የዓይናችን ብሌን
ይሁን ታፈረ
የሰላምን ፋይዳ ከቤተሰብ፣ ከአካባቢ፣ ከአገር አኳያ ብንመለከተው ለምን የዓይናችን ብሌን እንደምናደርገው እንገነዘባለን። ሰላም ከሌለ ቤተሰብ መስራት አይችልም፣ ልጁን ማስተማር አይችልም፣ ወደ ትምህርት ቤትም ይሁን ወደ ስራ የሄደው የቤተሰብ አባል ተመልሶ ወደ ቤቱ እንደሚመጣ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
አካባቢውም የደፈረሰ ሰላም ስለሚኖረው ምንም ዓይነት ግብይትም ይሁን የልማት ስራ አይኖርም። በድምሩም አገር እንደ አገር ማሳካት የምትፈልገውን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ አትችልም። በመሆኑም ዜጎች ለዚህ ሁሉ ችግር ሊያጋልጣቸውን የሚችለውን ሰላም እንደ ዓይናቸው ብሌን መጠበቅና መንከባከብ ይኖርባቸዋል። ለዚህም የፀረ ሰላም ሃይሎችን አጀንዳ መከላከልና መመከት ያስፈልጋል።
ፀረ ሰላም ሃይሎች በሚያስገርም ሁኔታ “ጀግናው የእገሌ ከተማ ህዝብ ሱቁን ዘግቶ ዋለ” ከሚል ዲስኩር እስከ “ሱቃችሁን አትክፈቱ” የሚል የሁከት ናፋቂነት መርዛቸውን ሲረጩ እንደነበር እናስታውሳለን። በተለይም በኤርትራ መንግሰት ዳራጎት የተቋቋሙት እንደ “ኢሳት” ያሉ መርዘኛ ሚዲያዎችና የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆች እንዲሁም በአንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ሀገራት እገዛ የሚዘወሩ ባንዳዎች በዚህ ረገድ አመፅን የማቀጣጠል ሚናቸውን ሲወጡ ነበር።
ወጣቱ የእነዚህን ፀረ-ሰላም ሃይሎች ዓላማና ግብ በሚገባ መረዳት ይኖርበታል። ፀረ-ሰላም ኃይሎቹ የትኛውንም የሀገራችንን ህዝብ የሚወክሉ አይደሉም። ሊወክሉም አይችሉም። ምክንያቱም ዓላማቸውና ግባቸው ከበስተኋላቸው የሚደጉማቸውን ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይል ፍላጎት ማስፈፀም ብቻ ስለሆነ ነው።
ሆኖም ይህ ፍላጎታቸው በኢፌዴሪ መንግስት በሳል አመራር እንዲሁም በህዝቡና በፀጥታ ኃይሎች ርብርብ ሊከሽፍ ችሏል። በተለይ ሀዝቡ ሰላሙን ለመጠበቅ ባደረገው ርብርብ የእነዚህን ሃይሎች ፍላጎት አክስሞታል። በመሆኑም ጊዜያዊ ችግር ከመፍጠር በስተቀር ፀረ ሰላም ሃይሎቹና አሸባሪዎቹ የፈለጉትን የሀገር ብተና ውጤት ሊያመጡ አልቻሉም። አይችሉምም።
በተለይ ሻዕቢያ ሚዲያዎችንና የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆችን እየከፈለ ጭምር በማሰማራት ሀገራችን ውስጥ አመፅ እንዲቀጣጠል ለማድረግ ይጥራል። በተለይ ‘ኢሳት’ ከኤርትራ መንግስት ገንዘብ እየተቀበለ የውሸት ወሬዎችን ያናፍሳል።
ዓላማውም የአስመራው መንግስት ሀገራችን ውስጥ ሁከት እንዲፈጠር ለማድረግ የሚያደርገውን የሴራ ሙከራ ማገዝ በመሆኑ የፈጠራ ወሬውን ሲያሰራጭ ሌሎች እንደ ፌስ ቡክ ዓይነት ማህበራዊ ድረ ገፆችም እየተቀባበሉ ያራግቡታል። ለሀገራችን በጎ የማይመኙ ኃይሎችም በፌስ ቡክ ላይ ብቅ እያሉ ጉዳዩን ያስተጋቡታል።
በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዳይኖርና ኢኮኖሚያችን እንዳያንሰራራ የሚፈልጉ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች መኖራቸው ይታወቃል። እነዚህ ሃይሎች ካደግን እንደምንለወጥና የተፈጥሮ ሃብታችንንም በዚያው ልክ እንደምንጠቀም ስለሚያውቁ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ተግተው የሚሰሩ ናቸው። እንደ ፌስ ቡክ ዓይነት ማህበራዊ ድረ ገፆችን በመጠቀምና እንደ ጃዋር መሃመድ ዓይነት ግለሰቦችን በመቅጠር ወጣቱን በተሳሳተ መንገድ ሊመሩት ይሞክራሉ።
ታዲያ ወጣቱ በእነ ‘ኢሳት’ና በእነ ጃዋር ውሸት አቀናባሪነት ሳቢያ እየተፈፀመ ያለውን ይህን የአመፃ አቀጣጣይነት ሚናን በሚገባ መረዳት አለበት። እውነታውን ከራሱ እማኝነት በመነሳት መገምገምም አለበት። አንድ ጉዳይ በፌስ ቡክ ዓይነት ማሀበራዊ ድረ ገፅ ብቻ ስለተነገረ እውነት ነው ብሎ መደምደም አይቻልም።
ሆን ተብሎ የአገራችንን ሰላም ለማወክ በፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች እንደሚቀነባበር መረዳት ይገባል። እናም ፀረ-ሰላም ኃይሎቹ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ስላለው ህገ መንግስታዊ ልዩ ተጠቃሚነትም ይሁን በየትኛውም ሀገር መንግስት ስራውን ለማከናወን የሚሰበስበውን ግብር አስመልክተው የሚያራግቡት አሉባልታ ቅስቀሳ መነሻውም ይሁን መድረሻው ይኸው ኢትዮጵያን የማተራመስ ተልዕኮ መሆኑን ወጣቱ ማወቅ ይኖርበታል። ማወቅ ብቻም ሳይሆን፤ የእነርሱን ማንነት በመገንዘብ ሊታገላቸውና ቅስቀሳቸውን ሊያከሽፍ ይገባል።
የሀገራችን ወጣት ባለ ራዕይና ተስፋ ያለው ነው። የዛሬው ትውልድ ወጣት እንደ ትናንቱ ወጣቶች እየታፈነ ለጦርነት አይወሰድም። ይህ ወጣት ዛሬ “ሰርተህ ተለወጥ፤ እኔ የምትሰራበትን ምህዳር አመቻችልሃለው” የሚል መንግስት ባለቤት ነው። ችግሩን በህዝባዊ መንፈስ የሚጋራው መንግስት አለው። መፍትሔም በአፋጣኝ የሚሰጥ መንግስት አለው። በየዕቅዶቹ ሁሉ ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ትልሞችን የሚይዝ መንግስት ባለቤትም ነው።
ይሁን እንጂ የሰላምን ፋይዳ ከሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በላይ የሚያውቀው የለም። ሰላም ባልነበርንባቸው ከዛሬ 27 ዓመት በፊት ምን ዓይነት ችግርና ስቃይ ውስጥ እንደነበርን ይታወቃል። ዛሬ ተመልሰን ወደዚያ ሁኔታ ውስጥ መግባት የለብንም። በተለይ በእርስ በርስ ጦርነት ሲማስን ለነበረውና የያኔው ወጣት፤ በዚያ ዕድሜ ክልል ውስጥ መገኘት ፍዳውን ያውቀዋል። የዚያ ትውልድ ወጣት ለዛሬው ወጣት ማስተማር አለበት። የሰላምን ዋጋ ልኬታ መንገር አለበት።
እርግጥ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰላም ከሌለ፣ ምንም ነገር እንደሌለ ለማወቅ አስረጅ አያሻውም። እናም በሰላሙ ላይ ለሚመጣበት ማንኛውም ፀረ-ሰላም ቦታ ሊሰጥ አይገባም። የፀረ ሰላም ሃይሎችን ፍላጎት እያመከነ ወደ ጀመረው የልማት መንገድ በቁርጠኝነት መግባት ይኖርበታል።
እዚህ ላይ አንድ መጠቀስ የሚገባው እውነታ አለ። እርሱም በየትኛውም ሀገር ውስጥ ችግሮች መኖራቸው ነው። እንኳንስ ለልማቱም ይሁን ለዴሞክራሲው ጀማሪ የሆነችው ሀገራችን ቀርቶ ባደጉት ሀገሮችም ውስጥ ቢሆን ችግር መኖሩ አይቀርም። የአልጋ በአልጋ መንገድ በየትኛውም ሀገር ውስጥ የለም። በመንግስት የስራ አስፈፃሚዎች ውስጥ ችግር ሊኖር ይችላል።
ዋናው ጉዳይ ችግሩን መፍታት የሚቻለው በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እንጂ የራሳቸው አጀንዳ ሳይኖራቸው የባዕዳን ተላላኪ በመሆን የፈጠራ ወሬን በሚረጩ ፀረ-ሰላም ሃይሎች አማካኝነት አይደለም። እነርሱ የዚህ የባዕዳን ጉዳይ ፈፃሚዎች እንጂ የዚህ ሀገር መፍትሔ ሰጪዎች አይደሉም።
ውክልናቸው ለባዕዳን እንጂ ለዚህ ሀገር አይደለም። እናም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ወጣቱ ማናቸውም መፍትሔ ያለው ለተጠቃሚነቱ እየሰራና ወደፊትም ከሚሰራው ህዝባዊ መንግስት እንጂ ከፀረ-ሰላም ኃይሎቹ አለመሆኑን በመረዳት፤ የውሸት ቅስቀሳቸውን በማክሸፍ ሰላሙን ማረጋገጥ አለበት። የተጠቃሚነቱ መሰረትና የዓይኑ ብሌን የሆነውን ሰላምን በመጠበቅ ተስፋውን ይበልጥ ማለምለም ይጠበቅበታል።