Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

  የትናንትናውን ምእራፍ ዘግተናል

0 370

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  የትናንትናውን ምእራፍ ዘግተናል

ዮናስ

በመላ አገሪቷ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ ኢትዮጵያውያን በተስፋ ተሞልተው የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን እያከናወኑ መሆናቸው፣ አገሩን ለሚወድ ማንኛውም ሰው ዕፎይታ ይሰጣል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር  በጅግጅጋ፣ በአምቦ በመቐለ በባህርዳር እና የጎንደር ከተሞች ከሕዝብ ተወካዮች ጋር ከመነጋራቸውም በላይ፣ በአዲስ አበባ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ እንዲሁም ከመላ አገሪቱ ከተውጣጡ 25 ሺሕ ወጣቶች ጋር ተገናኝተው የትናንትናውን ምእራፍ ዘግተዋል።

ኢትዮጵያ የሁሉም አገርና ቤት እንደሆነች፣ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲና ነፃነት እንደሚገባቸው፣ ወጣቶች ለአገራቸው እንዲቆሙ፣ ፋታ የማይሰጡ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን፣ መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ የፍቅርና የይቅርታ መሆን እንደሚገባው፣ በአገር ጉዳይ ኢትዮጵያውያን በሙሉ አብረው መሠለፍ ያለባቸው መሆኑም ላይ መግባባት በመፍጠር የተበላሸውን ምእራፍ ዘግተዋል።

ይህን የመሰሉ ለአገር የሚበጁ በጎ ነገሮች ሲታዩ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ያስደስታል፡፡ ነገር ግን የአገር የጋራ ጉዳይን እንደ ፀጉር በመሰንጠቅና ጨለምተኛ በመሆን መልካም ጅማሬዎችን ለማደብዘዝ እና የተዘጉ ፋይሎችን የሚከፍቱ ሃይሎች አሁንም ብቅ ብቅ እያሉ ነው። እነዚህ ሃይሎች አዲሱን የካቢኔ ሹመት ተከትሎ  የብሔር፣ የሃይማኖትና የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶችን እየታከኩ የጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዳይፈጠር እየሰሩ ነው ፡፡ በጎነት በክፋት ሲከበብ የምትጎዳው አገር ናት፡፡ የሚጎዳው ሕዝብ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አንድነት ማለት አንድ ዓይነትነት እንዳልሆነ ሁሉ፣ ልዩነት ማለት ደግሞ የመጠፋፋት ተቃርኖ አይደለም፡፡ የሐሳብ የበላይነት ሊኖር የሚችለው በነፃ ውድድር ፉክክር በማድረግ የሕዝብን ልብ መግዛት ሲቻል ነው፡፡ በር ዘግቶ በመዶለት ወይም በማሴር ሳይሆን በአደባባይ ለሕዝብ ዓላማን አስረድቶ ተቀባይነት ማግኘት ሲቻል ነው፡፡ ሕዝባዊ ነኝ ማለት የሚቻለውም ለሕዝብ ፍላጎት በመገዛት ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአሻጥርና ከሴራ  የዞረ ድምር ፖለቲካ መገላገል ይኖርባታል፡፡ ማታለልና ማጭበርበር፣ አድርባይነትና አስመሳይነት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገለል ማለት ይኖርባቸዋል፡፡ በጎነትን በክፋት የሚያበላሹ ከንቱ ድርጊቶች ናቸውና፡፡

 

በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፊታቸው በርካታ ሥራዎች ይጠብቋቸዋል፡፡ ሕዝብም ብዙ ነገር ይጠብቃል፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማከናወን ስላለባቸው ጉዳዮች በመዘርዘር ሐሳብ የሚያቀርቡ አሉ፡፡ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባው ማሳሰቢያዎቹ ኃላፊነት የተሞላባቸው እንዲሆኑ ነው፡፡ አሁን እየታዩ ያሉትና ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚቀርቡ አንዳንዶቹ  ማሳሰቢያዎች የኢትዮጵያን አስቸጋሪና ውስብስብ ፖለቲካ ያመዛዘኑና የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡ አለመሆናቸው ሳያንስ የተዘጉ ፋይሎችን የሚያነሱና ዳግም ወደትርምስ የሚገፉ አጀንዳዎች ናቸው፡፡

ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ አንገብጋቢ ለሚባሉ አጣዳፊ ጉዳዮች ጠቅላይ ሚንስትሩ እና መንግስታቸው ቅድሚያ እንደሚሰጧቸው ይፋ በማድረግ ነው የትናንትናውን ምእራፍ የዘጉት፡፡ ስለሆነም በሒደት  በቅደም ተከተል የሚፈቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ማጤን እንጂ የተዘጋ ፋይል ማንቀሳቀስ ህዝባዊነትም ኢትዮጵያዊነትም አይደለም፡፡ አዲሱ ምእራፍ ከጠባብ ግላዊና ቡድናዊ ፍላጎቶች በመላቀቅ አገሪቱን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳቦች የሚቀርብበት ነው፡፡   

በትናንትናው ምእራፍ ከሕግ በላይ መሆን አገር እንደሚያበላሽ በሚገባ ታይቷል፡፡ የሕግ የበላይነት ጠፍቶ ግለሰቦች ሕግ ሲሆኑም ተመልክተናል፡፡ ሕግ የተበዳዮች ጋሻ መሆን ሲገባው የበዳዮች መሣሪያ መሆኑንም በተዘጋው ምእራፍ ተስተውሏል፡፡ በትናንትናው ምእራፍ ዘረፋና ሌብነት አገር ለብልበዋል፡፡ ዜጎችን በገዛ አገራቸው ባይተዋር ተደርገዋል፡፡ መብታቸውን ሲጠይቁ ምላሻቸው ዱላ ሆኗል፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ነግሶ አገር ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃለች፡፡ ይህን የተዘጋ ምእራፍ እንደገና ለመክፈት መሞከር ጸረ ኢትዮጵያዊነት ነው።

አዲሱ የለውጥ ምእራፍ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ጉዳያቸው አንድ ላይ መቆምን ባህል እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከስሜታዊነት በመላቀቅ በምክንያታዊ አስተሳሰቦች መታገዝ የግድ የሚጠይቅ ምእራፍ ነው፡፡ ለተጠራጣሪነት እና ጨለምተኝነት ቦታ የሌለው ምእራፍ ነው። በልዩነት ውስጥ ሆኖ ለጋራ ጉዳይ አንድ መሆን እንደሚቻል የሚያረጋግጥ ምእራፍ ነው፡፡   

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ያቀረቧቸውን የካቢኔ አባላት ማንነትና የሚሸጋሸጉ ሚኒስትሮችን ሐሙስ ሚያዝያ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት፣ ያሰመሯቸው ቀይ መስመሮች በእርግጥም የትናንትናውን ምእራፍ መንግስትና ህዝብ ስለመዝጋታቸው የሚያጠይቅ ነው “የሚሾሙትም ሆነ ባሉበት የሚቀጥሉት እንዲገነዘቡ የምፈልገው፣ ሕዝብ ቅሬታ የሚያቀርብበት የአገልግሎት አሰጣጥ ማስተካከል ግዴታና አንደኛው ቀይ መስመር ነው፤” ሲሉ አገልግሎት አሰጣጥን የተመለከተው ያደፈ ምእራፍ መዘጋቱን ማጠየቃቸው ነው፡፡

“ሕዝብ የተለየ ነገር ወይም ወርቅ አንጥፉልኝ አላለም፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ መታወቂያ ለማውጣት ዝምድናና ጉቦ መክፈል እንደማይገባው ነው የሚጠይቀው በማለት በምሳሌ ማስረዳታቸውም እንዳይነሳ ተደርጎ የተዘጋ ፋይል መሆኑን ለማመላከት ነው፡፡ “የአገልግሎት አሰጣጥ ማረጋገጥ ከነበሩትም ከሚሾሙትም ሚኒስትሮች እንደሚፈለግ በፓርላማው ፊት በጥልቅ ማሳሰብ እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡

ሁለተኛው ቀይ መስመር ወይም የተዘጋው የትናንት ምእራፍ ሙስናን የተመለከተ ነው፡፡ “የሙስና ጉዳይ ሌላኛው ልናልፈው የማንችለው ጉዳይ ነው፡፡ በተደራጀና ባልተደራጀ መንገድ የሚደረግ ሙስናን መዋጋት ብቻ ሳይሆን፣ በየተቋማቱ የሚበላን የሀብትና የጊዜ ብክነት መቆም አለበት፡፡ ራሳችን በሙስና ውስጥ ባለመሳተፋችን ንፁህ ነን ማለት አይደለም፡፡ ይህም የማይታለፍ ቀይ መስመር ነው”በማለት ለጉዳዩ አጽንዖት ሰተዋል፡፡  ስለሆነም የተዘጋን ፋይል የሚገላልጡ ሃይሎች ከሆኑም ሊሆኑ የሚችሉት በዚህ አዘቅት ውስጥ የተነከሩት ናቸውና መላው ህዝብ ሊጠነቀቃቸውና በአዲሲ ምእራፍ መርሆዎች ብቻ ሊጓዝ ይገባዋል፡፡

 

የተዘጋውና የትናንት የምንለው ምእራፍ የተጨበጠና ከኢትዮጵያዊነት ባህል ያፈነገጠ ይልቁንም የሁሉንም ወገን አንገት ያስደፋውን በግጭት የተገለጠ የሽንፈት ታሪክ ነው፡፡ ይህንን አሳፋሪ የታሪክ ምዕራፍ በፍጥነት ዘግቶ  በሁሉም ሕዝቦች ይሁንታ ላይ የተመሠረተው የጋራ መፍትሔ ደግሞ አዲሱና አሳልፈን ልንሰጠው የማይገባ የዛሬና ነገ ምእራፋችን ነው፡፡ ለዚያ አሳፋሪና አውዳሚ ግጭት መንስዔ የነበሩ ምክንያቶችና ቆስቋሾች ጥርት ብለው ወጥተዋል፡፡ እንዲያውም ለአዲሱ ምእራፍ የማእዘን ድንጋይ ሆነዋል።  

 

ሕዝቡ ባህል ባደረገው የግጭት አፈታት ሥርዓት የበደለውን እየገሰፀ፣ የተበደለውን እንዲካስ የሚያደርግ አዲስ ምእራፍ ጀምረናል፡፡ የጠባሳም ሆነ የቁርሾ ምእራፍ ተዘግቷል፡፡ ይህንንም ሕዝባዊ ኮንፈረንስ ተጠርቶ ውይይት ሲደረግ እርስ በርሱ እየተላቀሰ አብሮነቱን በማረጋገጥ ምእራፉ መዘጋቱን አሳይቷል፡፡ ይህንን የመሰለ ፀጋ ያለው ሕዝብ መሀል የሚረጨው የመርዝ ምእራፍ ነው የትናንቱ እና የተዘጋው ምእራፍ ፡፡  

በታሪክ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያውያን መካከል ለግጭት የሚጋብዝ አጋጣሚ ተፈጥሮ አያውቀውም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ገዥዎች ምክንያት ግጭቶች እንዳጋጠሙ ይታወቃል፡፡ ይሁንና አንድ ሕዝብ በሌላው ላይ ተነስቶ የበላይ ለመሆንም ሆነ፣ በሌሎች ፍላጎቶች ምክንያት ይህ ነው የሚባል ግጭት አልተከሰተም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የሚታወቀው አገሩን ከተስፋፊዎችና ከወራሪዎች ሲጠብቅ ነው፡፡ በገዥዎች የተለያዩ በደሎች የደረሱበት ሕዝብ እርስ በርሱ እየተደጋገፈና እየተሳሰበ፣  ከትውልድ ወደ ትውልድ በመሸጋገር እዚህ ዘመን ደርሷል፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን አስጠብቆ ለዓለም ተምሳሌት የሆነ ሕዝብ፣ በብሔርም ሆነ በሃይማኖት ሊከፋፍሉት ያሰቡትን ሁሉ ሴራቸውን ሲያከሽፍ ኖሯል፡፡ ልዩነቶቹን ጌጥ አድርጎ አንድነቱን ኃይል ያደረገው ይህ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ አሁንም የጠባብነትንና የትምክህተኝነትን ምእራፍ ዘግቷል። ይህ ሕዝብ ከአኩሪ ባህሎች፣ ልማዶችና ወጎች በተጨማሪ ለአዲሱ ምእራፍ የሚበጅ አስገራሚ አገር በቀል ዕውቀት ያለው መሆኑንም መንግስት አስተውሎ ሊጠቀምበት ይገባል፡፡

የትናንቱ የአሻጥርና የሴራ ምእራፍ  ግብ ሥልጣን ጨምድዶ ይዞ ሕዝብን ነፃነት ማሳጣት ነው፡፡ ለዕልቂትና ለውድመት መዳረግ ነው፡፡ የትናንቱን አሳፋሪ ውርደት ላለመድገም የሚቻለው የትናንቱን ምእራፍ በመዝጋት ነው፡፡ ከአገር በላይ ለሥልጣን ቅድሚያ መስጠትን ትኩረት ያደረገው የትናንቱ ምእራፍ አደገኛ መሆኑ በሚገባ ታይቷል፡፡ ባልበሰለ የፖለቲካ አመራርና በሥልጣን ጥመኝነት የተቃኘው የትናንቱ ምእራፍ  አገሪቱን ጎድቷል። የሕዝቡንም ሕይወት አመሰቃቅሏል፡፡ አዲሱ ምእራፍ የሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ነው፡፡ አዲሱ ምእራፍ ህዝብ በአገሩ ጉዳይ ዋነኛ ባለቤት የሚሆንበት ነው፡፡ የትናንቱ እና የተዘጋው ምእራፍ ማንም ጉልበተኛ እየተነሳ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱን የሚገፍበት ያደፈና የጎደፈ ምእራፍ ነው፡፡

 

አዲሱ ምእራፍ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆነ ለሚመሩት መንግስትና ግምባር ሁለገብ ድጋፍ  የሚደረግበት ነው፡፡ ዳር ላይ ቆሞ የመተቸት ምእራፍ ተዘግቷል። አዲሱ ምእራፍ መልካሙን ነገር  ማመላከትና ማሳሰብ ነው፡፡ ከእሳቸውም ሆነ ካዋቀሩት ካቢኔ ብቻ የሚጠብቅ ሳይሆን ድጋፍ የማድረግ ምእራፍ ነው፡፡  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy