Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአንድ ሳንቲም ሶስት ገፅታዎች

0 234

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአንድ ሳንቲም ሶስት ገፅታዎች

                                                     ቶሎሳ ኡርጌሳ

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ ናቸው። አንዱ ለሌላው ግብዓት የሚሆን እንዲሁም አንዱ የሌላው ውጤት ነው። በአጭሩ የአንድ ሳንቲም ሶስት ገፅታዎች ናቸው ማለት ይቻላል። ሶስትም፣ አንድም። ሶስቱም የሀገራችን የህልውና ጉዳይ ናቸው።

የሀገራችን ህዝቦች አሁን የተገኘውን ሰላም ለማምጣት በአያሌው ታግለዋል። ሰላምን ጨምሮ የዘመናት ጥያቄያቸው የነበሩትን ልማትና ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ በርካታ መስዋዕትነቶችን ከፍለዋል። በቀደምት ስርዓቶች በርካታ ግፎች ቢደርስባቸውም፤ በመስዕዋትነታቸው በደላቸውን መሻር ችለዋል።

እናም በሰላምና መረጋጋት እጦት ይህ ትግላቸው እንዲቀለበስባቸው አይፈልጉም። መላው የሀገራችን ህዝቦች በተለይም ያለፈው አምባገነናዊና ‘የሁሉም ችግሮች መፍትሔ ጦርነት ነው’ የሚለው ስርዓት የፈጠረውን እልቂት በሚገባ ስለሚገነዘቡ የሰላምን ዋጋ ያውቃሉ። የትላንት የጦርነት ሰቆቃን ስለሚያውቁ ነው።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዛሬ እንደ ትናንቱ ጦርነት ያንዣበበትን የሰቆቃ ህይወት አይመሩም። በጆሯቸው ላይ የጥይት አረሮች አይጮሁም። ለአቅመ-አዳም የደረሱ ልጆቻቸው በግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና ወደ ጦርነት አይላኩም። እነዚህ ከዛሬ 26 ዓመታት በፊት የነበሩት ትውስታዎቻቸው በሰላም ትሩፋቶች ተሞልተዋል። ይህ አስተማማኝ የሰላም ምህዳርም የኋሊት እንዲቀለበስባቸው አይፈልጉም። እናም በልማትና በዴሞክራሲ ባህል ግንባታቸው ላይ አተኩረዋል።

በተገኘው አስማማኝና ዘላቂ የሰላም ቁመና ታጅበውም ህዳሴያቸውን ዕውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘው ቆመዋል። በሰላማቸውና በመረጋጋታቸው ከፍታቸውን ለማረጋገጥ ዝግጁ ሆነዋል። እናም እዚህም ሆነ እዚያ ይህን የሰላምና የመረጋጋት መንገድ ለመዝጋት የሚፈልጉ የውስጥም ይሁን የውጭ ሃይሎችን አይታገሱም።

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የሰላምና የመረጋጋት ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ተባብረው በመስራት ላይ ይገኛሉ። እርግጥ በየትኛውም ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የሚፈለግ ሰላም ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የሰላም ዋጋን ዋነኛ መዛኙ ኃይል ህዝብ ነው። ህዝብ ጥቅሙን የማያውቀው ሰላም ዕውን ሊሆን አይችልም።

ርግጥም ለአንድ ሀገር ልማትና ዕድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም። እንደ እውነቱ ከሆነ የሰላም ዋጋ በምንም አይነት ምድራዊ ዋጋ ሊለካ የሚችል አይመስለኝም።

ሰላም የሚተመንበት አሊያም የሚሰፈርበት ልኬት አለው ሊባል የሚችልም አይመስለኝም። ከግለሰብ የነገ ማንነት ህልም ጀምሮ እስከ የሀገር ህዳሴ ዕውን መሆን ድረስ ሰላም ዋጋው እጅግ የገዘፈ ነው። የአንድ ሀገር ሰላም የህዝቧቿ ሰላም ነው።

በመሆኑም ዜጎች መብትና ግዴታዎቻቸውን ሲያውቁና ሌላውን ለማስተማር ሲነሳሱ የሀገር ሰላም ይረጋገጣል። ልማትና ዕድገትም ይደረጃሉ፤ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችም በዚያው መጠን እያበቡ ይሄዳሉ። ርግጥ የሀገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ብቻ አይደለም—ዋነኛው ተዋናይ የሆነው የሀገራችን ህዝብ ጭምር እንጂ። ህዝቡ በያለበት ሆኖ ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ሃይል አቅም ሊኖረው አይችልም።

በሀገራችን ሰላም በመኖሩ ልማት ውን ሆኗል። ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ባለቤት ሆነናል። በተለይም የኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል መሆን ችለናል። ርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በርካታ ባለ ሃብቶችን በመሳብ ላይ ነው፡፡

በዚህም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል፡፡ በዚህም ሳቢያ ቀደም ሲል በምሳሌነት ያነሳኋቸውና ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ነው— በርካታ ዜጎችንም የስራ ባለቤት በማድረግ።

ርግጥ ሀገራችን እየተከተለችው ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ነፃ የመሬት አቅርቦት መዘጋጀቱ፣ የአበባ ማምረቻ ስፍራዎች በመንገድ እና በኤሌክትሪክ እንዲተሳሰሩ መደረጋቸው፣ የታክስ እፎይታ ጊዜ መኖሩ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገራችን እንዲሳቡ ዋነኛው ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል። ሀገራችን የምትከተለው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር አሁን ለተገኘው የኢንቨስትመንት አመቺነት ምህዳር ወሳኙን ሚና መጫወቱም እንዲሁ።

የኢፌዴሪ መንግስት ሀገሪቱንና ህዝቦቿን ከድህነት ከኋላቀርነት ለማላቀቅ የነደፈው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተግባራዊ በማድረግ ተስፋ ሰጪ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ የውጪው ዓለምና ባለሃብቶቻቸው ሳይቀሩ እየመሰከሩለት ይገኛሉ። ከመመስከር ባለፈም፤ የሀገራችንን መፃዒ ዕድል ከወዲሁ በአንክሮ አጢነው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ በልማት እግሮቻቸው ወደ ሀገራቸን እየተመሙ ነው። አዎ! ዛሬ የኢንቨስትመንት መንገዶች ወደ ኢትዮጵያ በማምራት ላይ ይገኛሉ።

እንደ እኔ እምነት በሀገራችን ውስጥ እየደገ የመጣ፣ ተጠቃሚ እንዲሁም መካከለኛ ገቢ ያለው የህዝብ ቁጥር መጨመሩ፣ ፈጣን የከተሞች ዕድገት መታየቱና ሳቢ የኢንቨስትመንት አሰራር መኖሩ ባለሃብቶችን እየሳበ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን በምስራቅ አፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ውስጥ አንዷ ስለሆነችና እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት አቅም ያላት መሆኗ ባለሃብቶቹ ለሚሳተፉበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

ሰላም ካለ ዴሞክራሲ ስር እንዲሰድ ማድረግ ይቻላል። መንግስት ባለፉት ዓመታት ባደረገው ጥረት የአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከማጎልበትና ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ነው።

በተለይ ከሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተጀመረው ድርድርና ውይይት ተጠቃሽ መሆኑን በማመላከት ሂደቱ በመቻቻል፣ በመደማመጥና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ በመመስረት ለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጠናከር የበኩሉን ሚና እያበረከተ ነው።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ ከተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ጋር የተደረጉ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች ዴሞክራሲያዊ ባህልን ከማጎልበት አንጻር ጠቃሚ ሚና ተጫውቷል።

በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረውን የመደራጀት መብት ተከትሎ የየራሳቸው ደጋፊዎች ያሏቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተውና በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የባህር መዝገብ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመስርተው ተግባራቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።

በተለይም የሽግግር መንግስቱን ተከትሎ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ዕውን ከሆነ በኋላ የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ እስከተካሄደው ምርጫ ድረስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብረው ለአምስት ጊዜያት በተካሄዱት ምርጫዎች እንዲወዳደሩ ተደርጓል።

መንግስት አምና ላይ የምርጫ ህጉን ከማሻሻል ጀምሮ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ሌሎች ህጎችን እስከ ማሻሻል ጭምር ድረስ በመሄድ የተዳቀለ የምርጫ ስርዓትን በመከተል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፅ የሚሰማበትን ሁኔታ በመፍጠር የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ቃል ገብቷል።

ርግጥ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከሚከተል እንዲሁም ዴሞክራሲን እንደ ሞትና ሽረት ጉዳይ አድርጎ ከሚመለከት ፓርቲና መንግስት የሚጠበቅ ነው። ያም ሆኖ ሰላም ካለ ዴሞክራሲና ልማት ይኖራሉ። አንዱ ከሌላው ጋር ያለው ግንኙነት የሚለያይ አይደለም። አንዱ ለሌላው ህልውና እና ውጤት ነው። እነዚህን የአንድ ሳንቲም ሶስት ገፅታዎች አጥብቆ መያዝ ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy