሠረት መጣሉን ያመላክታል:: ይህ ውጤት የተገኘው መንግሥት በተከተለው ትክክለኛ  ፖሊሲ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

አገራችን ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር በመቆጠር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኞችን ማስጠለል ብቻ ሰይሆን ለስደተኞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ጭምር ያልተቋረጠ ሙገሳን አግኝታለች።

 

ሰሞኑን የአየርላንድ ፕሬዚዳንት ይህን በተመለከተ የሰጡትን ምስክርነት መመልከት ተገቢ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ለበርካታ የጎረቤት አገራት ስደተኞችን በማስተናገድ እያደረገች ያለችው ተግባር ሊመሰገን የሚገባው ነገር ነው ሲሉ አመስግነዋል። ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት የነበረውን የአገራችንን ሁኔታ ስናስታውስ እንኳን ለሌሎች አገሮች ዜጎች መጠለያ ልትሆን ይቅርና የራሷ ህዝቦችም በጦርነትና በረሃብ ሣቢያ የትውልድ ቀያቸውን  ጥለው የሚሰደዱባት አገር ነበረች።

 

ስደተኞችን ማስጠለል የሚፈጥረው ማህበራዊም ሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ከባድ ቢሆንም አገራችን አቅም በፈቀደ ሁሉ ሁኔታዎች እንዲሟሉላቸው እያደረገች ትገኛለች። ኢትዮጵያ ይህን እያደረገች ያለችው በህዝቦች መካከል ያለው መተሳሰብ የበለጠ እንዲጠናከር በማሰብ እንጂ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ስደተኞችን ማስተናገድ የሚያመጣው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም።  

 

የአገራችን ምጣኔ ሀብት ሲጀምር ከጎረቤት አገራት ጋር በንግድ፣ በባህል፣ በሠላም ማስከበር፣ ወዘተ…ትስስሩ እየጠነከረ መምጣት ጀምሯል። ኢትዮጵያና ጅቡቲ የጠነከረ ግንኙነት መመሥረት በመቻላቸው ምክንያት ሁለቱ አገራት በፖለቲካ፣ ምጣኔ ሀብትና  ማህበራዊ ጉዳዮች ጥብቅ ቁርኝት መፍጠር ችለዋል።

 

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ዘመናዊ የመንገድ ግንባታ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ በአየር በረራ መስመሮች ማስፋፋት፣ የኃይል አቅርቦት . . . በማካሄድ የሁለቱን አገራት ህዝቦች ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጋለች። አገራችን የምትከተለው ፖሊሲ የአካባቢው አገሮች በምጣኔ ሀብት ጥቅም እንዲተሳሰሩ ለማድረግና የቀጠናው ሠላም ዘለቄታዊነት እንዲኖረው የምታደርገውን ጥረት ያሳያል።

 

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ማለትም ከደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን፣  ከኬንያ እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር አካባቢውን በምጣኔ ሀብት ሊያስተሳስሩና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ማለትም የመንገድ፣ የኃይል አቅርቦት፣ የአካባቢ ሠላም፣ ንግድ ወዘተ . . . እንዲስፋፉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነች። እንዲሁም ኢትዮጵያ በተለያዩ የአፍሪካ (በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን፣ ዳርፉር፣ አብዬ) አገራት የሠላም ማስከበር ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። እነዚህ ሁሉ መልካም ነገሮች የመነጩት አገራችን ከምትከተለው የህዝቦችን የጋራ ጥቅም ታሳቢ ያደረገ የውጭ ፖሊሲ መሆኑን መገንዘብ የሚያዳግት አይሆንም። በተመሳሳይ  አትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መሠረት ስትጥል አገሪቱ ያለባትን ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እጥረት ለመፍታት እንዲቻል እንዲሁም በተመጣጣኝ ክፍያ ለጎረቤት አገሮች ኃይል በማቅረብ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ እንጂ በሌሎች የተፋሰሱ አገራት ላይ ጫና ለመፍጠር በማሰብ አይደለም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy