Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዶ/ር አብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ተሰየሙ

0 691

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዶ/ር አብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ተሰየሙ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 3ኛ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ዶ/ር አብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አድርጎ ሰይሟል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀገሪቱ በተከሰተው የፀጥታ ችግር የመፍትሄ አካል በመሆን ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ለለቀቁት የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ያላቸውን አክብሮት በመግለጽ ንግግራቸውን ጀምረዋል፡፡

ይህ የስልጣን ሽግግር በሀገሪቱ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ታሪካዊ ክስተት መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አብይ የህዝብም ፍላጎት የተንፀባረቀበት ነው ብለዋል፡፡

የሃሳብ ልዩነት አለመግባባትን የሚፈጥር ሳይሆን በመርህ ላይ በመመስረት መግባባት ላይ ሲደረስ የተሻለ ውጤትን ይዞ ይመጣል ነው ያሉት፡፡

ዲሞክራሲ ከመንግስት ለህዝብ የሚበረከት ስጦታ ሳይሆን ከሰብዓዊ ክብር የሚመነጭ እንደመሆኑ መጠን ህገ መንግስቱን በአግባቡ መተግበርም እንደ አንድ መፍትሄ ይቆጠራል ብለዋል፡፡

ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፤ የመሰባሰብና የመደራጀት መብቶች በህገ መንግስቱ መሰረት ሊከበሩ እንደሚገባ እና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ተናግረዋል፡፡

የራስን ዲሞክራሲያዊ መብት ለመጠየቅ የሌሎችን መብት መጋፋት ሳይሆን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄን ማቅረብ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በሃገራችን ዲሞክራሲ እንዲያብብ፤ ነጻነትና ፍትህ እንዲሰፍን፤ የህግ የበላይነት እውን እንዲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ለረጅም ጊዜያት ከኤርትራ መንግስት ጋር የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት እና ሁለቱም ሃገራት የጋራ ጥቅሞቻቸውን እንዲያስከብሩና የሁለቱ ህዘቦች ግንኙነት መልሶ እንዲጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም እንዲይይዝም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሙስናና ብልሹ አሰራር ከሀገሪቱ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ሁሉም የሀገሪቱ ህዝብ የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

ሙስናን ለማጥፋት ጸረ ሙስና ተቋም ማቋቋም ሳይሆን ህብረተሰቡ በሙስና ላይ ያለውን አስተሳሰብና አመለካከት መቀየር ላይ ሊሰራ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በሁሉም ዘርፍ የተሳካ ውጤት ቢያስመዘግብም የወጪ ንግድ በሚፈለገው መጠን አለማደግ፤ የዋጋ ንረትና ኑሮ ውድነት፤ የውጭ እዳ ጫና፤ በግብርናው ዘርፍ በዘመናዊ ቴከኖሎጂ አለመደገፍ እና የመሳሰሉት ፈተና መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት ትምህርት እንደ አንድ የመፍትሄ ቁልፍ ቢሆንም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከመንግስት የበለጠ ስራ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

የወጣቱ ጥያቄ የኢኮኖሚና የእኩል ተጠቃሚነት ብቻ ሳይሆን የዲሞክራሲና የፍትህ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ የወጣቶች ጥያቄ በአግባቡ ባለመስተናገዳቸው ህዝቡን ለብሶት ዳርገዋል፤ በመሆኑም ያለወጣቶች ተሳትፎ የታለመውን እድገት ማሳካት እንደማይቻል ነው አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ወደፊት የወጣቶችን የስራ እድል ፈጠራ ላይ ጠንክሮ በመስራት ለለውጥ መዘጋጅ አግባብነት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ተናግረዋል፡፡

መንግስት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገት ጥረት ቢያደርግም አሁንም ቢሆን እጅግ በርካታ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡

ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሃገሪቱ የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት እንዲችሉ ለማድረግ መንግስት አብሮ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ለሃገሪቱ ችግሮች የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርቡ እና ከመንግስት ጋር በጥምረት እንዲወጡ እድል ሊሰጣቸው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ወደ ሃገራቸው ተመልሰው በልማት ስራ ላይ እንዲደማሩ ለማድረግ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠትም ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ለጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ እምነት ሰጥተዋቸው ለዚህ ክብር ላበቋቸው የኢህአዴግ ድርጅትን አመስግነው በህይወት ለተለዩዋቸው እህናታቸውን ጨምሮ ለቤተሰቦቻቸው ብሎም ለመላው ህዝብ ያላቸውን ክብርና ምስጋና አስተላልፈዋል፡፡

ሪፖርተር፦ ሰለሞን አብርሃ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy