Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትውልዱ ያለ ቦታው…

0 222

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ትውልዱ ያለ ቦታው…

ገናናው በቀለ

ጠያቂ ትውልድ መብቱን አውቆ የሚጠይቅና ግዴታዎቹንም የሚወጣ ማለት ነው። ህይወት እና ንብረት በሚያወድም ተግባር ላይ የሚሳተፍ አይደለም። ጠያቂ ትውልድን በተንሸዋረረ አመለካከት በመተርጎምና አመለካከትን በማዛባት መጠቀሚያ ለማድረግ የሚሞክረው የቀለም አብዮተኞች ብቻ ናቸው።

የቀለም አብዮተኞች ሰዎችን በአካል ከመግደላቸው በፊት አስቀድመው አዕምሮአቸውን በመግደል ተስፋ እንዲቆርጡና እነርሱ ወደ ሚፈልጉት አገራዊ ውድመት እንዲያመሩ ያደርጋሉ። እናም በማስገንዘብ ጠያቂው ወጣቱ ትውልድ አጀንዳው ሌላ በመሆኑ ያለ ቦታው መዋል የለበትም።

እንደሚታወቀው ሁሉ ወጣቶች ባለፉት 16 የፈጣን ዕድገት ዓመታት ውስጥ የመንግስት ልማታዊ አቅጣጫን በሚገባ ተገንዝበዋል። ማንኛውንም ጊዜያዊ ችግር መንግስት እየፈታው ነው። በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ማልማት ካልቻሉ ባለሃብቶች ቦታ በመቀማት ጭምር ወጣቶችን ወደ ስራ የማስገባት ተግባር እያከናወነ ነው። ውጤትም እየተገኘበት ነው። ይህ ሁኔታም መንግስት ምን ያህል ለወጣቱ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ትኩረት የመስጠት ተግባሮች እውን እየሆኑ ነው።

እርግጥ አንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ድርጅት በባህሪው ህዝባዊ ከሆነ፤ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያማከሉ መሆናቸው አይቀርም። የኢትዮጵያ መንግሥትም በባህሪው ህዝባዊና ልማታዊ በመሆኑ፤ ከ26 ዓመታት በላይ በአብዛኛዎቹ መስኮች ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል።

ቀደም ባሉት ሥርዓቶች በማንነቱም ይሁን በኑሮው አንገቱን ደፍቶ ይሄድ የነበረው ወጣት፤ ዛሬ ቀና ብሎ በአገሪቱ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በኢኮኖሚው ላይ ባበረከተው አስተዋጽኦ መጠን በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገሰገሰ ነው። ይህም በፌዴራላዊ ሥርዓቱ የተገኘ ውጤት ነው።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለያዩ የአነስተኛና ጥቃቅን እንዲሁም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ውስጥ ተሳታፊ በመሆን ተጠቃሚ መሆናቸውን ማንሳት ይቻላል። ስለሆነም ወጣቶች በአሁኑ ወቅት የላቀ ተጠቃሚ ለመሆንም ቁርጠኛ አቋም ከመንግስት ጋር መስራት ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም ወጣቶች ከፌዴራል ሥርዓቱ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ የሥርዓቱ ባለቤቶች ጭምር ስለሆኑ ነው።

መንግስት ቀደም ባሉት ጊዜያት በአገሪቱ ውስጥ ድህነትን አቅም በፈቀደ መጠን በመቀነስ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እንደሚደርግ፤ ትምህርትን፣ ጤናን፣ የመሠረተ-ልማት አውታሮችን እንደሚያስፋፋ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ስር እንዲሰድ አደርጋለሁ በማለት የገባውን የተስፋ ቃል ተፈፃሚ አድርጓል። አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ረገድም የገባውን ቃል አላጠፈም። ነገም ይሁን ከነገ ወዲያ ይህን ህዝባዊ ተግባሩን ይፈፅማል።

ታዲያ ወጣቱ ሥርዓቱ የእርሱ እንደ መሆኑ መጠን ሊጠብቀው ይገባል። በተለያዩ ጊዜያት እያሰለሱ በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶች መነሻቸውና መድረሻቸው ሥርዓቱን በውል ካለመገንዘብ አሊያም ጥቅማቸውን ለማሳደድ የሚሹ ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች የሚነሱ መሆናቸው ግልፅ ነው። እነዚህን ሃይሎች አደብ ለማስገዛት መንግስት ማናቸውንም ተግባሮች እንደሚከውን ቃል ገብቷል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የማናቸውም ችግሮች መፍትሔ የሚመነጨው በአገሪቱ በህዝብ አመኔታ ከተመረጠው መንግስት እንጂ የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ ብሎም የሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪ በመሆን በህዝቦች ስቃይ ትርፍ ለማጋበስ በሚፈልጉ ሃይሎች አለመሆኑን ወጣቶች ያውቃሉ።

በመሆኑም መንግሥት የአዳዲስ ልማታዊ ሃሳቦችና አሰራሮች አመንጪ ብሎም ለወጣቶች ችግር የሚደርስ ህዝባዊ አካል መሆኑን በመገንዘብ ከእነዚህ ሃይሎች አሉባልታ በመራቅ የቀለም አብዩተኞች እኩይ ዓላማ መጠቀሚያ ላለመሆን መትጋት አለባቸው።

ምንም እንኳን ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ስልጣንን ለግል ጥቅማቸውና ለኑሮ ማደላደያነት ለማዋል በሚሹ የተለያዩ ሃይሎች አማካኝነት የተፈጠረ ጊዜያዊ ችግር ቢኖርበትም፤ ችግሩ በአገሪቱ በመመዝገብ ላይ የሚገኘው ልማታዊ ድል ጊዜያዊ እንቅፋት መሆኑን መረዳት ያለበት ይመስለኛል። ወጣቶች የመንግሥትን የለውጥ ሃይልነት ስለሚያውቁ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እንደማይወጣና እንደሚለወጥም ማመን የሚኖርባቸው ይመስለኛል።

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደሞከርኩት ወጣቶች በምንም ምክንያት የእኩይ ሴራ አራማጆች መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም። ይህን ሥርዓት ታግለውና መስዋዕት በመክፈል ጭምር ያመጡት የትናንትናዎቹ ወጣቶች ለዛሬው ወጣት አስረክበውታል። የዚህ ትውልድ ወጣት ደግሞ እነዚያ ውድ የህዝብ ልጆች በደማቸውና በአጥንታቸው የሰጡንን ሥርዓት የማስቀጠል ሃላፈነት የዚህ ትውልድ አደራ ነው።

ይህ ትውልድ ሃላፊነቱን በተገቢው መንገድ መወጣት ይኖርበታል—ድህነትን በመዋጋት። የትውልዱ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው። በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “የድህነትን ተራራ በዕውቀት ጥይት መናድ ይቻላል” እንዳሉት፤ ድህነትን ለመቅረፍ ዋነኛው መሳሪያ ትምህርት መሆኑን ወጣቶች መዘንጋት የለባቸውም።

በመሆኑም የዕውቀት መገብያቸው የሆነውን ትምህርት ቤቶችን ከማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከትና ሽኩቻ እንዲሁም ከዘረኝነት አስተሳሰብ እንዲፀዱ ማድረግ ይኖርበታል። ነተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከዘረኝነት አስተሳሰብ ርቀው የአንድ ሀገራዊ ዕድገት ማሳያ መሆን ይኖርባቸዋል።

በአሁኑ ሰዓት ሆን ተብሎ የአገራችንን ሰላም ለማወክ የቀለም አብዩተኞች እኩይ ሴራ እንደሚቀነባበር መረዳት ያስፈልጋል። ፀረ ሰላም ኃይሎቹ የራሳቸውን ውሸት እየጨመሩ ማናቸውንም አገራዊ ችግሮች ሊታከኩ ይፈልጋሉ። ወጣቶችን በማደናገር በጎዳና ላይ ነውጥ ግጭትን ሊያስነሱ ይሞክራሉ።

እርግጥ የአገራችንን ልማት በማደናቀፍ በጠያቂው ትውልድ ደም የራሳቸውን አሻንጉሊት መንግስት ለማቋቋም የቀለም አብዮት አራማጆቹ ነውጠኛ ጥረታቸውን ለማሳካት ወደ ኋላ ያሉበት አንድም ወቅት የለም። የወጣቱ አጀንዳ ግን ሌላ ነው። ስራ አግኝቶ ከድህነት አረንቋ መውጣት መሆኑ ግልፅ ነው።

እነዚህ ሃይሎች መቼም ቢሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት እንጂ ለወጣቱ ትውልድ አንድም ነገር የሚፈይዱት የለም። እናም ወጣቱ ጠያቂ ትውልድ አጀንዳው ሰላምና ተጠቃሚነት መሆኑን በመገንዘብ የእነዚህ ሃይሎች ጉዳይ አስፈፃሚ እንዳይሆን በእጅጉ መጠንቀቅ አለበት። ይሀ ትውልድ መፃዒ ህይወቱን ማለም ያለበት ከአገሪቱ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንጂ የራሳቸው አጀንዳ ካላቸው የቀለም አብዩተኞች መሆኑን ተገንዝቦ እዚህ አገር ውስጥ ለሚካሄድ ሁለንተናዊ የዕድገት እንቅስቃሴዎች የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy