Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጉዳቱ ምንድን ነው?

0 574

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጉዳቱ ምንድን ነው?

                                                          ዘአማን በላይ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ ከሆነ ጀምሮ አንፃራዊ ሰላም ማግኘት ተችሏል። ትናንት በአንዳንድ አካባቢዎች የነበረው የሰላም እጦት ከአዋጁ ወዲህ መሻሻል መሻሻል እየታየበት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ አዋጁ ባይታወጅ ኖሮ ሊፈጠር የሚችለውን ጉዳት ከፍተኛ ነበር። ታዲያ ለዚህ አንፃራዊ ሰላም መገኘት በህዝባዊ ወገንተኝነት የሚንቀሳቀሰውና በዲስፕሊን የታነፀው እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በሚገባ የሚገነዘበው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ከሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን የሰጠውን ህዝባዊና ሀገራዊ ግዳጅ የህዝብን መብት ለማስከበር በመንቀሳቀሱ ነው። ርግጥ ሰላሙን የማይፈልግ ህዝብ ባለመኖሩ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ከመከላከያ ሰራዊታችን ጋር እየሰራ ነው። ህዝቡ ከአብራኩ የወጣውን መከላከያ ሰራዊት እንደ ዋስትናው የሚቆጥረው በመሆኑ ትናንትም ይሁን ዛሬ በደጀንነት አብሮት እንደተሰለፈ ነው።

ግና የሀገራችንን ሰላም የማይፈልጉ አንዳንድ ሃይሎች መከላከያ ሰራዊታችንን በውሸት ሊያጠለሹት ሲሞክሩ ይታያሉ። ርግጥ እዚህ ላይ ‘ሰራዊቱ ሰላምን በማስከበር ስራ ላይ መሰማራቱ ጉዳቱ ምንድነው?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ህዝቡ ሰላሙን እየፈለገና ሰራዊቱም ተግባሩን እየተወጣ እያለ ሰራዊቱን በሐሰት ለመፈረጅ የሚፈገው ሃይል ፅንፈኛውና አንዳንድ የሀገር ውስጥ ተከታዮቻቸው መሆናቸውን ጥያቄው ምላሽ ስለሚሰጥ ነው።

በአሁኑ ወቅት መከላከያ ሰራዊቱ ህዝቡ ተረጋግቶ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እንዲያካሂድ እያስቻለው ይገኛል። ይህም ሰራዊቱ የህዝቡን የሰላም ጥያቄ ከመመለስ ባሻገር፤ ለዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ መድን ሆኖ እየሰራ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ሰራዊቱ በሀገር ቤት ውስጥ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈፀም ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን እንዳይወጣ የሚፈልጉ ወገኖች አንዳንድ ፅንፈኞችና ወኪሎቻቸው መሆናቸውን ሁሉም ዜጋ ሊገነዘበው ይገባል።

ርግጥ የእነዚህ ሃይሎች ፍላጎት ግልፅ ነው። ይኸውም እነዚህ ሃይሎች ኢትዮጵያ ተዳክማና ህዝቦቿን መመገብ አቅቷት ወደ አዘቅት ውስጥ ገብታ ማየት የሚሹ ናቸው። ይህች በአስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እየተጓዘች ለአፍሪካዊያን ወንድሞቿ አርአያ መሆን የቻለች ሀገር እንደ ሶሪያ፣ የመን፣ አራቅና አፍጋኒስታን እንድትሆን የሚከጅሉ ናቸው። ሆኖም የሀገራችን ህዝብ ሰላምን እንደም አጥብቆ እንደሚሻ እንኳን የተገነዘቡ አይደሉም። ስለ ሰላም ጠቀሜታ ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ የሚያውቅ የለም። ሰላም ያመጣለትን ትሩፋቶች ላለፉት 27 ዓመታት በሚገባ የተገነዘበ ህዝብ ነው። ማንም የሰላምን ጠቀሜታ ሊነግረው አይችልም።

ያም ሆኖ ሁከትና ብጥብጥ አራማጆቹ በተቻላቸው መጠን የሰራዊቱን ስም ለማጉደፍ ቢንቀሳቀሱም መከላከያ ሰራዊታችን ህዝብና ሀገር የጣሉበትን ሃላፊነት እንደተለመደው በብቃት ከመወጣት ወደ ኋላ አይልም። ታማኝነቱ ለህገ መንግስቱና ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ብቻ በመሆኑም ይህን ሃይል በአሉባልታ ወሬ ከመደበኛ ተግባሩ ማናጠብ አይቻልም።

ርግጥ ሰራዊቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ መሳተፉ የሁከትና የብጥብጥ ሃይሎችን አያስደስታቸውም። ምክንያቱም ሰራዊቱ የተላኩበትን መልዕክት ከግብ ሳያደርሱ መንገድ ላይ እንዲቀሩ የሚያደርጋቸው ስለሆነ ነው። ታዲያ ይህ ህዝባዊ ሰራዊት በህገ መንግስታዊ እምነቱ፣ በዓላማ ፅናቱና በማይነጥፍ ጀግንነቱ በተደጋጋሚ ብቃቱን ያስመሰከረ ነው። የሀገሩን ዳር ድንበር በደምና አጥንቱ ያስከበረና የውድ የህዝብ ልጆችን አደራ ተቀብሎ የሚሰራ ነው። በዚህም ፀረ ሰላምና ፀረ ልማት ኃይሎችን በመደምሰስ ለልማቱ አስተማማኝ ሰላምን መፍጠር ችሏል። እንኳንስ በሀገሩ ውስጥ ቀርቶ፣ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮም በሁለት ተቃራኒ ኃይሎች ሳይቀሩ ያለ አንዳች ልዩነት በህዝባዊነቱ የመረጡት ብቸኛ የህዝብ ወገን ነው።

ታዲያ ‘ሰራዊቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ መሳተፉ ጉዳቱ ምንድነው?’ የሚለውን ዕውነታ ለማሳየት ባሰናዳኋት በዚህች አጭር ፅሑፍ፤ የዚህን ህዝባዊ ሃይል ተዘርዝረው የማያልቁ የስኬት ምስጢሮች መግለፅ የሚቻል አይመስለኝም። ግና የስኬቶቹ ምስጢሮች ለውድ አንባቢያን መገለፅ ስላለባቸው ‘ዓባይን በጭልፋ’ እንዲሉ፤ በመጠኑም ቢሆን ‘እንካችሁ’ ማለት ይኖርብኛል። በእኔ እምነት ምስጢሮቹ ጠቅለል ብለው ሲታዩ፤ ሰራዊቱ በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የማይናወጥ ፅኑ እምነትና አቋም ያለው፣ የዓላማ ፅናትን የተላበሰ፣ ተልዕኮውን ሲፈፅም ህዝብን እያማከረና በህዝብ እየታገዘ መሆኑ እንዲሁም ህዝባዊ ወገንተኝነቱ በጠንካራ መሰረት ላይ በተከታታይ ተቋማዊ ግንባታዎች የተገነባ መሆኑን መግለፅ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።

ታዲያ እነዚህ የሰራዊታችን ስኬቶች ለእንደ እኔ ዓይነቱ ዜጋ የሚያስተምሩት በርካታ ጉዳዩች ይኖራሉ። ይኸውም ስኬቶቹ ምክንያት ፍርሃትን ሳይሆን አክብሮትን፣ በጥላቻ ፈንታ ጥልቅ ህዝባዊ ፍቅርን፣ ከራስ ይልቅ ለህዝብና ለሀገር መስዕዋት መሆንን፣ እያንዳንዱን ተልዕኮ በሃይል ሳይሆን ዲሲፕሊን በተሞላበት የህዝብ ወገንተኛ ሆኖ መከወንን ያስተምረናል።  

ባለፉት ስርዓቶች የነበሩት ሰራዊቶች ህዝቡ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ባስታጠቃቸው ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ተጠቅመው ወገናቸውን እንዳልጨፈጨፉ፣ የአዛውንቶች፣ ሴቶችና ህጻናትን ህይወት እንዳላጠፉ፣ ጨቅላ ህፃን የሙት እናቷን ጡት ስትጠባ የሚያሳይ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሰቃቂ ትዕይንት እንዳላሳዩን፤ ዛሬ ታሪክ ተቀይሮ ሌላ ዓይነት ህዝባዊ ወገንተኛ ሰራዊት ተፈጥሯል። ህዝባችንም ሰራዊቱ ከአብራኩ የወጣ በመሆኑ በተልዕኮው ሁሉ ከጎኑ ነው።

ቀደም ሲል እንዳልኩት ሰራዊቱ ታገዥነቱ ለህገ መንግስቱና ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ በመሆኑ፣ ህገ መንግስቱም ይሁን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ ህዝቦች ባፀደቁት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ እየተመራ አደጋውን ለመቀልበስ ይሰራል። እናም ልክ እንደ ሰሞኑ ሀገራችን አድጋ የረሃብ፣ ድህነትና መሃይምነት ተምሳሌነቷ ተፍቆ ማየት የማይፈልጉ፣ መበታተንና ተስፋ አልባነታችንን የሚናፍቁ የውጭና የውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎች ሲፈጠሩ፣ ሴራውን እንዲያከሽፍ በአዋጅ ይታዘዛል።

ታዲያ ይህን ተግባሩንም ከኤርትራ ወረራ እስከ አልሸባብ የግብረ ሽበራ ተግባርን እንዲሁም ከሰሜን እስከ ደቡብ ባሉ የሀገራችን አካባቢዎች ሻዕቢያ እያስታጠቀ በሚልካቸውን አሸባሪዎችና ፀረ ሰላም ሃይሎች ላይ ህዝባዊ ክንዱን በማሳረፍ ያረጋገጠ ሃይል ነው። ትናንትም የመጀመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ በህገ መንግስቱ መሰረት ለ10 ወራት ሲታወጅ ተልዕኮውን ከህዝብ ጋር በመሆን በፍፁም ህዝባዊነትና በዲሲፕሊን በታነፀ አሰራር መፈፀም የቻለ ሃይል ነው። በዚህም በወቅቱ በሀገሪቱ ላይ አንዣቦ የነበረው የስጋት ደመና እንዲገፈፍ አድርጓል።

ዛሬም የህዝቡ የሰላም ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑና ህገ መንግስቱና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ በመውደቃቸው ሳቢያ የህዝቡ እንደራሴ የሆኑት የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አባላት በአብላጫ ድምፅ ባፀደቁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ በተሰጠው የስልጣን ወሰን ብቻ አየተሳተፈ ነው። የሰራዊቱ በአዋጁ ላይ መሳተፍ እንደ እሬት ያንገሸገሻቸው እነዚህ ፀረ ሰላም ሃይሎች፤ በሁከና በግርግር እንዲሁም የህዝብን መሰረታዊ መብቶች በጠራራ ፀሐይ በመግፈፍ ለመጠቀም የሚሹ ‘የስው ደም ነጋዴዎች’ ናቸው። በአሜሪካና በአውሮፓ የተንደላቀቀ ኑሯቸውን እየመሩና ልጆቻቸውን እያስተማሩ እዚህ ሀገር ውስጥ በድሃ ልጅ ደም ለመጫወት የሚሞክሩት ፅንፈኞች በሰራዊቱ ተሳትፎ በአያሌው ተከፍተዋል፤ ተበሳጭተዋል።

ይህ ብስጭታቸውም ‘ከህዝብ በፊት እኔ እሰዋለሁ’ ብሎ የተሰለፈ ሃይልን ስም ለማጉደፍ እንዲሯሯጡ አድርጓቸዋል። የስም ማጉደፍ ዘመቻውም ከሰራዊቱ ህዝባዊ አመለካከት ጋር ፈፅሞ የማይሄድና “ሰብዓዊ መብቶችን ይገፋል” ተራ ዘለፋ ብቻ ነው። ርግጥ ይህ “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” ዓይነት ተራ ዘለፋ ምክንያቱ ግልፅ ይመስለኛል። ይኸውም ሰራዊቱ ግዳጁን ሲወጣ ከህዝብ ጋር እየተመካከረ መሆኑን ስለሚያውቁ፤ ሃሳባቸው “ሰራዊቱ ከሚወደው ህዝብ ጋር ተልዕኮው ከሌላ ጊዜ በበለጠ ያቀራርበዋል፤ በዚህም ሳቢያ እኛን ህዝቡ አይሰማንም” ከሚል የፍራቻ አስተሳሰብ የመነጨ መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።

ያም ሆኖ እነርሱ ያላወቁት ነገር ህዝቡ በተለይ ወጣቱ ባለማወቅ ካልሆነ በስተቀር ከትናንት በስቲያም፣ ትናንትም ይሁን ዛሬ እምነቱ ያፀደቀው ህገ መንግስት በፈጠረውና የህዝብ ወገን በሆነው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ላይ ብቻ ነው። ምክንያቱም ሰራዊቱ በአዋጁ ላይ የተሳተፈው አንድም ህገ መንግስቱ ስለሚያዘው፣ ሁለትም የህዝቡ የዕለት ተዕለት ተግባር ህግና ስርዓት ባለው መልኩ እንዲከናወን ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ስለሆነ ነው።

ይህን ዕውነታ ሀገር ውስጥ የሚገኘው ህዝብ በሚገባ የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ፤ በአሁኑ ወቅት ህዝቡና ሰራዊቱ ተቀናጅተው በመስራት ውጤት እያስገኙ ነው። ይህ የህዝብ ሰራዊት በአዋጁ ላይ መሳተፉ ጉዳቱ ለሁከትና ለብጥብጥ አርበኞች እንጂ ለህዝቡ አይደለም። ህዝቡ ከሰላሙ ተጠቃሚ ነው። እናም ሰላምን አጥብቆ የሚሻው የሀገራችን ህዝብ የሰላም ሰራዊት ከሆነውና ህዝብን የተልዕኮው አጋር አድርጎ ከሚንቀሳቀሰው መከላከያ ሰራዊታችን ነገም ይሁን ከነገ ወዲያ በአዋጁ ተጠቃሚነቱ ይበልጥ መረጋገጡ አይቀሬ ነው። ክብርና ሞገስ እየሞተ ለሚያኖረን ህዝባዊው መከላከያ ሰራዊታችን ይሁን!   

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy