Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዲፕሎማሲ ልዕልናችን

0 340

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዲፕሎማሲ ልዕልናችን

ገናናው በቀለ

በቅርቡ ሱዳንና ግብጽ በተናጠል ያደረጉት የሁለትዮሽ ግንኙነት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ባለው የሶስትዮሽ ግንኙነት አንዳችም ለውጥ ያልታየበት ነው። ይልቁንም ሁለቱ አገራት ተገናኝተው በመካከላቸው የተፈጠሩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እንዲመካከሩ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና ተጫውታለች።

ሁለቱ አገራት ከስብሰባቸው በኋላ ያወጡዋቸው መግለጫዎች ኢትዮጵያን የሚጎዱ አይደሉም። ሊሆኑም አይችሉም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ዛሬም የበላይነቱን ይዞ የቀጠለ ስለሆነ ነው። ይሀም የዲፕሎማሲ የበላይነታችን በግድቡ ግንባታም እየተጠናከረ መምጣቱንም የሚያሳይ ነው።

አገራችን ከህዳሴው ግድብ አኳያ እያከናወነችው ያለችው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ዛሬ ላይ የታችኛዎቹን የተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብፅንና ሱዳንን በጊዜ ሂደት አሁን ለያዙት አቋም አብቅቷቸዋል። በእኔ እምነት ይህ የዲፕሎማሲ ጥረት የትናንት ገፅታችንን ከመቀየር ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ምክንያቱም ባለፉት ስርዓቶች ሀገሪቱን ጨምድዶ ይዞ የነበረው የከፋ ድህነትና እነዚያ መንግስታት የነበራቸው የአስተሳሰብ ውስንነት ዛሬ ላይ በመሰበሩ ነው።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በህዝብ ተሳትፎና በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ራዕይን ሰንቆ ላለፉት 27 ዓመታት ገደማ ተጉዟል።

በሂደቱም የህዝቡን ልማታዊ ተጠቃሚነት በየደረጃው የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ለውጤት መብቃት ችሏል። በዚህም ህዝቡን ከጫፍ እሰከ ጨጠጫፍ በማንቀሳቀስ ሀገራችን የያዘቻቸውን ፕሮጀክቶች በራሳችን አቅም መገንባት የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

በዚህም የዘመናት ቁጭታችን የሆነውን በተፈጥራዊው የውኃ ሀብታችን የመጠቀም መብታችንን በበቂ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ታጅቦ በማረጋገጥ ላይ ይገኛል። ይህም ሀገራችን ትናንት የነበራትን የአቅም ውስንነት የቀረፈና የተለየ የአስተሳሰብ ዘውግ በመፍጠርም የታችኛውን የተፋሰስ ሀገራት በአመዛኙ ወደ እኛ እሳቤ ማቅረብ የቻለ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም።

እርግጥም ኢትዮጵያ ላለፉት 16 ተከታታይ ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት እያስመዘገበች በመሆኑ፤ በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ በመጠቀም መብቷ በማትደራደርበት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተጠናከረ የመጣው የህዝቧ የልማት ቁርጠኝነት እንዲሁም መንግስት የሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ዘላቂና ከባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆን ችለዋል፡፡ ይህ ተግባሯም ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ ውጭ አሮጌና ዘመን ያለፈባቸው አስተሳሰቦች ዋጋ ቢስ እንዲሆኑ ያደረገና ግብፆች አሁን ለደረሱበት የአቋም ለውጥ (መወላወል የሚታይበት ቢሆንም) መሰረት የጣለ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ አሮጌው የቅኝ ገዥዎች ስምምነት የተፋሰሱ ሀገራትን በውሃው እኩል ተጠቃሚነት እንዲሆኑ በሚያደርገው የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ መተካት ለአማራጭና ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች ስትገልፅ ቆይታለች፡፡

እርግጥ ሀገራችን የኢንቴቤውን ስምምነት ስትቀበል በምክንያታዊነት ላይ ተመስርታ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ደረጃ የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት የሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት መብት የሚያስጠበቅና እኩል ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ እንጂ፤ ልክ እንደ ቅኝ ገዥዎቹ ስምምነት በጣት ለሚቆጠሩ ሀገሮች መብት የቆመ አለመሆኑን ስለምትገነዘብ ነው።

በዚህ የግንዛቤ መነሻዋም የተፋሰሱ ሀገራት የኢንቴቤውን ስምምነት እንዲፈርሙ ለዓመታት ያላሰለሰ ጥረቶችን አድርጋለች። ይህ ጥረቷም ቀደም ሲል ስምምነቱን ላለመቀበል ስታንገራግር የነበረችውን ግብፅን በጉዳዩ ላይ ወጣ ገባ የሚል አቋም እንድትይዝ ጭምር አድርጓል። ይህም አገራችን በግድቡ ዙሪያ በፊትም ይሁን አሁን የያዘችው አቋም ፍትሐዊና ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

የአገራችን ፍትሐዊ አስተሳሰብ አንዱን ለመጉዳትና ሌላውን ለመጥቀም ከማሰብ የመነጨ አይደለም። ይልቁንም ከዕድገታችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የሀገራችን የዕድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግርን የሚቀርፉ ጥቂት የማይባሉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን በተሳካ ሁኔታ መገንባት ተችሏል። ጥረቱን አጠናክሮ በመቀጠልም በአባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ነው።

በታላቁ መሪያችን በአቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት መሰረቱ የተጣለው ይህ ግድብ፤ አሁን ያለውን የሀገራችንን የሃይል አቅርቦት ከሶስት እጥፍ በላይ የሚያሳድግ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ የወጡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ ግድቡ በሙሉ አቅሙ ስድስት ሺህ 450 ሜጋ ዋት ማመንጨት ሲጀምር ለበርካታ ዓመታት ያህል በቀን ሁለት ሚሊዮን ዮሮ ለሀገራችን ማስገኘት ይችላል። ይህም ህዝቡ በታሪካዊነቱ ያስቀመጠው ሁለንተናዊ አሻራ ተመልሶ የታሪካዊ ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችለዋል።

ምንም እንኳን ትናንት ሐብትን በጋራና በፍትሐዊ ሁኔታ የመጠቀም መርህን ተከትላ የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ላይ የምትገኘው ሀገራችን፤ ዛሬም ከዚህ መርህዋ ዝንፍ የምትል አይሆንም። ግድቡም ወንድም የሆነውን የግብፅ ህዝብ እንደማይጎዳ፣ ይልቁንም ከግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚሆን በፅናት ታምናለች።

ይህ እምነቷ ከምንም ተነስቶ የሚባል አይደለም—መሬት ላይ ያለውን የግድቡን ግንባታ መሰረት ያደረገ እንጂ። ከዚህ በመነሳትም እምነቷንና የትኛውንም ወገን ያለመጉዳት መርህዋን በተለያዩ ወቅቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች አስረድታለች። በሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረቷም ግንዛቤም ማስያዝ ችላለች።

እናም የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የዲፕሎማሲ ጥረት አጠናክሮ በመቀጠሉ ቀደም ሲል ጎረቤት ሱዳን፣ አሁን ደግሞ ወንድሞቻችን ግብፆች እውነታውን እየተረዱ መምጣት የቻሉ ይመስላል—አንዳንዴ በቅኝ ግዛት ውል እንተዳደር የሚል ሃሳብ ቢያነሱም። ይህ ሁኔታም የሱዳንና የግብፅ መንግስት አሁን የያዙትን አቋም እንዲይዙ ማድረግ የቻለ ይመስለኛል። ይህ በጎ መንገድ እንዲበረታታም የግብፅን መንግስት ኦፊሴላዊ መግለጫን ከዚያች ሀገር ሚዲያዎች ለይቶ መመልከት ያስፈልጋል። እግር በእግሩም እስካሁን እየተደረገ እንዳለውና ፍሬ እያፈራ እንደሚገኘው ዓይነት የዲፕሎማሲ ጥረቶች መጠናከር አለባቸው።

ለዚህም በአንድ በኩል፣ የሀገራችንን መቼም የማይቀየር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ዕውን የሚያደርግና ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት አካሄድ በዘመነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ማሳየት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከህዳሴው ግድብ አኳያ ሶስቱም ሀገራት የሄዱበት በሰከነ መንገድ የመደማመጥ መንፈስ እንዲጠናከር ተገቢውን ጥረት ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

ከዚህ ውጭ በግድቡ ዙሪያ ግብፅም ይሁን ሱዳን በሁለትዮሽ መንገድ የሚፈፅሙት ነገር የለም—ጉዳዩ የሶስትዮሽ ስለሆነ። ውሃውን ስለ መሙላት ጉዳይ ከሆነም ጉዳዩ ግልፅነትን ለመፍጠር ካልሆነ በስተቀር ዋነኛዋ ባለመብቷ ሀገራችን ናት። እናም የሁለቱ መሪዎች በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያደረጉት ውይይት ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማያመጣ መገንዘቡ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ተሰሚነትን ያተረፈው የአገራችን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለእንዲህ ዓይነቱ ተግባር ክፍተት የሚተው አይደለምና።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy