Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ነች

0 1,030

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ነች

ኢብሳ ነመራ

ባለፉት ዓመስት ዓመታት ሃገሪቱን በጠቅላይ ሚንስትርነት የመሩት ሃይለማርያም ደሳለኝ በፍቃዳቸው የኢህአዴግ ሊቀመነበርነትና የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመነበርና የኢፌዴሪ ጠቃላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ዶ/ር አብይ በኢህአዴግ ምክር ቤት የግንባሩ ሊቀመንበር መሆናቸው ይፋ ተደርጎ በግንባሩ አሰራር መሰረት ለጠቅላይ ሚኒስትርነት መታጨታቸው እንደተገለጸ በርካታ ወገኖች ዶ/ር አብይና በቀጣይ እሳቸው ሚመሩት መንግስት መወሰድ የሚገባቸው እርምጃዎች ያሏቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በዶ/ር አብይና በሚመሩት መንግስት ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ መሃከል የሃገሪቱ ምሁራንና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠቃሾች ናቸው። የውጭ አካላትም አስተያየት ሰጥተዋል። ከእነዚህ መሃከል፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን የሚሉት ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ፍሪደም ሃውስ ይጠቀሳሉ።

የሃገሪቱ የመንግስት ስልጣን ምንጭና ብቸኛ ባለቤት የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ በአጠቃላይ ሁሉም ዜጋ፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችንና ኡጋዞችን የመሳሰሉ ባህላዊ መሪዎች፣ ምሁራን፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ በኢትዮጵያውያን የተደራጁ ሲቪክ ማህበራት ሌሎችም በሃገራቸው ጉዳይ ላይ የመሰላቸውን አስተያየት የመስጠት ሊገሰስ የማይችልና በህገመንግስት የተረጋገጠ፣ ከሞራል አኳያም ተቀባይነት ያለው መብት አላቸው። ኢትዮጵያውያን የሃገሪቱ ጉዳይ የራሳቸው ጉዳይ በመሆኑ፣ የራሳቸውን ጉዳይ በሚመቻቸው መንገድ የመቃኘት ባለመብቶች ናቸው። እናም በመንግስታቸው ላይ የሚሰጡት አስተያየት፣ የሚያቀርቡት ተቃውሞ ገንቢ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል።

የውጭ አካላት በመንግስት ላይ የሚሰጡት አስተያየት ግን ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት ዘላቂ ጥቅምና ፍላጎት ብቻ ግብ ያደረገ ሊሆን አይችልም። መንግስታት ከሌሎች ሃገራት ጋር በመጠቃቀም ላይ የተመሰረተ ግኑኝነት እንዲኖራቸው መፈለጋቸው እውነት ቢሆንም፣ አጋጣሚ በፈቀደላቸው ልክ ግንኙነት የመሰረቱበትን ሃገር አካሄድ በራሳቸው ፍላጎት መቃኘት ይፈልጋሉ። ዓለም አቀፍ የመብት ተማጓች ነን የሚሉ ድርጅቶችና ለተለያየ ዓላማ የተደራጁ ሲቪክ ማህበራትም እንደመልአክ ንጹህ አይደሉም። ያደራጃቸውንና በገንዘብ የሚደግፋቸውን መንግስት ሌላ አካል ጥቅም ማስጠበቅ ቀዳሚ ግባቸው ነው። እናም  የሌሎች ሃገራት መንግስስታት አካሄድ በቋቋማቸው መንግስትና አካል ፍላጎት እንዲቃኝ ጥረት ያደርጋሉ። ይህ ፍላጎታቸው ዒላማ ካደረጉት ሃገር ዜጎች ፍላጎት ጋር የሚጣጣምበት አጋጣሚ ሊኖር ቢችልም፣ ቅድሚያ ግባቸው ግን ይህ አይደለም። ይህ የራሳቸውን ጥቅም ሲያሳድዱ እንደአጋጣሚ ሊሆን የሚችል ነው።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የዶ/ር አብይ አህመድን የኢህአዴግ ሊቀመነበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መሾም አስመልክቶ ኢትዮጵያን የሰጡዋቸውን አስተያየቶች ምንም ይሁኑ ምን፣ ዓላማቸው የተሻለች ኢትዮጵያን ማየት በመሆኑ ይሄ፣ ያ ብዬ አስተያየት ልሰጥባቸው አልፈልግም። ይሁን እንጂ የውጭ አካላት የሰጡዋቸው አስተያየቶች መድረሻ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አይደሉም የሚል እምነት ስላለኝ፣ በተለይ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ፍሪደም ሃውስ የተሰኙት ተቋማት የሰጧቸውን አስተያቶች ከኢትዮጵያውያን መብትና ነጻነት፣ ጥቅምና ፍላጎት አኳያ ልመለከታቸው ወድጃለሁ። ሁለቱ ተቋማት የሰጡዋቸው አስተያየቶች በአብዛኛው ተመሳሳዮች ናቸው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ፍሪደም ሃውስ የተሰኙት ተቋማት የዶ/ር አብይን ወደመሪነት መምጣት መነሻ በማድረግ ከሰጧቸው አስተያየቶች መሃከል ‘የህሊና እስረኞች’  እንዲፈቱ፣ ከስምንት ዓመታት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቁትን የጸረሽብርተኝነትና የሲቪክ ማህበራት ምዝገባ አዋጆች እንዲሰረዙ ወይም እንዲሻሻሉ በሚል ያቀረቧቸውን እንመልከት።

እስረኞችን በተመለከተ መንግስት በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደቆየው በያዘው አመለካከት ወይም አመለካከቱን ህግን አክብሮ በሰላማዊ መንገድ በማራመዱ ብቻ በቁጥጥር ስር የዋለ፣ የተከሰሰና በጥፋተኝነት የተፈረደበት ሰው የለም። እርግጥ ፖለቲከኞችና የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት አራማጅ የሆኑ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፤ ተከሰዋል፤ በጥፋተኝነት ተፈትዶባቸዋል። የተከሰሱትና የተፈረደባቸው ግን ከፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው ጋር በተያያዘ በሃገሪቱ የወንጀል ህግ እንዲሁም ልዩ ባህሪ ያላቸውን ወንጀሎች ለመከላከል በተደነገገ ህግ ወይም በህገመንግስቱ መሰረት የታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ነው። ይህ ድርጊቱን ወንጀል ያደርገዋል። ሁሉም ዜጋ በህግ ፊት እኩል ነው የሚለው መርህ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ አመለካካት አራማጆችንም ስለሚመለከት፣ ፖለቲከኝነት በህግ ከመጠየቅ ሊያስጥላቸው አይችልም። የፖለቲካ እንቅስቃሴ በህግና በስርአት የሚመራ ነው። ስርአተ አልበኝነት አይደለም። እናም የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠሩና ጥፋተኝነታቸው ህግ በሚያዘው መሰረት በቀረቡ ማስረጃዎች ተረጋግጦ ቅጣት የተወሰነባቸውን ግለሰቦች የህሊና ወይም የፖለቲካ እስረኛ አድርጎ መወሰድ ተገቢ አይደለም።

ይሁን እንጂ፣ ፖለቲከኞች በጎም ይሁኑ ክፉ ተከታይ ወይም እንወክለዋለን የሚሉት የህብረተሰብ ክፍል ሰለሚኖር፣ በወንጀል ሲጠረጠሩ ወይም በጥፋተኝነት ሲፈረድባቸው ተቃውሞ መቀሰቀሱ የተለመደና የሚጠበቅ ነው። በተለይ የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል በሌላቸው ሃገራት ይህ ሁኔታ እጅግ የተለመደ ነው። የፖለቲከኞችን በወንጀል መጠርጠርና በጥፋተኝነት መቀጣት ከሌሎች የወንጀል ተጠርጣሪና ጥፋተኛ ዜጎች ልዩ የሚያደርገው ይህ ሁኔታ ብቻ ነው።

እንደ ሁኔታው በወንጀል የተጠረጠሩና የተፈረደባቸው ፖለቲከኞች ጉዳይ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሃከል፣ በፖለቲከኞቹ ተከታዮችና በመንግስት መሃከል ወዘተ የመረረ አለመግባባት ሊፈጥር ይችላል። ይህ እየተባባሰ ከሄደ የተለያየ አመለካከት በሚደግፉ የህብረተሰብ ክፍሎች መሃከል መተማመን እንዲጠፋ ሊያደርግ ይችላል። ሁኔታው ወደአውዳሚ ሁከት ሊያመራም ይችላል። ይህም በልዩነት ውስጥ ያለ ሃገራዊ መአንድነትን ያሳሳል። ለውጭ ጠላቶች መስረጊያ ቀዳዳም ሊከፍት ይችላል። እናም ሁኔታዎችን ተመልክቶ ህገወጥ ለሆነ ድርጊት የተሰለፉና ህገወጥ ድርጊት ፈጽመው በቁጥጥር ስር ለዋሉ ፖለቲከኞች ምህረትና ይቅርታ ሊያደርግ ይችላል። የኢፌዴሪ መንግስት የይቅርታና የምህረት ህግና ድንጋጌ የኖረው ለዚህ ነው። በኢትዮጵያ ምህረትና ይቅርታ ህገመንግስታዊ መሰረት አለው። በዚህ መሰረት ከአንድ ወር በፊት በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ለዋሉና በጥፋተኝነት ለተፈረደባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ አራማጆች  ይቅርታ ተደርጎላቸዋል። ከዚህ በፊትም ይቅርታ ሲያደርግ ቆይቷል። ለሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም እስከበጀ ደረስ ለወደፊትም ይቀጥላል።

አመነሰቲ ኢንተርናሽናልና ፍሪደም ሃውስ የተሰኙት ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ነን ባይ ድርጅቶች የኢፌዴሪን መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን አቋምና ከዚህ በፊት የወሰዳቸውን እርምጃዎች ያውቃሉ። ይህን ጥያቄ ሲያነሱም አዲስ አይደለም። አሁን ዶ/ር አብይ ወደአመራር ሲመጡ ጥያሬ ማንሳታቸውም ምንም አይገርምም። ይሁን እንጂ በወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱና ቅጣት የተወሰነባቸው ስራቸው ፖለቲከኛ የሆነ ግለሰቦች ካሉ እነዚህን በይቅርታ የመፍታት ጉዳይ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በውጭ አካላት ጥያቄ የሚወሰን ሳይሆን በኢትዮጵያ ህዝብና በወከለው መንግስት ብቻ የሚወሰን ነው። አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ፈሪደም ሃውስ በማንኛውም ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት የሚችሉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የተቋቋሙትም ዓላማቸውም የኢትዮጵየን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ማስጠበቅ ሳይሆን ያቋቋሟቸውንና በገንዘብ ድጋፍ የሚያስተዳደሯቸውን መንግስታትና ባለጸጎች ጥቅም ማስጠበቅ በመሆኑ ጆሮ ሊሰጣቸው አይገባም።

እነዚህ ተቋማት የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ ይሰረዝ ይህ ካልሆነ ይሻሻል ብለዋል። በመሰረቱ ሽብርተኝነት የኢትዮጵያ ብቻ ሰጋት አይደለም። ዓለም አቀፍ ስጋት ነው። በመሆኑም ሃገራት የጸረ ሽብርተኝነት ህግ እንዲያወጡ የተባበሩት መንግስታትም ሆነ የአፍሪካ ህብረት የጸረ ሽብርተኝነት ኮንቬንሽኖች ያዛሉ። ኢትዮጵያ እነዚህን ዓለም አቀፍ ከንቬንሽኖች የፈረመች ሃገር በመሆኗ የጸረሽብርተኝነት ህግ ማውጣት ይጠበቅባታል። በመሆኑም፣ ኢትዮጵያ የጸረሽብርተኝነት አዋጇን እንድትሰርዝ የቀረበው ጥያቄ ዓለም አቀፍ ስርአትን ያውቃሉ ተብለው ከሚጠበቁት አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ፈሪደም ሃውስ የማይጠበቅ ነው። የሚወክሉትን አካል ጥቅም በማስጠበቅ ፍላጎት ታውረው በዘፈቀደ የተናገሩት ተደርጎ ሊወሰድም ይችላል። እናም ኢትዮጵያ የጸረ ሽብርተኝነት ህጓን አትሰርዝም።  

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሽብርተኝነት መረብ ውስጥ ባሉ ቡድኖችና ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ያተኮሩ ቡድኖች የሽብር ዒላማ ነች። ከዚህ ቀደምም ተደገጋሚ የሽብር ጥቃት ተፈጽሞባት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰለማዊ ዘጎቿን ህይወት አጥታለች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች አካላቸው ጎድሏል። የዚህ አይነት የሽብርተኝነት ድርጊትን አስቀድሞ መከላከልና ከተፈጸመም በኋላ አሸባሪዎች የሚገባቸውን ቅጣት እንዲያገኙ ማደረግ የመንግስት ሃላፊነት ነው። የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁን የወጣው ይህን በህዝብ ላይ የተጋረጠ ተጨባጭ የሽብር ስጋት ለመከላከል ዓላማ ነው። የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ ከሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር የለም። አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ፈሪደም ሃውስ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተጋረጠውን ይህን የሽብር አደጋ ያውቁታል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ በህይወት የመኖር መብትና የመኖር ዋስትናው መረጋገጥ ጉዳያቸው ስላልሆነ የጸረ ሽብርተኝነት ህጉ እንዲሰረዝ እስከመጠየቅ የዘለቀ አቋም አንጸባርቀዋል።

የጸረሽብርተኝነት ህጉን ማስተካከል ካስፈለገም፣ ጉዳዩ የኢትዮጵየውያን ብቻ ነው። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ድርድር እየተደረገ ነው። በዚህ ድርድር የሃገሪቱን የሽብር ተጋላጭነት ስጋት ከግምት ያስገባ መሻሻል ሊደረግ ይችል ይሆናል። አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ፍሪደም ሃውስ በዚህ ጉዳይ ላይ አፋቸውን ቢዘጉ ለኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ነው።

ሁለቱ የመብት ተሟጋች ነን ባይ ድርጅቶች ሌላው ለአዲሱ መሪ ያቀረቡት ጥያቄ የሲቪክ ማህበራትንና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ምዝገባ አዋጅን መሰረዝ ወይም ማሻሻል የሚመለከት ጉዳይ  ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያወቀው ይህ አዋጅ የኢትዮጵየውያን ሲቪክ ማህበር ወይም በጎ አድራጎት ድርጅት የማደራጀት መብት ላይ አንዳችም ገደብ አይጥልም። ይህ ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያውያን የሚያቋቁሟቸው ሲቪክ ማህበራት በማንኛውም የሃገሪቱ ጉዳይ ውስጥ፤ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ . . . ያለምንም ገደብ መሳተፍ ይችላሉ።

የውጭ በጎ ሲቪክ ማህበራትን በተመለከተም አዋጁ ማህበራቱ በሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ጉዳዮች ውስጥ ያለምን ገደብ እንዲሳተፉ ይፈቅዳል። ይሁን እንጂ የውጭ ሲቪክ ማህበራት በሃገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ገብተው የማቡካት መብት አልተሰጣቸውም። ይህ የሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የኢትዮጵያውያን ብቻ ጉዳይ ስለሆነ ነው። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የውጭ ሲቪክ ማህበራት ቀዳሚ ዓላማ ያቋቋማቸውንና በገንዘብ የሚደገፋቸውን መንግስትና ሌሎች አካላት ጥቅም ማስጠበቅ ነው። ይህን ቀዳሚ ዓላማቸውን ለማሳካት የኢትዮጵያውያንን ጥቅምና ፍላጎት፣ መብትና ነጻነት የሚጻረር ድርጊት ከመፈጸም ወደኋላ እንደማይሉ ግልጽ ነው። ይህ በተለያዩ ሃገራት፣ በኢትዮጵያም በተወሰነ ደረጃ በተጨባጭ ታይቷል። እናም የኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበራት ምዝገባ አዋጅ፣ የውጭ ሲቪክ ማህበራት የሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገቡ የከለከለው የህዝቡን ጥቅምና ፍላጎት፣ መብትና ነጻነት ከውጭ ተጽእኖ ለመከላከል ነው፤ በቃ። ይህ ሉዓላዊነትን የማስከበር ጉዳይ መሆኑም መታወቅ አለበት።

ሌላው ከሲቪክ ማህበራት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጉዳይ በውጭ ሲቪክ ማህበርነት የሚመደቡትን ድርጅቶች የሚመለከት ነው። አዋጁ ከአጠቃላይ በጀታቸውን ከ15 በመቶ በላይ ከውጭ የሚያገኙ ሲቪክ ማህበራት እንደውጭ ሲቪክ ማህበር እንዲመዘገቡ ይደነግጋል። ይህ የሆነው ከውጭ የሚመጣው ገንዘብ ሌጣውን እንደማይመጣ ስለሚታወቅ ነው። የለጋሹን ፍላጎትና አጀንዳም ተሸክሞ ነው የሚመጣው። ይህ ፍላጎትና አጀንዳ ከአብላጫው የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ጋር ላይጣጣም ይችላል። እናም ድንጋጌው ከገንዘብ ጋር ለሚመጣ የውጭ ተጽእኖ ቀዳዳ ላለመክፈት የተቀመጠ ነው። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት እነዚህ ከ15 በመቶ በላይ ባጀታቸው ከውጭ የሚመጣ ማህበራት በኢኮኖሚያዊና መህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለምንም ገደብ መሳተፍ ይችላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በአሁኑ ወቅት የጸረሽብርተኝነትና የሲቪክ ማህበራት ምዝገባ አዋጅን የመሰረዝ ወይም የማሻሻል ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ አይደለም። ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ከተነሱ ተቃውሞዎች በአንዳቸውም የእነዚህ ሁለት አዋጆች መሰረዝ ወይም መሻሻል ጥያቄ አልቀረበም። ይህ አዋጆቹን የማሻሻልና የመቀየር ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ አለመሆኑን ያመለክታል። እናም የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ እስኪሆኑ ድረስ አዋጆቹ የጸኑ ይሆናሉ።

በአጠቃላይ፣ አምነስቲ ኢነተርናሽናልና ፍሪደም ሃውስና ሰሞኑን የመሪ ለውጥ መደረጉን ተከትለው ያቀረቧቸውም ይሁን ከዚህ በፊት ሲያቀርቧቸው የቆዩት አብዛኞቹ ጉዳዮች የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት፣ መብትና ነጻነት ብቸኛ ግብ ያደረጉ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ተቋማቱን የመሰረቱና የሚያስተዳድሩ አካላት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት አኳያ ለመቃኘት የሚያስችል ቀዳዳ እንዲያገኙ የቀረቡ ናቸው። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ብቻ ስለሆነች ተቆርቋሪ መስለው የሚቀርቡ የውጭ አካላት የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ቦታ ሊሰጣቸው አይገባም።  

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy