Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስኬቶች ይዳብሩ፤ ተግዳሮቶች የሚከስሙ!

0 479

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስኬቶች ይዳብሩ፤ ተግዳሮቶች የሚከስሙ!

አባ መላኩ

አገራችን ባለፉት 27 ዓመታት በርካታ ስኬቶችንና ተግዳሮቶችን አሳልፋለች። ለአንድ አገር ስኬትም ሆነ ውድቀት ምክንያቱ የዜጋው (ትውልዱ) ጥንካሬና ድክመት ላይ የተመሰረተ ነው።  ያለፈውን ትውልድ አንዳንዴ እያመሰገናቸው አንዳንዴም ደግሞ እየወቀስናቸው ይኸው አሁን ድረስ ዘልቀናል። እነርሱ ለአገራቸው የመሰላቸውን ሰርተው አልፈዋል። ይህ ወቅት ደግሞ የእኛ ትውልድ ተራ ነው። እኛስ በነገው ትውልድ መነጽር እንዴት እንታይ ይሆን?  ብለን ራሳችንን ጠይቀን ይሆን? አንድ አባባል ትዝ አለኝ “ይሉሽን ባልሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ”።

 

በአድዋ ድል ጥቁሮች ሁሉ  የአባቶቻችንን ገድል ለዘለዓለም ይዘክሩታል፤ ስማቸውንም ያወድሱታል።  የእኛ ትውልድም ያከናወናቸው በርካታ ስኬቶች እንዳሉት ቅቡል ሃቅ ነው። ለአብነት እንኳን እናንሳ  ብንል ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ለዚህ ትውልድ ስም መጠሪያ ፕሮጀክት ነው። በዚህ ፕሮጅክት ሳቢያ ብቻ ቀጣዩ ትውልድ እንደሚያመሰግነን   በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ይሁንና በእኛ ትውልድ የተመለከትነው አሳፋሪ የሚባሉ ድርጊቶችም ተስተውለዋል። በማንነት ላይ የተመሰረተ ጥቃት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበርካታ የአገራችን አካባቢዎች በዘርና በሃይማኖት ላይ የተመሰረተ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ተመልክተናል። በዚህም ሳቢያ በርካታ ንጹሃን በማያውቁት ነገር እዳ ከፋዮች ሆነው ነበር።

 

እንደእኔ እንደኔ ይህ ወቅት ለአገራችን ስኬቶች መጎልበት  መልካም ነገርን ይዞ የመጣ ወቅት ነው ብዬ አስባለሁ። ዛሬ ላይ አገራችን  አዲስና ወጣት ጠቅላይ ሚኒስትር አገኝታለች። በበርካታ አካባቢዎች ይታዩ የነበሩ መደነቃቀፎች እልባትያገኙ ይመስላሉ። አገራችን እያስመዘገበች ያለችውን ስኬት ማጠናከር እንዲሁም ተግዳሮቶችን  ለመቅረፍ ጥረት እነደሚያደርጉ ከአንደበታቸው አድምጠናል። ባለፉት 27 ዓመታት አገራችን መሰረታዊ ለውጦች ካሳየችባቸውት ነገሮች መካከል ቀዳሚው ከዴሞክራሲ ስርዓት ጋር መተዋወቅና ህገመንግስታዊ አገር ለመሆን መብቃቷ፤ ፌዴራላዊ ስርዓት  በመተግበር ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደርና ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን ማሳደግ የሚችሉበትን ሁኔታ መመቻቸቱ ቀዳሚ ስኬቶች ናቸው። በዚህም ሳቢያ የአገሪቱን አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆም ምክንያት ሆኗል።  

 

ሌላኛው የአገራችን ስኬት ተደርጎ  ሊወሰድ የሚችለው ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉ ነው። የህዝቦች የዘመናት የነጻነትና እኩልነት ጥያቄ  ህገመንግስታዊ ዋስትና ባለው መልኩ ምላሽ ማግኘት በመቻሉ በአገራችን ዘላቂና ዋስትና ያለው ሰላም ማስፈን ተችሏል። በዚህም ሳቢያ ህዝብና መንግስት አትኩሮታቸውን ወደ ልማት ማድረግ በመቻላቸው  አገራችን ባለፉት 15 ዓመታት ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኤኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች። በዚህም በርካታ ዜጎች በፍጥነት በሚባል መልኩ ከድህነት መውጣት ጀምረዋል። በእርግጥ በርካታ ወገኖቻችን አሁንም  ከድህነት ወለል በታች እንደሆኑ ቢታወቅም ለውጡ የማይካድ ነው። አገራችን በያዘችው የእድገት ፍጥነት መጓዝ ከቻለች በመጪዎቹ አስርት አመታት ከከፋ ድህነት መላቀቅ እንደምትችል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።  አሁን ላይ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ27 ዓመታት በፊት ከነበረበት ከአራት እጥፍ በላይ ማሳደግ ተችሏል።

 

ባለፉት 27 ዓመታት በአገራችን ማህበራዊ መገልገያዎች መስፋፋት ማለትም በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል።  ትምህርት ከፍተኛ ለውጥ የታየበት ዘርፍ ነው። በትምህርት ላይ ማለትም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ከ31 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኛሉ። የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋን ከ95 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል።  በፌዴራል መንግስት ብቻ ወደ 50 የሚጠጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ። ዛሬ ላይ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች በመረጡት የትምህርት መስክ ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው። በጤናው ረገድም በአገራችን በርካታ ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ የዞን ሆስፒታሎች፣ ሪፈራል ሆስፒታሎች፤ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ፍተሃዊ በሆነ መንገድ መገንባት ተችሏል። በመከላከል ላይ መሰረት ያደረገው የአገሪቱ የጤና ፖሊሲ እጅግ ውጤታማ ሆኗል። ተላላፊ በሽታዎችን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል። በዚህም የህጻናትንና የእናቶችን ሞት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል።  

 

የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዕድገት የአገራችን ሌላው ስኬት ነው። አገሪቱን ፈርሳ እንደገና የምትገነባ እስክትመስል ድረስ በሁሉም አካባቢውች በርካታ ግንባታዎች በመካሄድ ላይ ናቸው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት መዲናዋን አዲስ አበባን ጨምሮ ትናንሽ ከተሞችን መመልከት መልካም ነው።  አዲስ አበባ ፈርሳ የምትገነባ ከተማ ሆናለች። የቀድሞ ደሳሳ ቤቶች እየፈረሱ በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ማህበራዊ መገልገያዎች፣ የንግድ ተቋማት ወዘተ በመገነባት ላይ ናቸው። በአፍሪካ በጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ረገድ እንደኢትዮጵያ መንግስት ጥረት ያደረገ ተጨባጭ ስኬትም ማስመዝገብ የቻለ  አንድም መንግስት አለ በዬ አላምንም። ይሁንና በአገራችን የግንባታው ዘርፍ ከዜሮ ሊባል የሚችል ደረጃ የተነሳ በመሆኑ አሁንም በአገራችን የግንባታው ዘርፍ ብዙ ስራ የሚጠይቅ ነው። በመሰረተ ልማት ግንባታ ማስፋፋት በተለይ በመንገድ ረገድም ሌላው የአገራችን ትልቅ ሰኬት ነው። አገሪቱን ከጎረቤት አገራት የሚያገናኙ ትላልቅ አውራ ጎዳናዎች፣ የባቡር ሃዲድ ዝርጋታ፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች (ኤርፖርቶች) ወዘተ በመገንባት  ላይ ናቸው። በመንገድ ደረጃ አርሶና አርብቶ አደሩን ጥቅም ታሳቢ ያደረጉ ቀበሌዎችን ከቀበሌዎች፣ ቀበሌዎችን ከወረዳዎች ወዘተ የሚያገናኙ በርካታ የገጠር መንገዶችን መገንባት ተችሏል።

 

መንግስት የሃብት ክፍፍሉ ፍተሃዊ ለማድረግ በርካታ ሃብትን የሚያፈሰው መሰረተ ልማት በማስፋፋት፣ የትምህርትና ጤና ተቋማትን በመገንባት፣ መንገድ በማስፋፋት፣ የሃይል አቅርቦት በማሳደግ፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን በማስፋፋት ላይ ነው። ይህ ተጨባጭ እውነታ ነው። በትምህርትም ሆነ በጤና አገልግሎት ላይ የጥራት ችግር ቢኖርም በለፉት 27 ዓመታት አገራችን እነዚህን ዘርፎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማደረግ አኳያ  ስኬታማ መሆን ችላለች። አዲሱ አመራር ህብረተሰቡን በማስተባበር እነዚህን ስኬቶች ማሳደግ ይጠበቅበታል።

 

በእኔ እይታ ባለፉት 27 ዓመታት አገራችን ገጠሟታል ብዬ ከማስባቸው ጉዳዮች መካከል አንኳር የሆኑትን ለመጥቀስ ያክል በ1983 ዓ.ም አምባገነኑ ደርግ ስርዓት ውድቀትን ተከትሎ የነበሩ በርካታ የታጠቁ አካላት አገሪቱን ለመቀራመት ያደረጉት ትንቅንቅ፤ የኤርትራ መንግስት  በአገራችን ላይ የፈጸመው ወረራ፣ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ማብቃት ተከትሎ በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል፤ የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ በአገራችን የተነሳው ሁከት ናቸው። ይሁንና መንግስትና ገዥው ፓርቲ በተከተሉት የሰከነ አካሄድ እነዛን ከባድ ወቅቶች ማለፍ ችለዋል።

 

ባለፈው ዓመት  ጀምሮ በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች የተነሱ ሁከቶች ሌላው የአገራችን ተግዳሮቶች  እንደሆኑ ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ሁከቶች መሰረታቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቢሆኑም አካሄዳቸው ግን  ጽንፍ የረገጠ እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ነው። የመልካም አስተዳደር ችግሮች በየትኛውም አገር የሚፈጠሩ ነገም የሚኖሩ መፍትሄም የሚሰጣቸው በሂደት እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው። ከዚህም ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግሮች በነውጥና ሁከት ምላሽ ሊያገኙ አይችሉም። መንግስትም ህዝብ የጠየቃቸውን የመልካም አስተዳደር ጠያቄዎች አድበስብሶ ከማለፍ ይልቅ ወቅታዊ ምላሽ ሊሰጥ የገባል። የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን መፍታት ወይም መፍትሄ ማፈላለግ የመንግስት ሃላፊነት  ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡም ጭምር ነው።

 

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት የመልካም አስተዳዳር ችግሮች የአንድ ወቅት ክስተቶች አይሆኑም። የዴሞክራሲ ባህላችን እየዳበረ  በሄደ ቁጥር ጠያቂ ህብረተሰብ ይፈጠራል፤ ጠያቂ ህብረተሰብ ደግሞ ትንሽም ቢሆን መብቱን መስጠት አይፈልግም። የመልካም አስተዳደር  ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በሁከትና ብጥብጥ ሳይሆን በመቀራረብና በመነጋገር ብቻ መሆን መቻል ይኖርበታለ። ከዚህም ባሻገር መንግስት የህግ የበላይነትን ከድርድር ማቅረብ የለበትም።     

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy