Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

…መገለጫዎቹ እና ጠባቂዎቹ

0 268

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

…መገለጫዎቹ እና ጠባቂዎቹ

                                                               ሶሪ ገመዳ

የመከላከያና የደህንነት ተቋማት የፌዴራላዊ ስርዓቱ መገለጫና ጠባቂዎች ናቸው። ከሌሎቹ መንግስታዊ ተቋማት የሚለያቸው ምንም ነገር የለም። ልክ እንደ ሌሎቹ የመንግሥት ስራዎች አስፈፃሚ ተቋማት ሁሉ፣ እነዚህ ተቋማትም በህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ተለይቶ የመሰጣቸውን ስራዎች የሚያከናውኑ አካላት ናቸው።

ተቋማቱ ህግና ስርዓትን ተከትለው የሚሰሩ እንጂ ከየትኛውም ተቋም የበላይ ወይም የበታች አይደሉም። ፌዴራላዊ ስርዓቱ ያዋቀራቸው በህግና በስርዓት ላይ የተመሰረተ፣ የአገርን የህዝብን ጥቅሞች እንዲያረጋግጡ ለማድረግ ነው። ተግባራቸውን በተሰጣቸው የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ የሚያከናውኑ የስርዓቱ መገለጫዎችና ጠባቂዎች ናቸው። ይህ ማንነታቸውም አገራችን በጊዜያዊ ችግር ውስጥ ስትገባ በገሃድ የታየ ነው። አገራችንን ከፅንፈኞችና ከፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ሴራ የታደጓት ተቋማት ናቸው። ከዚህ አኳያ ህዝባዊውን መከላከያ ሰራዊታችንን በአብነት ማንሳት እንችላለን።

መከላከያ ሠራዊታችን በህገ -መንግሥታዊ እምነቱ፣ በዓላማ ጽናቱና በማይነጥፍ ጀግንነቱ በተደጋጋሚ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ የሀገሩን ዳር ድንበር በደምና አጥንቱ አስከብሯል፡፡ ፀረ – ሠላምና ፀረ -ልማት  ኃይሎችን በመደምሰስ ለልማቱ አስተማማኝ ሠላም አስፍኗል፡፡ በዓለም- አቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ በሁለት ተቃራኒ ኃይሎች ጭምር ያለ አንዳች ልዩነት በመመረጥ ብቸኛ የዘመናችን ሠራዊት ሆኗል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ተዘርዝረው የማያልቁ ስኬቶቹ ምስጢር ደግሞ ህዝባዊነቱ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም፡፡

የዚህ ሁሉ ስኬቶች ምክንያትም ፍርሃትን ሳይሆን አክብሮትን፣ በጥላቻ ፈንታ ጥልቅ ወገናዊ ፍቅርን ማትረፍ በመቻሉ ይመስለኛል፡፡ ሠራዊታችን በአንድ እጁ ጠብ-መንጃ፣ በሌላኛው አካፋና ዶማ ይዞ በልማቱም እየተሳተፈ ነው፡፡ ከአርሶ አደሩ ማሳም አይለይም። ያርሳል፣ ይዘራል፣ ያርማል፣ ያጭዳል፣ ይወቃል፡፡

ሰራዊቱ በየተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና ሁሉ የወገኖቹን ችግር በመረዳት የመፍትሄ አካል የመሆን ተግባራትን ተወጥቷል፤ እየተወጣም ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩት ሠራዊቶች ህዝቡ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ባስታጠቃቸው ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ተጠቅመው ወገናቸውን እንዳልጨፈጨፉ፣ የአዛውንቶች፣ ሴቶችና ህጻናትን ህይወት እንዳላጠፉ፣ ጨቅላ ህፃን የሙት እናቷን ጡት ስትጠባ የሚያሳይ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሰቃቂ ትዕይንት እንዳላሳዩን፤ ዛሬ ታሪክ ተቀይሮ ሌላ ዓይነት ሀገራዊ ሠራዊት ተፈጥሮ ህዝባችን ከአብራኩ በወጡት ልጆቹ እየኮራ ነው፡፡

ሠራዊቱ ከሰው ሰራሽና ከተፈጥሮ አደጋ ጋር ተጋፍጦ፣ ለአንዴ ብቻ የሚኖራትን ህይወቱን ለዕልፎች የመኖር ተስፋ አለምልሟል፡፡ ምን ይህ ብቻ! ይህ ለህገ-መንግስቱና ለህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ዘብ የቆመስው ሰራዊት፤ ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያንና አረጋዊያት የሚጦር፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጅ-አልባ የሆኑ ህፃናትን የሚያሳድግና የሚያስተምር፣ ከራሱ በላይ ለህዝቡና ለሀገሩ ጥቅም ሲታትር ውሎ የሚያድር ነው፡፡

የዚህን ህዝባዊ ሰራዊት የሰላምና የልማት ተሳትፎ በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ አንደኛው ሀገራችን አድጋ የረሃብ፣ ድህነትና መሃይምነት ተምሳሌነቷ ተፍቆ ማየት የማይፈልጉ፣ መበታተንና ተስፋ – አልባነታችንን የሚናፍቁ የውጭና የውስጥ ፀረ-ሠላም ኃይሎች ካሉ ይህን እኩይ ሴራቸውን ማክሸፍ ነው፡፡ ይህንን ከኤርትራ ወረራ እስከ አል-ሸባብ የግብረ-ሽበራ ተግባርን በመመከት እንዲሁም ከሰሜን እስከ ደቡብ ባሉ የሀገራችን አካባቢዎች ሻዕቢያ እያስታጠቀ በሚልካቸውን አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ሃይሎችን ላይ ህዝባዊ ክንዱን በማሳረፍ እውን አድርጓል፤ ነገም ይህን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ እናም ይህ ሠራዊት ኢትዮጵያ ጠላቶቿ እንዳለሙት የብጥብጥና የትርምስ ሀገር ሳትሆን የአህጉሪቱ መዲና፣ የድሃ ህዝቦች መብትና ጥቅም ተሟጋች እንድትሆን ያስቻላት ነው ብል ከእውነታው መራቅ አይሆንብኝም፡፡

ሁለተኛው የልማት ገጽታው ዕውቀቱን፣ ጉልበቱንና ካለው አነስተኛ ገቢ በፍጹም ህዝባዊና ሀገራዊ ፍቅር የሚገልጽ ቀጥተኛ የልማት ተሳትፎ ማድረግ ነው፡፡ ሰራዊቱ በዚህ በኩል የነበረውን ድርሻ በቀላሉ መግለጽ ይከብዳል፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ የትልቋ ኢትዮጵያ እውነተኛ ተምሳሌት ብቻ አይደለም— መሃንዲስ፣ መምህር፣ አርሶና አርብቶ አደርም ጭምር ነው፡፡ መንገድ ገንብቶ ህዝቦችን አገናኝቷል፡፡

ግድብ ሰርቶ አርብቶ አደሩ ወደ አርሶና ከፊል አርብቶ አደርነት እንዲቀየር አስችሏል፡፡ ትምህርት ቤት ሰርቶም የመማር ዕድሉ ያልነበራቸውን ከዕውቀት ጋር አገናኝቷል፡፡ የጤና ተቋማት ላይ ዕውቀቱን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን አፍስሶ ለዕልፎች የመኖር ዋስትና ሰጥቷል፡፡ የእናቶችንና ህፃናትን ሞትን በመቀነስ ረገድም በተግባር ተሳትፏል፡፡ በምህንድስናና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ብቃት ያላቸው ሙያተኞቹን በማሳተፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር አብዮት ለኩሷል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እንደ አንድ ሀገር ሰራዊት በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት የሚያከናውናቸው ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው፤ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰላምና ለልማት መሆኑ ግንዘቤ ሊያዝ ይገባል። ምክንያቱም ሰራዊቱ የተደራጀው ሀገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ በመሆኑ ነው።

የየትኛውም ሀገር መከላከያ ሰራዊት የተደራጀበት ሥርዓት ነፀብራቅ እንደመሆኑ መጠን፤ ሰራዊታችንም በሀገራችን የተመሰረተው ፌዴራላዊ ሥርዓት ፍላጎቶች ነፀብራቅ መሆኑ አያጠያይቅም። በዚህ መሰረትም በህዝቦች መፈቃቀድ እውን የሆነው ፌዴራላዊ ስርዓት ድህነትን በጠላትነት ፈርጆ በመንቀሳቀስ የፀረ-ድህነት ትግሉን እያጧጧፈ ነው። ሰራዊቱም በዚህ ጥረት ውስጥ ለአገርና ለከባቢው ሀገሮች የሰላምና የልማት ትሩፋቶች ዕውን መሆን እንዲተጋ ተደርጓል። በዚህም የስርዓቱ መገለጫና ጠባቂ መሆን ችሏል።

የዚህ ፅሁፍ አንባቢ መከላከያ ሰራዊታችን አንድ ጊዜያዊና ሊፈታ የሚችል ችግር በተፈጠረ ቁጥር ለምን የጦርነትና የግጭት አማራጭን እንደማይከተልም ማወቅ ያለበት ይመስለኛል።

ሰራዊቱ የስርዓቱ መገለጫ በመሆኑ ቅድሚያ ለሰላምና ለልማት የሚሰጥ ነው። እርግጥ ሰራዊቱ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ህልውናዋ ተጠብቆ፣ ዜጎቿም ሠላማቸውን አግኝተው መኖር እንዲችሉ ማድረግ ቀዳሚውና አብይ ተግባሩ ነው። ከዚህ በመለስ ያሉት ጉዳዩች ግን የሚታዩት ለሰላምና ለልማት ካላቸው ትርጉም አኳያ መሆኑ አያጠያይቅም።

እዚህ ላይ በከፋ ኋላ ቀርነትና በድህነት አረንቋ ውስጥ ጠልቃ ለኖረችው ኢትዮጵያ ሰላምና ልማት የህልውናዋ ጉዳይ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። በመሆኑም ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለን ሁለንተናዊ መስተጋብር ይህን ችግራችንን በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። እናም አካባቢያዊ ሠላም መስፈንና ልማት መኖር ሀገሪቱ ለተያያዘችው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ ብልፅግና መረጋገጥ ቀጣይነት የሚኖረው ድርሻ የላቀ ብቻ ሳይሆን፣ በቀጣናው የተረጋጋ ሠላምና ልማት መገኘት ለአገራዊ ልማታዊ ጉዞ ስኬትም ከፍ ያለ ሚና ይጫወታል።

መንግሥት ለሀገሪቱ ሠላም መስፈንና ልማት እውን መሆን ትኩረት እንደሚሰጥ ሁሉ፤ የጎረቤት ሀገሮች ሠላም መረጋገጥና ልማት መፋጠን ካለው ፅኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግን ቀዳሚው ምርጫ አድርጎ ይዟል። በውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ በግልፅ እንደተመለከተው፤ የሀገራችን ሠላምና ልማት ለአካባቢያዊ ብልፅግና ድርሻ የመኖሩን ያህል፣ አካባቢያዊ ሠላምና ልማትም ለኢትዮጵያ ዕድገት መፋጠን የሚኖረው አዎንታዊ ሚና ከፍተኛ ነው።

በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው የተፋጠነ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የተጀመረው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀ በመሆኑ በውጤቱም ለአገሪቱም ሆነ ለአካባቢያዊ ሠላም የራሱ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በዚህም ምክንያት ሰራዊቱ እንደ ስርዓቱ መገለጫና ጠባቂ መጠን ተግባሩን ከአገራዊ ተጠቃሚነት ጋር ይመለከተዋል። ከእነዚህ ተግባሮቹ ውጭ የሚያከናውነው አንዳች ነገር አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy