Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዛሬም ያልተሻገርነው ችግር…  

0 340

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዛሬም ያልተሻገርነው ችግር…  

ወንድይራድ ኃብተየስ

ሰውን የሚሸጡ፣ በሰው ደም ለመበልፀግ የሚፈልጉ ሕገ ወጥ ደላሎችን ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ  ለሕግ አሳልፎ መስጠት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነትና ግዴታ ነው። ሕገ ወጥ ስደት የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት ነው። የችግሩ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነውን የሕገ ወጥ ደላሎችን ምሽግ ለማፈራረስ መንግሥትና ሕዝብ በቅርበት መሥራት ቤተሰቦችም ልጆቻቸውን መምከርና ማስተማር አለባቸው። የኢፌዴሪ መንግሥት  ወጣቶች በየአካባቢያቸው የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ጥረቱን ማጠናከር ይኖርበታል። ሕገ ወጥ ደላሎችና ኢ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ ያላቸው አካላት ሊጋለጡና ለሕግ ሊቀርቡ ይገባል።

ስደት አዲስ ሂደት አይደለም። የሰው ልጆች ምድር ላይ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ   ስደት አብሯቸው የኖረ ክስተት ነው። ሰዎች በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ አስገዳጅ ምክንያቶች አሊያም በፍላጎት ከተወለዱበት ወይም ከሚኖሩበት አካባቢ ወይም አገር ለቀው ድንበር አቋርጠው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ወይም አገራት በመሄድ ለመኖር ሊሰደዱ ይችላሉ። ስደት በሁሉም የዓለማችን ክፍል የሚታይ ይሁን እንጂ በታዳጊ አገሮች በተለይ ደግሞ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ችግሩ ገዝፎ ይታያል።  

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ እያስተዋልን ያለነው የስደት ዓይነት ሕይወትን ሊያሳጣ አካልን ሊያጎድል የሚችል ድርጊት ነው። በየዓመቱ በአሥር ሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ሕገ ወጥ ስደት አንዱ ምክንያት ነው። መተኪያ በሌላት ሕይወት ላይ ቁማር መጫወት አይቻልም። ለዚህም በሰሜናዊቷ የአፍሪካ አገር ሊቢያ በአፍሪካ ስደተኞች ላይ የተከሰተው የባርነት ሽያጭ ማሣያ ይሆናል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚፈፀም ነው ብሎ ማሰብ እስከሚከብድ ድረስ በስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን  አስፈሪም ጭምር ነው።

ሰዎች በሕጋዊም ሆነ በሕገ ወጥ መንገድ አካባቢያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ከሚያደርጓቸው ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ጦርነት፣ ድህነት፣ ረሃብ፣ የሥራ ዕድል አለመኖር፣ የተሻለ ክፍያ ፍለጋ፣ የዴሞክራሲ እጦት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት ወይም የትራንስፖርትና የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ የሰዎች ፍላጎት ማደግ ተጠቃሾች እንደሆኑ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። የአብዛኛዎቹ ስደተኞች መዳረሻ አውሮፓና እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ይሁን እንጂ በርካታ አፍሪካዊያን ስደታቸውን የሚጀምሩት ወደ ጎረቤት አገራት በመሸሽ ወይም በመኮብለል ነው።  

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት እንደሚያመላክተው በመላው ዓለም ከ230 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ 59 በመቶ የሚሆኑት ስደተኞች ባደጉት አገሮች ይገኛሉ። በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ደግሞ ቀሪውን 41 በመቶ በማስተናገድ ላይ ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ የስደተኞች ቁጥር  እያሻቀበ መጥቷል። በዚህም ሣቢያ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም ስደተኞች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ለማቅረብ እየከበደው እንደሆነም አስታውቋል።

 

ትናንት በጦርነት፣ በድርቅና ረሃብ ትታወቅ የነበረች አገር – ኢትዮጵያ ዛሬ ከአካባቢው ለሚሰደዱ ዜጎች መጠለያ ሆናለች። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ከሰሃራ መለስ ካሉ አገራት ከፍተኛውን የስደተኛ ቁጥር የምታስተናግድ አገር ለመሆን በቅታለች። በቅርቡ በተደረገ ጥናት ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ እና ኤርትራ የመጡ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች።  ይህን ያህል ቁጥር ያለውን ስደተኛ ማስተናገድ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ውሱን ሃብት ያላቸው አገሮች ምጣኔ ሀብት ላይ የሚፈጥረው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አውሮፓዊያኖች ለስደተኞች በራቸውን ከርችመዋል። ኢትዮጵያ ደግሞ ያላትን ውሱን ሃብት ቀንሳ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኛን እየተቀበለች ታስተናግዳለች። ይህ ተግባር በዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን እያስመሰገነን ይገኛል።

 

የኢፌዴሪ መንግሥት በአገሪቱ የሚገኙ ስደተኞች ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩላቸው እያደረገ  ነው። ለአብነት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። በርካታ ስደተኛ ወጣቶችም በተሰጣቸው የትምህርት ዕድል እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ለመማር ችለዋል። ከዚህ ባሻገር በርካታ ስደተኞች በአገሪቱ ውስጥ በሥራ ላይ ተሰማርተው ኑሯቸውን በሠላም እየገፉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በዚህ የሚያኮራ ተግባሯ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ምስጋና ተችሯታል። በሌላ በኩል በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በልዩ ልዩ ምክንያት ወደተለያዩ አገራት በመሰደድ ላይ ይገኛሉ። የክፍያው ሁኔታ እንደመካከለኛው ምሥራቅ ወይም እንደ ምዕራባዊያኑ አይሁን እንጂ ሥራ ለማይንቅና  መሥራት ለሚፈልግ ዜጋ፣ ሰርቶ መብላት ለሚሻ ሁሉ ሠርቶ መለወጥ የሚቻልበት ሁኔታ ተመቻችቷል።

በአገሪቱ በርካቶች ከምንም ተነስተው ሰርተው መለወጥ እንደሚቻልም በተግባር አሳይተዋል። በማሳየትም ላይ ናቸው። በስደት ኑሮ ዕድለኛ ዜጎቻችን ገንዘብ ያገኙ ይሆናል።  ነገር ግን ስደት ዴሞክራሲያዊ መብትን ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ክብርን የሚገፍ ሁኔታ ነው። ስደት የአፍሪካዊያንን ሰብዓዊ ክብር ምን ያህል እንደገፈፈ አይተናል። በሥልጣን ሽኩቻና በረብሻ ውስጥ ያለችው አፍሪካዊቷ አገር ሊቢያ ረዳት ላጡ፣ በበረሃ ለተንገላቱ፣ ለራባቸውና ለጠማቸው ፍጡራን ላይ የፈፀመችው ተግባር ከሰብዓዊነት የራቀ  ነው። የሊቢያን ሁኔታ እንደአብነት አነሳነው እንጂ በርካታ አገሮች ለስደተኞች የሚሰጡት ክብርና ስደተኛን የሚይዙበት ሁኔታ አሳዛኝ ነው። በአገር ሰርቶ መኖር ከዚያም አልፎ መበልፀግ እየተቻለ ሕይወትን፣ አካልንና ስብዕናን በሚጎዳ መልኩ መሰደድ ተገቢ አይደለም።

ለሕገ ወጥ ደላሎች ገንዘብ እንጂ የደሃ ልጅ ህይወት ቁብ አይሰጣቸውም። በኢትዮጵያ  ሕገ መንግሥት ዜጎች ወደፈለጉት አገር ተንቀሳቅሰው መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደፈለጉት አገር መሄድና መሥራት እየቻሉ  ለሕገ ወጥ ደላሎች ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል ሕይወታቸውንና አካላቸውን ለአደጋ ማጋለጣቸው አግባብነት የጎደለው ነገሮችን በሰከነ መንፈስ ካለማሰብ የሚመጣ ችግር ነው።  ወጣቶች ሕገ ወጥ ደላሎች ስለስደት መልካምነት የሚነግሩንን የተረት ተረት ታሪክ ቆም ብለን ልንፈትሽ ይገባናል። አንዳንዶች ዛሬም ሕገ ወጥ ስደት በእህትና ወንድሞቻችን ላይ ያደረሰውን ዘግናኝ ሁኔታ በዐይናቸው እየተመለከቱ በሕገ ወጥ መንገድ በመሰደድ “ለመደለብ” ያልማሉ።

በሕገ ወጥ ደላሎች የፈጠራ ወሬ ተደናብረው ስደትን የተከተሉ በርካታ እህትና ወንድሞቻችን በየበረሃውና በየባሕሩ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው አልፏል። አካላቸው ጎድሏል። ሕገ ወጥ ስደት  በወገኖቻችን ላይ ካደረሰው አካላዊ እና የሥነ ልቦና ጉዳት ባሻገር የአገራችንንም ገፅታ እጅጉን ጎድቶታል። መሥራትና አገር መለወጥ የሚችለውን የሰው ኃይልን በማራቆትም በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ ጫና በመፍጠር ላይ ይገኛል።  በመሆኑም ወጣቶች ስደትን ሲሹ ውሣኔቸውን መልሰው መላልሰው ሊያስቡበት ይገባል።

ከፍተኛ ገንዘብ ለሕገ ወጥ ደላሎች በመክፈል ለአደጋ ከመጋለጥ ይልቅ ያንን ገንዘብ በአገር ውስጥ መነሻ በማድረግ መሥራትና መለወጥ ይቻላል። በአሁኑ ወቅት አገራችን ማንም በአነስተኛ ገንዘብ መነሻ መሥራት የሚችልበትን ሁኔታ አመቻችታለች። መንግሥትና ሕዝብም ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ በመሆናቸው ይህን ዕድል ወጣቱ ሊጠቀምበት ይገባል።   

ኢትዮጵያን ተባብረን ማሳደግ የሁላችንም ኃላፊነትና ግዴታ ነው። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ስደት፣ ወጣቱን፣ የተማረውንና መሥራት የሚችለውን ትኩስ ኃይል የሚያሳጣ በመሆኑ ለዕድገት ፀር ነው። ዛሬ ወጣቶቻችን የሚሰደዱባቸው አገሮች የተለወጡትና ያደጉት በወጣቶቻቸው ጥረት መሆኑን በመገንዘብ እኛም ተባብረን  በአገራችን በመሥራት መለወጥና መበልፀግ እንችላለን። አሁን ላይ በአገራችን በርካታ ነገሮች በመለወጥ ላይ በመሆናቸው ምጣኔ ሀብታችን በፍጥነት በማደግ ላይ ነው። ይህን ዕድገት ማስቀጠል ከቻልን “መጪው ዘመን የከፍታ ዘመን ነው” እንደተባለው በጥቂት ጊዜያት እኛም ወደከፍታው እንደምንወጣ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy