Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቅድሚያ ተጋላጭነትን ለመቀነስ…

0 629

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቅድሚያ ተጋላጭነትን ለመቀነስ…

                                                  ዘአማን በላይ

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወቅታዊ የኑሮ ሁኔታ ቀደም ሲል ከነበረው ‘ማንነታቸው’ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ተሻሽሏል፡፡ ትናንት አንገታቸውን ደፍተው፣ ተሸማቀውና የድህነት ተምሳሌት በመባል መጠቋቀሚያ በመሆን አሳዛኝ የሃፍረት ካባን ደርበው አጎንብሰው ይሄዱ ነበር። ዛሬ ግን ምስጋና ይህን  ስርዓት ለማምጣት ውድ ህይወታቸውን ቤዛ ላደረጉት የህዝብ ልጆች ይግባቸውና ከአንገታቸው ቀና ብለው መሄድ ጀምረዋል፡፡ በተለይ ባለፉት 16 ዓመታት ይህን የያኔውን ‘ማንነታቸውን’ ለመቀየር በመንግስት መሪነት ጠንክረው በመስራት አዳፋ ካባቸውን በየደረጃው አሽቀንጥረው ጥለዋል፤ እየጣሉም ይገኛሉ፡፡

ዛሬ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን በመዋጋት ህዝባቸውን ከችግር ማላቀቅ በሚገባቸው ወቅት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለት መንገዶችን የመጠቀም አስፈላጊነትን ተገንዝበዋል፡፡ እነርሱም ውስጣዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል በህዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ የልማት ትልምን መከተል እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ ተቋማትን የማስፋፋት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡

ታዲያ እነዚህ አቅጣጫዎች በዋነኛነት የፀረ ድህነት ትግሉን ከዳር የማድረስ ዓላማና ግብ ያላቸው ሲሆኑ፤ በአንድ በኩል በነፃነትና በሉዓላዊነት መርህ ላይ ተመስርተው ዕድገታቸውን የሚያፋጥኑበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተፈጥሯዊ ሃብታቸው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ተቀናጅተውና ተባብረው ለመስራት ምቹ ዕድል የሚፈጥሩላቸው ናቸው፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ዕውን ከሆነበት ከዛሬ 23 ዓመት በፊት የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የዜጎቹን እኩል ተጠቃሚነት በየደረጃው ለማረጋገጥ ዋነኛ ጠላት በሆነው ድህነትን የመቅረፍ ስራ ትኩረት ሰጥቶ ተግባሩን በሚገባ ተወጥቷል፡፡ በዚህም በአንድ በኩል፤ ውስጣዊ ችግሮች ላይ በማተኮርና አቅም በፈቀደ መጠን እልባት በመስጠት ተግባር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር በሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ተቋማት የማስፋፋት ስራን አከናውኗል፡፡ እያከናወነም ነው፡፡

የሀገራችን የፀረ ድህነት ትግል በህዝቦች ሰፊ ተሳትፎ ታጅቦ በመጓዙና ችግሮቹን በመፈተሽ እንደ ክብደታቸው በቅደም ተከተል ለመቅረፍ በተከናወነው ብልህነት የተሞላበት መንግስታዊ አካሄድ ሀገሪቱንና የህዝቦቿን ኑሮ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያስቻለ ነው፡፡ ይህም ሀገራችንን በዓለማችን ከፈጣን ዕድገት ባለቤቶች ጎራ እንድትመደብ ያደረጋት ነው፡፡ ትናንት የድህነት ተምሳሌት የነበረችው ሀገራችን፣ ዛሬ የዕድገት ምሳሌ መሆን ችላለች፡፡ ታዲያ ለዚህ ውጤት መመዝገብ ዓይነተኛው ምክንያት ገዥው ፓርተና መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን በመለየትና እልባት ለመስጠት ያከናወነኑት ጥረቶች መሆናቸውን ለመገንዘብ አዳጋች አይሆንም፡፡

ርግጥ ባለፉት 16 የዕድገት ዓመታት የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች በተለይም የዘመናት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ምላሽ መስጠቱ እንዲሁም የትምህርት፣ ጤና፣ የመንገድ፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች መሰረተ ልማት ተቋማት እንዲስፋፉ ማድረጉ፣ የመልካም አስተዳደርና ፍትህን የማግኘት ጉዳዮች አቅም በፈቀደ መጠን በየደረጃው እንዲከናወኑ ባደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ሀገራችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር ተችሏል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳዮቿ ላይ ዋነኛ ትኩረት ሰጥታ ስትሰራ የቆየችና የህዝቦቿን የልማት ተጠቃሚነት በየደረጃው ለማረጋገጥ መንቀሳቀሷን የሚያመላክት ሃቅ ይመስለኛል፡፡

ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን የውስጥ ተጋላጭነታችን በሚፈለገው መጠን ተቀርፏል ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ምንም እንኳን ሀገራችን ውስጥ እየተመዘገበ ያለው የልማት ዕድገት ከህዝቡ ቁጥር መጨመር ብሎም ከማስፈፀም አቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ በሚፈለገው መጠን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንዳይሆን ቢያደርግም፣ እዚህ ሀገር ውስጥ ዜጎች በየደረጃው ከተገኘው ዕድገት ተጠቃሚ መሆናቸው የሚካድ እውነታ አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታም የሀገራችንን ዕድገትና ብልፅግና የማይመኙ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ከፀረ-ሰላምና ከሽብር ኃይሎች ብሎም ከፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ጋር በመቀናጀት ወጣቶችን ባልተገባ መንገድ በማሰማራት በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጥሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ የውስጥ ተጋላጭነትን አቅም በፈቀደ መጠን በትክክለኛው አፈፃፀም መቅረፍ የሚገባ ይመስለኛል፡፡

ርግጥ የውስጥ ተጋላጭነታችንን መቅረፍ ባልቻልን ቁጥር፤ ለውስጥና ለውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች ይበልጡኑ የሚጋለጠው ከሀገራችን የህዝብ ብዛት ውሰጥ ግማሽ ቁጥር ያለው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ይህ ኃይል ትኩስና ያለበት የዕድሜ ደረጃ በበቂ ሁኔታ ለማመዛዘንና ለስሜታዊነት ቅርብ የሚያደርገው በመሆኑ በቀላሉ ለእነዚህ ሃይሎች የውሸት ስብከትና አሉባልታ የመጋለጥ ዕድሉ የሰፋ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ስለሆነም በማንኛውም ወቅት በሚነሱ ውዥንብሮች ውስጥ ባለማወቅ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኖ የችግር ሰለባ ሊሆን መቻሉ አይቀሬ ነው፡፡

ምንም እንኳን መንግስት በወጣቶች ፓኬጅ ላይ የተጠቀሰውን የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በማቋቋም ወደ ስራ እንዲገባ በቢለዩን የሚቆጠሩ ብሮችን ቢመድብም እንዲሁም ክልሎችም ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በጀት ቢይዙም አሰራሩ ወጥነት ያለው አይመስልም፡፡ ለወጣቶች ስራ ፈጠራ የተያዘው በጀት የተከፋፈለው ይህን ያህል አጥጋቢ አይደለም፡፡ የአፈፃፀም ችግር አለ፡፡  በየቦታው ቅሬታዎች ይደመጣሉ፡፡ ቅሬታዎች ተገቢ ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ለሚቀርቡት ቅሬታዎችና ጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ ከመስጠቱ ላይ ነው፡፡ አፈፃፀሙ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ የወጣቶችን ተጠቃሚነት አንድ ስንዝር እንኳን ለማስተጓጎል የሚችሉ የቢሮክራሲ ውጣ ውረዶች ወይም ህጎች ካሉ ሊፈተሹ ይገባል፡፡ ይህም የውስጥ ተጋላጭነትን የመድፈን አንዱ ተግባር ይሆናል።

ተደጋግሞ እንደሚገለፀው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ተግባሮች ጋር የተያያዙ በመሆናቸው በቂ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ፌዴራል መንግስትና ክልሎች ለወጣቶች በቂ በጀት መድበው ሳለ፤ በአፈፃፀም ጉዳይ ሳቢያ ይህ የተቀደሰ ተግባር ሊሰናከል አይገባም፡፡ በጀት ሰጪውም ይሁን በበጀቱ የሚጠቀመው አካል በተገቢው ሁኔታ መናበብ አለባቸው፡፡ ችግሮችን ፊት ለፊት በመነጋገርና በማሳመን  ወጣቶችን በሀገራችን እየተመዘገበው ካለው ዕድገት ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል፡፡ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ 25 ሺህ ከሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንደተናገሩት፤ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር የተቀዛቀዘውን የሀገራችንን ኢኮኖሚ ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ አንድ መንገድም ይሆናል፡፡

መንግስት በጋራ ሰርተን በጋራ እንደግ በሚል ልማታዊ እሳቤ ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በጀት መድቦ ሲያበቃ፤ አስፈፃሚው ክፍል ይህን ታላቅ ተግባር በአሰራር ግድፈቶች የሚሸረሽረው ከሆነ አፈፃፀሙ አሳሳቢ መሆኑ አይቀርም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተግባርም የውስጥ ተጋላጭነታችንን እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡ እናም ስለ ወጣቶች ሲታሰብ በቅድሚያ ችግሮች የሚቀረፉት የውስጥ ተጋላጭነት ከመቀነስና ከመቅረፍ እንዲሁም በጥቂቱም ቢሆን የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ከማድረግ አኳያ እየተመዘነ መሆን ይኖርበታል እላለሁ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy