Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላምና ህዳሴያችን

0 309

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላምና ህዳሴያችን

                                                        ታዬ ከበደ

ኢህአዴግና መንግሥት በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰቱትን ችግሮች አንድ በአንድ በመለየት እና ለችግሮቹም መፈጠር መንስዔው የአመራሩ ድክመት መሆኑን በግልጽ በመቀበል ችግሮቹ የሚፈቱባቸውን አቅጣጫዎች አስቀምጠው ወደ ሥራ ገብተዋል።

ይሁን እንጂ እንቅስቃሴው በተጀመረ ማግስት በተከሰተው የሰላም እጦት የተነሳ በቅድሚያ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ በማስፈለጉ ትልቁ ትኩረት ሰላምን በማስፈን ላይ በማድረጋቸው ከህዝቡ ጋር በመሆን ውጤት ማምጣት ችለዋል። በዚህም በአሁኑ ሰዓት በአገራችን በሁሉም አካባቢዎች ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም መንግስትና ህዝብ የጀመሩትን የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። እናም ህዝቡ ከገዥው ፓርቲና ከመንግስት ጋር በመሆን በአንድ በኩል ሰላሙን እየጠበቀ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ህዳሴውን ማፋጠን ይገባዋል።

እርግጥ ሰላም ከሌለ ምንም ዓይነት ተግባር መከወን አይቻልም። እንኳንስ በአገር ደረጃ አንድ ነገር ማከናወን ቀርቶ በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ወጥቶ መግባት አስቸጋሪ ይሆናል። የሰላምን ጠቀሜታ መለኪያ ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ የሚያውቀው የለም። ይህ ህዝብ ከትናንት በስቲያ በፊውዳላዊው አገዛዝ ስር የማቀቀ፣ ትናንት ደግሞ በአምባገነኑ የደርግ ስርዓት የአፈና መዋቅር ውስጥ ሁለንተናዊ መብቶቹ ተረግጠው በስቃይ ውስጥ የኖረ ነው።

ይህ ህዝብ የደርግን የጭቆና ቀንበርና ስቃይ አልቀበልም ብሎ ደርግን በሚገባው ቋንቋ ለማናገር ለ17 ዓመታት ያህል በጦርነት ውስጥ ያለፈ ነው። ጦርነት ምን ያህል አስከፊ፣ ምን ያህል የሰው ህይወት ቀጣፊ፣ ምን ያህል ንብረት አውዳሚና ትውልድን አሸማቃቂ መሆኑን ለዚህ ህዝብ መንገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ይሆንብኛል። እናም ዛሬ ላይ በሀገራችን ውስጥ አንዳንዴ በሚፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ ሰላም ሲታወክ ህዝቡ በግንባር ቀደምትነት የሰላሙ ባለቤት ሆኖ ቢቆም እምብዛም የሚደንቅ አይሆንም።

ትናንት ያለፈበት አስከፊ መንገድ ዛሬ ያገኘውን አስተማማኝ ሰላም ገለል አድርጎ ቦታውን እንዲረከበው ቅንጣት ያህል ፍላጎት የለውም። በትውስታነት የኋሊት የሚሸሸውና ዳግም እንዳይመጣም ዶሴውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዘጋው የያኔው አባጣና ጎርባጣ መንገድ ተመልሶ እንዳይመጣ ለሰላሙ ፀር የሆኑ ሃይሎችን በማውገዝ፣ በማጋለጥና ተገቢውን ትምህርት እንዲወስዱ በማድረግ በባለቤትነት መንፈስ የመንቀሳቀስ ፍላጎቱ መሰረት ይኸው ይመስለኛል።

ለነገሩ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላም ይህን ያህል ዋጋ የሰጠው የሞት ሽረት ጉዳይ የሆኑትን ልማትንና ዴሞክራሲን ለማምጣት ያደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል የኋሊት እንዳይቀለበስበት ከመፈለግ ነው። ሰላም ከቁሳቁስ መጥፋትና መውደም ጋር ብቻ እንደማይያያዝ የሚገነዘበው፤ ነገ የሚገነባው ትልቅ ምጣኔ ሃብት ያለውና ለዘመናት ተነፍጎት የነበረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባት ስር እንዲሰድ ስለሚሻ ነው።

ይህ ህዝብ ላለፉት 27 ዓመታት ገደማ የተራመዳቸው የልማት አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ያውቃል። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን ዋቢ አድርጎ መቅረብ የሚችል ህዝብ ነው።

ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ካሉ፣ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግስት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና መደግ እንደሚቻል ሩብ ክፍለ ዘመንን እልፍ ባለ ዓመት ጊዜ ውስጥ ትምህርት ወስዷል።

የደርግ ሥርዓት ከመውደቁ በፊት የሀገራችን ምጣኔ ሃብታዊ አሃዝ ከዜሮ በታች እንደነበር የማይዘነጋው ይህ ህዝብ ስለሰላም ቢናገር የሚበዛበት አይደለም። አምባገነኑ ስርዓት እንደወደቀም በአንድ በኩል ሰላምን የማረጋጋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደቀቀውን ኢኮኖሚ ለማቃናት የከፈለውን ከባድ መስዕዋትነት በሚገባ ይገነዘባል።

ያኔ ተራራ የሚያክለውን የሀገሪቱን ድህነት ለመዋጋት የተለያዩ መርሆዎችን ቢሰንቅም የሚፈለገው ዓይነት ለውጥ እንዳልመጣና ለረጅም ጊዜ በሀገራችን ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን የድህነት አዙሪትን ለመቀልበስ እንዳልተቻለ በማወቁ ሌላ መንገድ እንዲቀየስ ማስፈለጉን የሚያስታውስ ህዝብ ነው። በመሆኑም በአንድ በኩል የሀገሪቱን ሰላም ማረጋጋትና የታጠቁ ሃይሎችን ወደ ልማት የማዞር ስራ፣ በሌላኛው ዘውጉ ደግሞ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን የማምጣትና ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲና ስትራቴጂን እውን ለማድረግ የወሰደው ጊዜና የጠየቀው ሁሉን አቀፍ መስዕዋትነት ከዚህ ህዝብ አዕምሮ ውስጥ የሚጠፉ አይመስለኝም።

ሰላሙም እውን ሆኖ የታሰበው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገብ ሂደት ውስጥ ሁሉም ዜጋ ድህነት በሚባለው አንገት አስደፊ በሽታ ላይ መዝመት ችሏል። ይህ ተግባርም መጠናከር አለበት። ምክንያቱም ይህ ህዝብ ህዳሴውን ውን ለማድረግ እየተጋ ያለ በመሆኑ ነው።

የዚህ ሀገር ህዳሴያዊ ዕድገት ማንም ተመኝቶት የሚያገኘው አይደለም። ዛሬ ምስጋና ለልማታዊው መንግስት ይግባውና በሁሉም ዘርፎች መጠነ ሰፊ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው። ዛሬ ሀገራችን የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተገቢው ሁኔታ አጠናቃ፤ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን ለማምጣት የተለመችበትን ሁለተኛውን የዕድገት ትልም ከተያያዘች ወደ ሶስተኛው ዓመት ተሸጋግራለች።

ታዲያ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አያሌ ለውጦች ተመዝግበዋል። ምንም እንኳን የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሀገራችን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት በኢኮኖሚው መስክ ሊፈጥረው የሚችለው እጅግ አነስተኛ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል የሚካድ ባይሆንም፤ ችግሩ ግን ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ የፈጠረ አይደለም።

በተለይም ከምርት አኳያ የተፈጠረ ችግር ባለመኖሩ በያዝነው ዓመትም ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል። ታዲያ ይህ የሚሆነው ሁሉም የህበረተሰብ ክፍል እድገትን ሊቀለብስ የሚችል ተግባሮችን መኮነን ሲችል ነው። ለአንድ የጋራ ሀገራዊ ዓላማ ያለ ንትርክ መደሰለፍ ሲችልም ጭምር።

ባለፉት 26 ዓመታት በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት የሀገራችንን ኢኮኖሚ ስር ከሰደደ ድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ እንዲሁም የህዝቡን ኑሮ ደረጃ በደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ የኢኮኖሚ ማህበራዊ የልማት ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ተቀርፀው ስራ ላይ ውለዋል።

ውጤታቸው ስኬታማ እንደነበርም ከእነዚህ ዓመታት በፊት የነበረችውንና የዛሬዋን ኢትዮጵያ በማየት መመስከር የሚቻል ይመስለኛል—“ማየት ማመን ነው” እንዲል ብሂሉ። የትናንቷ ኢትዮጵያ ከዛሬዋ ጋር የጎላ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ልዩነት አላት። ደርግ ከእነ ዕዝ ኢኮኖሚዋ ባለ ባዶ ካዝና አድርጓት ጥሏት የሄደው የትናንትዋ ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ላይ በበሊዮን የሚቆጠር በጀት መዳቢ ሆናለች። ይህም እዚህ ሀገር ውስጥ ህዝቦቿ በድንበር ምክንያት ሳይጋጩ በሰላማዊነታቸው ያገኙት ውጤት መሆኑ አይካድም።

ላለፉት ስምንት ዓመታት በላይ በሁለት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ውስጥ ያለፈችውና በማለፍ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ፤ የትናንት ቁስሏን ከመመልከት ይልቅ ህዘቦቿን በአንድነት እያሳተፈች በልማት ጎዳና በመገስገስ ላይ ትገኛለች። በዚህም ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ የምትሻለዋን ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ደፋ ቀና እያለች ነው። ይህ ጥረቷ እንዲሳካ ዜጎች ከመንግስት ጎን ሆነው ሰላማቸውን ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy