Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጉዞው ይቀጥላል

0 299

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጉዞው ይቀጥላል

አለማየሁ አ

ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ለመያዝ የበቃ ፓርቲ ነው። ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንዲኖረው የሚያደርገው ቀዳሚው ጉዳይ የሃገሪቱ መሰረታዊ የፖለቲካ ቅራኔ የነበረውን የብሄር ቅራኔ ለመፍታት በተደረገው የትጥቅ ትግል ውስጥ የጎላ ድርሻ የነበረው መሆኑ ነው። በተመሳሳይ መነሻ ምክንያት  ወደትጥቅ ትግል የገቡ በርካታ ብሄራዊ ድርጅቶች መኖራቸው ባይካድም፣ አንዳንዶቹ ድርጅቶች ከኢህአዴግ ወይም ከአባል ድርጅቶቹ በእድሜ የሚቀድሙ ቢሆንም ወታደራዊውን ደርግ በማስወገድ ትግል ውስጥ ኢህአዴግ የጎላ ድርሻ ነበረው።

ይህ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ፣ የሃገሪቱ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ሆነው በመከባበርና በእኩልነት ላይ በተመሰረተ አንድነት የሚኖሩባትን ፌደራላዊት ኢትዮጵያ በማዋቀሩ ሂደት ውስጥም ጉልህ ሚና ነበረው። ፌደራላዊት ኢትዮጵያ ከተመሰረተችም በኋላ በህዝብ ውክልና ባገኘው የመንግስት ስልጣን በሰጠው አመራር፣ በተለይ የህዝቡ ዋና ጠላት የሆነውን ድህነት ለማስወገድ ያከናወነው ተግባርና ያስገኘው ውጤት ታሪካዊ ስፍራ እንዲኖረው ያደርገዋል።

ኢህአዴግ በህዝብ ውክልና ሃገር በመራባቸው ያለፉ ሃያ ሶስት ዓመታት በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የኢኮኖሚ እድገትና የህዝቡ ኑሮ ላይ ተጠባጭ መሻሻል ያመጣ ልማት ማስመዝገብ ተችሏል። አሁንም ኢትዮጵያ በዓለማችን በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ሃገራት አንዷ ነች። ኢትዮጵያ የፀረ ድህነት ትግሏ ውጤታማ ሆኖ የህዝቧን የተሻለ ህይወት ለማረጋገጥ የሚያስፈልጋትን አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን ሰላም ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የሃገሩን ሰላም ግብ አድርጎ የምስራቅ አፈሪካን ቀጠናን ሰላም በማስጠበቅ በኩል ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘ ተግባር አከናውኗል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላት ተሳተፎና ተሰሚነት እንዲያድግ ማድረግ አስችሏል።

በአጠቃላይ ኢህአዴግ እንደድርጅት በሃገሪቱ ታሪክ ሲጠቀሱ የሚኖሩ በርካታ ስኬቶች እንዲመዘገቡ ማድረግ ችሏል። ከአሁን በኋላ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ኢህአዴግ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ መሆኑ እውነት ነው። ኢህአዴግ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስትራቴጂዎቹንና ፕሮግራሞቹን በማሳካት ረገድ ጉልህ ታሪካዊ ሚና እንዲኖረው ያስቻለው ቀዳሚው ጉዳይ ድርጅታዊ ጥንካሬው ነው። ድርጅታዊ ጥንካሬ ከዓላማ ጥራት፣ አባላቱ አላማው ላይ ካላቸው ግልጽ ግንዛቤ፣ ዓላማውን ለማሳካት ካለ ቁርጠኝነትና ዲስፕሊን ይመነጫል። እንደ ድርጅት የሚመራበት መተዳደሪያ ደንብና የደንቡ ተግባራዊነትም የጥንካሬው ምንጭ ነው።

ኢህአዴግ በርካታ ውስጣዊ ፈተናዎች ገጥመውት ማለፍ የቻለ ፓርቲ ነው። ለምሳሌ በ1993 ዓ/ም ገጥሞት የነበረው ውስጣዊ ብልሽትና መሰንጠቅ የፓርቲውን ህልውና የተፈታተነ ነበር። ይህ ወቅት ሃገሪቱ ከኤርትራ ወረራ ጉዳት ማገገም ወደመጀመር የተሸጋገረችበት ነበር።  ከወረራው ጉዳት ማገገም አቅቷት ደካማ ሆና ቢሆን ኖሮ በማንኛውም ሰአት ወረራው ሊያገረሽ የሚችልበት እድል ነበር። በዚህ ምክንያት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ችግር ሃገሪቷንም ለከፋ አደጋ ያጋለጠ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ ሃገሪቱን በመታው አስከፊ ድርቅ 14 ሚሊየን ገደማ የሚሆኑ ዜጎች ለምግብ እጥረት ተጋለጠው ነበር። በኢህአዴግ የውስጥ ችግር መንግስት ስራውን በአግባቡ ማከናወን አቅቶት ቢሆን ኖሮ፣ ይህ የምግብ እጥረት ወደችጋርነት አድጎ ምናልባት በሃገሪቱ ሌላ በአስከፊነቱ ሲጠቀስ የሚኖር ሞትና ስደት ያጋጥም ነበር።

ይሁን እንጂ፣ ኢህአዴግ የራሱም ህልውና ሳይጠፋ ሃገሪቱንም ለከፋ አደጋ ሳያጋልጥ ውስጣዊ ችግሩን ፈትቶ በተሃደሶ ጠንክሮ መውጣት ችሏል። ብዙዎቹ አንጋፋ ነን የሚሉና ታዋቂ በሚባሉ ፖለቲከኞች የሚመሩ የሃገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራቢ ሃገርን የማስተዳደር ሃላፊነት ሳይኖርባቸው በውስጣቸው የተፈጠረውን ቀላል ችግር በድርጅታዊ መተዳደሪያ ደንብ ላይ በመመስረት ዴሞክራሲያዊ በሆነ ስርአት መፍታት ተስኗቸው መፍረሳቸውን ወይም ጥንካሬያቸውን ሙሉ በሙሉ አጥተው ስማቸው ብቻ ከመቅረቱ አኳያ ሲመዘን ኢህአዴግ ምን ያህል የላቀ አቅም ያለው ድርጅት እንደሆነ ያሳያል። የቀድሞው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ (አንድነት) የውስጥ ችግራቸውን መፍታት አቅቷቸው ጠፍተዋል፤ ከነበሩበት ደረጃ ወርደው ትናንሽ ፓርቲዎች ሆነዋል።

ኢህአዴግ በ2004 ዓ/ም ማገባደጃ ላይ ሊቀመነበሩ የነበሩትን የቀድሞ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በድንገት በሞት አጥቷል። ይሁን እንጂ የሊቀመንበሩ በድንገት በሞት መለየት ድርጅቱን አላናጋም። በዚህም ኢህአዴግ ከግለሰቦች በላይ የሆነ ህልውና እንዳለው አስመስክሯል።  

ይህን አጋጣሚ ተከትሎ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት አራቱም የግንባሩ እህት ድርጅቶች (ህወሃት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን) እያንዳንዳቸው በ45 ድምጽ የሚወከሉበት የኢህአዴግ ምክር ቤት ተሰብስቦ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ በሆነ ስርአት ሊቀመነበሩን መርጧል፤ የደኢህዴኑን ሊቀመነበር አቶ ሃይለማርያምን።

ኢህአዴግ አሁንም ሊቀምነበሩን አጥቷል። ድንገተኛ ሊባል በሚችል ሁኔታ ሊቀመነበሩ የነበሩት ሃይለማርያም ደሳለኝ በገዛ ፍቃዳቸው ከደኢህዴንና ከኢህአዴግ ሊቀመነበርነት ለመለቀቅ ጥያቄ አቅርበው ጥያቄያቸው በእናት ድርጅታቸው ደኢህዴንና በግንባሩ ኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተቀባይነት አግኝቷል። በቀጣይ 180 አባላት ያሉት የድርጅቱ ምክር ቤት ሊቀመነበሩን ይመርጣል። ሊቀመነበር የሚመረጠው እህት ድርጅቶቹ ከሚያቀርቧቸው እጩዎች መሃከል በምስጢራዊ የድምጽ አሰጣጥ ስርአት ነው። አብላጫ ድምጽ ያገኘው እጩ የግንባሩ ሊቀመነበር ይሆናል።

የኢህአዴግ የሊቀመንበር ምርጫ በኢህአዴግ ውስጥ አያበቃም። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ አብላጫ መቀመጫ አግኝቶ መንግስት የመሰረተ ገዢ ፓርቲ በመሆኑ፣ ሊቀመንበሩ ሃይለማርያም ደሳለኝ የኢፌዴሪ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸውና ከዚህ ሃላፊነታቸውም ለመነሳት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ በማቅረባቸው ምክር ቤቱ ጥያቄያቸውን ከተቀበለ ሌላ እጩ ጠቅላይ ሚኒስትር አቅርቦ ማስመረጥ ይጠበቅበታል። ኢህአዴግ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ አድርጎ የሚያቀርበው ሊቀመነበሩን ነው። በመሆኑም የኢህአዴግ ሊቀመነበር ምርጫ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። የሃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን መለቀቂያም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በይፋ ተቀባይነት እንዳገኘ በምትካቸው አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሰየማል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በሃገራቸው ሰላምና ልማት ተጠቃሚ በሚሆኑ፣ በሃገራቸው ድህነትና የሰላም እጦት ተጎጂዎቸ በሚሆኑ፣ በዚህም ምክንያት የሃገራቸው እጣ ፈንታ በሚሳስባቸው የኢትዮጵያዊነት ዜግነት ባላቸው ሰዎች የተወከሉ አባላት ባሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምጽ ብቻ ነው የሚመረጠው። ይህ ሂደት ምርጫው የህዝብ መሆኑን ያመለከታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ማንም – ኤርትራዊም፣ ግብጻዊም፣ . . . ድምጽ በሚሰጡበት፣ ውጭ ሃገር በሚኖሩና የየራሳቸው ፖለቲካዊ አጀንዳ ባላቸው፣ አንዳንዶቹም የሃገሪቱ ጠላቶች ተለጣፊ በሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦች በሚያዘጋጁት ማህበራዊ ሚዲያ በሚሰጥ ድምጽ አይመረጥም።

ለኢትዮጵያ በሰላማዊ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር መምረጥ የተጀመረውን ዴሞክራሲን የማበልጸግ ሂደት የማስቀጠል ጉዳይ ነው፤ የህዝቡን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት የማሰቀጠል ጉዳይ ነው። እስካሁን ያለው ሂደት እንከን አልባ የጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ ሊካሄድ እንደሚችል ያመለክታል። የሃገሪቱ ሰላም ባለቤት የሆነውና በሃገሪቱ ልማት ተጠቃሚ የሚሆነው ህዝብ ሰላሙን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ በባለቤትነት ስሜት በመንቀሳቀስ ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ድጋፍ የማደረግ የሞራል ሃላፊነት አለበት። እናም ከጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ ጋር በተያያዘ የሚጎተት የሚቆምም ነገር አይኖርም። ጠቅላይ ሚኒስትር የመምረጡ ስራም በሰላም ይከናወናል፤ ዴሞክራሲን የማበልጸግና ልማቱን የማስቀጠሉ ተግባርና ጉዞም እስካሁን በመጣበት ክብደትና ፍጥነት ልክ ይቀጥላል።    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy