Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጉዳት ለደረሰባቸዉ 302 የኢንቨስትመንት ተቋማት ድጋፍ እየተደረገ ነው

0 315

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጉዳት ለደረሰባቸዉ 302 የኢንቨስትመንት ተቋማት ድጋፍ እየተደረገ ነው

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረዉ አለመረጋጋት ጉዳት ለደረሰባቸዉ የኢንቨስትመንት ተቋማት መንግስት ድጋፍ ማድረግ ጀምሯል።

ጉዳት ለደረሰባቸዉ የኢንቨስትመንት ተቋማት ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ ተናግረዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዛሬ በሰጠዉ መግለጫ፥ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ከአንድ ዓመት ተኩል ወዲህ በተከሰተው አለመረጋጋት ጉዳት የደረሰባቸዉ 302 የኢንቨስትመንት ተቋማት ናቸው ብሏል።

ከነዚህ ዉሰጥ 53 የኢንቨስትመንት ተቋማት በአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ዘርፍ የተሰማሩት ናቸዉ።

እነዚህ ተቋማት በብዛት ብቻ ሳይሆን በጉዳት መጠንም ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገዱ ሲሆን፥ 178 ሚሊየን ብር ኪሳራ ደርሶባቸዋል።

የጉዳት መጠናቸዉ የተለያየ ቢሆንም በ48 የቡና ማዘጋጃ ኢንዱሰትሪዎች ላይም ወደ 65 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ኪሳራ እንደደረሰ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በስድስት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ በደረሰ ጉዳት ደግሞ የ105 ሚልየን ብር ኪሰራ ደርሷል ነው የተባለዉ።

እንደ አቶ ፍጹም አረጋ ገለጻ ከሆነ፥ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት ጉዳት የደረሰባቸው ድርጅቶች በባለሙያዎች እንዲለዩ እና የጉዳት መጠናቸዉ እንዲጠና ተደርጓል።

ከተደረገው የልየታ ስራ በኋላም ለጉዳታቸው በመንግስት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ተወስኗል ብለዋል።

ለዚህም ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የተመደበ ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና ንግድ ባንክ ጋር በመሆን ኮሚሽኑ ስራውን እያስፈጸመ መሆኑንም ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥም ለ200 በላይ ለሚሆኑት የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በተፈጠረዉ የጸጥታ ችግር ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸዉ የማግባባት ስራ በተለያየ መልኩ እንደተሰራ ነዉ ያብራሩት።

በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለባለሀብቱ የሚሰጠዉን የሰላም ዋስትና የማስገንዘብ ስራ ተከናውኗል።

በኢንቨስትመንት ላይ ላሉትም ሆነ ወደ ዘርፍ ለመግባት ወስነው በፀጥታዉ ጉዳይ በስጋት ውስጥ ለነበሩትም ጭምር ችግሩን እንዲገነዘቡ ስራዎች በስፋት ተሰርተዋል ነዉ ያሉት አቶ ፍጹም።

እነዚህ ስራዎች በመሰራታቸውም ባለሀብቶቹ በመንግስት እና በህዝብ ላይ ያላቸው እምነት እየተጠናከረ መምጣቱንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በቀጣይ አንድ አመት በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ ብቻ እስከ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ቁርጠኝነታቸውን የገለጹ ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች መኖራቸውንም አስታውቀዋል።

ሀገሪቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆናም ባለፉት ስድስት ወራት የካፒታል መጠኑ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የደረሰ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማግኘቷን ነው አቶ ፍፁም ያስታወቁት።

አሁን ከተመዘገበው የኢንቨስትመነት ዕድገት በተጨማሪ ሃገሪቱ ባላት የኢንቨስትመነት አማራጮች ባለሃብቶች ሙሉ እምነት እንዲኖራቸው ሳለም በዘላቂነት ማስጠበቅ እንደሚገባ አንስተዋል።

በተለይም የውጭ ሃገራት ባለሃብቶች በሃገሪቱ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ሲሰማሩ በርካታ ዕድሎች ይዘው እንደሚመጡ የተናገሩት ኮሚሽነሩ፥ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የስራ ዕድል ፈጠራ እና ሀገሪቱን ከአፍሪካ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ ይገኝበታል ብለዋል።

ለዚህም መንግስት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የጀመራቸው ሂደት ከግብ እንዲደርስ ህዝቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲውጣም ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy