Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ማንም አሻራውን ያላኖረ እርሡ ከእኛ አይደለም!”

0 427

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ማንም አሻራውን ያላኖረ እርሡ ከእኛ አይደለም!”

 

ወንድይራድ ሃብተየስ

አንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ አንድ ህልም አንድ ምኞት የኖረው በህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ላይ ብቻ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ  ከአድዋ ድል በመለጠቅ ህዝቦችን በአንድ ጥላስር ማሰባሰብ የቻለ የህዝቦችን ቀልብ መግዛት የቻለ የዘመን ክስተት ፕሮጀክት ነው። ይህን ፕሮጀክት  ያቀደ፣ ለተግባራዊነቱ የተጋ በአጭሩ በዚህ ፕሮጀክት ላይ አሻራውን ያሳረፈ ሁሉ ምስጋና ሊቸረን ይገባል። በዚህ ታላቅ አገራዊ ፕሮጀክት ላይ አሻራውን ያላኖረ ዜጋ ከእኛ ሊሆን ከቶ አይቻለውም። በእርግጥ  ያስተዛዝበን እንደሆን እንጂ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከዳር እንደሚያደርሱት በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል። በተግባርም ታይቷል፤ ዛሬ ላይ ይህ ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን የሚጠይቅ ፕሮጀክት ከ65 በመቶ በላይ  ማድረስ ተችሏል።

ህዝብ ከተባበረ የማይፈጽመው ነገር የለም። ከመቶ አመታት በፊት አባቶቻችን ልዩነታቸውን ወደጎን አድርገው ዘመናዊ መሳሪያዎችን  እስከአፍንጫው የታጠቀውን ወራሪውን የጣሊያን ሃይል ለመፋለም ከያሉበት ተሰባስበው፣ ስንቃቸውን ተሸክመው ባህላዊ መሳሪያቸውን እንግበው  ጠላት እመሸገበት ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ድረስ በእግራቸው ተጉዘው ወራሪውን ሃይል አሳፍረው መልሰውታል። ይህ የአባቶቻችን የአገር ወዳድነትና የአልበገርም ባይነት ስሜት ለመላው  ጥቁር ህዝቦች ኩራት እንደሆነ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ለታዳጊ አገሮች ሁሉ ፋና ወጊ የሆነ ፕሮጀክትን በመገንበት ላይ ነው። ለእኛ ኢትዮጵያዊያኖች ከሃይል ማመንጫነት ወይም ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳነቱ ባሻገርም እንደሆነ ዓለም ሊገነዘበው  የሚገባ እውነታ አለ። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአንድነታቸው መገለጫ የአብሮነታቸው ማረጋገጫ ማህተም ነው።

ይህ ፕሮጀክት  የአንድ መቶ ሚሊዮን  ህዝቦች ህልም ነው። የአንድ መቶ ሚሊዮን  ህዝቦች አንድና ተመሳሳይ ፕሮጀክት ነው። የእያንዳንዱ አገር ወዳድ ዜጋ በሚችለው ነገር ሁሉ ለአብነት በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በቁሳቁስ፣ በዕውቀት፣ በሃሳብ፣ በጸሎት  ለዚህ ፕሮጀክት ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው። ለህዳሴው ግድብ እየተደረገ ያለውን ህዝባዊ ድጋፍ በተመለከተ አንድ አባት እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር። “ከሙታንና  በማህጸን ካሉ ሽሎች ውጪ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ አሻራውን በማኖር ላይ ነው። በነገራችን ላይ ለዚህ ፕሮጀክት ስኬት ኢትያጵያዊያኖች ብቻ ሳይሆኑ የትውልደ ኢትዮጵያዊያኖችም ድጋፍ ከፍተኛ  ነው። ልፋታችንን በአይናችን አይተነዋል። አሁን ላይ የፕሮጀክቱን 65 በመቶ ማጠናቀቅ ተችሏል።

የዚህ  ፕሮጀክት ወጪ ከባድና ወገብ የሚያጎብጥ  ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሸክሙን ተቋቁመውታል። መንግስት ጠንካራና የተሳካ  የህዝብ ግንኙነት ስራ መስራት በመቻሉ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ የእኔነት ስሜት  በሁሉም ዜጋ ውስጥ እንዲፈጠር ማድረግ በመቻሉ እያንዳንዱ ዜጎች ካለው ጥቂት ገቢ ላይ በመቀነስ ቦንድ በመግዛትና ዕርዳታ በመለገስ አጋርነታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።  ዛሬ በአገራችን በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም እንደህዳሴው ግድብ የህብረተሰቡን ቀልብ የገዛ ፕሮጀክት የለም። ይህ ግድብ ከሃይል ማመንጫነቱ ባሻገር የአገራዊ መግባባትና የገጽታ ግንበታ ስራችን ዋልታና ማገር  ሆኗል። በዚህ ፕሮጀክት ሳቢያ የተፈጠረው አገራዊ አንድነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተመሳሳይ አይዲዮሎጂ ወይም የፖለቲካ አተያይ ሊኖረው አይችልም። እንዲኖረውም አይጠበቅ። ይሁንና በመሰረታዊ የአገራችን ጉዳይ ዘለቄታዊ ጥቅም ላይ ግን ከቶ ልንለያይ አይገባንም።  ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የኢህአዴግ ወይም የኦነግ ወይም የቅንጅት ወይም የሌላ የሌላ ፓርቲዎች አይደለም። ይህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ህዝቦች ነው። መንግስታት ይመጣሉ፤ መንግስታት ይሄዳሉ፤ በተመሳሳይ  ፓርቲዎች ይመጣሉ፤ ፓርቲዎችም ይሄዳሉ። አገርና ህዝብ ግን ለዘለዓለሙ ቀጣይ ናቸው። በመሆኑም ይህ ፕሮጀክት የእኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንጂ የመንግስት ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች አይደለም። በመሆኑም ማንም በዚህ ፕሮጀክት ላይ አሻራውን ማሳረፍ  ያልቻለ ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፈ አይደለም።

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ህዝብና መንግስት ከድህነትንና ኋላቀርነትን ለመላቀቅ የሚያደርጉት ጥረት ውጤት  ነው። ለአገራችን ድህነት በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ቢቻልም አለመተባበራችን ግን ዋንኛው ጉዳይ ይመስለኛል። አሁን ላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  መተባበርና መደጋገፍ በመጀመራቸው ባላፉት 15 ዓመታት ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ናቸው። ይህን መሰረቱ ግብርና የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር ካልተቻለ የአገራችን ዕድገት መንገራገጩ የማይቀር ነው። በመሆኑም  ፈጣኑን ዕድገታችንን ለማስቀጠል የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድ የግድ ነው። ይህ ደግሞ እውን ሊሆን የሚችለው ዘርፉ የሚፈልገውን ከፍተኛ የሆነ የሃይል አቅርቦት ማመንጨት ሲቻል ብቻ ነው።

ለኢንዱስትሪው አብዮት  ስኬት ደግሞ የመጀመሪያው ነገር   የሃይል አቅርቦትን ማሳደግ መሆኑን የተረዳው መንግስት  በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር በጀት በመመደብ ከውሃ፣ ከንፋስና ከእንፋሎት ሃይል ማመንጫዎችን በመገንባት ላይ ነው። ኢትዮጵያ በ1983 ዓ. ም   የነበራት 350 ሜጋ ዋት ሃይል አሁን ላይ ከ4300 ሜጋ ዋት በላይ ማድረስ ተችሏል። ቁጥሮችን ለማወዳደር ፈልጌ ሳይሆን መንግስት ባለፉት 27 ዓመታት  የሃይል አቅርቦትን ለማሳደግ ያደረገውን ጥረት ለማሳየት እንጂ። በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ይህ አሃዝ ወደ 11ሺህ ሜጋ ዋት እንደሚያድግ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ከአራትና አምስት ዓመታት ብኋላ ደግሞ ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት እንደሚያድግ የተጀመሩ ስራዎች አመላካች ናቸው።  

የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ  እቅድ ሲነድፍ የፋይናንስ ምንጭ ብሎ የለየው የኢትዮጵያን ህዝብ እንጂ ብድርና ዕርዳታን አይደለም። ምክንያቱም በአባይ ላይ የሚገነቡ የልማት ስራዎች ላይ የሶስተኛ አካላት ጣልቃ ገብነት ስለነበረበት ነው። እስካሁንም መንግስት ባቀደው መንገድ   ፕሮጀክቱን በውስጥ ገቢ ብቻ በመከናወን ላይ ነው። ይህን ፕሮጀክት ከሌሎች ፕሮጀክቶቻችን ለየት የሚያደርገው እጅግ ግዙፍ መሆኑ እንዲሁም ወጪው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ህዝቦችና መንግስት የሚሸፈን ብቻ መሆኑ ሳይሆን ለአገራዊ መግባባትና ለገጽታ ግንባታ ስራችን ስኬት ማሳያ መሆኑ ጭምር ነው።  

 

የኢትዮጵያ መንግስት የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ይፋ ሲያደርግ  ያራምደው የነበረው “በተፋሰሱ አገራት መካከል ፍተሃዊ የውሃ  ክፍፍል” የሚለው መርህ  አሁንም የአገራችን  ጠንካራ አቋም ነው። ኢትዮጵያ ቀድማ ይዛ  የተነሳችውን አቋም ሁሉም የአባይ ተፋሰስ አገራት አቋማቸው አድርገው እንዲይዙት ማድረግ ችላለች። ይህ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው።   

 

የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት እቅድ ሲነድፍ የፋይናንስ ምንጭ  ብሎ የለየው የኢትዮጵያን ህዝብ እንጂ ብድርና ዕርዳታ ባለመሆኑ ግብጻዊያን ግድቡን ለማስተጓጎል ያደረጉት ጥረት ሁሉ መና ቀርቷል። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የአንድ ሚሊዮን ህዝቦች ህልም ነው። ዛሬ ይህ ህልም እውን ወደመሆኑ ተቋርቧል።  መንግስታት ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ስርዓትም ይለወጣል፤ ነገር ግን አገርና ህዝብ ቋሚነና ዘላቂ በመሆናቸው ሁላችንም በምንችለው ሁሉ ለፕሮጀክቱ እውን መሆን የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። መንግስት ይህን ፕሮጀክት ሲያቅድ የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ በመተማመን ነው። በመሆኑም አሁንም አገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ የሚችለውን ያህል ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy