Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተገቢ ንግግር፤ ለሚገባው ህዝብ!

0 300

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተገቢ ንግግር፤ ለሚገባው ህዝብ!

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ ትግራይንና ህዝቧን የሚመጥኑና ማንነታቸውን የሚገልፁ ታላላቅ ክስቶችን አንስተዋል። ከክስተቶቹ መካከል ጥቂቹን ለመግለፅ ያህል፤ ትግራይ የተለያዮ ሃይማኖቶችና ባህላዊ ትውፊቶች እና ባዕዳን ወራሪዎች የተመከቱባት አድዋ መገኛ እንዲሁም በሺህዎች የሚቆጠሩ የፍትህና የነፃነት ታጋዩች መፍለቂያ መሆኗን አውስተዋል። ኢትዮጵያ ያለ ትግራይ፣ ትግራይም ያለ ኢትዮጵያ ሞተር እንደሌለው መኪና የሚቆጠር መሆኑን አስረድተዋል—የትግራይን ህዝብና የሀገሩን ጥብቅ ቁርኝት ሲገልፁ። የትግራይ ህዝብ ወርቅ ስለመሆኑም አንስተዋል። ትክክል ነው።

ሆኖም አንዳንድ ፅንፈኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚሏቸውን ነገር ሲያጡ፣ “እንዴት ህዝቡን ወርቅ ነው ይላሉ?” በማለት የተለመደ የጥላቻ ፈረሳቸውን በየማህበራዊ ሚዲያው ሲለፍፉ ይታያሉ። ይህም የደፈና ጥላቻ አባዜ የሚለው ነገር ቢያጣ የለመደውን የጥላቻ ዜማ ከማቀንቀን የሚመለስ አለመሆኑን የሚያስረዳ ነው። በእኔ እምነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ህዝብ ወርቅ መሆኑን የገለፁበት አግባብ ትክክልና ተገቢ ነው። ይህም የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ወርቅ ነው። በተለይ የትግራይ ህዝብ ሀገራችንን ለመውረር ጦርነት የሚፈልጉ ባዕዳን ሃይሎች የሚገቡበት፣ ከንጉሱ ጀምሮ እስከ ደርግ ድረስ የታገለና ያታገለ ህዝብ ነው። በእሳት የተፈተነ ወርቅ ነው።

ይህ ህዝብ የሀገራችን ስልጣኔ መነሻና ማገር ነው። ለኢትዮጵያ አንድነት ከጥንት የሳባዊያን ዘመን እስከ ዋስና ጠበቃ ሆኖ በመስራት የሚታወቅ፣ እንደ ሌላው የሀገራችን ህዝብ ለፍቶና ጥሮ ግሮ የሚያድር ታታሪ ህዝብ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ የትግራይ ህዝብ ከጎረቤት ክልሎችም ይሁን ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር በደም፣ በባህልና በቋንቋ የተሳሰረ ነው። ትግራይ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያም ትግራይ እንድትሆን ያደረገ ህዝብ ነው።

የኢትዮጵያዊነት ቀንዲልና መቅረዝም ነው—ይህ ህዝብ። ርግጥ የትግራይ ህዝብ ዛሬ ለተፈጠረችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ሲል የሞተ፣ የቆሰለ፣ ንብረቱን ያጣ ነው። በተለያዩ ወቅቶች ኢትዮጵያን ሊወሩ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የመጡ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ቅሌታቸውን ተከናንበው እንዲመለሱም ያደረገ ነው። በእሳት ተፈትኖ ከእሳት ውስጥ የወጣ ወርቅ ህዝብ ነው።

በትጥቅ ትግሉ ወቅት የትግራይ ህዝብ ያላየው የፍዳ ዓይነት የለም። ሞቷል፣ ቆስሏል፣ ደምቷል፣ ንብረቱን አጥቷል፣ ተሰድዷል። ሌላም ሌላ ነገር ሆኗል። በእውነቱ በትጥቅ ትግሉ ወቅት እንደ ትግራይና አካባቢው አበሳውን የበላ ህዝብና ቦታ ተፈልጎ የሚገኝ አይመስለኝም። ምክንያቱም ይህ ህዝብ ከሚኖርበት አካባቢ ባሻገር፤ በመላ ሀገሪቱ እንደ ጠላት ተቆጥሮ ሲታደን የነበረ በመሆኑ ነው።

ርግጥ አምባገነኑ የደርግ ስርዓት በሹል ጉጠቶቹና የተሳሉ ጥፍሮቹ ያልቧጠጠው፣ ስለት ባለው ቢላዋው ያልሸረካከተው፣ በብረት ለበስ ታንኮቹ ያልደፈጠጠው የህብረተሰብ ክፍል የለም። እንደ ትግራይ ህዝብ ግን የደርግ የአፈና አገዛዝ እንደ መርግ የተጫነበት የህብረተሰብ ክፍል የሚገኝ አይመስለኝም። ሁሉም የብሔረ ትግራይ ተወላጅ ሊባል በሚችል መልኩ በደርግ “ጥቁር መዝገብ” ውስጥ ሰፍሮ ሲታደን እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።

ህዝቡ በወቅቱ መቼ ታፍኖ እንደሚወሰድ አያውቅም። በደርግ እስር ቤቶች የታጎረው ህዝብም ቢሆን በየትኛው ለሊት ስሙ ተጠርቶ የጥይት አረር እንደሚበላው የሚያውቅበት አንዳችም መንገድ አልነበረውም። ጉዞው የሰቀቀን መንገዱም አሜኬላ እሾህ የበዛበት ነበር። የትግራይን ህዝብ ሲለበልበው የነበረው እሳት እንዲህ ዓይነት ነበር።

ታዲያ ይህ ፈታኝ የጭቆናን አገዛዝ መቋቋም ስላቃተው ጥቂት ልጆቹ ፅናትን ተላብሰው “ዱር ቤቴ” በማለት ወደ ደደቢት አቀኑ። ሌሎች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችም ተቀላቀሏቸው። ትግሉ 17 ዓመታትንም ፈጀ። የትግራይ ሀዝብም ከ70 ሺህ የሚልቁ ልጆቹን ህይወት ገበረ። ለዛሬዋ ኢትዮጵያም መሰረት ሆነ። ታዲያ ይህ በእሳት የተፈተነ ህዝብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ወርቅነት ቢያንሰበት እንጂ የሚበዛበት አይመስለኝም።

ለኢትዮጵያ በጎ የማይመኙ ህዝቦች መግቢያቸው በዚሁ ክልል ነው። ጦረኛው የኤርትራ መንግስት በእብሪት ባድመንና አካባቢውን በወረረበት ወቅት፣ የትግራይ ህዝብ ከአካባቢው ሚሊሻ ጎን በመሆን በሜካናይዝድ የተደራጀውን የሻዕቢያ ጦር የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ተጠናክሮ ወደ አካባቢው እስኪደርስ ድረስ መክቶና ገትቶ ባለበት ቦታ እንዲቆም ያደረገ ነው። በወቅቱ በርካታ የትግራይ ሚሊሻዎች ህይወታቸውንና አካላቸውን አጥተዋል። ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል፤ ከሚኖሩበት ቀዬና መንደር ተፈናቅለዋል። ህፃናትም ትምህርት ቤት ውስጥ ሆነው በግፍ ተጨፍጭፈዋል። በወቅቱ በሻዕቢያ የተወረሩት አካባቢዎች ጥቂት ቢሆኑም ቅሉ፤ ሁሉም የክልሉ ተማሪዎች ከ10ኛ ክፍል በላይ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ተደርጎ ወደ ማሰልጠኛ ማዕከሎች ከትተዋል።

በህዝብ የሚደገፈው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ተጠናክሮ ወደ አካባቢው ከዘለቀ በኋላም፤ ሁሉም የክልሉ ህዝብ ዳር ድንበራቸው ከተነካባቸውና ከተቆጡት ከሌሎቹ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በአንድነት በመሆን እንደ አድዋ ወራሪውን ጦር አከርካሪውን ሰብረው አባረውታል።

በወቅቱ አዋቂ፣ ሴትና በትጥቅ ትግሉ ወቅት አካላቸው የጎደለ ታጋዩች ሳይቀሩ በየፊናው ያሰለፈና ወራሪን እንደ ትናንቱ ያሳፈረ ህዝብ ነው። እናስ ይህ ህዝብ ወርቅ ስለመሆኑና በእሳት ስለመፈተኑ ቢነገርለት ሃጢያቱ ምኑ ላይ ነው? በደፈና ጥላቻ የሚመራው ፅንፈኛ ኃይልስ እስከ መቼ ነው ከትግራይ ህዝብ ላይ እንደ ተባይ ተጣብቆና ስሙን እያጠፋ የሚቀጥለው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዳሉት ይህ ህዝብ ከተራቆቱ ተራራዎች ጋር ታግሎ በአረንጓዴነት እንዲሸፈኑ ያደረገ የልማት አርበኛ ነው። ህዝቡ ስራ ወዳድና ታታሪ ነው። ድንጋይ ፈንቅሎና ተራራ ንዶ የዕለት ጉርሱን የሚሸፍን ነው። ያለውን አካፍሎ የሚበላ የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት ነው።

ታዲያ ይህን የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት የሆነን ህዝብ ሊጠሉ የሚችሉት ፅንፈኛ ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ብቻ ናቸው። ከጥንት ከጠዋቱ ጀምሮ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር ሲማስን የነበረን ህዝብ ሊጠሉት የሚችሉት በፌስ ቡክና በሌሎች የትስስር መረቦች ላይ በጥላቻ ፈረስ ላይ የሚጋልቡ ፅንፈኞች ብቻ ናቸው። ይህ ህዝብ የኤርትራ መንግስት እያሰረገ የሚያስገባቸውን ሰርጎ ገቦች ሌት ተቀን በመጠበቁ ሳቢያ ለልማት ማዋል የሚገባውን ጊዜ ያባክናል። በዚህም የሀገሩንና ዳር ድንበር በመጠበቅ እርሱ እየሞተ እኛን ያኖረናል። የትግራይ ህዝብ የወርቅነት ምስጢር እንዲህ ነው።

ምናልባት እግር ጥሎት ወደ ትግራይ ያመራ ሰው ኢትዮጵያ ያለ ትግራይ ትግራይም ያለ ኢትዮጵያ ባዶ መሆኑን ተገንዝቦ ይመለሳል። የትግራይ ህዝቡ ከሌላ አካባቢ ለመጣ ኢትዮጵያዊ የሚሰጠው ፍቅር ወደር የማይገኝለት ነው። በህዝቡ ዘንድ እንግዳ እጅግ የተከበረ ነው። ያለውን ነገር ያካፍላል። ማጀቱን ከፍቶ፣ ድስቱን ገልብጦ፣ ጮጮውን አንጠፍጥፎ ያጠጣል፤ ያበላል። በማናቸውም ጉዳዩች ላይ ከሀገሬው ህዝብ ይልቅ እንግዳ ቅድሚያ እንዲያገኝ ያደርጋል።

ትግራይ ውስጥ ለስራ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያዊነትን ክብር ይጎናፀፋል። የትግራይ ህዝብ ድህነት ይዞት ነው እንጂ፣ ምንም ነገር ከመስጠት አይቆጠብም። እናም እግር ጥሎት ወደዚያ ያቀና እንግዳ በኢትዮጵያዊነቱ ይኮራል። ሐሴትንም ያደርጋል። ያኔም ኢትዮጵያ ያለ ትግራይ፤ ትግራይም ያለ ኢትዮጵያ መኪና ያለ ሞተር እንደማለት መሆኑን ይገነዘባል። ስለ ኢትዮጵያዊነቱም አብዝቶ ያስባል። በዚያ ታታሪና ኢትዮጵያዊ ህዝብ መሃል መገኘቱም ራሱን እንደ እድለኛ የሚቆጥር ይመስለኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰሜናዊቷ ኮከብ ከተማ መቐለ ተገኝተው የተናገሩትም ይህንኑ ነው። በእኔ እምነት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባሎች ሁሉ ለሚገባው ህዝብ የተደረገ ተገቢ ንግግር ነው። ከዚህ ውጭ በደፈና ጥላቻ የታፈኑ ፅንፈኞች የሚያወሩት “የፀጉር ስንጠቃ” በትግራይ ህዝብ ላይ ከሚነዛው ከተለመደው ቆርጦ ቀጥል አሉባልታ ተለይቶ የሚታይ አይመስለኝም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy