Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሃገሩን ለባለሃገሩ

0 299

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሃገሩን ለባለሃገሩ

ኢብሳ ነመራ

የአሜሪካ መንግስት ጎንግሬስ በቅርቡ ኢትዮጵያን የተመለከተ የምክር ቤት ውሳኔ/House resolution 128  ወይም H.R 128 የተሰኘ የውሳኔ ሃሳብ ማጽደቁ ይታወሳል። ይህ የውሳኔ ሃሳብ በአሜሪካ በሚኖሩ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች፣  እንዲሁም በኤርትራ በመሸጉና በኤርትራ መንግስት ድጋፍ የኤፌዴሪን የመንግስት ስርአት በሃይል ለመናድ በሚንከራተቱ ቡድኖች አነሳሽነት በተወሰኑ የአሜሪካ ኮንግሬስ አባላት ተጽፎ የቀረበ ነው። ይህ የውሳኔ ሃሳብ የተወሰኑ የኮንግሬሱ አባላት እይታ ወይም ፍላጎት የተንጸባረቀበት ነው። የአሜሪካ መንግስትን አቋም አያንጸባርቅም። የተፈጻሚነት ጉልበትም የለውም። በአጭሩ የተወሰኑ የኮንግሬስ አባላት ያወጡት የአቋም መግለጫ ተደርጎ የሚወሰድ ሰነድ ነው።

ይሁን እንጂ፣ ሰነዱን እንደባዶ የወረቀት ጥራዝ ንቆ መተው አጉል የዋህነት ነው። ሰነዱ የሚናገረው ነገር አለ፤ እውነትም አለው። የሚያመለክተውም ነገር አለ፤ የአሜሪካ መንግስት የኮንግሬስ አባላት ገንዘብ ከተከፈላቸው በሎቢ ስም፣ ፈትሸው ባላረጋገጡት መረጃ የሃገራት ሉዓላዊነት ውስጥ ገብተው ህግ እስከመቀየርና መሰረዝ የሚደርስ ጥያቄ ለማንሳት አቋም የሚይዙ መሆናቸውን ያመለክታል።

ኤች አር 128 በኢትዮጵያ መንግስት ተፈጸመ ያላቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይዘረዝራል። ይሁን እንጂ ሰነዱን ያጸደቀው የአሜሪካ ኮንግሬስ አባላት እነዚህን መረጃዎች በራሳቸው ወይም በገለልተኛ አካል አጣርተው ትክክለኛነታቸውን አላረጋገጡም። ለማረጋገጥም አልሞከሩም። መረጃዎቹን የሰበሰቡት ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በአብዛኛው እዛው አሜሪካ ከሚኖሩና ኢትዮጵያ በአካል ተገኝተው ከማያውቁ ቡድኖችና ግለሰቦች ነው። እነዚህ ቡድኖችና ግለሰቦች አብዛኞቹ የኢፌዴሪን ስርአት በሃይል ለመቀየር የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ጠመንጃ ታጥቀው የኤርትራ በረሃ የሸፈቱም አሉበት።

ከተዘረዘሩት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ ትክክለኝነት ያላቸው መኖራቸው ባይካድም፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለማነሳሳት ያለወጉ የተጋነኑና የእውነታውን ከፊል ገጽታ ብቻ የሚያሳዩ ናቸው። የአሉባልታ መረጃዎቹን እንደወረደ ተቀብሎ ያጸደቃቸው ኮንግሬስ ምንም አይነት ማጣራት ያላደረገባቸው መሆኑ፣ መረጃዎቹ በተወሰነ ደረጃ ትክክል ቢሆኑ እንኳን ዋጋቸውን ያረክሰዋል።

በዚህ ኤች አር 128 የተሰኘ የተወሰኑ የአሜሪካ ኮንግሬስ አባላት የአቋም መግለጫ ከሆነው ሰነድ ላይ የሃገሪቱን ጉዳይ ለባለሃገሮቹ ቢተዉት መልካም ነው የሚያሰኙ የተወሰኑ ጉዳዮችን ለመመልከት ወድጃለሁ። በቅድሚያ ግን ሰነዱን ያዘጋጁና እጃቸውን አውጥተው ያጸደቁትን የኮንግሬስ አባላትን በእጅጉ እንድታዘብ ያደረጉኝን አንድ ሁለት ጉዳዮች ማንሳት እፈልጋለሁ። ይህም በአሜሪካ የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችንና የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸውን በሚመለከት ያላቸውን አቋም መነሻ ያደረገ ነው።

አሜሪካውያን ዜግነት ያላቸው ሰዎች ያለአሜሪካ መንግስት ውሳኔ መሳሪያ ታጥቀው በሉዓላዊ ሃገር ላይ የሃይል ጥቃት መሰንዘር እንደማይችሉ የሃገሪቱ ህግ ያዛል። አንድ አሜሪካዊ መሳሪያ ታጥቆ ሉዓላዊ ሃገር ላይ የሚዘመተው የአሜሪካ መንግስት ሲያውጅ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ በርካታ አሜሪካውያን (በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ) በይፋ በአሜሪካ ከተሞች ሆቴሎች እየተሰበሰቡ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሲያውጁ፣ ለጦር መሳሪያ መግዣ ገንዘብ ሲያሰባስቡ፣ ከአሜሪካ ተነስተው በይፋ ኤርትራ ውስጥ መሽገው  ኢትዮጵያ ላይ የጦርነትና የሽብር ጥቃት ሲሰነዝሩ አንድም የአሜሪካ ኮንግሬስ አባል ይህ ድርጊት የአሜሪካን ህግ የሚተላለፍ ነው ብሎ አላወገዘም።

እነዚህ አሜሪካውያን (ትውልደ ኢትዮጵያውያን) ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ለማዳከም በሚል እቅድ፣ በዚያ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያን ሃገር ቤት ለሚገኙት ዘመዶቻቸው የሚልኩት ገንዘብ በውጭ ምንዛሪነት መንግስት እጅ እንዳይገባ ለማድረግ፣ ከህጋዊ የገንዘብ ዝውውር ስርአት ውጭ በህገወጥ መንገድ እንዲልኩ በይፋ ሲያውጁ አንድም የአሜሪካ ኮንግሬስ አባል ይህን በአሜሪካ ህግ የተከለከለ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር አልተቃወመም። በህገወጥ መንገድ የሚዘዋወር ገንዘብ በአብዛኛው ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች እጅ እንደሚገባ እየታወቀ፣ አሜሪካ የምትዋጋቸው አይ ኤስን እና አልቃይዳን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች የገንዘብ ምንጭ ሊሆን የሚችለውን በይፋ የሚታወጅ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር አለመቃወማቸው እጅግ አስገራሚ፣ አሳዛኝም ነው።

ምንም ምርመራ የማያስፈልገውን አይናቸው ስር በይፋ የሚፈጸም አደገኛ ወንጀል ማየት ያልቻሉት የኮንግሬስሰ አባላት፣ እነዚሁ ወንጀለኞች ገንዘብ ከፍለው ኢትዮጵያን እንዲያወግዙ ሲጠይቋቸው ግን፣ ብእራቸውን አሹለው በራሳቸው መንገድ ትክክለኛነቱን ያላረጋገጡትን የአሉባልታ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመቸክቸክ በርትተዋል። ድንቄም የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ።

ያም ሆነ ይህ፣ ኤች አር 128 የተባለው ሰነድ ጸድቋል። ቀደም ሲል እንደተገለጸው በዚህ የአቋም መግለጫ ሰነድ ላይ የሰፈሩት በኢትዮጵያ መንግስት ተፈጸሙ የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመው ሊሆን ይችላል። ሰነዱ መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጽም ለመቀስቀስ በቅንነት የቀረበ ከሆነ በበጎነት ሊወሰድ ይችል ይሆናል። ሆኖም ባለፉ ዓመታት በሃገሪቱ ስር በሰደደው የመልካም አስተዳደር መጓደልና የህዝብ ሃብት ዘረፋ ሳቢያ የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ መንግስት ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ በማበጀት ዙሪያ፣  በሰብአዊ መብት አያያዝና ዴሞክራሲን በማጎልበት ዙሪያ ተጨባጭ እርምጃዎች እየወሰደ ነው። እናም ከዚህ አኳያ ሲታይ የአቋም መግለጫው የረፈደበት ነው።

በእስር ላይ የነበሩ ፖለቲከኞች ክሳቸው ተቋርጦና በይቅርታ እንዲለቀቁ መደረጉ፤ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየትና ለመደራደር የቀረበው ጥሪ፤ መጪውን ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ለማደረግ መንግስት የገባው ቃልና ለተግባራዊነቱ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት፤ እነዚህን መፍትሄዎች እውን ለማደረግ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ዳሳለኝ የመፍትሄው አካል ለመሆን በሚል ስልጣናቸውን በፍቃዳቸው መልቀቃቸውና አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሰየሙ ወዘተ ከተወሰዱት እርምጃዎች መሃከል ተጠቃሾቹ ናቸው። በሃገሪቱ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ይህ ሆኖ ሳለ፣ አጠቃላይ አካሄዱን ማጤንና ማበረታታት ከወዳጅ የሚጠበቅ መሆኑ ሳይዘነጋ፣ የአሜሪካ ኮንግሬስ ይህን ተስፋ ሰጪ እርምጃ እየወሰደ ያለውን መንግስት የሚያሳጣ ሰነድ ማጽደቁን በቅንነት መመልከት ይከብዳል።

ኤች አር 128 የተባለው የተወሰኑ የአሜሪካ ኮንግሬስ አባላት የአቋም መግለጫ ሰነድ መሰረዝና መሻሻል አለባቸው ያላቸውን ህጎችም ይዘረዝራል። በመሰረቱ ህግ ማውጣትም፤ ማሻሻልም በአብላጫ የህዝብ ድምጽ አሸናፊ በሆኑ አባላት የተዋቀረው፣ በህገመንግስቱ መሰረት ከፍተኛ የሃገሪቱ የስልጣን አካል የሆነው የህግ አውጪው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን ነው። ምክር ቤቱ ህግ የሚሰርዘው፣ የሚያሻሽለው ወይም የሚያጸድቀው የውጭ አካላትን ፍላጎት፣ ጥቅምና ጥያቄ እያሰበ ሳይሆን የኢትዮጵያውያንን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን ማመጎልበት ታሳቢ በማደረግ ነው።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ ኤች አር የተሰኘው የአቋም መግለጫ፣ መግለጫውን ማውጣት ያስፈለገበትን ምክንያት በሚዘረዝርበት ክፍሉ፤ በ2002 ዓ/ም የጸደቀው የሲቪክ ማህበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ምዝገባ አዋጅ፣ የሲቪክ ማህበራትን እንቅስቃሴ የሚገድብ በመሆኑ፣ በተለይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ጥርጣሬዎችን የሚመረምሩ ሲቪክ ማህበራት እንቅስቃሴ በመንግስት የስራ ሃላፊዎች የሚገደቡ በመሆኑ ይላል። ይህን መነሻ በማደረግ ባሳለፈው ትእዛዝ ደግሞ ይህ ህግ እንዲሰረዝ ያሳስባል።

በመሰረቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የሲቪክ ማህበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ምዝገባ አዋጅ የሲቪክ ማህበራትን እንቅስቃሴ የመገደብ ዓላማ የለውም፤ አይገድብምም። አዋጁ ኢትዮጵያውያን ያለምንም ገደብ ሲቪክ ማህበራት የማቋቋም መብት ያላቸው መሆኑን ያረጋግጣል። ከዚሀ በተጨማሪ የኢትዮጵያውያን ሲቪክ ማህበራት በማንኛውም ዘርፍ – ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ (ዴሞክራሲ፣ ምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ ወዘተ) ጉዳዮች ውስጥ ያለገደብ መሳተፍ ይችላሉ። ወደየውጭ ሲቪክ ማህበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ስንመለስ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ጉዳዮች ዙሪያ ያለምን ገደብ የመንቀሳቀስ ነጻነታቸው በአዋጁ ተረጋግጧ።

ይሁን እንጂ፣ አዋጁ የውጭ ሲቪክ ማህበራት በሃገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ መሳተፍ እንደማይችሉ ይደነግጋል። ይህ የሆነው የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያውያን ብቻ በመሆናቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ሃገራት ጥቂት ከተሜዎች በተሳተፉበት የጎዳና ላይ ነውጥ መንግስት ለመለወጥ የተካሄዱ ሙከራዎች የተቀነባበሩትና የተመሩት የሃገራቱ ጉዳይ በማይመለከታቸው የምእራባውያን ሲቪክ ማህበራት መሆናቸው በበርካታ ጥናቶች ተረጋግጧል። በመሆኑም የውጭ ሲቪክ ማህበራት በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ገብተው እንዲያቦኩ መፍቀድ፣ የህዝቡን ጥቅምና ፍላጎት ለምእራባውያን መንግስታትና ቱጃሮች ጥቅምና ፍላጎት አሳልፎ ለመስጠት ከመፍቀድ አይለይም። የበጀታቸውን 15 በመቶ በላይ ከውጭ የሚያገኙ ሲቪክ ማህበራትም እንደውጭ ሲቪክ ማህበር እንዲመዘገቡ ህጉ ያዛል። ይህ የሆነው የተለያዩ ሃገራትን ልምድና ጥናቶችን መነሻ በማድረግ፣ ከውጭ ለሲቪክ ማህበራት የሚመጣ ገንዘብ ምንግዜም ሌጣውን እንደማይመጣ፣ የለጋሾቹን ጥቅምና ፍላጎት በገንዘብ ተቀባይ ሃገር የማስፈጸም ተልዕኮንም ይዞ እንደሚመጣ በመረጋገጡ ነው።  

የሲቪክ ማህበራት ምዝገባ አዋጅ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ብቻ መሆኗን፣ የሃገሪቱ ጉዳይም የዜጎቿ ብቻ መሆኑን በማረጋጋጥ ሉዓላዊነቷን ማስከበርን ታሳቢ ያደረገ ነው። እናም አዋጁ ከኢትዮጵያውያን አንጻር ሲታይ ተገቢ ነው።

በአጠቃላይ የአሜሪካ ኮንግሬስ ያጸደቀው ኤች አር 128 የተባለ የአቋም መግለጫ በገለልተኛ አካል ወይም የውሳኔ ሃሳቡን ባጸደቀው አካል ያልተረጋገጡ አሉባልታዎች የታጨቀ ነው። ይህ ዋጋውን ያሳንሰዋል። መረጃዎቹ በከፊል ትክክል እንኳን ቢሆኑ መግለጫው ወቅቱን ያልጠበቀ ነው። በዚህ ላይ የኮንግሬሱ አባላት ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ በራሷ በአሜሪካ ለሚፈጸሙና በሃገሪቱ ህግ ለሚያስጠይቁ ወንጀሎች ዋጋ የማይሰጡ መሆናቸው፣ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ያላቸውን ተቆርቋሪነት ጥያቄ ላይ ይጥለዋል። መግለጫው የኢትዮጵያውያን ጉዳይ ብቻ የሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ገብቶ ሉዓላዊነትን የመዳፈር ልቅነትም ታይቶበታል። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ብቻ በመሆኗ፣ የአሜሪካ ኮንግሬስ አባላት የሃገሪቱን ጉዳይ ለባለሃገሮቹ ቢተዉ መልካም ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy