Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመግባባቱ ነፀብራቅ

0 380

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመግባባቱ ነፀብራቅ

                                                         ሶሪ ገመዳ

የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባውን አጠናቋል። አዲስ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትርም መርጧል። የድርጅቱ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ስለ መሪው ድርጅት ስብሰባ በሰጡት መግለጫ፤ በገባኤው ላይ የተካሄዱት ግምገማዎች በመግባባት መንፈስ ከመከናወናቸውም በላይ፤ ስብሰባውን ተከትሎ የተሰጡት ውሳኔዎችም የዚሁ የመግባባት መንፈስ ነፀብራቅ ናቸው። ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ አንድምታው እነደሚከተለው የሚገለፅ ነው።

በስብሰባው ላይ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባቀረባቸው ሁለት ሪፖርቶችና ከድርጅቱ ሊቀ መንበር የስራ መልቀቂያ ጋር በተያያዘ የመተካካት አጀንዳ ላይ ሰፊ ውይይት አካሂዶ ስብሰባውን በመግባባትና በአንድነት መንፈስ አጠናቋል። ምክር ቤቱ በቅድሚያ የመከረበት አጀንዳ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በታህሳስ ወር ያካሄደውን ግምገማ መነሻ በማድረግና በየብሄራዊ ድርጅቱ የተካሄደውን ራስን ፈትሾ የማስተካከል እንቅስቃሴ ባካተተው ሪፖርት ላይ ነው፡፡

በዚህ ሪፖርት አገራችን ባለፉት 27 አመታት በተጓዘችበት ሂደት የተመዘገቡ ለውጦች እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ያጋጠሙን ፈተናዎችና በእጃችን የገቡ መልካም እድሎች በዝርዝር ቀርበው በሰፊው ተመክሮባቸዋል። ኢህአዴግ በየምርጫው የህዝብ ድምፅ አግኝቶ አገር የመምራት ኃላፊነቱን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ በተካሄዱ ጥረቶች ግልፅ ነው። በዚህም በሁሉም የህይወት መስኮች አገራዊ ተስፋችንን ያለመለሙ ለውጦች ተመዝግበዋል። ይህ ለውጥ ከምንም ነገር በፊት የጀመረው አገራዊ የዴሞክራሲ ትንሳኤን ያበሰረ ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ባለቤቶች በመሆናችንና አቅም በፈቀደ መጠን ይህንኑ ተግባራዊ በማድረግ የዜጎችና የህዝቦች መብትና ተሳትፎ የተከበረበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል።

አገራችን የሁሉንም ህዝቦች ተሳትፎ ባረጋገጠ አኳኋን ባፀደቀችው ህገ መንግስት የዜጎችና የህዝብ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተሟላ እውቅና አግኝተዋል። በብዝሃነት በተዋቀረችው አገራችን ውስጥ የዘመናት የህዝቦች ጥያቄ ሆነው የቆዩት የእኩልነት መብቶች ህገ መንግስታዊ ዋስትና ተጎናፅፈዋል። የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም እንዲገነባ ተደርጓል።

በጥቅሉ ባለፉት 27 አመታት የአገራችን ጉዞ አገራዊ የዴሞክራሲ ትንሳኤ የተወለደበት ሆኗል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትንሳኤ የተረጋገጠውም በእነዚህ አመታት ነበር። ኢትዮጵያ መጀመሪያ የዕዝ ኢኮኖሚ በመናድ መንግስት ቁልፍ ሚና በሚጫወትበት የገበያ ኢኮኖሚ ለመተካት የቻለችው በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ነው። የአገራችን ምጣኔ ሃብት ለተከታታይ 16 አመታት ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ተጉዟል። የዕድገታችን መነሻ ገጠርና ግብርና ነው። ዕድገቱ ሁሉንም የአገራችን አካባቢዎች ደረጃ በደረጃ እያዳረሰ በመጓዝ ላይ ይገኛል። ይህም አብዛኛውን የገጠር ነዋሪ ተጠቃሚ አድርጓል። በከተሞችም ከአነስተኛና ጥቃቅን እስከ ቀላልና ከባድ ኢንዱስትሪ በልዩ ልዩ የአገልግሎት መስኮች ልማት ተስፋፍቶ ዜጎች ከአገሪቱ እድገት ጋር ደረጃ በደረጃ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።

ኢትዮጵያ የተጓዘችበት የ27 ዓመታት የዕድገት ጉዞ ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላ በፍጥነት መረማመድ ያስቻላት ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩ ልዩ ችግሮች ሲያጋጥሙንና እነዚህንም በፍጥነት ባለመፈታታቸው ሳቢያ ለሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ተጋልጠናል። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመልካም አስተዳደር ችግር እየተባባሰ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስመረረና በስርዓቱ ላይ ያላቸው አመኔታ እንዲሸረሸር ምክንያት መሆኑ አይታበይም።

ሙስና እየተበራከተና የህዝብን ልማታዊ ጥረትና ተጠቃሚነት በእጅጉ እየጎዳም ሲሄድ መቆየቱም እንዲሁ። በተለይ ሙስና በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ እየሰፋ የመጣውንና አስተማማኝ የስራና የገቢ እድል ሊፈጠርለት የሚገባውን ወጣት ክፉኛ ተፅዕኖ እንደፈጠረበት ይታወቃል። ይህም ወጣቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጎታል።

ይህ የመግለጫው አንኳር ጉዳይ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ወጣቱ በተገቢው መንገድ አገሪቱ ከፈጠረችው ሃብት ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት ነው። ምንም እንኳን ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ስልጣንን ለግል ጥቅማቸውና ለኑሮ ማደላደያነት ለማዋል በሚሹ ኃይሎች አማካኝነት የተፈጠረ ችግር ቢኖርበትም፤ ችግሩ በሀገሪቱ በመመዝገብ ላይ የሚገኘው ልማታዊ ድል ጊዜያዊ እንቅፋት መሆኑን መረዳት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባሻገርም፤ የመንግሥትን የለውጥ ኃይልነት ስለሚያውቅ፤ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እንደማይወጣና እንደሚለወጥም ማመን ይኖርበታል፡፡

ፀረ ሰላም ኃይሎቹ የሚፈልጉት ወጣቱ በአሁን ወቅት ያገኘውን ተጠቃሚነት እንዳያጣጥም መሆኑን ተገንዝቦ ወጣቱ ሴራቸውን በመንቃት ወደ ልማት ስራው ላይ ማተኮር አለበት። እንደሚታወቀው ሁሉ ወጣቶች የዛሬ አፍላ የልማትና የዴሞክራሲ ኃይሎችና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ናቸው። ይህን የሚገነዘበው መንግስት በትምህርት የታነፀና የተገነባ አቅም እንዲኖራቸው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ብቃት በማሳደግ በሀገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓትና መልካም ልማታዊ አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን የነቃና ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው።

ይህን በማድረግም በአገሪቱ ወጣቶች አካባቢ ከሥራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የተሳታፊነትና ፍትሐዊ ተጠቀቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ እየጣረ ነው። እንዲሁም የሴቶችና የወጣቶች ፓኬጆች ትስስርና ተመጋጋቢነት ባለው ሁኔታ ተፈጻሚ እንዲሆን ትኩረት ሰጥቷል።

የተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ፣ ወጣቶች በህብረት ሥራ ማህበራት በመደራጀት የብድርና ቁጣባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገም ነው።

ወጣቱ ኃይል አፍላ ጉልበት ያለው በመሆኑ፤ ሀገራችን ይህን ለስራ ዝግጁ የሆነ ጉልበት በሚገባ መንገድ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይህን ጉልበት አጣጥሞ በተገቢው መንገድ መጠቀምም ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ናቸው። እነርሱን በማናቸውም ሀገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ በማስገባት ማሳተፍ ስራዎችን በአፍላ ጉልበት እንዲሁም በፈቃደኝነትና በፍላጎት ስሜት ሊተገብሩት ይችላሉ። ይህ ደግሞ የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም በወጣቶች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ውጤቱ መልሶ የሚከፍለው ሀገርን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ኢህአዴግ እንደ መሪ ድርጅት በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የያዘው አቋም ይህን ዕውነታ ታሳቢ ያደረገ ነው። እንዲህ ዓይነቱ በጋራ መግባባት ላይ የተያዘ አቋም ወደ መሬት ወርዶም ገቢራዊ መሆን ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy