Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምንም ደሃ ብንሆን እንሰራዋለን

0 549

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምንም ደሃ ብንሆን እንሰራዋለን

አለማየሁ አ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ 7 ዓመታትን አስቆጠረ። የግድቡ ግንባታ የተጀመረበት 7ኛ ዓመት መጋቢት 24፣ 2010 ዓ/ም በጉባ ተከብሯል።  አሁን የግድቡ ግንባታ ሊጠናቀቅ 35 በመቶ ብቻ ይቀረዋል።

ታለቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጀምሮ በዓመቱ የመጎብኘት እድል አግኝቼ ነበር። በዚህ ወቅት ግድቡ የሚያርፍበትን ጠንካራ የመሬት ወለል ለማግኘት ቁልቁል መሬት ሲማስ ነበር የተመለከትኩት። በወቅቱ በአካባቢው የነበረውን ሁኔታ ተመልክቶ ግድቡ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት አዳጋች ነበር። በ2007 ዓ/ም 9ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ በተከበረበት ወቅትም፣ ከ3 ሺህ በላይ ቁጥር ካላቸው ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልዑካን ጋር ግድቡን ጎብኝቼ ነበር፤ በዚያው ግድቡ በሚሰራበት ጉባ አድረን። ያኔ ምሽት በግድቡ ላይ ነበር ፌስቲቫል የተዘጋጀው። ከጥልቁ የግድቡ መሰረት ሽቅብ መወጣት ጀምሮ የነበረው የግድቡ የያኔ አናት ላይ ነበር ከ3 ሺህ በላይ ህዝብ ደማቁን ፌስቲቫል የታደመው። ይህ የያኔ የግድቡ አናት ስፋት ሮጠው የማይጨርሱት የድንጋይ ሜዳ ነበር።

ከአንድ ዓመት በፊትም በተመሳሳይ ግድቡን የመጎብኘት እድል አግኝቼ ነበር። በመጀመሪያው ቁልቁል ይታይ የነበረው የግድ ስራ አሁን ሽቅብ በመቶ ሜትሮች አንጋጠው የሚመለከቱት ኮረብታ ሆኗል። እጅግ ግዙፍ ግርማ ሞገስ ያለው ሆኖ ከአባይ ወንዝ ማዶና ማዶ የሚተያዩትን ተራራዎች ታኮ ቆሟል። አሁን በቅርቡ ደግሞ ግራ ቀኝ የሚደገፋቸው ታራራዎች ላይ የመጨረሻው ከፍታ ላይ ደርሷል። ከዚህ በተጨማሪ የኤሌትሪክ ማመንጫ ዩኒቶችና የሃይል ቤቶቹ እየተገነቡ ነው። አሁን ወሃው በየት ገብቶ፣ ሃይል እንደሚያመነጭ፣ ሃይል አመንጭቶ ሲያበቃ በየት በኩል እንደሚወጣ ይታወቃል።

ይህ ብቻ አይደለም። የህዳሴው ግድብ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር የሚያመነጨውን ሃይል ተሸክሞ የሃገሪቱ የኤሌትሪክ ሃይል ቋት ውስጥ የሚያስገባው ባለ 500 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ተዘርግቷል። ይህ የኤሌትሪክ ማስተላለፊያ መስመር አሁን ለግድቡ የሚያስፈልገውን ሃይል ከጣና በለስ የሃይል ማመንጫ ወደግድቡ ግንባታ ስፍራ እያደረሰ ነው። ግድቡ እንደተጀመረ የሚያሰፈልገውን ሃይል ያመነጩ የነበሩ 11 ያህል ግዙፍ የዲዝል ጄኔረተሮች አሁን አርፈዋል። ይህ የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ግድቡ ሲጠናቀቅ ደግሞ የሚያመነጨውን ሃይል ይዞ ይወጣል።

ግድቡ የሚጠበቅበትን 6450 ሜጋ ዋት ሃይል ለማመንጨት የሚያስችለውን ውሃ እንዲይዝ ውሃውን በሚያቅፉት ተራራዎች መሃከል ያለን ውሃ የሚያሾልክ ክፍተት የሚደፍን የኮርቻ  ቅርጽ ያለው አቃፊ ግድብ ግንባታም ወደመጠናቀቁ እየደረሰ ነው። አሁን የህዳሴው ግድበ ከሁለት ሶስት ዓመታት በኋላ እውን እንደሚሆን የግድቡ ባለቤቶች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እርግጠኞች ሆነዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ለኢትዮጵያውያን ሃብትም የብሄራዊ ኩራት አርማም ነው። የህዳሴው ግድብ ቢያንስ ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል 6450 ሜጋ ዋት ታዳሽ የኤሌትሪክ ሃይል ያመነጫል። ይህን የኤሌትሪክ ሃይል በነዳጅ ብንመነዘረው መቶ ሚሊየን በርሜሎች ይሆናል። በመቶ ሚሊየን በርሜል የሚለካ የነዳጅ ክምችት ማግኘት ለማንኛውም ሃገር ታላቅ የምስራች ነው። የህዳሴው ግድብ ይህን ያህል ትልቅ ሃብት ነው፤ ጭስ አልባ ነዳጅ።

ኢትዮጰያ ከአስር ዓመታት በፊት ታመነጭ የነበረው ጠቅላላ የኤሌትሪክ ሃይል ከ300 ሜጋ ዋት አይበልጥም ነበር። ያኔ ሃገሪቱ የኤሌትሪክ ሃይልን ጥቂት ከተሞቿን ከማብራት ያለፈ ለጉልበትነት መጠቀም የሚያስፈልጋት የኢንደስትሪ እድገት ደረጃ ላይ አልደረሰችም። አሁን ሃገሪቱ ከ4 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ሃይል ታመነጫለች። ይሁን እንጂ ከ10 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀረ አሁን  የሃይል እጥረት ስጋት አለ።

አሁን ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደኢንደስትሪ እያሸጋገረች ነው። እስካሁን ተገንብተው ወደስራ ከገቡት አራት ያህል ግዙፍ የኢንደስትሪ ፓርኮች በተጨማሪ በአስራዎቹ የሚቆጠሩ ተመሳሳይ ፓርኮች ይገነባሉ። በአስራዎቹ የሚቆጠሩ የግብርና ማቀነባባሪያ የኢንደስትሪ መንደሮችን የመገንባት እንቅስቃሴም ተጀምሯል። እነዚህ የኢንደስትሪ መንደሮች እያንዳንዳቸው ከአስር ዓመት በፊት በአጠቃላይ ሃገሪቱ የምታመነጨውን ሃይል ያህል የሚፈልጉ ናቸው። ከእነዚህ የኢንደስትሪ ፓርኮች በተጨማሪ በተናጥል የሚገነቡ የብረታብረት፣ የሲሚንቶና መሰል ግዙፍ ፋብሪካዎች አሉ። ከፍተኛ ሃይል የሚጠቀሙ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችም ይካሄዳሉ።

ይህን የእድገት ጉዞ እውን ማድረግ ካለኤሌትሪክ ሃይል የማይታሰብ ነው። እናም የህዳሴው ግድብ አሁን ባለነበት ሁኔታ የሃገሪቱን እድገት የሚያንቀሳቅስ ተስፋ ነው። እርግጥ የህዳሴው ግድብ የሚያመነጨው ሃይል ለዘለቄታው በቂ ነው ማለት ሳይሆን፣ ለመጀመሪያ እመርታዊ እርምጃ ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ ከውሃ ብቻ 45 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ የግዙፍ መሰረተ ልማት ግንባታ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረገበት ፕሮጀክትም ነው። ይህ በራሱ የቀጣይ እድገት ግብአት የሚሆን የሰው ሃይል የሚፈጥር እድል ነው። ግደቡ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር በቀጥታና በተዘዋዋሪ በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል። የህዳሴው ግድብ የሚሰራው ሃይቅ ለመዝናኛነትም ስለሚውል በቱሪዝም ልማት የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል። በሺህ የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች አሳ በማስገር ስራ ላይ የመሰማራት እድል ያገኛሉ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም የሚሻገር እሴት አለው፣ የሃገራዊ መግባባትና ኩራት ምንጭ ነው። ይህ የሆነው የኢትዮጵያውያንን በአባይ ተፋሰስ ወንዞች የመጠቀም መብት ሸብቦ የነበረው ድህነት የተሸነፈበት በመሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ወደሱዳንና ግብጽ ለሚፈሰው የአባይ ውሃ 80 በመቶ ያህል ውሃ የምታበረክት ቢሆንም፣ ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያን ሳያካትቱ የውሃ ድርሻ ውል ተስማምተው ነበር። በዚህ ስምምነት ለኢተዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ወንዞች ውሃ የመጠቀም መብት እውቅና ነፍገው ነበር። ኢትዮጵያ በዚህ ስምመነት ውስጥ ስላልተካተተች ስምምነቱ የማይገዛት ቢሆንም፣  ስምምነቱ የአባይ ተፋሰስ ወንዞቿን ለማልማት የሚያስፈልጋትን ገንዘበ እንዳታገኝ ዓለም አቀፍ ጫና የማሳደር አቅም ነበረው። መንግስታትም ሆኑ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ኢትዮጵያ የአባይ ተፋሰስ ወንዞቿን ለማልማት የምታቀርበውን የብድር ጥያቄ አይቀበሉም፤ መጀመሪያ ግብጽ መፍቀድ አለባት የሚል ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ። ሃገሯ የሚደርሰው የአባይ ውሃ ላይ ታሪካዊ የባለቤትነት መብት አለኝ የምትለው ግብጽ ደግሞ ፍቃድ አትሰጥም። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይህን ገደብ በመስበር ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም ለማስገንባት መወሰናቸው የሃገራዊ ኩራት መንጭ ያደርገዋል።

የዛሬ ሰባት ዓመት የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት ወቅት ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ያደረጉት ንግግር ይህን ሁኔታ በግልጽ የሚያሳይ ነበር። መለስ ዜናዊ ባደረጉት ንግግር፤

. . . ግድቡን ለመስራት ብድርና እርዳታ እንዳናገኝ የተለያዩ ሃይሎች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ምክንያት የፕሮጀክቱን ወጪ ለመሸፈን የሚተባበረን ሃገር ወይም ተቋም ማግኘት አልቻልንም። ስለሆነም ወጪውን ብቻችንን ከመሸፈን አልፈን በራሳቸን ቁጠባ ለመሸፈን የምንገደድበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪ ከ3 ቢሊየን ዩሮ በላይ ወይም ከ78 ቢሊየን ብር በላይ በመሆኑና ከዚህ ፕሮጀክትም ባሻገር ሌሎች በራሳችን ወጪ ልሸፍናቸው የሚገቡ በርካታ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው ወጪውን መሸፈን እጅጉን እንደሚከብደን ጥርጥር የለውም። ሸክሙን ለማቃለል ያደረግነው ጥረት ስላልተሳካና ያለፉት ሃምሳ ዓመታት ታሪካችን እንደማይሳካ ያረጋገጠልን በመሆኑ የሚኖረን አማራጭ አንድም ግድቡን አለመስራት ነው፤ አለበለዚያ እንደምንም በራሳችን መሸፈን ነው።

ከእአነዚህ ከባድ ሁለት አማራጮች መሃከል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ የትኛው እንደሚሆን ግልጽ ነው። በተለመደው ወኔው ‘ምንም ያህል ደሃ ብንሆን፣ ድህነታችንን ለማስወገድ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን። ስለዚህ ፕሮጀክቱ መሰራት አለበት’ እንደሚል ለአፍታም ያህል አልጠራጠርም።

ነበር ያሉት።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝብ በአባይ ተፋሰስ ውሃ እንዳይጠቀም አግዶት የነበረውን እጦት ለመስበር ተረባረበ። ከህጻናት እስከአዛውንት፣ ከመጨረሻው ደሃ እስከ ባለጸጋ፣ ምሁራን፣ የእምነት ኣባቶች ወዘተ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ግድቡን ለማስገንባት ቦንድ በመግዛት ድጋፍ አደረገ። እስካሁን ከህዝብ የቦንድ ግዢ ከ10 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል። በ2010 ዓ/ም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 837 ሚሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል። በዓመቱ መጨረሻ ላይ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል። በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን ባለፉት 7 ዓመታት የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የህዳሴ ግድብ ቦንድ ገዝተዋል።

እነሆ ምንም ደሃ ብንሆን ድህነታችንን ለማሰወገድ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ያሉ ኢትዮጵያውያንውያን ያላቸውን በመቆጠብ ያስጀመሩት ግድብ ሊጠናቀቅ 36 በመቶ ብቻ ቀርቶታል። እንዳጋመሱት እንደሚጨርሱትም እርግጠኞች ናቸው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy