Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቋሚው አቋም

0 229

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቋሚው አቋም

ገናናው በቀለ

ኢትዮጰያ ከተፋሰሱ አገራት ጋር ባላት ግንኙነት የምትከተለው አቅጣጫ ችግሮችን  በሰላማዊ ውይይትና በድርድር እንዲሁም በሰጥቶ መቀበል መርህ መፍታትን መሰረት ያደረገ ነው። ይህ የአገራችን አቅጣጫ ከተጨባጭ አቅም ላይ የተመሰረተና በዓለም አቀፍ ግንኙነትም ተቀባይነት ያለው ነው።

ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም ግብፅና ሱዳን አገራችን በዓባይ ወንዝ ተጠቃሚ እንዳትሆን አድርገዋት የቀዩ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ግን ትናንትም ዛሬም ይሁን ነገ ማንንም የመጉዳት ዓላማ ይዛ አታውቅም፤ አትይዝምም። የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማንኛውንም ህዝብ የመጉዳት ዓላማ የሌለው፣ እንዲያውም የተፋሰሱን አገራት በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ የሚያስተሳስር ነው። ይህም የአገራችንንና የህዝቧቿ ቋሚ አቋም መሆኑን የትኛውም ወገን መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል። እውነታው ይኸው ብቻ ነውና።

አገራችን በግድቡ ዙሪያ በፊትም ይሁን አሁን የያዘችው አቋም ፍትሐዊና ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ይህ የአገራችን ፍትሐዊ አስተሳሰብ አንዱን ለመጉዳትና ሌላውን ለመጥቀም ከማሰብ የመነጨ አይደለም። ይልቁንም ከዕድገታችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ባለፉት ዓመታት የሀገራችን የዕድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግርን የሚቀርፉ ጥቂት የማይባሉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን በተሳካ ሁኔታ መገንባት ተችሏል። ጥረቱን አጠናክሮ በመቀጠልም በአባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ነው። ሰባተኛ ዓመቱንም በቅርቡ አክብሯል።

የህዳሴውን ግድብ ችቦንና ዋንጫን እየተቀባበበሉ ዛሬ ለደረሰበት 65 በመቶ የግንባታ ደረጃ እንዲበቃ ያደረጉትና ለፍፃሜው እንደሚያበቁት እየገለፁት ያሉት የአገራችን ህዝቦች፤ ግድቡ አሁን ያለውን የአገራችንን የሃይል አቅርቦት ከሶስት እጥፍ በላይ ማሳደግ እንደሚችል ይገነዘባሉ። በቅርቡ የወጡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱትም፤ ግድቡ በሙሉ አቅሙ ስድስት ሺህ 450 ሜጋ ዋት ማመንጨት ሲጀምር ለበርካታ ዓመታት ያህል በቀን ሁለት ሚሊዮን ዮሮ ለአገራችን ያስገኛል። ይህም ህዝቡ በታሪካዊነቱ ያስቀመጠው ሁለንተናዊ አሻራ ተመልሶ የታሪካዊ ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችለው ነው።

ምንም እንኳን የተፈጥሮ ሐብትን በጋራና በፍትሐዊ ሁኔታ የመጠቀም መርህን ተከትላ የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ላይ የምትገኘው ሀገራችን፤ ዛሬም ከዚህ መርህዋ ዝንፍ የምትል አይሆንም። ግድቡም ወንድም የሆነውን የግብፅ ህዝብ እንደማይጎዳ፣ ይልቁንም ከግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚሆን በፅናት ታምናለች።

ይህ እምነቷ ከምንም ተነስቶ የሚባል አይደለም—መሬት ላይ ያለውን የግድቡን ግንባታ መሰረት ያደረገ እንጂ። ከዚህ በመነሳትም እምነቷንና የትኛውንም ወገን ያለ መጉዳት መርህዋን በተለያዩ ወቅቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች አስረድታለች።

ታዲያ ይህን የኢፌዴሪ መንግስት በጋራ የመልማት መርህን ቀደም ሲል ጎረቤት ሱዳን፣ አሁን ደግሞ ወንድሞቻችን ግብፆች እውነታውን እየተረዱ የመጡ ይመስላል—ብቅ ጥልም የሚለው አቋማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ። ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝቦች የትኛውንም አገር የመጉዳት ዓላማ የላቸውም።

የህዳሴው ግድብ ግንባታ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመርኩዞ ሁሉም ሀገራት እንዲጠቀሙ ከማለም የመነጨ ነው። ይህን የትኛውም አገር ሊገነዘበው ይገባል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም የአገራችን ህዝቦችም ይሁኑ መንግስት ለህዝብ የሚያስቡ እንጂ የሌሎች አገራትን ህዝቦች ተጠቃሚነትን የሚጋፉ አይደሉም።

የትኛውም የተፋሰሱ ሀገር ከዚህ ቀደም አድርጎት በማያውቀው መልኩ ህዳሴው ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ለማስጠናት በራቸውን ክፍት ያደረጉትም ለዚሁ ነው። ታዲያ ይህ የጋራ ተጠቃሚነት ቋሚ መርሆዋቸው መቼም ቢሆን የሚቀለበስ አይሆንም።   

ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝቦች ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት በተከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ ላለፉት 16 ተከታታይ ዓመታት ልማታቸውን ማሳደግ ችለዋል። በዚህም ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ነው። ይህ በአገር ውስጥ የተፈጠረው አቅምም ዜጎቿ የተፈጥሮ ሐብታቸውን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም የዚህ አቅም አንድ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል።

የሀገራችን ህዝቦች ምንም እንኳን ‘የጋራ ሃብታችንን በጋራ እንጠቀም’ የሚል ቀናዒ አስተሳሰብና አብሮ የማደግ ፅኑ አቋም ቢኖራቸውም፤ በሉዓላዊነታቸው ላይም ምንም ዓይነት ድርድር አያውቁም። ዓለም አቀፉ ህግም የውሃ ሀብታችሁን ለልማት አታውሉ ሊለን አይችልም፤ ያለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን የሰጥቶ መቀበልና የውይይት መርህን የሚከተል እንጂ አንዱ ለብቻው የተፈጥሮ ሃብትን አሟጦ የሚጠቀምበት አይደለም።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይነቱ የዜጎችንና የሀገራችንን ዕድገት በማፋጠን ብቻ የተወሰነ አይደለም። የተፋሰሱን አገራት ተጠቃሚነት በማሳደግ የሰላማችን ዋስትናም ጭምርም ነው።

እናም ግድቡ ከከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ለሚሰቃዩት እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ለመሳሰሉ ጎረቤቶቻችን ለችግራቸው ምላሽ የሚሰጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩተን የሚያሳድግ፣ ግንኙነታችንንም የማጠናከር ሚናው በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

በኢትዮጵያ ህዝቦች ሙሉ አቅም በመገንባት ላይ የሚገኘው የህዳሴው ግድብ የአገራችንን ተጠቃሚነት ብቻ ሳይሆን የተፋሰሱን አገራት ጥቅምንም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህ እውነታም ኢትዮጵያ የተፋሰሱን አገራት የመጥቀም እንጂ የመጉዳት አንዳችም ፍላጎት እንደሌላት ማረጋገጫ ነው።

ከላይ የጠቀስኩትን ግድቡ ለተፋሰሱ አገራት ያለውን ጠቀሜታ እንደ ሱዳን ያሉ የታችኛው የተፋሰሱ አገራት በሚገባ የተገነዘቡት ሲሆን፤ ግብፅ ውስጥ ግን ሁለት ዓይነት አስተሳሰቦች እየተራመዱ ነው። አንደኛው አስተሳሰብ (በመንግስት ደረጃ በኦፊሴላዊ የሚገለፀው) ሲሆን፤ የዓባይን ውሃ በፍትሃዊነት መጠቀም እንደሚገባ የሚነገር ነው። አልፎ…አልፎም ዓባይ የህልውና ጉዳይ መሆኑ ሲነገር ይደመጣል። ሁለተኛው አስተሳሰብ ደግሞ፤ በዚያች አገር ውስጥ በፅንፈኝነት የተሰለፉ ተቋማትና ሚዲያዎች የሚያራግቡት ጉዳይ ናቸው።

እነዚህ ተቋማትና ሚዲያዎች ባረጀው የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እየተመሩ “ታሪካዊው የውሃ መጠናችን ሊነካ አይገባም” ሲሉ ይደመጣል። ይህን እውን ለማድረግ ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎችን በማሰባሰብ የሀገራችንን ሰላማዊ ምህዳር ለመበጥበጥ የሚሹ፣ ከፍ ሲልም እነርሱ “ታሪካዊ የውሃ መጠናችን” የሚሉትን እ.ኤ.አ የ1929 እና የ1955 የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን ዛሬም በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እውን ለማድረግ በማሰብ በግድቡ ላይ ሳንካ ለመፍጠር እስከ ማሰብ የሚደርሱ ናቸው።

የግብፅ ፅንፈኛ አካላት በይፋ እንደ ጥንቱ “ዓባይ የብቻዬ ነው” የሚል አቋምን በመንግስት ደረጃ ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ ባያንፀባርቁም ቅሉ፣ ለዚህ ቡድን ታላላኪ ሆነው የሚሰሩ እንደ ግንቦት ሰባት፣ ጃዋር መሃመድና ኦነግ የመሳሰሉ ከሃዲዎች ቅዥት ግን ይፋዊ አገር ክህደት መሆኑ ሁሉንም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚያስማማ ዕውነታ ሆኖ አልፏል።

እርግጥ ‘ሀገሬን ክጄ ባንዳ በመሆን ልስራልህ’ የሚል ግለሰብና ቡድን፤ በባንዳነት የተሰለፈለትን አካል ያለመካዱ ርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። እናም በአሰሪውም ወገን ቢሆን ተዓማኒ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ሀገራቸውን የካዱት ተላላኪዎች አካሄድ ኢትዮጵያን በጥቁር ገበያ አውጥቶ ከመቸርቸር የማይተናነስ የጥፋቶች ሁሉ ጥፋት ነው ብሎ መደምደም የሚቻል ይመስለኛል። ባህላችንን፣ እሴቶቻችንን እንዲሁም የአበውንና የእመውን የአገር ፍቅር ታሪክን ብሎም ዛሬ ላይ በግድቡ ዙሪያ ያለውን አገራዊ መግባባት የሚያረክስ ድርጊት ነው።

ኢትዮጵያ የምትገነባው የህዳሴ ግድብ ከራሷ አልፎ የቀጣናውን አገራት የሚጠቅም መሆኑን እነዚህ የግብፅ ፅንፈኞች አካላት የተገነዘቡት አይመስልም። ቢገነዘቡትም እውነታውን ለመቀበል ፍላጎት ይኖራቸዋል ተብሎ አይታሰብም። ያም ሆኖ ግን የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝቡ በመገንባት ላይ የሚገኙት የህዳሴው ግድብ የትኛውንም ወገን የሚጎዳ አይደለም።

የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ እንጂ ሌሎች አገራትን የሚጎዳ ፕሮጀክት የመገንባት ፍላጎት የለውም። ሌሎችን የመጉዳት ታሪክም የለውም። የሚከተለው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲም ይህን እንዲያደርግ አይፈቅድለትም። በህዝባዊ ተጠቃሚነት የሚያምኑት የአገራችን ህዝቦችም ከዚህ የተለየ ፍላጎት የላቸውም። በመሆኑም የጋራ ተጠቃሚነትን ማጣጣም ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy