Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምሶሶው

1 402

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምሶሶው

                                                     ደስታ ኃይሉ

ባለፉት 16 ዓመታት በአገሪቱ ለተመዘገበው እድገት ግብርናው ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በተለይም በሁለተኛው የዕድገት ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትግበራ ዘመን የአትክልት ምርት እንዲጨምር ለማድረግ የአነስተኛ መስኖ ልማት፣ የምርጥ ዘርና የግብርና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብሮች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

እነዚህ ተግባራት በ2007 ዓ.ም በአትክልት ዘርፍ በሄክታር ይገኝ የነበረውን 106 ኩንታል በ2012 ዓ.ም ወደ 142 ኩንታል ያሳድጉታል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም በቤተሰብ ደረጃ ብዙዎችን የምግብ ዋስትና እንዲያረጋግጡ በማድረግ ግበርና የኢኮኖሚያችን ምሶሶ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው።

እንደሚታወቀው የሀገራችንን ኢኮኖሚ ትርጉም ባለው ደረጃ ለማሳደግና ህዝባችንን ከድህነት ለማውጣት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት መስጠት የግድ ይላል። በመሆኑም መንግሥት ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተገንዝቦ ሲሰራ ቆይቷል። በያዝነው ሁለተኛው የልማት ዕቅድ ላይም የተገኘውን አመርቂ ውጤት ይበልጥ አጎልብቶ ለመቀጠል እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ።

የግብርና ልማት መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ይችል ዘንድ በበሁለተኛው አምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትኩረት ተሰጥቶታል። እንደሚታወቀው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም የአርሶ አደሩ ጉልበት አለ።

በአገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ይህ ግብርናው ውጭ ከፍተኛ እምቅ ሃብት ነው። ይህ ሃብት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ሲሆን፤ ገና ምንም ያልተነካ እምቅ በመሆኑም ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው። ሀገሪቱን ለመለወጥ ወሳኙ ሃብት ተደርጎ መወሰዱም እንዲሁ።

ይህን መነሻ ታሳቢ ባደረገ ሁኔታም በያዝነው አምስት ዓመታት የግብርና ዘርፍ በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ የስምንት በመቶ ዕድገት የሚያስመዘግብ ይሆናል። ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚቻል ዕቅድ ተይዟል። በዚህም መሠረት የግብርናን ዘርፍ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት በመሠረታዊ አማራጭ ከነበረው ስምንት በመቶ ወደ 11 በመቶ ከፍ ከፍ እንዲያደርገው ዕቅድ ተይዟል። ይህ ዕቅድ ይሳካ ዘንድም በዋናነት አስተዋፅኦ የሚያደርጉት ዋነኛ የሰብል ምርቶች በ16 በመቶ ያድጋሉ ተብለው ይጠበቃሉ።

የዋነኛ የሰብል ምርቶች ከጠቅላላው የግብርና ምርት ተጨማሪ እሴት ያላቸው ድርሻ በአማካይ 40 በመቶ ይሆናል። በዚህ ምክንያት ይህ የዕድገት ጭማሬ በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕድገት ላይ ሊኖረው የሚችለው ግብረ መልስ ሳይካተት በግብርና ዕድገት ምክንያት ብቻ በዕቅዱ ዘመን አማካይ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በከፍተኛ የዕድገት አማራጭ 12 ነጥብ ሁለት በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ያም ሆኖ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም ግብርና በጥቅሉ ዋነኛው የዕድገት ምንጭ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው።

ይህን ለመከወንም መንግሥት ለዘመናዊ ግብርና ያልተደፈረውን የአገሪቱን አርሶ አደር የአስተራረስ ዘይቤ የመለወጥን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በቀየሰው መስመር እነሆ የሚታየ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው። አርሶ አደሩ በድርቅ በቀላሉ መጠቃት ምክንያቱም ደግሞ የዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ አለመኖር እንደሆነ ተረጋግጧል።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ኑሮው እንዲሻሻል ተገቢ ትኩረት አግኝቷል። ለዚህም በቂ ማሳያዎችንም ማቅረብ የሚቻል ይመስለኛል። መንግሥት የዘመናት ቁጭቱን አገራዊ መሠረት ባላቸው አቅጣጫዎች የመፍታት ትግሉን እያካሄደ ነው። አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን የመጀመሪያው የልማት ዕቅድ አረጋግጧል።

መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን የመንግሥትን ፖሊሲ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ተችሏል። የሚታይና አሳማኝ ውጤት ማምጣትም እንደተቻለም ከአርሶ አደሩ በላይ ምስክር የሚያሻው አይመስለኝም።

ምንም እንኳን ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች ስህተት ፈላጊ ሆነው ቢቀጥሉም፤ በግብርናው ዘርፍ ባመጣነው ለውጥ ብዙዎች በመስማማት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ፣ ለምርቱ ገበያ በማመቻቸትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን አሳድጋ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ትገኛለች።

አርሶ አደሩ የለውጥ መስመሩን ተረድቶ በእምነት ወደ ሥራው በመግባቱ በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ ለማምረት ችሏል። እንዲሁም በከርሰ ምድርና በገጸ -ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር አከናውኗል። በውኃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች ማቅረብ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሥራው ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል። ለገበሬው በዚያው ልክ ገበያው ተመቻችቷል።

አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ አማካይነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል። በዚህም ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው። የግብርናው ዘርፍም በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያው ሳያሳስበው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ አተኩሮ ለልማት ለውጥ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል።

አርሶ አደሩን በማህበር የማደራጀት ሥራ በተናጠል ሊፈቱ ያልቻሉ ችግሮች በጋራ እንዲፈታ አስችሎታል። መንግሥት ያቋቋመው የምርት ገበያም በተለይ ቡና፣ ሰሊጥ፣ በቆሎና ቦሎቄ በዘመናዊ ግብይት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት አረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሩ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የማድረግ ጥረት ለምርታማነቱ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።

መንግሥት ባስቀመጣቸው የግብርናው ዘርፍ የልማት ፕሮግራሞች፣ ስትራቴጂዎችና መርሀ ግብሮች በመጠቀም ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮችን በማበረታታትና በመሸለም በርካታ ውጤታማ አርሶ አደሮችን ለማፍራት ተችሏል። ሽልማቱ ብዙዎችን አነሳስቷል። በአሁኑ ወቅትም በርካታ ሞዴል አርሶ አደሮች በመፍጠርም ላይ ይገኛሉ። ስለሆነም በሂደት የተጎናፀፍነው ድል ለላቀ ሁለተኛው ዕቅድ እንዳነሳሳን ግልፅ ነው።

ከዚህ አኳያ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በትክክል ውጤትማ እየሆኑ ነው። በአፈጻጸሙ ከተጠበቀው በላይ መጓዙን መረጃዎች ያመለክታሉ። በሁለተኛው የልማት ዕቅድ ዘመንም ይህን የምርትና ምርታማነት ዕድገት መጠን ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟል።

ከዚህ ጎን ለጎንም የግሉ ዘርፍ በግብርናው ውስጥ መሳተፍ የጀመረው በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ውስጥ ነው። ከእነዚህ ዘርፎች ውጪ ባለሃብቱ የግብርና ልማት ውስጥ መሳተፍ የጀመረው በመንግስት በኩል በመስኩ በተደረገው የማበረታቻ ጥረት መሆኑ ይታወሳል። እነዚህን ባለሃብቶች ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ ተግባራትን ለመከወን እየተሰራ ነው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግስት እየተከተለ ባለው የግብርና ልማት ስትራቴጂ ትርፍ አምራች ዜጋዎችን ምፍጠር ተችሏል። እነዚህ አባቢዎች በድርቅ የተጎዱት አካባቢዎችን እየሸፈኑ ነው። ይህም የድርቅ አደጋ ተጋላጭነት ቢኖርም ችግሩን በራስ አቅም ለመቋቋም አስችሏል። ለዚህ መሰረቱ ደግሞ የኢኮኖሚያችን መሰረት የሆነው የግብርናው ዘርፍ ነው።

ይህን የአገራችንን 85 በመቶ ያህል ህዝብን ያቀፈ ዘርፍ ይበልጥ ማጎልበት የአገርን ኢኮኖሚመ ማሳደግ ነው። መንግስታዊ ትኩረቱ አርሶ አደሩን የምርቱ ተጠቃሚ በማድረግ ይበልጥ በዘመናዊ አሰራሮች እንዲሰራ ማድረግ ያስፈልጋል። መዋቅራዊ ሽግግር በመፍጠር የአገራችንን ህዳሴ የሚያሳልጥ ተግባር ነውና።

 

  1. milkyas says

    that is good

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy