Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ጋን በጠጠር ይደገፋል”

0 493

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ጋን በጠጠር ይደገፋል”

                                                                ዘአማን በላይ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን በተለያዩ መድረኮች ውሰጥ ከገለጿቸው በርካታ ጉዳዩች ውስጥ አንዱ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትምህርት ጥራትን በማጠናከር ውጤት ማምጣት እንደሚገባ ገልፀዋል። ሃሳቡ ትክክል ብቻ ሳይሆን በፍጥነት መስተካከል ያለበት ጉዳይም ነው። ምክንያቱም ያለ ትምህርት ልማትን ይበልጥ ማረጋገጥ ስለማይቻል ነው። ትምህርት ዜጎች ሀገራቸውን የሚገነቡበት አንድ መሳሪያ በመሆኑ ጥራቱን ማስጠበቅ ለነገ የሚተው ጉዳይ አይደለም። የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል።

እንደሚታወቀው በሀገራችን በተለያዩ ደረጃዎች በሚካሄዱ የልማት ስራዎች ውስጥ የእውቀት ድጋፎችንም የሚሻ ነበር። የዚህ ችግር ዋነኛው መንስኤ ደግሞ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሀገራችን ውስጥ ልማታዊ አስተሳሰብ ያለው፣ በእውቀትና ክህሎት የታነፀ በቂ የሰው ሃይል ሊፈራ አለመቻሉ እንደሆነ አያከራክርም። በልማቱ መስክ ላይ ተሰማርቶ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት የሚችል የሰለጠነ የሰው ሃይል በጥራትና በበቂ ሁኔታ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ችግር ይፈጥር እንደ ነበር ግልፅ ነው።

ርግጥ ነው ዛሬ ትምህርት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዘልቆ ገብቷል። በከተሞችም እንዲሁ ተስፋፍቷል። እድሜው ለትምህርት የደረሰ ህጻን ሁሉ የማዕዱ ተቋዳሽ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በአገሪቱ ያለው የትምህርት ሽፋንም ሰፍቷል፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት በሙሉ የሚታደሙበት ማዕድ ሆኗል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በገጠር ቀበሌዎች ሳይቀር ተስፋፍተዋል፡፡

ይህም ዛሬ ከሶስቱ ኢትዮጵያዊ አንዱ በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የትምህርትን አስፈላጊነት ከማስተማር ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር  በትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ህፃናት የምግብ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡

የወጣቱን የትምህርት እድል ለማስፋት የግል የትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ ተደርጓል። ይህ አገሪቱ ለልማት የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የጎላ ሚና አላቸው፡፡ እንዳልኩት የተማረና ብቃት ያለው ባለሙያ በሌለበት አገር ዘላቂ ልማት የሚታሰብ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ያሳየችው ውጤትም አገሪቱ እያስመዘገበች ላለው የምጣኔ ሃብት እድገት መሠረት ነው፡፡ በዚህም አገራችን የሚሊየሙን የልማት ግብ ከማሳካት ባሻገር፤ ለጥራት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው፡፡  ዛሬ በውጭ ባለሙያዎች የሚከናወንስራ በእጅጉ እየቀነሰ ነው። በልማቱ ስራ ላይ በወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ የውጭ ሙያተኞች ዕውቀት ጥገኛ ለመሆን የተገደድነውም በዚሁ ሳቢያ እንጂ፤ ሀገሪቱ ከዓለም ገበያ ዕውቀት ለመግዛት የምታፈሰው የገንዘብ አቅም ስለነበራት አልነበረም።

ያ ሁሉ አልፎ በአገራችን ባለፉት 27 ዓመታት ከተሰሩት ተግባራት አንዱ በአገሪቱ ፍትሃዊ የትምህርት ስርጭት እንዲኖር መደረጉ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክልል በርካታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች ተቋቁመው የትምህርት አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

በአገሪቱ የነበሩት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ታድሰዋል፣ የማስፋፊያ ግንባታም ተደርጎላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በልዩ ትኩረት እንዲስፋፉ በመደረጉ የተቋማቱ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል፡፡ ይህ የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ከማፍራት ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው ባለፉት 27 ዓመታት በተግባር ታይቷል፡፡ ተማሪዎች ስራ ፈጣሪ እንጂ ክፍት ስራ ፈላጊ እንዳይሆኑ በማድረግ ረገድም ውጤታማ ተግባር ተፈፅመዋል፡፡ ሆኖም በቂ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ አሁንም ብዙ መስራት ይጠይቃል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም እንዲሁ ተስፋፍተዋል። ተቋማቱ በአንድ በኩል አገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ያፈራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናቶችንና ምርምሮችን ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ጥናቶችና ምርምሮች ምን ያህል ወደ መሬት ወርደው እየተተገበሩ ናቸው የሚለውን ጉዳይም መፈተኝ ይገባል፡፡ አሊያ የሼልፍ ሲሳይ ነው የሚሆኑት፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ለረጅም ጊዜያት ከእህልና ገንዘብ ባልተናነሰ መልኩ የእውቀት ጥገኛ ሆነን የተጓዝንበት ምዕራፍ መፍትሄ ሳይበጅለት አልቀጠለም። ሀገራችን ውስጥ ዕውን በሆነው ልማታዊና ዴሞክራሲ መንግስት አማካኝነት ይህ ምዕራፍ ተዘግቶ ወደ አዲስ አስተሳሰብና የዕውቀት ሽግግር ለመጓዛችን በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል።

መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማሳደግም በትምህርት አመራር፣ በመምህራን ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል፣ በት/ቤቶች ማሻሻል እና በአይሲቲ ዙሪያ ሰፋፊ ተግባራት መከናወን ቢችሉም፤ እነዚህን ማሻሻያዎች አጠናክሮ በመተግበር እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት መሻሻል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ ይበልጥ መስራትን ይጠይቃል። በትምህርት ጥራቱ መሻሻሎች ቢኖሩትም አሁንም ፈተና መሆኑን መካድ አይገባም።

ከትምህርት ጥራት አኳያ እየታየ ያለውን ጅምር መሻሻል ይበልጥ ማጎልበት ይገባል። ለዚህም ትምህርት ሚኒስቴርና በየደረጃው የሚገኙ የመስኩ ተቋማት የወጣውን የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ኘሮግራም በተገቢው ሁኔታና በፅናት መተግበር የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል።

የትምህርት ጥራትን ለማሳደግም በትምህርት አመራር፣ በመምህራን ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል፣ በት/ቤቶች ማሻሻል እና በአይሲቲ ዙሪያ ሰፋፊ ተግባራት መከናወን ቢችሉም፤ እነዚህን ማሻሻያዎች አጠናክሮ በመተግበር እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት መሻሻል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ ይበልጥ መስራትን ይጠይቃል።

ዶክተር አብይ በትምህርት ጥራት ላይ መሻሻል እናመጣለን ያሉት መንግስት ብቻውን ይወጣዋል ከማለት ስሜት አይደለም። ሁሉም ዜጋ ለጥራቱ መሻሻል የበኩሉን እገዛ ማድረግ አለበት። በመሆኑም መምህራን፣ ተማሪዎችና መላው የመማር ማስተማሩ ማህበረሰብ ለትምህርት ጥራት ስራው መትጋት ይኖርባቸዋል።

ለብቻ ሮጦ አሸናፊም ተሸናፊም አይኖርም። ሁሉንም ነገሮች መንግስት እንዲሰራ መጠበቅ ተገቢ አይደለም። በህዝብና በሚመለከታቸው አካላት ያልተደገፉ ስራዎች ወደ መሬት ሊወርዱ አይችሉም። ሎሚዎቹን ሁላችንም ተከፋፍለን ልንይዛቸው ይገባል። ለአንድ ሰው ብቻ መተው እየተንጠባጠቡ ሊቀሩ አሊያም የተፈለጉበት ቦታ ሳይደርሱ ሊወሰዱ ይችላሉ። ጌጣችን ልማታችንና ሀዳሴያችን ነው። እናም “ጋን በጠጠር ይደገፋል” እንደሚባለው ሁሉም ዜጋ በትምህርት ጥራት ላይ የበኩሉን ጠጠር መወርወር ይኖርበታል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy