Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢትዮጵያ  ህዝቦች አንዳቸው ካላንዳቸው…

0 475

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያ  ህዝቦች አንዳቸው ካላንዳቸው…

አባ መላኩ

የኢትዮጵያ ህዝቦች መለየት በማይቻልበት ሁኔታ የተቀላቀሉና አንዱ ሌላውን መስሎ ሳይሆን  ሆኖ የሚኖሩ፤ የዘመናት የአብሮነትና የአንድነት ታሪክን የሚጋሩ፣ በጨቋኝና ገዢ ስርዓታት እንኳን ያልተለያዩ ህዝቦች ናቸው። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ደ/ር አብይ  የኢትዮጵያ ህዝቦችን አንድነት የገለጹበት ሁኔታ የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ መግዛት ችሏል። ኢትዮጵያዊያን በመተማ፣ በአድዋ፣ በካራማራ፣ ባድመ፣ ወዘተ አገራቸው ከወራሪ ጠላት ለመከላከል ሲሉ በአንድ ጉድጓድ ተቀብረዋል።  እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ይህን አይነት አንድነት አለን የምንል ህዝቦች ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት እየፈጸምናቸው ያሉ ነገሮች በ21 ክፍለ ዘመን የማይታሰቡና አሳፋሪ በመሆናቸው ዳግም በአገራችን ሊከሰቱ የማይገቡ ድርጊቶች ናቸው።  

ኢትዮጵያ የህዝቦቿ  ድምር ውጤት ናት። የኢትዮጵያ  ህዝቦች አንዳቸው ለሌላኛው ቆስለዋል፣ ሞተዋል፤ ተርበዋል፣ ታርዘዋ፤ በመሆኑም እነዚህ ህዝቦች በደምና አጥንት የተሳሰሩ በመሆናቸው ግንኙነታቸው ጊዜ አይፈታውም፤  ዘመንም አይሽረውም። ኦሮሞው፣ ያለአማራው፣ ያለትግሬው፣ ያለሶማሌው፣ ወዘተ በተመሳሳይ አማራው፣ ያለኦሮሞው አፋሩ፣ ሲዳማው፣ ጉራጌው ወዘተ አቅምም ሆነ ውበት አይኖረውም። የኢትዮጵያ ህዝቦች በተናጥል አያምሩም፤ አቅምም አይኖራቸውም። የኢትዮጵያ  ህዝቦች አንዳቸው ካላንዳቸው ጎዶሎና ባዶ መሆናቸውን ሁሉም ተገንዝበው መደጋገፍና መተጋገዝ ይኖርባቸዋል።

ከላይ እንዳነሳሁት የኢትዮጵያ ህዝቦች መለየት በማይቻልበት ሁኔታ አንዱ ሌላውን መስሎ ሳይሆን ሆኖ የሚኗኗሩ ህዝቦች ናቸው። በቀድሞዎቹ  ጨቋኝና አንባገነን መንግስትት ወቅት እንኳን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮነታቸው የጠነከረ ነበር። ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት  በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከቶች የህዝቦችን አብሮነት የአገራችንን አንድነት ክፉኛ ተፈታትኖታል። ይሁንና ህዝቦች ባሳዩት ትዕግስት ያንን ቀውጢ ጊዜያት ተሻግረነዋል። ትላንት የነበረው  አብሮነታችንና አንድነታችን ከእርስ በርስ እልቂት ታድጎናል፤ አገራችንንም ከመበታተንና ከመፍረስ አትርፏታል። በትላንት መልካምነት አጋጥሞን የነበረውን አደጋ ተሻግረነዋል። ዛሬ ደግሞ የነገን መደላድል ልንፈጥር ይገባል።     

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በባለፉት 27 ዓመታት የፈራናቸው ወጣቶች ለአብሮነትና መቻቻል የሚሰጡት ቦታ እምብዛም መሆኑን የታዘብኩት በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ሁከቶችን  ስመለከት በአብዛኛው ሲቀጣጠሉና ሲቀነቀኑ የተመለከትነው በእነዚህ አዲስ ትውልዶች መሆኑ ነው። መንግስት ወይም ኢህአዴግ በወጣቱ ላይ ተገቢውን ትኩረት ባለማድረጋው ወጣቱ ስለአብሮነትና አንድነት ጠቀሜታ  የሚያውቀው ነገር ባለመኖሩ፤ ወይም ጠዋት ማታ ስለብሄርና ክልል በመቀንቀኑ ሳቢያ ሁሉም ጓዳ ጓዳውን ማጽዳት እንጂ በአንድነት የሚያስተሳስራቸውን ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቀነ አልነበረም።

በቅርቡ በአገራችን  ተከስቶ በነበረው ሁከት  መታዘብ የቻልነው በዕድሜ በሰል ያለው የህብረተሰብ ክፍላችን የጥፋት ሃይሎችን  ሲገስጽ፣ ሁከተኞችን ሲቆጣ፣ ጉረቤቶቻቸውን ከጥቃት ለመከላከል ሲሯሯጡ ተመልክተናል፣ ንብረታቸውንም  ከውድመት ለመከላከል ጥረት አድርገዋል፤ ከአቅም በላይ ሲሆኑባቸው ደግሞ አብረው ሲላቀሱ፣ ሲያዝኑና ሲያስተዛዝኑ  ተመልክተናል። እኛ የምናውቀው ኢትዮጵያዊነት ይህ ነው። አዲሱ ትውልድ ሆይ ረጋ በል፤ ቆም ብለህ አስብ፤ ነገሮችን  አመዛዝን፤ ከስሜት ጅረት ውጣ፣ የስሜት ጅረት መዳረሻው መጠፋፋት አገር መበተን ነው። አባቶቻችን ይህችን አገር ያቆዩልን ተቻችለውና ተዛዝነው ነው፤ አባቶቻችን  አብረው የኖሩት ችግር ሳይገጥማቸው ቀርቶ አይደለም። ይሁንና መጥፎ ነገርን አይተው እንዳላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መልካም ነገሮችን በማጉላት መልካም መልካም ነገሩን በማሰብና በመናገር ጭምር ነው።   በስሜትና በሃይል የሚመጣ ነገር ለማንም አይበጅም፤ ምክንያቱም በሁከትና ነውጥ ለውጥ ለማምጣት የሻቱ አገራትን መጨረሻ ተመልክተናል።

የኢትዮጵያ  ህዝቦች ድንበር ሳይለያቸው ቋንቋ ሳይገድባቸው  ተጋብተው ተዋልደው ያለውን ተሰጣጥተው፣ አንዱ ለሌላው  ዋስ ጠበቃ ሆኖ የኖሩ ወደፊትም የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው፤ ተወደደም ተጠላም  ይህን አብሮነታቸውን ሊነጣጥል ማንም አይቻለውም። እባካችሁ ለማይረባ የፖለቲካ ትርፍ ብላችሁ  የአብሮነት እሴቶቻችን አትሸርሽሩብን። ፖለቲከኞች እባካችሁ የዘረኝነት ፖለቲካችሁን ለስልጣን እርካብነት አትጠቀሙበት።  የአገሬ ወጣት ሆይ ወደ ስሜታዊነት የፖለቲካ አዙሪት ሊከቱን ከሚሯሯጡ ዘረኛ ሃይሎች ራሳችሁን ጠብቁ። በህዝቦች መካከል አሜኬላ ለመዝራት  የሚሯሯጡ ሃይሎች የግል ጥቅም ፈላጊዎች ናቸው። እስካሁን እንደተመለከትነው በህዝቦች መካከል ሁከትና ብጥብጥ እንዲነግስ የሚሯሯጠው በአብዛኛው በግል ጥቅም ናላው የዞረና   ተማርኩ የሚለው አካል ነው። ይህን አካል ማስተካከል የሁላችንም ተግባር መሆን መቻል አለበት። ሌባን ሌባ ልንለው ይገባል። ሌቦች ዘረኛና ጎጠኛ ናቸው። ችግሮቻቸውን በብሄር ካባ  ለመጀቦን የማያደርጉት ጥረት የለም።

የህዝቦችን  አብሮነት ለመሸርሸር  በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ  መረጃዎች እውነትነት የራቃቸው በመሆናቸው  ከማህበራዊ ሚዲያ የሚገኝ መረጃ እንደትክክለኛ  መረጃ ባንመለከታቸው መልካም ነው። ማህበራዊ ሚዲያ ማንም የፈለገውን መረጃ  የሚያንሸራሽርበት ሚዲያ እንጂ ከዚህ ሚዲያ የሚገኝ መረጃ ሁሉ ትክክል ነው ማለት አይደለም።  በጥላቻ የተጠመዱ አካላትንም በቃችሁ ልንላቸው የሚገባው ትክክለኛ ወቅት አሁን ነው። ሁሉም አካላት  ሰከን ይበል፤ ሰክኖ ማሰብ ውጤቱ መልካም ነው። ወጣቶች ሆይ በስሜታዊነት እየተነሳችሁ የአብሮነት እሴቶቻችንን አሽቀንጥራችሁ አትጣሉብን።  የጥበትና ትምክህት ሃይሎች እንኳን ህዝብን ቤተሰብን የሚነጣጥል መሰሪ አካሄድን የሚከተሉ በመሆናቸው ተገቢው ጥንቃቄ ካላደረግን እንዲሁም አካሄዳቸውን ካልነቃንባቸው ነገም አገራችንን ወደቀውስ ሊያመሯት ይችላሉ።

አገራችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ የቻለችው ህዝብና መንግስት በቅርበት መስራት በመቻላቸው ነው። ህዝብን በማሳተፍ ልማት መፋጠን እንደምንችል ባለፉት ዓመታት የነበሩ ተሞክሮዎች አመላክተውናል።  ድህነት የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ በመሆኑ የጋራ ጠላታችን ነው፤ የጋራ ጠላታችንን ደግሞ በጋራ ልንታገለው ይገባል። ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር አይተነዋል። ያሉንን ጥቂት የልማት ስራዎች አይናቸውን አጥፍተን ተጨማሪ መጠየቅ ከስር ከመሰረቱ የሚያስኬድ ነገር አይደለም።  የባለሃብቶችንም ንብረት እያወደምን የስራ እድል አጣን ማለቱ አግባብ አይመስለኝም። ባለሃብቶችም ዛሬ የፈጸምነውን ጥፋት እየተመለከቱ ንብረታቸውን ኢንቨስት ማድረግ ስለሚፈሩ ከእዚህ ያለ ድርጊት ልንቆጠብ ይገባል።

አገራችን ባለፉት 27 ዓመታት ስኬታማ መሆን የቻለችው ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ በመቻሏ ነው። ሰላማችን  ሁለመናችን ነው። በመሆኑም በሰላማችን ላይ ምንም አይነት እንቅፋት ማስቀመጥ የለብንም። መንግስት ለቅሬታዎች በወቅቱ ምላሽ ይሰጥ።  ለሁሉም የህዝብ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ መስጠት እንደማይቻል መንግስት ተረድቶ በወቅቱ “አይሆንም” ወይም “አይቻልም” የሚል  ምላሽ መስጠት በራሱ መልስ ነው። እንዲሁም መንግስት የአገልግሎት አሰጣጡን ያቀላጥፍ፤ ሁሉም እኩል የሚስተናገድበት ሁኔታን ይፍጠር፤ የህግ የበላይነትነ ለደርድር አይቅረብ፤ ፍትሃዊ ነትን ማንገስ ነው። ህብረተሰቡም መረዳት ያለበት ነገር  የተጠየቀ ነገር ሁሉ እለቱን ይስተካከላል ብሎ ማሰብ ተገቢነት ተጠቃሚነት ይንገስ። ልማትም ሆነ ዘላቂ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው በመንግስት ብቻ አለመሆኑን ህብረተሰቡ ተረድቶ ለተሻለች ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስትዋጽዖ ያበርክት።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy