Artcles

በተቃራኒ ጽንፍ የረገጡት መች ሊረቡን!

By Admin

April 24, 2018

በተቃራኒ ጽንፍ የረገጡት መች ሊረቡን!

አባ መላኩ

እንደኔው እናንተንም  ይህ አባባል አግርሞት ይጭርባችሁ  ይሆን ስል አሰብኩና ላካፍላችሁ ወደድኩ።  “ግማሽ የደረሰን ጠርሙስ ለመሙላት እውስጡ ያለውን አፍሶ እንደገና  ለመሙላት መነሳት በየትኛውም መስፈርት ኪሳራና ድካም እንጂ ትርፍ አይኖረውም”።   አባባሉን ያገኘሁት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰላምና መረጋጋትን በተመለከተ በየአካባቢው  ከተካሄዱ መድረኮች ላይ አንድ ግለሰብ ከሰጡት አስተያየት ነው። በእርግጥ አባባሉ አዲስ ባይሆንም  ግለሰቡ የተጠቀሙበት ቦታ ግን ለእኔ ተስማምቶኛል። በአገራችን ድክመቶች እንዳሉ ሁሉ በርካታ መልካም ጅምሮችም እንዳሉ መገንዘብ ተገቢ ነው። የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የአንድ ጀንበር ስራ አይደለም። ባለፉት 27 ዓመታት በርካታ ዓለም የመሰከረው ተጨባጭ ለውጦችን አስመዝግበናል፤ በማስመዝገብም ላይ ነን።  አገራችን በፈጣን የለውጥ ጎዳና ላይ ትሁን እንጂ ያልተከናወኑ ነገር ግን ሊከናወኑ የሚገቡ በርካታ ስራዎች እንዳሉ መካድ አይቻልም። የሚገርመኝ አንድ ነገር አለ። የእኛ አገር የፖለቲካ አካሄድ ሁሉን በማጥላላት ላይ የተጠመደ አይነት ነው።

አገራችን የምትገኘው በምስራቅ አፍሪካ በተለምዶ የአፍሪካ ቀንድ በመባል በሚታወቀው አካባቢ ነው።  ይህ አካባቢ ደግሞ በዓለም የሚታወቀው ባለመረጋጋት፣ በድርቅ፣ በጦርነት፣ በስደት ብቻ በበርካታ መጥፎ ነገሮች ነው።  እንደሶማሊያና ኤርትራ ያሉ አገራት የሚገኙበት አካባቢ በመሆኑ የነገን በእርግጠኝነት መገመት የማይቻልበት ሁኔታ የሚስተዋልበት፤ ይህን አካባቢ ዓለም በስጋት ቀጠናነት የሚመለከተው ነው።  አበው ሲተርቱ “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንዲሉ በአካባቢው ጠንካራ መንግስት ያላትና አካባቢውን በፖለቲካም ይሁን በኢኮኖሚ እየመራች ያለችው ኢትዮጵያ ናት። ታዲያ ይህች አገር ቀውስ ቀውስ ሸቷት ይቅርና እንዲሁም ቀጠናው  የስጋት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምናስተውለው አንዳንድ አካሄዶች ለአገራችንም ሆነ ለቀጠናው ከዚያም አልፎ ለአፍሪካና ለዓለም ሰላምና መረጋጋት መልካም እንዳልሆኑ መረዳት የሚከብድ አይመስለኝም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ሁኔታዎች እየተሻሻሉ መጥተዋል።   

ለውጥ ለመልካም  ነገር፤ ለውጥ ለዕድገት  የሚጠላ ነገር አይደለም።  ይሁንና የእኛ አገር የለውጥ አካሄድ ይህን የተከተለ ነው ብዬ አፍ ሞልቼ ለመናገር ይከብደኛል። ሁሉም  በየጽንፉና በየጥጋጥጎ ሆኖ መጓተትን ስራዬ ብሎ ተያይዞታል፤ ሁሉንም የእኔ ነው፣ ከእኔ ውጭ የሆነውን አልየው አልስማው ማለት ይፈልጋል። ባልተለመደ ሁኔታ በርካታ ሰዎች  በዘር፣ በሃይማኖት፣ አልፎ አልፎም በቀቤለና በጎጥ ተከፋፍለው መናከስንና መቋራቆስን ተያይዘውታል። አንዳንዴ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሰዎችን አስተሳሰብ ስመለከት የጋራ አገር ያለን  አይመስለኝም። ይህ ኢትዮጵያዊ ባህላችን አይደለም።

በአገራችን በሁሉም ዘርፎች  መልካም ጅምሮች ይስተዋላሉ፤ እነዚህን አጠናክሮ ደካማ ጎኖችን በማረም የተያያዝነውን የህዳሴ ጉዞ ማጠናከር የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነት መሆን ይገባዋል።   ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት መሙላት የጀመረውን ጠርሙስ ለማፍሰስ የሚዳዳቸው እኔ ያልኩት ካልሆነ ምድር ይገልበጥ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ማስተካከል የሁላችንም  ሃላፊነት ሊሆን ይገባል። መልካሙን ነገር ሁሉ በማጥላላት አባዜ የተጠመዱ ሰዎች ቀላል ቁጥር ያላቸው አይደሉም። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ስርዓት ምንም ጉድለት እንደሌለበት፣ ስርዓቱና አገሪቱ የእነርሱ ብቻ አድርገው የሚከራከሩም እንዳሉ ተመልክተናል። እነዚህ ሁለት ጽንፎች ለአገራችንና ለህዝባችን አይበጁም።  

ለመንግስት ጥያቄን  ለማቅረብ ወይም መንግስትን ለመቃወም  የግለሰቦችን ወይም የጋራ መገልገያዎችን ወይም የመንግስት መስሪያቤቶችን ንብረት ማውደም ወይም የኢንቨስተሮችን ንብረት ወዘተ  ላይ ጥቃት መሰንዘር በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት ያለው አካሄድ ሊሆን አይችልም። የዴሞክራሲ ስርዓታችን ገና ጅምር እንጂ ያበቃለት አይደለም። ሊስተካከሉ የሚገባቸው  ነገሮች እንዳሉ መንግስትም አምኖ ተቀብሎ በርካታ ማሻሻያዎችን በማድረግ ላይ ነው። በርካታ ዜጎች መብትና ግዴታዎቻቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ አይመስሉም። አንዳንዶቹ  ጥፋቶች ማንም በደመነብስ እንኳን ሊያወግዛቸው የሚችሉ ጥፋቶችን በአደባባይ ሲፈጽሙ ተጠያቂነት ያለ አይመስላቸውም። አንዳንዶቹ ጥፋቶች “አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” አይነት ንጹሃን ምንም በማያውቁት ነገር  የበቀል ሰለባ ሆነዋል።

መንግስትና ገዥው ፓርቲ  ድክመታቸውን አምነው በርካታ የለውጥ ስራዎችን በማካሄድ ላይ ናቸው።  ከሚኒስትር እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም የፓርቲ መርዎችን ለውጥ አድርገዋል። አዳዲስ አሰራርና አደረጃጀትም ተዘርግቷል። ይሁንና ዕለቱን ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ ሊገኝ እንደማይቻልም መታወቅ መቻል አለበት።  እንደኢትዮጵያ ያለ ጅምር የዴሞክራሲ ስርዓት ተከታይ አገር ይቅርና የሁለትና የሶስት መቶ ዓመታት የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ተሞክሮ አላቸው የሚባሉት ምዕራባዊያን ሳይቀሩ የዴሞክራሲ ስርዓታቸው ያለቀለትና የበቃ አለመሆኑን አውቀው በየጊዜው እየፈተሹ በማስተካከል ላይ ናቸው። የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዘላቂ ሰላም ይፈልጋል።  ሰላም ደግሞ የሁሉንም ይሁንታ ትፈልጋለች። እኛ በተበጣበጥን፣ እኛ በውስጥ ጉዳያችን በተሻኮትን ጊዜ ሁሉ ለጠላቶቻችን በር እንከፍታላን።

ከአንድነታችን ይልቅ ልዩነታችን ላይ የምናተኩር ከሆነ  ለማንኛችንም የማትበጅ አገር እንፈጥርና እንዳንጠፋፋ እሰጋለሁ። የግብጽ መንግስታት  ኢትዮጵያን በተመለከተ ለዘመናት የተከተሉት አካሄድ የተሳሳተ ነው። ለዚህም የመስለኛል ግብጻዊያን በተለያየ ጊዜ በአገራችን የውስጥ  ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚሯሯጡት። ኢትዮጵያ ግብጻዊያንን ለመጉዳት አንድም ነገር አከናውና አታውቅም። የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው አቋም ሁሉም የተፋሰሱ አገራት  ከጋራ ሃብታቸው ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር ነው።

ሰላም የልማታችን፣ የአብሮነታችን፣ የአንድነታችን በአጠቃላይ የሁሉም ነገር  ዋስትና ነው። ሰላም ለልማት፣ ሰላም ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት፣ ሰላም ለመድብለ ፓርቲ መጠናከር፣ ሰላም ለህዝቦች አብሮ መኖር፣ ሰላም ለአገር ዕድገት፣ ወዘተ ብቻ ሰላም የሁሉም ዋስትና ነው። ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር የለም። በአገራችንን የውስጥ ጉዳይ እንዳሻቸው ጣልቃ በመግባት እንደፈለጋቸው መፈተት ለሚፈልጉ ሃይሎች ቦታ ልንሰጣቸው አይገባም። የአገራችን ሰላም ለድርድር የሚያቀርብ አይደለም። ባለፉት 27 ዓመታት የአገራችን ህዝቦች የሰላምን ዋጋ ከማንም በላይ ተገንዝበውታል። የሰላም እጦት ሞትን፣ አካል መጉደልን፣ የንብረት መውደምን፣ ስደትን፣ ረሃብን፣ መታረዝን  በአጠቃላይ ድህነትን አስክትሎብናል። ለሰላም ዘብ መቆም ለሰላም መዘመር ያለበት መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰላም ወዳድ የህብረተሰብ ክፍል መሆን መቻል አለበት።

ልዩነትን በሃይል ማራመድ የሚቻልበት ወቅት አልፏል።  ህብረተሰቡ ጥያቄ እንዳለው መንግስትም አምኖ ችግሮችም መፍትሄ ለመስጠት ጥረት በማድረግ ላይ ነው። እንኳን በታዳጊ አገር ይቅርና በምዕራባዊያኖችም ዘንዳ ቢሆን ችግሮች በአንድ ጀንበረ አይፈቱም። የመንግስትን ጥረት በማገዝ ለችግሮች በጋራ መፍትሄ ማፈላለግ እንጂ  መንግስት ብቻ ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ ይፈልግ ማለት አግባብነት የጎደለው አካሄድ ነው። በመሆኑም መንግስት የጀመረውን የለውጥ ጉዞ በመደገፍ አገራችንን ወደ ከፍታው ማውጣት የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።