Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ማንነት ሲጋለጥ

0 323

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ማንነት ሲጋለጥ

ዳዊት ምትኩ

በአገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውና ራሱን አርበኞች የግንቦት ሰባት እያለ የሚጠራው ቡድን ከፍተኛ አመራር የሆኑት ነዓምን ዘለቀ ሰሞኑን ከቢቢሲ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ሃርድቶክ ፕሮግራም ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የድርጅቱን አቋምና እንቅስቃሴ አስመልክቶ ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር።

እርግጥ የቢቢሲው ፕሮግራም የታቀደው በቅርቡ በአገራችን የተጀመረውን ለውጥ፣ በተለይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለህዝቡ የሰጡትን ተስፋና እያካሄዱት ያለውን እንቅስቃሴ ቡድኑ እንዴት እንደሚመለከተው ነበር። ሰውዬው የሰጡት ምላሽ ግን እጅግ አስገራሚ፣ አስቂኝና እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነው።

አቶ ነዓምን በቅርቡ በአገራችን ውስጥ የተካሄደው ሰላማዊ እንቅስቃሴ “አኛም አለንበት” ባይ ናቸው። ጋዜጠኛው በትጥቅ ትግል የሚያምን ድርጅት ሰላማዊ ትግልን ሊቀላቀል እንደማይችል በመግለጽ የትጥቅ ትግል ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል። ይህም ለሽብር ቡድኑ አሳፋሪ ውርደት ሆኗል።

እርግጥ አርበኞች ግንቦት ሰባት እዚህ አገር ውስጥ ያደረገው እንቅስቃሴ የለም። እንቅስቃሴው የየትኛውም አሸባሪ ቡድን አይደለም። የህዝቡ ብቻ ነው። ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የሽብር ቡድኑ ማንነት የሚፈቅድለት አይደለም።

በትጥቅ ትግሉም ቢሆን በኤርትራ መንግስት የተላከውን መልዕክት ሳያደርስ በአገራችን ህዝብና መንግስት መንገድ ላይ ከመቅረት በስተቀር አንድም የፈየደው ነገር የለም። እናም የአቶ ነዓምን የሽብር ቡድን ጉራ በኪሱ ብቻ ነው። በኢሳት ላይ ከመለፍለፍ በስተቀር ምንም ጠብ የሚል የፖለቲካ መሰረት የሌለው የባዕዳን ተላላኪ ነው።

እርግጥ የቢቢሲው ጋዜጠኛ ከኢትዮጵያ በተገነጠለችው ኤርትራ ውስጥ ሆኖ የኢትዮጵያዊያንን ጥቅም ማስከበር ይቻላል ወይ? በማለት ለአቶ ነዓምን ያቀረበላቸው ጥያቄ አስቂኝ ምላሽን ያስከተለ ነበር። ይኸውም ሰውዬው በጂቡቲ፣ በኬንያ፣ በሱዳንና በሶማሊያ ውስጥ ሆነን ትግል ማካሄድ ስላልቻልን ነው በማለት የሰጡት መልስ ነው።

ይህ ምላሻቸው ሁለት ነገሮችን ያሳያል። አንደኛው የሽብር ቡድኑ ልክ እንደ ፈጣሪው የኤርትራ መንግስት ተግባሩን በውሸት ላይ የሚያከናውን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥንካሬን የሚያመላክት ነው።

የሰውዬው ውሸት አርበኞች ግንቦት ሰባት የተሰኘው የሽብር ቡድን ጥንስሱ ኤርትራ ውስጥ ተጀምሮ አሜሪካ ውስጥ የተቋቋመ ቡድን መሆኑን የዘነጋ ነው። ቡድኑ በኤርትራ መንግስት ከምርጫ 97 በኋላ በኤርትራ መንግስት ሃሳብ አመንጪነት አስመራ ውስጥ ተመክሮ የተቋቋመ ነው። በሻዕቢያ እስትንፋስ የሚመራም ነው። የራሱ ህልውና እንኳን የሌለው ተላላኪ ነው።

የአስመራው አስተዳደር “ተጣመር” ሲለው ዓይኑን ሳያሽ ከሌላ ፀረ ሰላም ኃይል ጋር የሚቀናጅ፤ “ተነጠል” ካለው ደግሞ ከመቅፅበት የሚቆራኝና በአስመራው መንግስት “የሙቀት መጠን” የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው። የኢትዮጵያንና የሌሎች ጎረቤት ሀገራትን አሸባሪዎችንና ፀረ ሰላም ኃይሎችን አቅፎ የያዘው የኤርትራ መንግስት አጀንዳ ሲያጣ የሚያቆራኘው፤ ጥርጣሬ ሲያድርበት ደግሞ “ተነጠል!” የሚለው የሙቀት መለኪያው “ቴርሞ ሜትሩ” ነው ማለት ይቻላል።

የኤርትራ መንግስትን የብተና ፖሊሲ ተከትሎ በተወጠረለት ቀጭን መስመር ላይ የሚራመድ እንጂ፤ ከስም በስተቀር ከኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር የለውም። ለሁከት ስራ ሲላክ ጥብቆውን አንጠልጥሎ የሚሮጥ ቡድን ነው።

ይህ በሻዕቢያ ሳንባ የሚተነፍሰው የትምክህት ኃይል አስመራ ውስጥ ቁጭ ብሎ ሳይጠሩት “አቤት!”፣ ሳይልኩት “ወዴት?” ብሎ የሚጠይቅ ነው። መሬት ላይ በሌለ ተጨባጭ ማንነቱ ከተለያዩ አካላት (በተለይም ከዲያስፖራው) “ለትግል” እያለ የሚሰበስበው ገንዘብ በአሸባሪው ዶከተር ብርሃኑ ነጋ የግል የባንክ ደብተር ውስጥ የሚገባ የቡድኑ አባላት ሲናገሩ ማድመጥ የተለመደ ነው።

በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ወገኖች “የአርበኞች ግንቦት ሰባት” መሪ የሆኑት አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋና ጓደኛቸው አቶ ነዓምን ዲያስፖራው የሚሰጠውን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው በማዋል፣ ልክ እንደ ኤርትራ መንግስት ተቃዋሚነትንና ግጭትን እንደ ንግድ እየተጠቀሙበት ነው የሚል ስሞታ እየቀረበባቸው ይገኛል።

ከዚህም አልፎ የሚገኘው የዲያስፖራ ድጋፍ ለኤርትራ መንግስት የደቀቀ ኢኮኖሚ ማገገሚያ እየሆነም እንደሆነ ይነገራል። አንዳንዶችም ‘ግንቦት ሰባት ከዲያስፖራው የሚያገኘውን ድጋፍ የኤርትራ መንግስት ልክ ውጭ ካሉት ዜጎቹ እንደሚሰበስበው የሁለት በመቶ መዋጮ ይቆጥረዋል’ ሲሉ ይደመጣሉ። በእንዲህ ዓይነት ለመሪዎቹ ጥቅም ሲባል የተቋቋመ ቡድን ከመዋሸት በስተቀር ሌላ አማራጭ የለውም።

በሌላ በኩልም ቡድኑ ከኤርትራ በስተቀር በሌሎቹ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ አካሂደዋለሁ የሚለውን “የትጥቅ ትግል” ማከናወን አለመቻሉ የኢፌዴሪ መንግስትን ጥንካሬ ያመላክታል።

እርግጥ ከሁከትና ከብጥብጥ ማትረፍ ከሚፈልገው የኤርትራ መንግስት በስተቀር ሌሎቹ የቀጣናው አገራት በልማት ተሳስረው ህዝባቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው። እናም ተላላኪዎችንና አዋኪዎችን በሙሉ ዓይናቸው ሊያይዋቸው አይፈልጉም። በዚህም ምክንያት እነ ነዓምን ዘለቀ ምሽጋቸው እዚያው ኤርትራ ውስጥ ብቻ ተወስኖ ቀርቷል።

የምስራቅ አፍሪካ አገራት ዛሬ አሸባሪዎችን የሚሸከሙበት ጫንቃ የላቸውም። አገራቱ ሽብርተኝነት በልማትና በሰላም ላይ የሚያንዣብብ አደጋ በንፁሃን ዜጎች ህይወት ጥፋት ላይ የሚያነጣጥር የፈሪ ዱላ መሆኑን ያውቃሉ።

የጅምላ ጥፋትን የሚያስከትለው ይህ የጥፋት መንገድ የትኛውንም አገር ለችግር የመዳረግ ብቃት ያለው መሆኑንም ይገነዘባሉ። አገራቱ ለዚህ ችግር ሲጋለጡ የነበሩና የሽብር ጥቃት ስለባም በመሆናቸው እነ ነዓምንን ዓይናቸውን ሊያዩዋቸው አይፈልጉም።

ከዚህ ይልቅ ለሰላም ከሚተጋው የኢፌዴሪ መንግስት ጋር በልማት እጅ ለእጅ ተያይዘው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን እውን እያደረጉ ነው። በአሁኑ ሰዓት የቀጣናው አገራት ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ረሃብና ጦርነት ማብቃት አለበት ብለው ቆርጠዋል።

አገራቱ ‘ለዚህ ሁሉ ያደረሰን ዋነኛ ጠላታችን ማነው?’ ብለው ጠይቀው ትክክለኛውን ምላሽም አግኝተዋል። ድህነትንም ዋነኛው ጠላታችን ነው ብለው ደምድመዋል። ከጎረቤቶቻቸው ጋር በልማት ተቆራኝተው ለማደግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን አውቀው ኢትዮጵያን እንደ ቀጣናዊ የልማት አስተሳሳሪ ድር ቆጥረው በጋራ እየሰሩ ነው። አገራቱ ሰላምን እያረጋገጡ ይህን ቀጣናዊ የትስስር ልማት ለማስቀጠል የኤርትራንም ይሁን የተላላኪዎቹን ጣልቃ ገብነት አይፈልጉትም። ይሀም የኢትዮጵያ መንግስት በቀጣናው ውስጥ በሁሉም መስኮች ያለውን ተሰሚነት የሚያሳይ መሆኑን አቶ ነዓምንና አምሳያዎቻቸው ሊያውቁት የሚገባ ይመስለኛል። እርሳቸው ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጋዜጠኛው እንኳን ሳይቀር የሞገታቸው መነሻው ይህን እውነታ ስለሚያውቅ ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy