Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲመጣ…

0 1,028

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲመጣ…

                                                        ዘአማን በላይ

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 93 ንዑስ አንቀፅ አምስት ላይ፤ “በሀገሪቱ የአስቸኳይ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ከአባላቱና ከህግ ባለሙያዎች መርጦ የሚመድባቸው ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ ያቋቁማል። ቦርዱ አዋጁ በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በሚፀድቅበት ጊዜ ይቋቋማል።” የሚል የሆነ ድንጋጌ ሰፍሯል።

ይህን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ተከትሎም ፓርላማው ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ15 ቀናት ውስጥ መርምሮ በማፅደቅ፤ የአዋጁን አፈፃፀም የሚመረምሩ የቦርድ አባላትን በህጉ መሰረት ሰይሟል። ተግባራቸውን በገለልተኝነት ይወጡ ዘንድም ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን አድርጓል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 ንዑስ አንቀፅ ስድስት መሰረት በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት ስራውን ጀምሯል።

ከእነዚህ ስራዎቹ ውስጥ በተቋቋመ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የታሰሩትን ሰዎች ስም ዝርዝርና የታሰሩበትን ምክንያት ለህዝብ ይፋ ማድረግ ነው። ይህን ተግባሩንም በይፋ  ጀምሯል። የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ወርዶፋ በቅርቡ እንደገለፁት፤ ቦርዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት በሁከትና ብጥብጥ የጠረጠራቸው አንድ ሺህ 107 ሰዎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በስድስት የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ቀጣና ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውንም ገልፀዋል። በዚህ መሰረትም በቀጣና አንድ አዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በሚገኙ አምቦ፣ ቢሾፍቱ፣ ዱከም፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ፍቼ እና ሞጆ አካባቢዎች 450 ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ ሴቶች መሆናቸው ተመልክቷል።

በኮማንድ ፖስቱ ቀጣና ሁለት ውስጥ በሚካተቱት ከባሌ፣ ከምስራቅ ሸዋ፣ ከአርሲና ምዕራብ አርሲ ዞኖች ደግሞ 39 ወንድ ተጠርጣሪዎች በሀዋሳ በቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ታውቋል። በቀጣና ሶስት ኮማንድ ፖስት ውስጥ ከሚገኙ መካከል ከድሬዳዋና ሐረር ከተሞች ተጠርጥረው የተያዙ 178 ሰዎች በድሬዳዋ በቁጥጥር ስር ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ ሴቶች ናቸው።

ከጅማ እስከ ነቀምቴ ያሉት አካባቢዎችን በሚያጠቃልለው የኮማንድ ፖስቱ ቀጣና አራት ደግሞ ሶስት ሴቶችን ጨምሮ 388 ተጠርጣሪዎች በነቀምቴ ከተማ እንዲሁም በባህር ዳር በሚገኘው የኮማንድ ፖስቱ ቀጣና አምስት ደግሞ 43 ወንድ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ይገኛሉ። የኮማንድ ፖስቱ ቀጣና ስድስትም ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በሰመራ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረጉባቸው ምክንያቶች፤ በፀጥታ ሀይል እና በሰላማዊ ዜጋ ላይ የግድያ ወንጀል መፈፀም፣ ቤት ማቃጠል፣ የመንግስት እና ህዝባዊ ተቋማትን ማውደም እና የፋይናንስ ተቋማትን ማቃጠል እንዲሁም ሌሎች የወንጀል መሂናቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም ህገ ወጥ የጦር መሳሪያን በማዘዋወር፣ መንገድ በመዝጋት፣ ብሄርን ከብሄር በማጋጨት፣ የንግድ፣ የትራንስፖርት እና የመማር ማስተማር ሂደትን በማስተጓጎል ተጠርጥረው የተያዙም ግለሰቦች እንደሚገኙ ታውቋል። የተጠርጣሪዎቹ ስም ዝርዝር ወደ ተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ክልሎች የተላከና ቤተሰቦቻቸውም ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በየቀበሌዎቻቸው ማየት ይችላሉ። መርማሪ ቦርዱ ተጠርጣሪዎቹ የሚገኙበትን ሁኔታ በየቦታው ተገኝቶ አያያዛቸውን ይከታተላል።

እስካሁን ድረስ ለቦርዱ 130 ጥቆማዎች ደርሰውታል። ከእነዚህ ውስጥ እርሱን የሚመለከቱትን 82 ጥቆማዎች እያጣራ ይገኛል። ኮማንድ ፖስቱን የተመለከቱትን ደግሞ ለሚመለከተው አካል መላኩን አስታውቋል። እንግዲህ እነዚህ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የተከናወኑ የመርማሪ ቦርዱ ተግባራት የሀገራችን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ራሱን ረባሱ የሚፈትሽበት አሰራር ያለው መሆኑን የሚያመላክት ነው።

በእኔ እምነት ቦርዱ ስራ በጀመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይህን መሰሉን ውጤት ይዞ መቅረቡ ሊበረታታ የሚገባው ነው። ምክንያቱም ተግባሩ ህገ መንግስቱን ተፈፃሚ ከማድረግ አኳያ የሚመዘን በመሆኑ ነው። ይህ ሁኔታም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የህግ የበላይነት እንዳይጣስ ያደርጋል። “ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው” የሚለውን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ገቢራዊ ለማድረግ የሚያስችልም ነው።

ታዲያ ይህ የቦርዱ ህገ መንግስታዊ አሰራር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አሁንም ግን ቦርዱ በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩትን ኃላፊነቶችን በሂደት መወጣት ያለበት ይመስለኛል። በቀጣይም በህገ መንግስታችን አንቀፅ 93 ንዑስ አንቀፅ ስድስት ስር ከ “ሀ” እስከ “ሠ” ድረስ የተዘረዘሩትን ድንጋጌዎች ገቢራዊ በማድረግ፤ ህገ መንግስታዊ ኃላፊነቱንና ተግባሩን በብቃት መፈፀም ይኖርበታል። የተሰጡትን ጥቆማዎችም ባልተራዘመ ጊዜ ውስጥ ምላሽ በመስጠት ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ከህገ መንግስቱ ማዕቀፍ አኳያ ማረጋገጥ አለበት ብዬ አስባለሁ።

የቦርዱ ተግባር የተለያዩ ፅንፈኛ ሃይሎች በቀጥታም የሁን በተዘዋዋሪ በኮማንድ ፖስቱ ላይ ሆን ብለው እያካሄዱ ያሉትን ስም የማጠልሸት ዘመቻን አፍ ያሲዛል ብዬ አምናለሁ። ርግጥም የተለያዩ ፅንፈኛ የመገናኛ ብዙሃንና እንደ ቪኦኤ (የአማርኛው ክፍል) ዓይነት ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው ሚዲያዎች እንዲሁም ሀገራችን ሁሌም በትርምስ ውስጥ እንድትኖር የሚሹ አካላትን አሉባልታንም መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ዕውነታ ተንተርሶ ሃቁን በመግለፅ ርቃኑን ማሳየት አሊያም ትክክለኛ ከሆነም ስህተትነቱን በማመላከት ጉዳዩን ፈር ለማስያዝ ጥረት ማድረግ አለበት።

በእነዚህ ፅንፈኛና የፖለቲካ ዝማሜ ባላቸው ሚዲያዎች አማካኝነት የሚተላለፉና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተዓማኒነት ለማጉደፍ የሚሰነዘሩ ጉዳዩች ካሉም ክትትል በማድረግና ያገኘውንም ግኝት ለህዝብ በማሳወቅ የሚነዙትን ውዥንብሮች የማጋለጥ ተግባሩን መፈፀም አለበት እላለሁ።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈፃሚዎች አሊያም አንዳንድ የፀረ-ሰላም ኃይሎችን አጀንዳ ለማሳካት ሲሉ በሚንቀሳቀሱ አካላት አማካኝነት ከአዋጁ መሰረታዊ እምነትና አሰራር ውጭ የሚፈፀም ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ካለም ይህን ፈልፍሎ በማውጣት ሊያሳውቅና ተገቢው የማስተካከያ ርምጃም እንዲወሰድ ማድረግ ይኖርበታል።

ምናልባት በአዋጁ አስፈፃሚዎች በኩል በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚስተዋሉ ህፀፆች ካሉና ህፀፆቹም ኢ-ሰብዓዊ መሆናቸውን ሲያምን በተሰጠው ተግባርና ሃላፊነት መሰረት ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ሀገራችን የምትመራበትን ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ማሳየት አለበት ብዬ አምናለሁ። እያንዳንዱ ዜጋም ለቦርዱ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ለስራው መቃናት ምርኩዝ ሊሆነው እንደሚገባ እንደ ዜጋ ለመግለፅ እወዳለሁ። ይህም የሀገራችን ህገ መንግስታዊ ስርዓት ራሱን በራሱ እንዲያርም (Check and Balance) በሚደረገው ጥረት ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል። አማን ያሰንብተን።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy