ሰላም ለሁላችን!
ገናናው በቀለ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፓርላማ ንግግራቸው የውጭ ግንኙነትን አስመልክቶ በተለይ ለኤርትራ መንግስት ያደረጉት ጥሪ በሁለቱ በታሪክና በደም በተሳሰሩ ህዝቦች መካከል የሻከረውን ግንኙነት ሊያሻሽል የሚችል ነው። ጥሪው በጦርነት ተዋግተው የበላይነትን መያዝ ቢያቅታቸውም በፕሮፓጋንዳቸው ህዝባችንን እያተራመሱ ያሉትን የሽብር ቡድኖች እንቅስቃሴ ሊያመክን የሚችል ነው። እንዲሁም በሁለቱም አገራት ህዝቦች መካከል አስተማማኝ ሰላምን ያመጣል።
በመሆኑም የኤርትራ መንግስት ለሰላም የቀረበለትን ጥሪ ደግሞ ደጋገሞ በማጤንና አቋሙን ሊያስተካክል የሚገባ ይመስለኛል። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሰላም ጥሪ ሁለቱንም ህዝቦች ይበልጥ የሚያቀራርብና በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረገው ትግል አንድ አካል ስለሆነ፤ የኤርትራ መንድሥት ጉዳዩን ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ ሊመለከተው ይገባል።
እርግጥ የኤርትራ መንግስት በቀጣናው ሀገሮች ላይ አሸባሪዎችን በመደገፍ የሚያካሂደው የትርምስ ስትራቴጂ፣ በተለይም እንደ አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ ኦነግና ኦብነግን የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖችን አሰልጥኖ በየጊዜው ወደ የሀገራችንን በማሰማራት ከሚያከናውነው ተግባር ግልፅ ነው። እነዚህ ሃይሎች መዋጋት አቅቷቸው መነሻው ከወደ አስመራ የሆነ ፕሮፖጋንዳን እያካሄዱ ነው። በዚህም ለህዳሴው እየተጋ የሚገኘውን የሀገራችንን ህዝብ በሁከት ተግባር ሲጠምዱት እንደነበር ግልፅ ነው። ሆኖም እነዚህ የከሰሩና ለባዕዳን የሚላላኩ ፖለቲከኞች ምንም ዓይነት ዘላቂ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ አይደሉም።
እንደሚታወቀው ሁሉ የኢፌዴሪ መንግስት በዓለም አቀፍ መርህዎች የሚመራና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ስላለው ግንኙነት የሚመራበት ግልፅ የሆነ መስመር አለው። በኢፈዴሪ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ላይ እንደተገለጸው፤ አገራችን ከማንኛውም አገር ጋር በጋራ ተጠቃሚነትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ግንኙነቷን ታከናውናለች። ይህን አጠቃላይ መርህም ኤርትራ እንድትጠቀምበት ሲባል አገራችንን የመሩት ሶስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ቁርጠኛ የሰላም ሃሳባቸውን አንቀባርቀዋል። ቀደም ሲል ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት፣ ቀጥሎም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ “አስመራ ድረስ ሄጄ ለመደራደር ዝግጁ ነኝ” የሚል ቁርጠኛ አቋማቸውን በመግለፅ እንዲሁም አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “…ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለአመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን። የበኩላችንንም እንወጣለን።…” ፅኑ የሰላም ፍላጎታቸውን አሳይተዋል።
ይሁን እንጂ በሻዕቢያ በኩል የተሰጠው ምላሽ ያውና አንድ ነው፤ ለመነጋገር ቅድመ ሁኔታን ማስቀመጥ። እንዲህ ዓይነቱ ተግባር የትም የሚያደርስ አይደለም። የኤርትራ ሹማምንቶች ስለ ሰላም ሲሉ ማናቸውንም ጉዳዩች ማከናወን ያለባቸው ይመስለኛል። የአገሪቱ ህዝብ በውስጡ እየተፈጠረበት ላለው ችግር የኢትዮጰያዊያን ወንድሞቹን ድጋፍ ይሻል።
እንደሚታወቀው ሁሉ የኤርትራ መንግስት ላለፉት 27 ዓመታት በተከተለው የአፈና አገዛዝ፣ የጦርነት ኢኮኖሚ ፍልስፍና እና የጥገኝነት ፖለሲ ሳቢያ በሀገሪቱ ውስጥ የፈጠረው ምስቅልቅል ውጤት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ይህ አካሄዱም ሀገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ውጥረትና የኢኮኖሚ ድቀት ማስከተሉ የአደባባይ ምስጢር ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ በአቶ ኢሳያስ ፈላጭ ቆራጭነት የሚመራው የኤርትራው አስተዳደር የሚከተለው የጥገኝነት ኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲሁም የሀገሩን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ ለማስተካከል ከመጣር ይልቅ፤ ከውልደቱ ጀምሮ በተጠናወተው የጦረኝነት አባዜ እየተመራ የትርምስ ስትራቴጂን ቀምሮ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
በዚህም ሳቢያ በሀገሩ ውስጥ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግና ከማስፋፋት ይልቅ መሳሪያ ገዝቶ አሸባሪዎችን በማስታጠቅ እንደ ምርት ወደ ጎረቤት አገሮች በመላክ ስራ ላይ ተተጠመደ መንግስት ስለሆነ ለሀገሩ ህዝብ ኑሮ መለወጥ የሚያስብበት ጊዜ የለውም። ይባስ ብሎም በህዝቡ ላይ የቋያ እሳትን በመለኮስና ስርዓቱን አስመልክቶ ትንፍሽ እንዳይል እግር ተወርች አስሮት አበሳውን ማብላት ስራዬ ብሎ ተያይዞታል። ዛሬ ግን ይህን ታሪኩን በመለወጥ ከኢትዮጵያዊያን ጋር መነጋገር ይኖርበታል።
እርግጥ የኤርትራ መንግስት የሚመራው ቡድን በመንግስትነት ራሱን ካደራጀበት ከዛሬ 27 ዓመት ጀምሮ በዜጎቹ ጉልበትና ዕውቀት እንዲሁም በሀገሩ ተፈጥሮአዊ ፀጋዎች ለማደግ ከማሰብ ይልቅ፤ በሌሎች ሀገራት አንጡራ ሃብት ላይ በጥገኝነት በመንጠላጠል ለመበልፀግ የሚፈልግ የቀቢፀ-ተስፈኞች ስብስብ ነው።
በዚህም ምክንያት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደ ካሮት ቁልቁል እያሳደገ ዛሬ ላይ ደርሶ ህዝቡን ለከፋ የኑሮ እንግልት ዳርጎታል። በዚህም ህዝቡ ክፉኛ ተማሯል። ከሻዕቢያው የአፈና ቀንበር ጋር ተዳምሮ ኑሮ የመርግ ያህል ከብዶታል። ስደትን እንደ ህይወቱ መቀየሪያ መፍትሔ በመቁጠርም በለስ ከቀናው ወደ ጎረቤት ሀገሮች ይተምማል። አገራችን ውስጥም በተፈጠረለት ምቹ ሁኔታ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ ይማራል። ይህም የሁለቱን አገራት ህዝቦች ትስስር የሚያጠናክረው ሆኗል።
እርግጥ የኤርትራ መንግስት ፍላጐቱን በአካባቢው ሀገራት ላይ በኃይል ለመጫን ይፈልጋል። ይህ ደግሞ ከትናንት ጀምሮ የተጣባው ተውሳክ ነው ማለት ይቻላል። ወታደራዊ ጀብደኝነትን እንደ “መጨረሻ ካርድ”ም ይመለከታል። እስካሁን ድረስ ጠብ የሚል ጥቅም ባያስገኝለትም።
ሻዕቢያ ከሁሉም ጐረቤቶቹ ጋር በፈጠረው ግጭት ከጋራ ጥቅም አኳያ ማግኘት ይገባው የነበረው ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት የለም፤ በራሱ ጊዜ አቋርጦታልና። በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር የነበረው ግንኙነት መቋረጡ ለኢኮኖሚው ማሸቆልቆል ቀዳሚው ተጠቃሽ መሆኑ በርካቶችን የሚያስማማ ጉዳይ ነው። ይህ ሁኔታም ፊቱን ወደ አረብ አገሮች በማዞር የተፈጥሮ ሃብቱን ጭምር በመሸጥ እንደ መተዳደሪያ ይዞታል። ከዚህ ይልቅ የኤርትራ መንግስት በኢፌዴሪ መንግስት የቀረበለትን የሰላም ሃሳብ ቢቀበል ተያይዞ ማደግ ይችላል። በማቅረብ ላይ የሚገኘው ቅድመ ሁኔታ ከዘላቂ ተጠቃሚነት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር አለመኖሩን በመረዳት ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ይገባዋል።
የኤርትራ መንግስት የኢፌዴሪ መንግስት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ በቀጣናው ሀገራት መካከል ሰላም ሰፍኖ ልማታዊ ትስስር እንዲጎለብት ፈርጀ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል። ውጤትም እያገኘበት ነው። በኤሌክትሪክ ሃይል፣ በየብስ፣ በባቡርና በሌሎች የመሰረተ-ልማት አውታሮች ቀጣናውን ለማስተሳሰር የሚያደርጋቸው ጥረቶች ተጠቃሽ ናቸው።
በመሆኑም ኤርትራ እንደ ማንኛውም ጎረቤት አር ከእነዚህ ትሩፋቶች እንድትጠቀም የሰላም ጥሪውን መቀበል ይኖርበታል። ሰላም ለሁላችንም ጠቃሚ በመሆኑ ከቁርቋሶ ወደ ተያይዞ ማደግ እንድንቀየር የኤርትራ መንግስት በእጁ ያለውን የሁከትና የትርምስ ኳስ አሽቀንጥሮ በመጣል ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት መትጋት ይኖርበታል።