Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትሩፋቶቹን ለማግኘት…

0 245

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ትሩፋቶቹን ለማግኘት…

                                                     ይሁን ታፈረ

የሰላም መኖር ለኢንቨስትመንት ያለውን ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም። የሰላም መጥፋትም ኢንቨስትመንት እንዳይኖር እንደሚያደርገውም እንዲሁ። ስለሆነም አገራችን አሁን ከተመዘገበው የኢንቨስትመነት ዕድገት በተጨማሪ፤ ባላት የኢንቨስትመንት አማራጮች ባለ ሃብቶች ሙሉ እምነት እንዲኖራቸው ሰላምን በዘላቂነት ማስጠበቅ ያስፈልጋል።

የውጭ አገራት ባለ ሐብቶች በአገሪቱ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ሲሰማሩ በርካታ ዕድሎች ይዘው ይመጣሉ። ከእነዚህ ውስጥ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም አገሪቱን የአፍሪካ የኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ ረገድ የራሳቸው ሚና ይኖራቸዋል። ታዲያ እነዚህን ትሩፋቶች ለማግኘት አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን ይገባል።

በአሁኑ ወቅት ባለፉት ሥርዓቶች የወጡና የግሉን ዘርፍ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚገቱ ህጎችና ደንቦች ተወግደው በልማታዊ መስመር ራዕይዎች ተተክተዋል። በዚህም ለውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። በዚህም መሰረት በአሁኑ ሰዓት አገራችን ለኢቨስትመንት የምትመች አገር ሆናለች።

እስካዛሬ ድረስ ጎረቤት ኬንያ በአበባ ምርት ቀዳሚ ነበረች በአሁኑ ወቅት ግን አገራችን ዋነኛ ተፎካካሪ መሆን ችላለች። ኢትዮጵያ የመጓጓዣና ኃይል ማመንጫ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በማስፋፋቷ ወደ አፍሪካ ለመምጣት የሚሹ የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎችን መሳብም የቻለች አገር ሆናለች።

የአገራችን የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጥራት ያለው የቆዳ ጫማዎች እና ምርቶች በማቅረብ በዓለም ገበያ እየታወቀ መጥቷል። በተለይም ሀገራችን ባላት አስተማማኝ የኃይል ምንጭ፣ ተመጣጣኝ የጉልበት ዋጋ እና እያስመዘገበችው ያለው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን እየሳበች ነው።

በተለይም አገራችን አስፈላጊውን መሠረተ ልማት በማሟላት እና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በማዘጋጀት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ዝቅተኛ የማምረቻ ወጪ ወደ ሚጠይቃቸውና ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ወዳላት ኢትዮጵያ ነቅለው እንዲመጡ እያደረገች ነው። ይሁንና ሀገራችን ለምን ለኢንቨስተመንት ተመራጭ እንደሆነች ማውሳቱ ፋይዳው የላቀ በመሆኑ ወደዚያው ማምራት ይገባል።

ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የአገራችን ኢንቨስትመንትን የመሳብ ብቃት የመነጨው ከምንም ተነስቶ አይደለም፤ ካለን የኢንቨስትመንት አሰራር ተመራጭነት የመነጨ እንጂ። እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በርካታ ባለሃብቶችን በመሳብ ላይ ይገኛል።

በዚህም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል። በዚህም ሳቢያ ቀደም ሲል በምሳሌነት ያነሳኋቸውና ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ነው፤ በርካታ ዜጎችንም የስራ ባለቤት በማድረግ።

እርግጥ ሀገራችን እየተከተለችው ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ነፃ የመሬት አቅርቦት መዘጋጀቱ፣ የአበባ ማምረቻ ስፍራዎች በመንገድ እና በኤሌክትሪክ እንዲተሳሰሩ መደረጋቸው፣ የታክስ እፎይታ ጊዜ መኖሩ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገራችን እንዲሳቡ ዋነኛው ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል። ሀገራችን የምትከተለው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር አሁን ለተገኘው የኢንቨስትመንት አመቺነት ምህዳር ወሳኙን ሚና መጫወቱም እንዲሁ።

የኢፌዴሪ መንግስት አገሪቱንና ህዝቦቿን ከድህነት ከኋላቀርነት ለማላቀቅ የነደፈው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተግባራዊ በማድረግ ተስፋ ሰጪ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ የውጪው ዓለምና ባለሃብቶቻቸው ሳይቀሩ እየመሰከሩለት ይገኛሉ። ከመመስከር ባለፈም፤ የሀገራችንን መፃዒ ዕድል ከወዲሁ በአንክሮ አጢነው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ በልማት እግሮቻቸው ወደ አገራችን እየተመሙ ነው። ዛሬ የኢንቨስትመንት መንገዶች ወደ ኢትዮጵያ እያመሩ ነው።

በአገራችን ውስጥ እየደገ የመጣ፣ ተጠቃሚ እንዲሁም መካከለኛ ገቢ ያለው የህዝብ ቁጥር መጨመሩ፣ ፈጣን የከተሞች ዕድገት መታየቱና ሳቢ የኢንቨስትመንት አሰራር መኖሩ ባለሃብቶችን መሳብ ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪ አገራችን በምስራቅ አፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ውስጥ አንዷ ስለሆነችና እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት አቅም ያላት መሆኗ ባለሃብቶቹ ለሚሳተፉበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

እርግጥ በኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚ ውስጥ የፋይናንስ፣ የቴሌኮም እና የጅምላ ንግድን ጨምሮ ሌሎች ዋና ዋና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች የተከለከለ ነው። ይህም የሀገራችን የፋይናንስና ለሌሎች ተቋማት ራሳቸውን እስኪያጎለብቱና በአስተማማኝ ሁኔታ ተወዳዳሪ እስኪሆኑ ድረስ እንዲሁም መንግስት በተመረጠ አኳኋን በልማት ስራው ላይ ስለሚሳተፍ ነው። ይሁንና የውጭ ባለሃብቶች በሲሚንቶ፣ በቡና፣ በወይን እና በብስኩት ማምረት ዘርፎች ውስጥ በመሳተፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መገኘታቸው ሀገራችን የውጭ ባለሃብቶችን የሚያበረታታ አካሄድ እየተከተለች መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

የውጭ ባለሃብቶች ሀገራችን ከምትከተለው ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ስርዓት አኳያ በመንግስት የተያዙ የምጣኔ ሃብት ዘርፎች ውጪ እንዲሁም በህግ ተደነገጉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በስተቀር ኢንቬስተሮቹ ወደ ሀገራችን ገብተው በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሳተፉ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ተችለል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ሀገራችን ያላት የተረጋጋ ሥርዓት እና ርካሽ የጉልበት ክፍያ እንዲሁም ለባለ ሃብቶች የተዘጋጀው የተሻለ የታክስ ድጎማና የእፎይታ ጊዜ ብሎም በታዋቂው አየር መንገዷ የዓለም ገበያን በቀላሉ ለመድረስ መቻሏ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንድትሆን አድርጓታል።

ይህን ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የአገራችንን አካሄድ በአግባቡ በመጠቀም ከኢንቨስትመንት የምናገኛቸውን ትሩፋቶች በተገቢው መንገድ ማጣጣም ይኖርብናል። ለዚህ ደግሞ አስተማማኝ ሰላም ወሳኝ ነው። ሰላም ከሌለ ስለ ልማት ማሰብ አይቻልም። ስለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበትም እንዲሁ። ያለ ሰላም እንኳንስ የውጭ ኢንቬስተሮችን መሳብ ቀርቶ፣ እንደልብ ወጥቶ መግባትም አይቻልም። እናም የሀገራችንን ሰላም አስተማማኝ ማድረግ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ወቅታዊ ተግባር ነው።

ሰላም ስንሆን የውጭ ባለሃብቶች የሚፈጥሩልንን የውጭ ምንዛሬ መጠቀም እንችላለን። ሰላም ስንሆን በኢንቨስትመንቱ ሳቢያ የሚፈጠሩ የስራ ዕድሎችን እንጠቀማለን። ሰላም ስንሆን ከውጭ ባለሃብቶች የቴክኖሎጂ ሽግግርን በመውሰድ ራሳችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እያዛመድን የሽግግር ማዕከል መሆን እንችላለን። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአገራችን ህዳሴ በቅርቡ እውን ማድረግ እንችላለን። ስለሆነም እነዚህን ትሩፋቶች ለማግኘት ሰላምን በሁሉም ደረጃ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy