Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህዝባዊውን ኃይል የማጠልሸት አባዜ

0 279

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህዝባዊውን ኃይል የማጠልሸት አባዜ

                                                         ዘአማን በላይ

ፅንፈኛው ሃይል መከላከያ ሰራዊቱን በማይገባ ስሞች እያጠለሹት የሚገኙት ፀረ ሰላም ሃይሎች የሰራዊቱን ማነነት የሚያውቁ አይደሉም። ቢያውቁም ለማወቅ የሚፈልጉ አይደሉም። መከላከያ ሰራዊታችን ሰላምና መረጋጋትን ከመፍጠር ባሻገር ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ እየሰራ ነው። በተለይ አሁን በምንገኝበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ሰራዊቱ ህብረተሰቡን እያወያየ ነው። በአቅራቢያው ከሚገኝ ህብረተሰብ ጋር በመሆን  በልማት ስራዎች ይሳተፋል። በግዳጅ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ለሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመስጠትና ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል።

እንደሚታወቀው ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊታችን እሴቶች ውስጥ አንዱ “ከራስ በፊት ለሀገርና ለህዝብ” የሚለው ነው፡፡ ካለፉት ሥርዓቶች ፍጹም በተለየና ታይቶ በማይታወቅ መልኩ፣ ሠራዊታችን ለህዝብና ለሀገር የሚኖር፣ ህዝባዊ ፍቅርና አመኔታን ያተረፈ ሠራዊት መሆኑን ያረጋገጠ ነው፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የህዝብን ባህልና ወግ በማክበርና በማስከበር፣ በፍላጎታቸው ጸድቆ የዘመናት ጥያቄያቸውን የመለሰውን ህገ – መንግሥት ልዕልና ከመጠበቅና ከፍሬው ሀገሪቱ ተቋዳሽ እንድትሆን ከማድረግ አልፎ የልማት አጋርነቱን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡

በጦርነት ምክንያት ዕልፎች ለሞት፣ ስደትና ፍትህ – አልባነት ተጋልጠውባት የነበረችው ሀገራችን ዛሬ የሞት ሳይሆን የተሻለ የህይወት፣ የድህነት ሳይሆን የተስፋ ሰጪ ልማት፣ የስጋት ሳይሆን በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት የመገንባት ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡ ለዚህ ደግሞ የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተው ህዝባዊ ሠራዊታችን አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም፡፡

መከላከያ ሠራዊታችን በህገ -መንግሥታዊ እምነቱ፣ በዓላማ ጽናቱና በማይነጥፍ ጀግንነቱ በተደጋጋሚ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ የሀገሩን ዳር ድንበር በደምና አጥንቱ አስከብሯል፡፡ ፀረ ሠላምና ፀረ ልማት ኃይሎችን በመደምሰስ ለልማቱ አስተማማኝ ሠላም አስፍኗል፡፡ በዓለም- አቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ በሁለት ተቃራኒ ኃይሎች ጭምር ያለ አንዳች ልዩነት በመመረጥ ብቸኛ የዘመናችን ሠራዊት ሆኗል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ተዘርዝረው የማያልቁ ስኬቶቹ ምስጢር ደግሞ ህዝባዊነቱ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም፡፡

ከዚህ በፊት የነበሩት ሠራዊቶች ህዝቡ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ባስታጠቃቸው ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ተጠቅመው ወገናቸውን እንዳልጨፈጨፉ፣ የአዛውንቶች፣ ሴቶችና ህጻናትን ህይወት እንዳላጠፉ፣ ጨቅላ ህፃን የሙት እናቷን ጡት ስትጠባ የሚያሳይ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሰቃቂ ትዕይንት እንዳላሳዩን፤ ዛሬ ታሪክ ተቀይሮ ሌላ ዓይነት ሀገራዊ ሠራዊት ተፈጥሮ ህዝባችን ከአብራኩ በወጡት ልጆቹ እየኮራ ነው፡፡

ሠራዊቱ ከሰው ሰራሽና ከተፈጥሮ አደጋ ጋር ተጋፍጦ፣ ለአንዴ ብቻ የሚኖራትን ህይወቱን ለዕልፎች የመኖር ተስፋ አለምልሟል፡፡ ምን ይህ ብቻ! ይህ ለህገ-መንግስቱና ለህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ዘብ የቆመስው ሰራዊት፤ ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያንና አረጋዊያት የሚጦር፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጅ-አልባ የሆኑ ህፃናትን የሚያሳድግና የሚያስተምር፣ ከራሱ በላይ ለህዝቡና ለሀገሩ ጥቅም ሲታትር ውሎ የሚያድር ነው፡፡

የዚህን ህዝባዊ ሰራዊት የሰላምና የልማት ተሳትፎ በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ አንደኛው ሀገራችን አድጋ የረሃብ፣ ድህነትና መሃይምነት ተምሳሌነቷ ተፍቆ ማየት የማይፈልጉ፣ መበታተንና ተስፋ – አልባነታችንን የሚናፍቁ የውጭና የውስጥ ፀረ-ሠላም ኃይሎች ካሉ ይህን እኩይ ሴራቸውን ማክሸፍ ነው፡፡

ይህን ከኤርትራ ወረራ እስከ አል-ሸባብ የግብረ-ሽበራ ተግባርን በመመከት እንዲሁም ከሰሜን እስከ ደቡብ ባሉ የሀገራችን አካባቢዎች ሻዕቢያ እያስታጠቀ በሚልካቸውን አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ሃይሎችን ላይ ህዝባዊ ክንዱን በማሳረፍ እውን አድርጓል፤ ነገም ይህን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

እናም ይህ ሠራዊት ኢትዮጵያ ጠላቶቿ እንዳለሙት የብጥብጥና የትርምስ ሀገር ሳትሆን የአህጉሪቱ መዲና፣ የድሃ ህዝቦች መብትና ጥቅም ተሟጋች እንድትሆን ያስቻላት ነው ብል ከእውነታው መራቅ አይሆንብኝም፡፡

ሁለተኛው የልማት ገጽታው ዕውቀቱን፣ ጉልበቱንና ካለው አነስተኛ ገቢ በፍጹም ህዝባዊና ሀገራዊ ፍቅር የሚገልጽ ቀጥተኛ የልማት ተሳትፎ ማድረግ ነው፡፡ ሰራዊቱ በዚህ በኩል የነበረውን ድርሻ በቀላሉ መግለጽ ይከብዳል፡፡

መከላከያ ሰራዊቱ የትልቋ ኢትዮጵያ እውነተኛ ተምሳሌት ብቻ አይደለም— መሃንዲስ፣ መምህር፣ አርሶና አርብቶ አደርም ጭምር ነው፡፡ መንገድ ገንብቶ ህዝቦችን አገናኝቷል፡፡ ግድብ ሰርቶ አርብቶ አደሩ ወደ አርሶና ከፊል አርብቶ አደርነት እንዲቀየር አስችሏል፡፡

ትምህርት ቤት ሰርቶም የመማር ዕድሉ ያልነበራቸውን ከዕውቀት ጋር አገናኝቷል፡፡ የጤና ተቋማት ላይ ዕውቀቱን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን አፍስሶ ለዕልፎች የመኖር ዋስትና ሰጥቷል፡፡ የእናቶችንና ህፃናትን ሞትን በመቀነስ ረገድም በተግባር ተሳትፏል፡፡ በምህንድስናና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ብቃት ያላቸው ሙያተኞቹን በማሳተፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር አብዮት ለኩሷል፡፡ ካለው እያካፈለ፣ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ጋር እየዋለ ድርብ ድርብርብ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ ሌላ ሌላም ተግባሮችን ከውናል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሀገራእን የቀየሰችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን ዕውን በማድረግ ረገድ ጠላትን ተዋግቶ ከማሸነፍ ያልተናነሰ ድል አስመዝግቧል፡፡ የተራቆተውን የሀገሪቱን የደን ሽፋን ወደ ነበረበት ለመመለስና የአካባቢን ሥነ-ምህዳር ለመጠበቅ የበኩሉን ኃላፊነት ለመወጣት ባደረገው ጥረት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የቻለ ኃይል ነው፡፡

የሰራዊቱ አባላት ለሀገራዊ ግዳጅ በተሰማሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ለማልማት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን ተክለዋል፡፡ ከሠራዊታችን ድርሻ ላይ ተቀንሶ በሚጠጡት ውኃ፣ በሚደረግላቸው ከሀገር ፍቅር የመነጨ እንክብካቤ ፀድቀዋል፡፡

በእርግጥ “ከራስ በፊት ለሀገርና ለህዝብ” ብሎ የተነሳ ኃይል መነሳት ብቻ ሳይሆን ያወቀ፣ ያመነና እምነቱን ስንቁ አድርጎ ወደ ተግባር የለወጠ ኃይል ውጤታማነቱ ላያስገርም ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሰራዊቱ በተግባሩ ህዝባዊ ስለሆነ ነው፡፡ ይህ በተጨባጭ የሚታይ ተግባሩ የሀገራችን ህዝቦች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ህይወታቸውን እንዲመሩ አስችሏቸዋል፡፡

ይህ ሁኔታም ፅንፋውን ሃይል አንገብግቦታል፡፡ የፅንፈኛው ሃይል ፍላጎት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለማፍረስ መጣር በመሆኑ በቅድሚያ ለዚህ ፍላጎታቸው መሳካት ችግር ሊሆን የሚችለውን እንደ መከላከያ ዓይነት ተቋማትን ስም ማጥፋት ስራቸው ሆኗል፡፡

ይሁንና መከላከያ ሰራዊታችን ዛሬም ህዝባዊነቱን ጠብቆ ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ ሆኖ ተግባሩን መከወን ይቀጥላል፡፡ ልክ እንደ ትናንቱ ዛሬም፣ ነገም ይሁን ከነገ ወዲያ ከህብረተሰበቡ ጋር ሆኖ በልማትና በሌሎች ተግባሮች አብሮ መስራቱን አያቆምም፡፡ ጽንፈኛው ሃይል ስላልተገነዘበው እንጂ በህዝቡና በሰራዊቱ መካከል ያለው ጠንካራ ፍቅርና ትስስር እንዲሁ በቀላሉ የሚናድ አይደለም—ግንኙነቱ በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ነውና፡፡ እናም ፍላጎታቸው “ላም አለኝ በሰማይ…” መሆኑን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy