የኦሮሚያ ክልል ከባለሀብቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ አስታወቁ።
ርእሰ መስተዳደሩ ከቤት ንብረታቸው ላይ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ከተለያዩ ባለሀብቶች የተበረከተውን የገንዘብ ድጋፍ በተረከቡበት ወቅት ነው ይህንን ያሉት።
አቶ ለማ መገርሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከባለሀብቶች ጋር ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ መልኩ ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ ነው።
በክልሉ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንም መስኮች ለተሰማሩ እና መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶችም በራችን ክፍት ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ስራ ላይ ላሉትም ይሁን አዲስ ወደ ኢንቨስትመንት ስራ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አቶ ለማ ተናግረዋል።
ኢንቨስትመንም የግልሰብ ሀብት ብቻ ሳይሆን የሀገር በህት ነው ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ፥ ስለዚህም በዘርፉ ለሚሰማሩ አካላት ለየት ያለ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልፀዋል።
ርእሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ አያይዘውም ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ የሚያበረታታ መሆኑን እና ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዛሬው እለትም የተለያዩ ባለሀብቶች እና የህብረተሰብ ክፍሎች ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ለአቶ ለማ መገርሳ አስረክበዋል።
ኬኬ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል የግል ኩባንያ በተወካያቸው በኩል 15 ሚሊየን ብር ለርእሰ መስተዳደሩ ያስረከበ ሲሆን፥ ኢስተርን ኢንደስትሪያል ዞን ደግሞ የ14 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።
እንዲሁም የድሬደዋ ከተማ ነዋሪዎች የ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር፤ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተማሪዎች የ100 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።