Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጋራ አመለካከትንና ተግባርን ለመፍጠር…

0 713

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጋራ አመለካከትንና ተግባርን ለመፍጠር…

                                                       ሶሪ ገመዳ

በአገራችን ውስጥ መጠየቅም፣ መተቸትም፣ መተራረምም ሊኖር የሚችለው በወሳኝነት ከህዝቡ ሲመጣ ነው። መንግሥትና ሕዝብ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መምከራቸው ዘላቂ ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ለማስፈን ወሣኝ የሆነውን የጋራ አመለካከትና ተግባር ለመፍጠር ያስችላል። በተለይ አመራሩ ወደ ህዝብ በተጠጋ ቁጥር ይበልጥ እየፀዳ እንዲሄድ ያደርገዋል። በተዛባ የሥልጣን አተያይ የግል ጥቅሙን ሲያሳድድ የነበረ አመራር የሚታረመውና የሚታነጸው ከህዝብ ጋር ሲቀላቀል መሆኑ ግልፅ ነው። እናም ህዝቡ የፖለቲካው ወሳኝ ሃይል መሆኑን መገንዘብ ያሻል።

በአገራችን ህግ መንግስት ላይ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸውንና ሉዓላዊነታቸው የሚገለፀውም በህገ-መንግስቱ መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካኝነት እንደሚሆን ደንግጓል።

ይህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ በግልፅ እንደሚያሳየው ማንኛውም የፖለቲካ ስልጣን የሚያዘው የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት በሆነው ህዝብ ይሁንታ ብቻ መሆኑን ነው። ህዝቡ ሲፈልግ ይሾማል፤ ሳይፈልግ ደግሞ ይሽራል። ይህን መብት ለህዝቦች የሰጡት ራሳቸው ህዝቦች ናቸው። ሌላ የትኛውም ወገን አይደለም። እናም የመንግስት ማናቸውም ተግባራት ከዚህ አኳያ የሚመዘኑ ይሆናሉ።

እርግጥ በህገ-መንግስቱ የተለያዩ አንቀፆች ላይ የተቀመጡት ሁሉም መብቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በትግላቸው የተጎናፀፏቸው ትሩፋቶች ናቸው። እነዚህን ህገ መንግስቱ ያረጋገጠላቸውን መብቶች ተጠቅመውም የበርካታ ትሩፋቶች ባለቤቶች ሆነዋል።

ዛሬ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ለውጥ ባለቤቶችና ለሌሎች አፍሪካውያን አርአያ የሚሆን ዕድገት በሁሉም መስኮች እያስመዘገቡ ነው። በዚህም የህዳሴያቸውን ጉዞ ቅርብ ለማድረግ ግስጋሴያቸውን ተያይዘውታል።

ሆኖም በዚህ ሂደት ውስጥ የመንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት ይበልጥ መስፈን ይኖርበታል። የመንግስት አሰራሮች ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው መንፈስ እውን መሆን አለበት። ይህ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሀገሪቱ ህዝቦች መንገስት እንደያከናውነው የሚፈልጉት ጉዳይ ነው።

እናም መንግስት ሁሌም በአሰራሮቹ ላይ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን የህዝቦችን ህገ መንግስታዊ ፍላጎት እውን ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህም በመሆኑ በየጊዜው ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የየወራት ስራዎቹን ያቀርባል። ያስገመግማል። መጠንከርና መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዩች ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶችንም ይቀበላል።

የመንግስት የተጠያቂነት አሰራር የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ ነው። በዴሞክራሲ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ አስተሳሰብ፣ በጊዜ ሂደት ለምርጫ የሚሰጠው ትርጉም የሚያድግና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም እየሰፋ የሚመጣ ብሎም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ እየጎለበተ የሚሄድበት አውድ ነው። ይህ ተጨባጭ ሁኔታም በጅምር ላይ ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ረዥም ዕድሜን ያስቆጠረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በምንም መልኩ አንድ ሊሆን እንደማይችሉ የሚያመላክት ነው።

እናም የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስንመለከተው ሂደቱ 26 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ጅምር በመሆኑ ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች የሉበትም ለማለት የሚያስደፍር አይመስለኝም። አሁን የምንገኝበት ደረጃ የህዝብ አስተሳሰብ አድጓል፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርም በሚፈለገው መጠን ሰፍቷል ለማለት አይቻልም።

እናም ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው መንግስት የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሆነውን ዴሞክራሲ በጥልቀት ማስፋትና ማጎልበት ይጠበቅበታል። የአሰራሩን ተጠያቂነትና ግልፅነት በዚያኑ ልክ ለህዝቡ ማረጋገጥ አለበት።

ዴሞክራሲ ሲጎለብት ይበልጥ አሳታፊ፣ ግልፅነት የተሞላበትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ ሊያሳትፍ የሚችል ይሆናል። ይሁንና አንዳንድ ፅንፈኛ ሃይሎች መንግስት ዴሞክራሲን ለማስፋት ፍላጎት የሌለው አድርገው ሊስሉት ሲሞክሩ ይታያል። ይህ ስህተት ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ገዥው ፓርቲ ከአምባገነኑ የደርግ ስርዓት ጋር ያደረገው መራርና እልህ አስጨራሽ ትግል የነበረው አንዱ ጉዳይ የዴሞክራሲ እጦት ነው። ደርግን አስወግዶ ስልጣን ከያዘም በኋላ ቢሆን፣ ይህን የህዝቦችን ጥያቄ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን ጥረት አድርጓል።

ገዥው ፓርቲ ገና ከስልጣን መባቻው ወቅት ጀምሮ የታጠቁና ወደ 17 የሚጠጉ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማወያየትና በማከራከር ባህሉ የሚታወቅ ነው። ይህም ዴሞክራሲን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማስቻል ክርክርና ድርድር ማድረግ ለገዥው ፓርቲ አዲስ ጉዳይ አለመሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።

እዚህ ሀገር ውስጥ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ለማሳለጥ የሚከናወኑ ማናቸውም ሁነቶች ማንንም ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ሳይሆን የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የታገሉላቸውን መብቶች በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆመ ታስቦ የሚከናወን ተግባር መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

ስለሆነም  በገዥው ፓርቲም ይሁን በመንግስት በኩል የሚከናወኑ ጉዳዩች ሁሉ ለሀገርና ለህዝብ ጠቀሜታ ሲባል እንጂ፣ ለታይታ አሊያም ለሌላ ጉዳይ የሚከናወኑ አይደሉም፤ ሊሆኑም አይችሉም።

ያም ሆኖ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችን መጠናከርና ማበብ ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች መኖር አለባቸው። መንግስት በሀገሪቱ ዴሞክራሲን የሚያጠናክሩ ፖርቲዎች መኖር አለባቸው። ተደጋግሞ እንደሚነገረውም የመንግስት ፍላጐት የሀገራችን የመድብለ ፖርቲ ስርዓት ዳብሮ እና ጐልብቶ ማየት ነው።

የአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ጤናማነቱ ተጠብቆ ሊጓዝ የሚችለው ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተሳትፎ እየጐለበተ ሲመጣ ነው። በመሆኑም በተለይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን በማብቃትና ከጅምላዊ አካሄድ በመታቀብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ማበብ ሀገራዊ ግዴታ ያለባቸው ይመስለኛል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቡ እንዲያስተዳድሩት የሚፈልጋቸውን ይመርጣል እንጂ፣ እንዳለፉት ስርዓቶች የሚያስተዳድሩት ራሳቸውን መርጠው አሊያም በገዥ ፓርቲ ተመርጠው የሚሄዱበት አሰራር ዶሴው ተዘግቷል። በውጭ አገር በተደላደለ ኑሮ የሚኖሩ ፅንፈኞች ግን ይህን የተዘጋ ዶሴ ከ27 ዓመት በኋላ አዋራውን አራግፈው ሊጠቀሙበት የፈለጉ ይመስላል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ምህዳር ግን ይህን ዶሴ የሚያስተናግድበት ቦታ የለውም። እናም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አንድ አመራር ወደ ህዝብ የሚቀርበው ወሳኙ ሃይል ህዝብ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው። የጋራ አመለካከትንና ተግባርን ለመፍጠር ጠቃሚ መሆኑንም ስለሚያምን ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy