Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ድብቁ ዓላማ

0 384

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ድብቁ ዓላማ

                                                     ቶሎሳ ኡርጌሳ

የቀለም አብዮት (Colour Revolution) ከራሳቸው ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ፍልስፍና ውጭ የሌሎችን መስማትና ማየት የማይፈልጉ አክራሪ ኒዮ-ሊበራል ሃይሎች በአንድ ሀገር ውስጥ የህዝቡን ጥቅም ሳይሆን የእነርሱ ፍላጎት የሚያሳካ ተላላኪ ወይም አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት የሚያደርጉት ጣልቃ ገባዊ ጥረት ነው። የቀለም አብዮቱ በዋነኛነት ከውጭ የሚመራ ሲሆን፤ ሀገር ውስጥ ባሉ የስልጣን ጥም ያሳበዳቸው ተቃዋሚዎች እንዲደገፍ ተደርጎ ይነደፋል።

ይሁንና አንድ የቀለም አብዮት እንዲካሄድበት የተወሰነበት ሀገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ አንድነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ‘በሙያው የተካኑት’ የቀለም አብዮተኞች ሲናገሩ ይደመጣል። ተግባሩን ለመከወንም የዚያችን ሀገር ስም ጥላሸት በመቀባት የሊበራሊዝምን አጀንዳ የሚያቀነቅኑት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከፍተኛ ከፍተኛ ሽፋን እንዲሰጡ ይደረጋል።

እነዚህ ሚዲያዎች የቀለም አብዮቱ በህዝቡ ፍላጎት የተነሳ በማስመሰል በስፋት ይደሰኩራሉ። እናም የዚያች ሀገር ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብና መስፋት እንዲሁም ተቃዋሚዎች ያሉበት ሁኔታ ተጣምመው፣ ተንጋደውና ጎብጠው ይቀርባሉ— የቀለም አብዮቱን ለማስነሳት ጥርጊያ መንገድ በሚፈጥር ሁኔታ።

የቀለም አብዮት በአብዛኛው የሚካሄደው በምርጫ ወቅቶች ቢሆንም፤ ለዘመቻው ያቺ ሀገር ምቹ ሁኔታ እንዳላት በታመነበት ጊዜም ሊከናወን ይችላል። እርግጥ ለገዛ ዜጎቻቸው ኃላፊነት የማይሰማቸውና በሰዎች ደም በአቋራጭ ቤተ-መንግስት መግባት ብቻ የቀንና የሌሊት ህልማቸው የሆነው የሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎች እሳቱን አቀጣጥለውት ወላፈኑን ባህር ማዶ ሆነው የሚሞቁት አክራሪ ኒዮ-ሊበራል ሃይሎች ባስነሱት የቀለም አብዮት አማካኝነት የሚረግፈው ሰው ምናቸውም አይደለም።

እንዲያውም ከምግባራቸው ጋር የማይገናኘውን የሰብዓዊ መብትና የግጭት ፈቺዎች ነን ባይ ካባን በደረቡ ዋነኛዎቹ የቀለም አብዮት አቀጣጣይ ባልደረቦቻቸው አማካኝነት በሁኔታው እየሳቁ ጉዳዮን ለሪፖርት ፍጆታነት በመደጋገም ይጠቀሙበታል። “በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት” ይሏል እንዲህ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የቀለም አብዮት ዋነኛ መንስኤዎች ተብለው የሚጠቀሱት፤ የምዕራቡን ዓለም ርዕዩተ-ዓለም የማስፋፋት ስትራቴጂ፣ የኃይል አቅርቦትና ሽብርተኝነትን መዋጋት የሚሉ አስባቦች መሆናቸውን በየጊዜው የሚወጡ ድርሳናት ያስረዳሉ። እነዚህን ህልዮቶችና ፍላጎቶች ለስኬት እንዲበቁ የሚደረገውም በሰብዓዊ ዕርዳታና በዴሞክራሲ ስም በሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (INGOs) አማካኝነት መሆኑንም እንዲሁ፡፡

በጆርጂያ፣ በዩክሬንና በኪርጊዚስታን የተካሄዱት የቀለም አብዮቶች ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ ሀገሮች ውስጥ ቀደም ሲል ለተካሄደው የቀለም አብዮት ስኬታማነት የዓለም አቀፉ መያዶች ድርሻ ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር፤ የመያዶቹ ጣልቃ ገብነት ባይኖር የየሀገራቱን ፖለቲካዊ ምህዳር መቀየር የማይታሰብ እንደሆነ ብዙዎቹን ያስማማ ሃቅ ነው።

የያኔዎቹ የጆርጂያው “ሮዝ”፣ የዩክሬይኑ “ብርትኳናማ” እና የኪርጊዚስታኑ “ቀይ አበባ” አብዮቶች ተከታታይነትና የጡዘታቸው አምሳያነት እንዲሁም የተቀናበሩት በዴሞክራሲ ስም በሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደሆነ ይነገራል፡፡

ከዚህ በባሻገርም በኡዝቤኪስታንና በአዘርባጃን የተፈጠረው ያለመረጋጋት እንደ ሌሎች የቀለም አብዮት ሰለባ ሀገሮች ስኬታማ ሊሆን ያልቻለው፤ በዋነኛነት በየሀገራቱ የነበረው ተጨባጭ ሁኔታ ምቹ አለመሆን ነው።

ሆኖም ‘የእኛን ብቻ እንጂ የራስህን መፅሐፍ ፈፅሞ አታንብበው፤ መመሪያህም አታድርገው’ በሚል ከእኔ ወዲያ ላሳር ፅንፍ የወጣ ኒዮ-ሊበራላዊ እሳቤ አማካኝነት በተለያዩ ሀገራት ውስጥ የተካሄደው የቀለም አብዮት ዘመቻ በየሀገራቱ ባለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አውድ (Context) ምክንያት እንዲሁም የቀለም አብዮቱ በፈጠረው ሀገራዊ ምስቅልቅል ሁኔታ ሳቢያ ስኬታማ ሆኗል ለማለት አይቻልም።

ሁላችንም እንደምናስታውሰው፤ በምርጫ 97 ወቅት በአንድ በኩል ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ የህዝብን አመኔታ እንዲያጣና በአመፅ ተተራምሶ የትርምሱ ውጤት የሆነ መንግስት እንዲቋቋም በሚፈልጉት የቀለም አብዮት አራማጆች ከፍተኛ ፍልሚያ ማካሄዳቸውን እናስታውሳለን።

ምንም እንኳን ይህ ፍልሚያ በመንግስትና በቀለም አብዮት አራማጆቹ ስትራቴጂዎች መካከል የተካሄደ ቢሆንም በስተመጨረሻው መንግስት የፖለቲካና የህዝብ የበላይነትን ማረጋገጥ በመቻሉ ገና በእንጭጩ ሊከሽፍ ችሏል።

አዎ! በወቅቱ በሀገራችን ጭላንጭሉ ታይቶ የነበረው የቀለም አብዮት ሳይወለድ በመጨንገፉ ሳቢያ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሻረ ብስጭት ውስጥ ያሉት እነ ሂዮማን ራይትስ ዎች ዓይነት በሰብዓዊ መብት ስም የሚነግዱ ፅንፈኛ ኒዮ ሊበራል ሃይሎች የሀገራችንን ገፅታ በተደጋጋሚ ከማጠልሸት አልቦዘኑም—በግልና በዘመቻ መልክ።

ያም ሆኖ በምርጫ 97 ወቅት መንግስት የፖለቲካና የህግ የበላይነትን በማያሻማ ሁኔታ በማረጋገጡ ምክንያት የቀለም አብዮት ሀገራችን ውስጥ ስላልተከሰተ፤ እነዚህ በሰብዓዊ መብት ስም የሚነግዱ የቀለም አብዩተኞች በምርጫ 2002 ወቅትም እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ ከማለት አልቦዘኑም።

የቀለም አብዮተኞቹ ምንም እንኳን በወቅቱ ወደ ሀገራችን መምጣት ባይችሉም፤ በሀገራችን እንዲከሰት የሚሹትን የቀለም አብዮት ከመደገፍ ወደ ኋላ አላሉም። የቀለም አብዮት አራማጆቹ ፅንፈኛ ሃይሎችን በመደገፍ የሚሹት “አብዮት” እንዲቀጣጠል ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎችንም በወቅቱ ቢያካሂዱም አልቀናቸውም። እናም ውጤቱ በቀለም አብዮተኞቹ የህልም ቅዥት ሳይሆን፣ በድምፅ ሰጪው የኢትዮጵያ ህዝብ ሚዛናዊና ፍትሐዊ ውሳኔ ሊደመደም ችሏል።

ያም ሆነ ይህ ግን ሁሌም ደካማና አሻንጉሊት መንግስት ተመስርቶ የሀገራችን ህዝቦችና መንግስት የጀመሩት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ እንዳያድግ የቀለም አብዮትን የሚያቀነቅኑት ሃይሎች፤ ዛሬም ድረስ የጥፋት እጃቸው ከሀገራችንና ከህዝቦቿ ላይ አላነሱም። በምርጫ 2007 ወቅትም የተቻላቸውን ቢያደርጉም አልሰመረላቸውም።

ከዚያም በኋላ በሀገራችን ውስጥ ሰላም እንዳይፈጠር የመጣር፣ የጎዳና ላይ ነውጦችን በተለያዩ መንገዶች የመደገፍ፣ እንዲሁም ለቀለም አብዩት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ጣልቃ ገባዊ ስራቸውን አከናውነዋል። በአሁኑ ወቅትም የቀለም አብዩት አዝማሚያ እየታየ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት መግለፁ ይታወሳል።

የቀለም አብዩተኞች ለሌላ ሀገር ዜጎች ያሰቡ በመምሰል በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሽፋን ተግ ራቸውን መከወን ነው። ሆኖም ድብቁ ዓላማቸው የራሳቸውን ርዕዩተ-ዓለም በማራመድ የአንድን ሀገር አንጡራ ሃብት በዲታዎቻቸው አማካኝነት እንዲበዘበዝ ማድረግ ነው። ለዚህም ስለ ህዝቡ ደንታ ቢስ የሆነ አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት ይጥራሉ።

ሆኖም ይህን ማድረግ አሁን ባለው ሁኔታ ፈፅሞ የሚቻል አይመስለኝም። ኢትዮጵያ ውስጥ መሰረቱ ተጥሎ በመገንባት ላይ የሚገኘው ስርዓትና መንግስት ታዛዥነቱ ለህዝቡና ለህዝቡ ብቻ ስለሆነ ነው። ህዝቡ በሀገሩ የሚያገኘውን ተጠቃሚነት መቼም ቢሆን ለባዕዳን አሳልፎ መስጠት አይሻም። እናም የቀለም አብዩት ድብቅ ዓላማ ይኸው መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ለሰላሙ በመትጋት በሀገሩ የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚው እርሱ ብቻ መሆኑን ማረጋገጥ መቻል አለበት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy