Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምቹ ሁኔታ ፈጣሪው

0 256

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምቹ ሁኔታ ፈጣሪው

                                                       ሶሪ ገመዳ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚነሳው የህዝቡ የሰላም ባለቤትነት እውን ሲሆንናና አፈጻጸሙ ተገምግሞ አላስፈላጊ መሆኑ ሲረጋገጥ መሆኑ ግልፅ ነው። እስካሁን ባለው ሂደት ሕዝቡ ሰላሙን ለመጠበቅ ኃላፊነቱን እየተረከበ መጥቷል። የአዋጁ ዓላማ ይህንኑ ሁኔታ ማመቻቸት ነው።

አሁን በምንገኝበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰላምን እያረጋገጠ ነው። በአገሪቱ ላይ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ ማስቆም ችሏል። ወላጆች ያለ ምንም ስጋት ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክ ችለዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም ኮማንድ ፖስቱ ከህዝቡ ጋር እየተወያየ ሕዝቡ የየአካባቢውን ሰላም ጥበቃ በባለቤትነት እንዲይዝ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ላይ ይገኛል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፈፃሚና ባለቤት ህዝቡ እየሆነ ነው። ይህ ህዝብ ትናንት በሰላም እየኖረ ሀገሩ ውስጥ ከተገኘው ልማት በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ የመጣ መሆኑን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ሲናገር እያደመጥን ነው። በዚህም ህዝቡ በየትኛውም መስፈርት ለሰላም እንጂ ለሁከትና ለብጥብጥ ቦታ የሌለው መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ገቢራዊ በሆነባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ ሁከት ተፈጥሮ በነበረባቸው አንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ሰላምና መረጋጋት ዕውን እንዲሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑ እየተገለፀ ነው። ለዚህም ይመስለኛል—በቅርቡ የፌዴራል አቃቤ ህግ ዋና አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ በሆነባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ ለተገኘው ውጤት የህዝቡ ሰላምን የመሻት ፍላጎት መሆኑን አስረግጠው የተናገሩት።

በእነዚህ ጊዜያቶች ውስጥ አዋጁን የተላለፉና በህዝቡ ጥቆማና የማጋለጥ ስራ በህግ ጥላ ስር የዋሉት ግለሰቦች ጉዳያቸው እየታየ ሲሆን፤ ወደፊትም ኮማንድ ፖስቱ ከህዝቡ ጋር በመሆን የሀገራችንን ሰላም አሁን እየተገኘ ካለው ይበልጥ አስተማማኝ የማድረግ ስራዎችን ያከናውናል። ይህ ደግሞ ልክ በሰላም ወዳዱ ህዝቡ ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚታጀብ በመሆኑ፤ ሁከት ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎችና በመላው የሀገራችን ክፍሎች አስተማማኝ ሰላምን ለመጎናፀፍ የሚያስችል አካሄድ ይመስለኛል።

በእኔ እምነት እነዚህ በጥቂት ቀናት ውስጥ የተገኙት ሰላምን ዕውን የማድረግና የህዝቡን ዕለታዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔዎችን የማይፃረሩ ድርጊቶችን የመከላከል ብሎም አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራ አማካኝነት ሀገራችን ወደ ምትታወቅበት የሰላም ተምሳሌትነቷ መመለሷ አይቀሬ ነው።

እንኳንስ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውና ላለፉት 27 ዓመታት የተገኘውን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶች በማናቸውም ሳንካዎች እንዳይደናቀፉ በሚሻ ህዝብ ባለበት ሀገር ውስጥ ቀርቶ፤ በየትኛውም ሀገር ውስጥ ቢሆን ይህን መሰሉ የህዝቡን ሰላም የሚያረጋግጥ አዋጅ ተፈፃሚ መሆኑ የሚቀር አይደለም።

ያም ሆነ ይህ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በህዝቡ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉትን ብዥታዎች ለማጥራት ያለመ መሆኑ መዘንጋት ያለበት አይመስለኝም። ለምሳሌ ሁከት በተፈጠረባቸው ቦታዎች ብጥብጡን ሲመሩ የነበሩ አንዳንድ በውጭ የሚገኙ ፅንፈኛ ኃይሎችና የውስጥ አምሳያዎቻቸው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአሁኑ ወቅት አገራችን ውስጥ በህዝቡ ድጋፍ እየፈጠረ ያለው የሰላም ድባብ ስላበሳጫቸው በአዋጁ ዙሪያ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን እያራመዱ ነው። ይህ ፍላጎታቸው ደግሞ አገራችን ሁሌም በሁከትና በብጥብጥ ውስጥ እንድትኖር ካላት ፍላጎት የተነሳ ነው።

ህዝቡ ላለፉት 27 የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት የተራመዳቸው ተስፋ ሰጪ መንገዶች እንዲሁም አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ ዛሬ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ይገነዘባል። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን ዋቢ በማድረግ መግለፅ የሚችል ነው።

የሀገራችን ህዝብ በመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ በተከናወኑት ልማት ተግባራት ራሱ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ ነው። ሀገሩም በልማቱ መስክ የአፍሪካ ተምሳሌት ሆናለች። የቀጣናውን ሀገራት በልማት ለማስተሳሰር በምታደርገው ጥረት ተጠቃሽ መሆኗንም ያውቃል። በአረንጓዴ የልማት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመሪነት ሚናዋን እየተጫወተችም እንደሆነ ይገነዘባል።

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ የቀጣናውን ሀገራት ሰላም እያስከበረችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት እንዳላትም ይረዳል። ይህ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ቁመናችን እንዳይሸራረፍም ሰላምን በፅኑ እንደሚሻ እሙን ነው። ባለፉት አስር ወራቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን ገቢራዊ ለማድረግ ያሳየው ቁርጠኝነት የዚህ እውነታ ማሳያ ነው።

ይህ አገራችን ሰላም መረጋገጥ መሰረቱ ህዝቡ መሆኑ አይካድም። በዚህም ሳቢያ ባለፉት አስር ወራቶች የሀገራችን ሰላም በመደበኛው ህግ ሊፈቱ ከሚችሉ ጥቃቅን ጉዳዩች ውጪ በአብዛኛው ወደ ነበረበት የተመለሰው ህዝቡ ለሰላም ካለው የማይናወጥ ፍላጎት የመነጨ ነው።

ሰላምን በፅኑ የሚሸው የሀገራችን ህዝብ ደሙን ዋጅቶና አጥንቱን ከስክሶ ያመጣው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መንገድ እንዳይደናቀፍ እንዲሁም የኋሊት እንዳይቀለበስ አይፈቅድም።

ከዚህ በላይም ህዝቡ ቀደም ሲል ያነሳቸው የነበሩት ጥያቄዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የስራ ጊዜ እንደሚመለሱ በሚገባ ያውቃል። ወቅታዊ የሆኑት የወጣቶች ህጋዊ ተጠቃሚነት ጉዳይና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እነደሚመለሱ ያውቃል።

በተጨማሪም እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ ግጭቶች እንደሚስተካከሉና ማንነትን ለይቶ የሚከናወኑ ጥቃቶች እንደሚቀሩ ይገነዘባል። እነዚህና ሌሎች የህዝቡ ጥያቄዎችን በተገቢው መንገድና በውይይት ምላሽ እንዲያገኙ አዋጁ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ስለሚያውቅ ከአዋጁ ጎን ተሰልፏል። አፈፃፀሙንም በራሱ እየተከታተለ ነው።  

እዚህ ላይ አንድ እውነታን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይኸውም አዋጁ ሊነሳ የሚችለው ህዝቡ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በሚያደርገው ቅንጅታዊ ስራ በአገራችን ውስጥ አስተማማኝ ሰላም ሲፈጠር መሆኑን ነው። ለአዋጁ መታወጅ ምክንያት የሆኑት ጉዳዩች በአስተማማኝ ሁኔታ ሲወገዱም ጭምር ነው።

ከዚህ ውጭ የትኛውን አካል ለማስደሰት አዋጁን ማንሳት አይቻለም። አሊያም አንዳንድ አካላትን ለማስከፋት ሲባል አዋጁ ባለበት እንዲቀጥል አይደረግም። ዋናው ጉዳይ የህዝቡ ሰላም አስተማማኝ መሆኑ ሲረጋገጥና አገራችንም ወደ ተለመደው ሰላማዊ ምህዳር በአስተማማኝ ሁኔታ ስትገባ ነው። በህዝቡ ጥረት ይህ እንደሚሆን መጠራጠር አይገባም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy