Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ማረጋገጫው…!

0 305

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ማረጋገጫው…!

ዳዊት ምትኩ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ሰባተኛ ዓመት ግድቡ እየተገነባ በሚገኝበት በጉባ ተከብሯል። የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ በአከባበሩ ወቅት በጉልህ ያልተጠቀሱ አንዳንድ የግድቡ እውነታዎችን በማንሳት ሃቆቹ የሀገራችን ህዝቦች ምን ያህል በድህነት ላይ ቆርጠው መዝመታቸውን ማረጋገጫ መሆኑን ለማሳየት እሞከራለሁ።

በወቅቱ እንደተነገረው ግድቡ ኃይል ከማመንጨት ተግባሩ በተጨማሪ፣ በውስጡ የመነጨውን ኃይል የሚያከፋፍሉ ከ35 በላይ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊና ማከፋፈያ ግንባታዎችንም እየተካሄዱበት ነው። ከአምስት ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የከፍተኛ መስመሮችና ከ70 በላይ የማከፋፈያ ጣቢያዎች በተለያየ የግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ።

በርካታ የግንባታ ክፍሎችን የያዘው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፤ በአሁኑ ሰዓት የግንባታው ክንውን በጥቅሉ 65 በመቶ ደርሷል። የግድቡ ዋናው ክፍል 140 ሜትር ከፍታ ሲኖረው አንድ ሺህ 180 ሜትር ርዝመት ይሸፍናል። እንዲሁም ከሚያስፈልገው 10 ሺህ ሜትር ኪዩቢክ ሙሌት ውስጥ 90 በመቶ ተጠናቋል። እነዚህ እውነታዎች ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ኃይል ከማመንጨት ባሻገር፤ ብሄራዊ አንድነት የተፈጠረበትና ህዝቦች በድህነት ላይ በጋራ እየተረባበሩ መሆናቸው አንድ ማረጋገጫ ናቸው።

እርግጥ የአገራችን ህዝቦች በየትኛውም የልማት ስራ ላይ ፋና ወጊ ናቸው። በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የባንዴራቸው ፕሮጀክት መሆኑን በመገንዘባቸው ለግድቡ ከፍፃሜ መድረስ እየተረባረቡ ነው። እጅግ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሳይቀሩ ለግድቡ ግንባታ ከዕለት ቀለባቸው ጭምር እየቀነሱ በገዛ ፈቃዳቸው እያከናወኑ ያሉት የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የቀሳቁስና የሞራል ድጋፍ እጅግ የሚያኮራ ነው።

ነጋዴው የህብረተሰብ ክፍልም ለግድቡ ግንባታ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ነው። ምንም እንኳን ይህ የህብረተሰብ ክፍል ከመንግስት ሰራተኛው ጋር ሲነፃፀር የሚገባውን ያህል ለግድቡ ግንባታ የበኩሉን እገዛ አድርጓል ብዬ ባላምንም፤ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት ግን በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም።

እንደሚታወቀው ሁሉ ግድቡን ለመገንባት ለዘመናት ሳይደፈር የቆየውን የዓባይን ወንዝ የመድፈር ተግባር በዚህ ትውልድ እውን ሆኗል። ይህ ትውልድ የትናንቱን ትውልድ የልማት ጥያቄ፣ የዛሬውን ትውልድ ተጠቃሚነትና የነገውን ትውልድ አደራ ተቀብሎ እየሰራ ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዚህ ረገድ ሁነኛ ማሳያ ነው። መቻላችንን የምናሳይበት የቁርጠኛ ህብረታችን አንድ መገለጫ ሆኗል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በዕውቀቱ ለመደገፍ የገባውን ቃል አሁንም ቀጥሏል። ምንም እንኳን ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ የተለያዩ ሃይሎች የፈለጉትንና ያሻቸውን ቢያወሩም፤ በኢትዮጵያ ህዝቦች ርብርብ ግንባታው ዛሬም ድረስ ለአንድ ሰከንድ እንኳን አልተቋረጠም። “የነብርን ጭራ አይዙም፣ ከያዙም አይለቁም” እንዲሉ አበው፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች ይህን ፕሮጀክት አውን ለማድረግ ልማቱን በነብር ጭራ መስለው ይዘውታል። አይለቁትም።

በተምሳሌታዊ ዘይቤው የነብርን ጭራ ከለቀቁ በነብሩ መበላት ስለሚሆን፤ ተምሳሌታዊውን የህዳሴ ግድቡን ግንባታ በመተው ወደ ድህነት አረንቋ ውስጥ መዘፈቅ አይሹም። ማደግና መበልጸግ እንደሚችሉ አንድ ማሳያ የሆነውን የግድቡን ግንባታ በመተው የድህነት መገለጫ ሊሆኑ አይከጅሉም። ያ ታሪክ በሂደት እየተቀረፈ፣ ህዝቡም ከዕድገት የሚያገኘውን ጥቅም እያጣጣመ ነው።

እናም የህዳሴው ግድብ ለአንዲት ሰኮንድም ሊቆም የማይችለው ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በጋራ ተጠቃሚነት ማናቸውንም ልማታዊ ተግባሮች ማከናወን እንደምንችል ማሳያ መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው። በሌላ በኩልም እዚህ ሀገር ውስጥ እየተፋጠነ ባለው የልማት ተግባር ዘርፈ ብዙ ኢንዱስትሪዎች “እየበቀሉ” ነው። ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ መንግስት እየተሰራ ነው።

ታዲያ ይህን የዕድገት ፍላጎት በአግባቡ ለማስኬድ የኤሌክትሪክ ሃይልን ከከባቢ ብክለት በነፃ መንገድ መጠቀም የግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ ታዳሽ የተፈጥሮ ሃይላችንን መጠቀም ይኖርብናል። ይህን ካላደረግን አሁንም ከነበርንበት የከፍታ ቦታ ተንሸራትተን የኋሊት በድህነት አረንቋ ውስጥ ልንዘፈቅ እንችላለን። ይህን ደግሞ የሚፈቅድ ትውልድ የለም። እናም የህዳሴው ግድም ለአፍታም ቢሆን የማይቆምበት ሁለተኛው ምክንያት ይኸው ይመስለኛል።

እኛ ስናድግም የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራትም የሁኑ ሌሎች የቀጣናው ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። እኛ ከቀጣናው ሀገራት ተነጥለን ልንለማ አንችልም። የእኛ እድገት የቀጣናው ሀገራት ጭምር ነው። የግድቡ ግንባታ የቀጣናውን ሀገራት የኤሌክትሪክ ሃይል ችግርም የሚቀርፍ ነው። እናም ሶስተኛው ግድቡ ለአንድ ሴኮንድም ቢሆን ሊቆም እንዳይችል የሚያደርገው ምክንያት ይኸው ይመስለኛል።

መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እነዚህን እውነታዎች በሚገባ ያውቃሉ። ምንም ዓይነት ብዥታ የለባቸውም። ለግድቡ ግንባታ የቦንድ ግዥ ዋንጫው በየክልሉ ሲዞር ከተጠበቀው በላይ ገንዘብ በማውጣት ቦንድ የሚገዙትም ለዚሁ ነው።

ይህ ዕውነታ በሀገር ቤት ውስጥ ብቻ የሚገለፅ አይደለም። በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዚሁ ግድብ ግንባታ እየፈፀሙት ካለው ቀላል የማይባል የቦንድ ግዥን ጨምሮ ካሉበት ቦታ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት የግድቡን ግንባታ በመጎብኘትና ሌሎች ኢትዮጵያዊንም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በማነሳሳት ረገድ እየተጫወቱ ያሉት ሚናም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ይህ ቁርጠኛ ከድህነት የመውጣት የህብረት ስሜት ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ድረስ የሚታይ ነው። ማንም በገሃድ ሊያየው የሚችልም ጭምር ነው። እናም ይህ የህዝቦች አንድነት የራስን የተፈጥሮ ሃብት በራስ አቅም የማልማትና በእርሱም ራስንና ከባቢውን የመጥቀም መገለጫ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

እርግጥ አሁን ያለውንና ግድቡን ከፍፃሜ ለማድረስ ያለውን የህዝቡን ስሜት በተገቢው መንገድ መምራት ከተቻለ፤ ትናንት “ዓባይ የሌላው ሲሳይ” የሚለውን አባባል፤ “ዓባይ የእኛና የጎረቤቶቻችን ሲሳይ” ወደሚለው የተጠቃሚነት እሳቤ መለወጣችን አጠያያቂ አይሆንም። የየትኛውም ሀገር የልማት ምንጭ ህዝብ በመሆኑ፣ ከዚህ አኳያ በተለይ ታታሪው የሀገራችን ህዝብ ለማደግ ያለውን ቀናዒ አስተሳሰብና ተግባር በሚፈለገው ፍጥነትና ደረጃ ማስኬድ ይገባል።

ይህን ቁርጠኛ የህብረት መንፈስና ህዝባዊ ስሜት ግለቱን ጠብቆ እንዲሄድ ማድረግ አሁንም ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር መሆኑን መዘንጋት አይገባም። በሰባተኛው የግድቡ ግንባታ ክብረ በዓል ላይ የተገለፁት የግድቡ እመርታዎች ይህ ህዝብ የሚመራውና የሚያሰራው አካል ካለ በአንድነት ተያይዞ ምን ያህል ድህነትን ሊቀርፍ እንደሚችል ማረጋገጫ ነው። በመሆኑም ህዝባዊ ጥረቱን እያጎለበቱና ለበለጠ የልማት ድል እያነሳሱ መሄድ ያስፈልጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy