Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህዝባዊው ቁርጠኝነት

0 266

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህዝባዊው ቁርጠኝነት

                                                          ታዬ ከበደ

ዘንድሮም በአገራችን ያጋጠመን የድርቅ አደጋ መንግስት በዘረጋው የቅድመ ትንበያ አሰራር አስቀድሞ የሚታወቅ ነው። ይህም መንግሥት ለህዝብ ችግር ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ካለው ቁርጠኝነት የመነጨ ነው። ምንም እንኳን ያለንበት ጊዜ አስቸጋሪ ቢሆንም፤ መንግስት ድርቁን ለመቋቋም የሚያስችል ለአስቸኳይ የእህል ግዥ ከፍተኛ ገንዘብ መድቦ ግዥ በማካሄድ እህል እያቀረበ ነው።

በአሁኑ ወቅት የልማት አጋሮቻችን ዕርዳታና ድጋፍ እንዲያቀርቡ ጥሪ ቢቀርብም፤ በዋነኝነት ለህዝቡ እርዳታ እያቀረበ ያለው መንግስት ነው። ይህም መቼም ይሁን መቼ መንግሥት የህዝቡን ችግር በቁርጠኝነት ለመፍታት ያለውን ህዝባዊ ወገንተኝነት ያሳያል።

እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት ላለፉት 16 ተከታታይ ዓመታት በሀገር ውስጥ ባስመዘገበው ዕድገት ሳቢያ ሰው ሰራሽም ይሁን የተፈጥሮ አደጋን እየተቋቋመ ነው። ይህ አቅሙም በሀገራችን ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የድርቅ አደጋ ሲከሰቱ አደጋው ወደ ረሃብነት እንዳይቀየሩ ማድረግ የቻለ ነው።

በአሁኑ ወቅትም ለጋሽ ሀገራት ይህ ነው የማይባል ድጋፍ ሳያደርጉ መንግስትና ህዝቡ በአንድነት በመሆን እህል በመግዛት ለተረጂዎች እያከፋፈለ ነው። ይህም የህዝቡና የመንግስት አቅም እየጎለበተ መምጣቱን የሚያሳይ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስታችን የምትመራው አገራችን ላለፉት 16 ተከታታይ ዓመታት ባስመዘገበችው ዕድገት ችግሮችን እየተቋቋመች መጥታለች። ወደፊትም በቀየሰችው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አማካኝነት የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየፈታች ህዳሴዋን ማረጋገጧ አይቀሬ ነው።

ጥቂት ቀደምት ምሳሌዎችን ላንሳ። የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ዕመርታችን የሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዘገቡ አገራችን በኢኮኖሚ ዕድገት ጎዳና በአፍሪካ ከሚገኙ ሶስት አገራት ግንባር ቀደም በመሆን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ለማስመዝገብ በቅታለች፡፡ የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገትም ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥር በግማሽ ያህል እንዲቀንስና በየደረጃውም ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻለ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የድርቅ ችግር መንግሥት አቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍ እያደረገ ነው ሲባል ቀደም ሲል የተሰሩ ስራዎች የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ መገንዘብ ይገባል። በተለይም የኢፌዴሪ መንግስት በየጊዜው በወሰዳቸው ተከታታይ ድህነትን የመቀነስ ርምጃዎች ድምር ውጤት ለዛሬው ድርቅን ተቋቋሚነታችን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረጋቸው የሚካድ አይመስለኝም።

ከ1994 ዓ.ም በፊት የተከናወኑ የኢኮኖሚ መዋቅር ማስተካከያና ማሻሻያ ፕሮግራሞች የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴውን ከማነቃቃታቸው ባሻገር፤ የኋሊት ሲጓዝ የነበረውን የኢኮኖሚ ዕድገት ትክክለኛ አቅጣጫውን ይዞ እንዲጓዝ ያደረጉ መሆናቸውን እየተመዘገቡ ካሉት ዘርፈ ብዙ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገቶች መገንዘብ ይቻላል።

ለፈጣንና ቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገት የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ መኖር ወሳኝ መሆኑ ስለታመነበት፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የፊስካልና የሞኒተሪንግ ፖሊሲዎችን በማጣጣም እንዲሁም ዝቅተኛ የመንግስት በጀት ጉድለትንና የውጪ አሸፋፈን እንዲኖር በማድረግ ብሎም የገንዘብ እንቅስቃሴው ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ዋጋ ዓመታዊ ዕድገት ጋር የተዛመደ እንዲሆንና የውጭ ምንዛሬ ምጣኔዎችን ለማስተካከል ያለሰለሰ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህም ውጤት ተገኝቷል።

ባለፉት 16 ዓመታት ለሁለት ዓበይት የኢኮኖሚ ዘርፎች (ለግብርና እና ለኢንዱስትሪ) ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአርሶና የአርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ፣ የግሉ ዘርፍም በግብርና እና በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፎች እንዲሳተፍ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሀገራዊ ምርትን ለማሳደግ መቻሉን ነው።

በድህረ – ማሻሻያ ፕሮግራሙ ለመሰረተ ልማት ግንባታና ለስራው የሰው ሃይል ልማት በመንግስት የተሰጠው ትኩረት የላቀ በመሆኑ የተገኙ ውጤቶችም አበረታች ሆነዋል፡፡ እርግጥም በመንገድ ግንባታ፣ በኤሌትሪክ ሃይልና በቴሌኮሙኒኬሽን እንዲሁም በንጹህ ውኃ አቅርቦት ረገድ የተገኘው መሻሻል አገልግሎቶቹን ለማስፋፋት የጠየቁት ከፍተኛ የፋይናንስና የሙያ ክህሎቶች፤ የተፈራውን ያህል ስራዎቹን ሊያስተጓጉሏቸው አለመቻላቸውን የተገኙት ውጤቶችን አይቶ መመስከር የሚቻል ይመስለኛል።

ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የኢኮኖሚ ዕመርታችን የሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዘገቡ ሀገራችን በኢኮኖሚ ዕድገት ጎዳና በአፍሪካ ከሚገኙ ሶስት ሀገራት ግንባር ቀደም በመሆን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ለማስመዝገብ በቅታለች።

የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገትም ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥር እንዲቀንስና በየደረጃውም ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻለ ነው። እናም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በገበያ ተኮር ስርዓት እንዲራመድ በማድረግ፣ ዕድገቱ ቀጣይና ተከታታይ እንዲሆን ብሎም የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ችሏል።

በዚህም በመጀመሪያው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሸን ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን በአመርቂ ሁኔታ መፈፀም ተችሏል። በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሀገሪቱ እያስመዘገበችው ካለው ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ተጠቃሚ በመሆን የነብስ ወከፍ ገቢያቸው እንዲያሳድጉ አስችሏቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የሚሊዮነር ባለሃብቶች ቁጥር እያደገ መጥቷል። በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሶስት ዓመት አፈፃፀም ካጋጠን ያለመረጋጋት ጉዳይ በስተቀር አመርቂ ነው ማለት ይቻላል።

ታዲያ ግብርናው በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ኢትዮጵያችንን በኢንዱስትሪ የበለፀገች ለማድግና መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማቀላቀል፣ መንግስት በነደፈው በሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሰፊ ርብርብ እያደረገ ነው። ዕቅዱ በቀሩት ጊዜያት ውስጥም በአጥጋቢ ውጤት እንደሚሳካ ቀደምት ተግባራት ውጤታማነት በመነሳት ለመተንበይ የሚከብድ አይደለም።

ታዲያ እነዚህ ተግባራት ድርቁን ለመቋቋም የሚያስችሉን ቀደምት ስራዎች ናቸው። መንግስትም የተከሰተውን የድርቅ ችግር ብዙም የልማት አጋር ሃይሎች ድጋፍ ሳይኖረው በራስ አቅም ሊቋቋመው ችሏል።

ህዝቡም መንግስት በተከተለው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ ድርቁን በመቋቋም ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው። ወደፊትም ማንኛውንም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮችን መቋቋም የሚያስችል አቅም ተገንብቷል ማለት ይቻላል። ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን የድርቅ አደጋ ለመመከት መንግሥት በህዝባዊ ቁርጠኝነት ለተረጂዎች አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ነው። ሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ህዝብን መመገብ ቀላል ባይሆንም መንግሥት ግን ቅድሚያ ለህዝቡ የሚሰጥ የህዝብ አጋር በመሆኑ የአቅሙን እየተወጣ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy