Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በዕርግጠኝነት አይደገምም!

0 269

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በዕርግጠኝነት አይደገምም!

አባ መላኩ

ሰሞኑን በጅግጅጋ አንድ ታላቅ ህዝባዊ  ኮንፍረንስ ተካሂዷል። “አይደገምም! መቼም የትም” የሚለውን የኮንፍረንሱን   ተካፋዮችን ቃል ስሰማ እውነትም ከልባቸው መሆኑን ለመረዳት አልከበደኝም። በዚህ ታላቅ ህዝባዊ  ኮንፍረንስ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብይ አህመድ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ እንዲሁም ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል። በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ  በርካታ ሰላማዊ ዜጎቻችን ሞተዋል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ተፈናቅለዋል፣ ቤት ንብረታቸው ወድሟል። ይህን ሰይጣናዊ ድርጊት ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል። በግጭት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ ሃይሎች ምን ያህል ጸረ ህዝብ መሆናቸውን ለመረዳት የሚከብድ አይደለም።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ይህን አንገታችንን ያስደፋ  ድርጊት ለመኮነን እንዲሁም ከህዝቡ ጋር በመወያየት መፍትሄ ማፈላለግን ከሁሉም ነገር በፊት  ቅድሚያ መስጠታቸው የሚያስመሰግናቸው ተግባር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጊቱን “ያልተገባ፣ ከኢትዮጵያዊነት ባህል ያፈነገጠና የሁላችንንም አንገት ያስደፋ የሽንፈት ታሪካችን   ሲሉ” ኮንነውታል። ይህ ድርጊት በኢትዮጵያችን መቼም ይትም መደገም የለበትም። ይህ ድርጊት እስካሁን በነበሩት አንባገነን ስርዓቶች እንኳን አልተስተዋለም። አበው ሲተርቱ ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም ይላሉ፤  ያለፈው አልፏል፤ ዳግም እንዲህ ያለ ቅጥ ያጣ አካሄድ እንዳይከሰት ሁሉም ባለድርሻ አካል ማለትም መንግስትም የመንግስትነትን እንዲሁም ህዝብም የህብረተሰብ ድርሻውን በአግባብ መወጣት ይኖርባቸዋል። የህግ የበላይነት መቼም የትም ለድርድር የሚቀርብ ነገር መሆን የለበትም።   

ዶክተር አብይ እንዳሉት  “በግጭቱ ሁለቱም ወገኖች ተሸናፊና ከሳሪ  እንጂ አሸናፊና አትራፊ አልሆኑም”። እውነት ነው በአንድ አገር ህዝቦች መካከል የሚፈጠር ግጭት ከሳሪ እንጂ አትራፊ  ወገን ሊኖር ከቶ አይቻላቸውም። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልም ሆነ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ ሞተም፣ ቆሰለም፣ ተፈናቀለም፣ ንብረቱ ተዘረፈም ጉዳቱ የሚተርፈው  ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው። ለዚህ ነው እንዲህ ያለ ድርጊት በቀጣይ እንዳይከሰት ሁላችንም በጋራ ልናወግዘው እና በጋራ ልንከላከለው የሚገባው ሲሉ የኮንፍረንሱ ተካፋዮች በአጽንዖት የተናገሩት።  

ሁለቱ ህዝቦች   የዳበረ የአብሮነት ባህል  ያላቸው በባህልና በሃይማኖት የተሳሰሩ ለዘመናት አብረው የኖሩ ህዝቦች ናቸው።  ሁለቱም ህዝቦች ችግሮች ሲከሰቱ እልባት የሚሰጡባቸው ጠንካራ ባህላዊና በሃይማኖታዊ ስርዓቶች ያላቸው ብሄሮች ናቸው።   የሶማሌ ኡጋዞችና የኦሮሞ በአባገዳዎች ማንኛውንም ችግሮቻቸውን በውይይት መፍታት የሚያስችል የዳበረ ልምድ ያላቸው ናቸው። አባ ገዳዎችና  ኡጋዞች በግጭት አፈታት ሂደት እንኳን ለአካባቢው ማህበረሰብ ይቅርና ለአገራችን ችግሮችም መፍትሄ መስጠት የሚችሉ ናቸው። በመሆኑም እነዚህ አካላት  ከመንግስት ጋር በቅርበት በመስራት የተጎዱትን አካላት በመካስ የህዝቦችን አብሮነት ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።

የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች መለየት በማይቻልበት ሁኔታ የተቀላቀሉ አንዱ ሌላውን መስሎ ሳይሆን  ሌላውን ሆኖ የሚኖሩ፤ የዘመናት የአብሮነት ታሪክን የሚጋሩ ህዝቦች ናቸው። የእነዚህ ህዝቦች አፈጣጠር በበርካታ ነገሮች እጅግ የጠበቀ አንድነት የሚንጸባረቅበት፣ ጠንካራ ትስስር የሚስተዋልበት ነው።  እነዚህ ህዝቦች ለዘመናት ክፉውንም ደጉንም አብረው አሳለፈው፤ ተፋቅረው ለዘመናት ኖረዋል፣ እየኖሩም ነው፤ ነገም ይህ አብሮነታቸው ይቀጥላል። ምክንያቱም አንዱ ካላንዱ ጎዶሎና ባዶ ነውና። የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች አንዱ ለሌላው ቆስሏል፣ ሞቷል፤ ተርቧል፣ ታርዟል፤ በመሆኑም በደምና አጥንት የተሳሰረው ግንኙነታቸው ጊዜ የሚፈታው፤  ዘመንም የሚሽረው አይደለም። እነዚህ ህዝቦች ችግሮቻቸውን በባህላቸውና በሃይማኖት መሪዎቻቸው አማካኘነት ቁጭ ብለው በመፍታት ጥቅመኞች ያስቀመጡላቸውን ቅርቅፍቶች አንድ በአንድ ማስወገድ ይኖርባቸዋል። አሁን ላይ የምናስተውላቸው መንገራገጮች ሁሉ ያልፉና የህዝቦች የቀድሞው አንድነትና መተሳሰብ ይቀጥላል። የትላንት የህዝቦች አብሮነትም  ህያው እንደሆነ ዘመናትን ይሻገራል።

አዎ እነዚህ  ህዝቦች በርካታ መልካምና መጥፎ ታሪክን ተጋርተዋል። ከላይ እንዳነሳሁት መለየት በማይቻልበት ሁኔታ አንዱ ሌላውን መስሎ ሳይሆን ሆኖ የሚኗኗሩ ህዝቦች ናቸው። ለሁለቱ ህዝቦች ግጭት  ዋንኛ አቀንቃኞች ጥቅማቸው በተለያየ መንገድ የተነካባቸው አካሎችና ነገሮችን በቅጡ ማገናዘብ ያልቻሉ ታዳጊ ወጣቶች ናቸው። እነዚህ ሃይሎች በቀላሉ ለሌሎች ሃይሎች ድብቅ የፖለቲካ   መጠቀሚያነት ውለዋል።

በግጭት ወቅት የነበረውን ሁኔታ መገንዘብ እንደተቻለው  በዕድሜ በሰል ያለው የህብረተሰብ ክፍላችን የጥፋት ሃይሎችን  ሲገስጽ፣ ሁከተኞችን ሲቆጣ፣ ነገሮችን ለማብረድ ሲኳትን፣ ጉረቤቶቻቸውን ከጥቃት ለመከላከል ሲሯሯጡ፣ ንብረታቸውንም  ከውድመት ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ፤ ከአቅም በላይ ሲሆኑባቸው ደግሞ አብረው ሲላቀሱ፣ ሲያዝኑና ሲያስተዛዝኑ ተመልክተናል።  ይህ ነው የኢትዮጵያዊያን ባህል፤ ይህ ነው አብሮነት መገለጫው። የብሄርን ካባ አጥልቆ ህዝቦችን በማጋጨት ጊዜያዊ ጥቅም መፈለግ፣  በበቀል ስሜት እየተነዱ ከእኔ አይደለም ተብሎ የታሰበውን ሁሉ በማፈናቀልና በመግደል ለችግሮች መፍትሄ ማግኘት አይቻልም። በዚህ ጎዳና  የተጓዙትን አገራትን መጨረሻ ምን እንደሆነ በደንብ ተመልክተናል።

የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች ድንበር ሳይለያቸው ቋንቋ ሳይገድባቸው  ተጋብተው ተዋልደው ያለውን ተሰጣጥተው፣ አንዱ ለሌላው ዋስ ጠበቃ ሆነው  የኖሩ ወደፊትም የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው፤ ተወደደም ተጠላም ይህን አብሮነታቸውን ሊነጣጥል ማንም  አይቻለውም። እባካችሁ ለማይረባ የፖለቲካ ትርፍ ብላችሁ በዚህ ቆሻሻ ተግባር ላይ የተሰማራችሁ አካላት እጃችሁን ሰብስቡ፤ የህዝቦችን  የአብሮነት እሴቶች በመሸርሸር የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ነገ እናንተንም ጠራርጎ እንደሚያጠፋችሁ ልትረዱ ይገባል። ጽንፈኛና መርዘኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች እባካችሁ  የዘረኝነት ፖለቲካ ለስልጣን እርካብነት አትጠቀሙበት። ህብረተሰቡም ወደ ስሜታዊነት ሊከቱን ከሚሯሯጡ የጥቅመኛ ፖለቲከኞች አካሄዶችን ልንነቃባቸው ይገባል።

በኦሮሞና ሶማሌ ህዝቦች መካከል አሜኬላ ለመዝራት  ሩጫ ቢደረግም እነዚህ ህዝቦች ትላንትን በፍቅር እንደኖሩ ሁሉ  በእርግጠኘነት ነገም ግንኙነታቸው ህያው ነው። ምክንያቱም አንዱ ካላንዱ ባዶና ጎዶሎ  ነውና። አንዱ ሌላውን ድጋፍ ካልሆነው ኑሮን ሊዘልቁት አይቻላቸውም። የዘመናት ታሪካቸውም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው።  

አገራችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ የቻለችው ህዝብና መንግስት በቅርበት መስራት በመቻላቸው ነው። ህዝብን በማሳተፍ ልማት መፋጠን እንደምንችል ባለፉት ዓመታት የነበሩ ተሞክሮዎች አመላክተውናል።  ድህነት የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ ነው። በመሆኑም ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ያሉንን ጥቂት የልማት ስራዎች አይናቸውን አጥፍተን፣ ሰላማችንን አደፍርሰን ዕድገትና መለወጥን ማሰብ  የዋህነት ነው።

በየትኛውም መስፈርት  በህዝቦች ግጭት ሳቢያ  ጊዜያዊ ጥቅም የሚያተርፉ  አካላት ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል፤ ነገር ግን ትርፉ  ዘላቂነት ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም ይህ ቆሻሻ ተግባር ውሎ አድሮ ወደዱም ጠሉም እነርሱንም ጠራርጎ  ያጠፋቸዋል። በህዝቦች ግጭት ሁሉም አካል ኪሳራ እንጂ ትርፍ ሊያገኝ አይቻለውም። በመሆኑም በዚህ ድርጊት ላይ የተጠመዱ  አካላትን በቃችሁ ልንላቸው ይገባል። መንግስትም የህግ የበላይነት ለድርድር ማቅረብ የለበትም። ጥቅመኛ ፖለቲከኞች ወጣቱን  በስሜት ጅረት ውስጥ እየከተታችሁ የህዝቦችን የአብሮነት እሴቶችን አሽቀንጥራችሁ አትጣሉብን።

እንዲህ ያሉ ቅጥ ያጡ አካሄዶች ዳግም እንዳይከሰቱ  ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። መንግስት ለቅሬታዎች በወቅቱ ምላሽ ይሰጥ።  ለሁሉም የህዝብ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ መስጠት አይቻልም። በወቅቱ የሚሰጥ “አይሆንም” ወይም  “አይቻልም” የሚል ምላሽ በራሱ መልስ ነው። እንዲሁም መንግስት የአገልግሎት አሰጣጡን ያቀላጥፍ፤ ሁሉም  እኩል የሚስተናገድበት ሁኔታን ያመቻች። ህብረተሰቡም ግጭቶች ሲፈጠሩ ቀድሞ የነበሩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶቹን አጠናክረው ይቀጥሉ። መንግስትም  ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት በመስራት የተጣለበትን የህግ የበላይነትን የማስከበር ሃላፊነት በአግባብ ይወጣ። ከዚህም ባሻገር ሁሉም አካላት የአካባቢያችንን የጂኦ  ፖለቲክስ ሁኔታ ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

 

የተፈጠረው ችግር ከዚህ በኋላ ውሎ ሳያድር በማያዳግም እርቀ ሠላም እንዲቋጭም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልል ሕዝቦች መካከል ያለው ወሰን አስተዳደራዊ መለያ ከመሆን ባለፈ የልዩነት መነሻና የግጭት ምክንያት ሊሆን እንደማይገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሁለቱ ህዝቦች ደስታንና መከራን ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበሉ ያሳለፉትን የረጅም ዘመናት አብሮነትም ሕዝባዊ ገጽታ እንደተላበሱ ወደፊት እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል።

መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን እንደሚፈታ በማረጋገጥ፥ ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በፍጥነት ወደ ነበሩበት መልሶ የማቋቋም ስራ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።

የሁለቱ ክልል ህዝቦች አብሮነትና ወንድማማችነትም ትናንት የነበረ፣ ወደፊትም የሚዘልቅና ይበልጥ የሚያብብ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በሁለቱ ክልሎች መካከል የነበረው የአንድነት መንፈስ ወደ ቀድሞው እንዲመለስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣና የመፍትሄው አካል እንዲሆንም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ዛሬ የምትራመድበት የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዞ መላው ኢትዮጵያውያን በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሠላምና በመረጋጋት ድባብ ውስጥ መተባበር ከተቻለም ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻልም አስገንዝበዋል ።

ባለፉት ዓመታት የሠላም፣ የዴሞክራሲና ልማት ስኬቶች መመዝገባቸውን ነው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡(ኤፍ ቢ ሲ)

 

የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው  መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች  የመንግስት ባለስልጣንም ይሁን ሌላው ዜጋ  ዜጎች በሙሉ በሕግ ፊት እኩል ሲሆኑ ነው፡፡ መንግሥት ህግ ሲያስከበር   የሚችለው መጀመሪያ ራሱ ለአገሪቱ ህጎች ተገዢ የመሆን ለሌላው አርዕያ ሆኖ መቅብ  የመንግስት ስልጣንም በሕግ ካልተገደቡና ተጠያቂነት የነገሰበት መሆን መቻል አለበት።  የሕግ የበላይነት ለሰላም መረጋገጥ የመጀመሪያው መስፈርት ነው። ሰላም ሰላም ተብሎ ስለተዘመረ ወይም ሰላምን ስለተመኘነው ሰላም አይገኝም።  

የህግ የበላይነት ካልተረጋገገጠ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይቅሩና  ሰብዓዊ መብቶች በጠራራ ጸሃይ ይጣሳሉ፡፡ ይህን በአገራችን በተግባር ተመልክተናል፤ ሰዎች በዘራቸው ብቻ በጠራራ ጸሃይ ተገድለዋል፣ ተደብድበዋል፣ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።  ኃይለኞች ደካሞችን እንደፈለጉ ሲያጠቁ ሲዘርፉና ሲያዘርፉ ተመልክተናል። የአገር አንድነትና ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ ተመልክተናል፡፡ በዜጎች መካከል እኩልነት ለማስፈን ነው፡፡ ዘለቄታዊነት ያለው ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ መጓዝ ግን አደጋ ነው፡፡የሕግ የበላይነት በሌለበት ግን ጥቂቶች ኃይለኛ፣ ብዙኃኑ ደግሞ የጥቂቶቹ ሰለባ ይሆኑና ሥርዓት አልበኝነት ይነግሣል፡የአገር ሀብት የጥቂቶች መፈንጫ ይሆናል፡፡

እንደሚታወቀው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 12 ላይ የመንግሥት አሠራር ተጠያቂነት እንዳለበት ደንግጓል፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት ይላል፡፡ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ማንሳት እንደሚቻልም ተደንግጓል፡፡ ስለሥልጣን አካላት አወቃቀር በአንቀጽ 50 ላይ የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች የሕግ አውጪነት፣ የሕግ አስፈጻሚነትና የዳኝነት ሥልጣን አላቸው ይላል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን፣ ተጠሪነቱም ለአገሪቱ ሕዝብ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ የክልሎችም እንደዚሁ፡፡ በአንቀጽ 54 ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመላው ሕዝብ ተወካይ መሆናቸውንና ተገዥነታቸውም ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝብና ለህሊናቸው ብቻ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት የመንግሥትን ሥልጣን የያዘው አስፈጻሚው አካል ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የአገሪቱን የዕለት ተዕለት ሥራዎች በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ያስፈጽማል፡፡ ይህ የሕጎች የበላይ በሆነው ሕገ መንግሥት የተሰጠው ኃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን በሕጉ መሠረት እየተሠራ ነው ወይ? በርካታ ችግሮች አሉ፡፡

በአገሪቱ ውሎና አዳር ውስጥ በግልጽ ከሚታዩትና ከዚያም ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተቀስቅሶ ከነበረው አውዳሚ ግጭት በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በተሠራ የቅርብ ጊዜ ጥናት መገንዘብ የሚቻለው የችግሮችን መጠነ ሰፊ መሆን ነው፡፡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ጥናቱን ባካሄደባቸው ክልሎችና ተቋማት በተገኙ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ ባካሄደው ትንተና መሠረት፣ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኘው አስፈጻሚ አካል ችግሮች እንዳሉበት ነው፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች የመንግሥት መዋቅሮችን የሚመሩ አስፈጻሚዎች የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤቶችን ተግባርና ኃላፊነትን አሳንሶ ማየት፣ ምክር ቤቶች አስፈጻሚውን የመቆጣጠር ሥልጣን እንዳላቸው አለመቀበል ወይም አለመገንዘብ፣ የምክር ቤቶችን ቁጥጥርና ጫና በመፍራት እንዳይጠናከሩ መፈለግ በዋናነት ተጠቃሽ የተባሉ ችግሮች ናቸው፡፡ በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልሎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች በአስፈጻሚው ጫና ሲደርስባቸው የሕግ የበላይነት አለ ይባላል ወይ? የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች (በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልሎች) በሕግ የተሰጣቸው ሥልጣን ሲጣስ ምን ይሠራሉ?  ሕግ አውጭው አካል በአስፈጻሚው ሲጠለፍ እንዴት አይባልም ወይ?

ሌላው የአመለካከት ችግር የሕዝብ ተሳትፎ በሚረጋገጥባቸው አካላት ላይ እንደሚታይ ነው፡፡ በዋናነት ግን ችግሩ የሚጎላው የምክር ቤት አባላት ለራሳቸውም ሆነ ለምክር ቤቱ የሚሰጡት ግምት አናሳ እንደሆነ፣ የምክር ቤት ሥራ የሕዝብ ሥራ ነው ብሎ አስቦ አለመምጣት፣ የሕዝብ ወኪል ነኝ ብሎ አለመሥራት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ምክር ቤት ላይ ጥቅም የለም ብሎ ማሰብና ጠቅላላው ነገር የሚንቀሳቀሰው በአስፈጻሚው እንጂ በምክር ቤቱ አይደለም የሚል አስተሳሰብ መኖር ከተጠቀሱት ዋና ዋና ችግሮች መካከል የሚደመሩ ናቸው፡፡ በፌዴራል ደረጃ መንግሥትን የሚመራው አስፈጻሚ አካልን የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪዎች ናቸው የሚለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 72 ነው፡፡ ይህ እየታወቀ ባለበት አገር ውስጥ አስፈጻሚው አካል ለምን የችግሮቹ ምሳሌ ይሆናል? አስፈጻሚው አካልም ሆነ ሕግ አውጭው በሕግ የተቀመጠላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ካልቻሉ የሕዝብ ዋስትና ምንድነው? ሌላው የሚያሳዝነው ተግባር በጥናቱ የተመለከተው ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ምክር ቤቶች ድረስ በአስፈጻሚው አካል ያላቸው ተቀባይነትና ተደማጭነት ዝቅተኛ መሆኑ ነው፡፡ በሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች፣ መሻሻል የሚገባቸው አሠራሮችና ሌሎች ጉዳዮች በአስፈጻሚው ችላ ከመባላቸው በተጨማሪ፣ ምክር ቤቶች በሕግ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት አስፈጻሚውን መምራት ሲገባቸው የመታዘዝ ችግሮች እንዳሉ ተመልክቷል፡፡ ጣልቃ ገብነቱም በሚገርም መንገድ ቀርቧል፡፡ ይህንን ምን ይሉታል?

የሕግ የበላይነት ሲባል እኮ ከሕግ በታች ሆኖ መሥራት እንጂ እንዳሻ ሕግን እየደፈጠጡ መቀጠል አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር ለራስ የሚመች ሕግ እያወጡ መግዛት አይደለም፡፡ ዋናውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጨምሮ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች በአስፈጻሚው ላይ ተፅዕኖ መፍጠር እንዳቃታቸው ነው ጥናቱ ያቀረበው፡፡ ሌላው ቀርቶ አስፈጻሚው አካል ላይ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የሚጠበቅባቸው ቋሚ ኮሚቴዎችን ማጉላላት፣ ለማስተናገድ ዝግጁ አለመሆን፣ በቀጠሮ አለመገኘት፣ ጠንከር ያለ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን ለቁጥጥርና ለክትትል የሚወጡ ቋሚ ኮሚቴዎችን የማሸማቀቅ ችግሮች ይታያሉ ተብሏል፡፡ ይህም ከአስፈጻሚው አካል የሚደርስ ተፅዕኖ መገለጫ መሆኑ ተወስቷል፡፡ የሥልጣን የመጨረሻ አካል ነው የሚባለውን ሕዝብ በመወከል በሕግ ሥልጣን የተሰጣቸው ምክር ቤቶች በአስፈጻሚው ተፅዕኖ ሥር ከወደቁ ሌላው ምን ሊሆን ነው? ይህ የአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ በሙያ ማኅበራት፣ በብዙኃን ማኅበራትና በሚዲያው ላይ ጭምር በስፋት እንደሚታይና እነዚህን አካላት እንደ አጋዥ ኃይል ያለማየት ችግር እንዳለ በስፋት ተተንትኗል፡፡ በአጠቃላይ አስፈጻሚው አካል ግልጽነት የጎደለውና ተጠያቂነት የሌበት አሠራር በማስፈን የችግሮች ዋና ባለቤት ሆኗል፡፡  የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከልም ይህንኑ ነው ያፀናው፡፡ የሚሞግቱ ሐሳቦችን የሚያቀርቡና ብልሹ አሠራሮችን የሚታገሉ ግለሰቦች ላይ አስፈጻሚው አካል የማስፈራራት፣ የማሸማቀቅ፣ የመፈረጅና የመሳሰሉት ኢዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች ይፈጸምባቸዋል ሲባል ያሳፍራል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ መንገዶች በዜጎች ላይ የደረሱ እንግልቶችና መከራዎች ብዙ የሚባልባቸው ናቸው፡፡

ይህን ዓይነቱን አስከፊና ብልሹ ድርጊት አስወግዶ ለሕዝብ ፈቃድ ተገዥ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ መመኘት ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ ትግልና ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ የሕግ የበላይነት መሠረቱ በሚገባ ካልተጠናከረና ሥልጣን የያዙ ወገኖች የሕግ ገደብ ካልተደረገባቸው፣ በቅርቡ በአገሪቱ የተወሰኑ ሥፍራዎች ያጋጠመው ሁከት መጠኑ ሰፍቶ ይቀጥላል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፍላጎት ከልብ የመነጨና መስዕዋትነት ጭምር የሚከፈልበት መሆን የሚችለው፣ በቅድሚያ ሕግ እንዲከበር አርዓያ በመሆን ነው፡፡ ሕዝብ በትክክል የሥልጣን ባለቤት ሆኖ በሕግ የበላይነት ሥር የሚተዳደርበት ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ያለው የአምባገነንነት መገለጫ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩት አሳሳቢ ችግሮች እንዲወገዱና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የመንግሥት ሥልጣን የሕዝብ ፈቃድ መፈጸሚያ መሆን አለበት፡፡ አሠራሩ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ዜጎች በምንም ሳይሆን በሕግ ብቻ ዋስትና ሊያገኙ የግድ ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ አሁን ያለው አካሄድ መሠረታዊ ለውጥ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ሥልጣን የሚያዘው በነፃና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ኢፍትሐዊ የሆኑ አሠራሮችና ድርጊቶች መቆም አለባቸው፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ መስፈን አለበት፡፡ ከምንም ነገር በላይ ሕዝብ መደመጥ አለበት፡፡ ሕገወጥነት መቼም ቢሆን ሊወገድ ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግልጽነትና ተጠያቂነት ይረጋገጥ፡፡ የሕዝብ ተሳትፎና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው ተጠያቂነት ሲኖር ብቻ ነው

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy